ለሦስተኛ ጊዜ በሚካሄደውና ገቢው ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ሥራ ታስቦ በየዓመቱ የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በወሊሶ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ወንጪ ሐይቅ ላይ ይካሄዳል፡፡ 300 የሚደርሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞችና ሌሎች ዜጎችን በሚያሳትፈው ውድድር እንደሚካፈሉ ተገልጿል፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች እንደገለጹት፣ ውድድሩ የስፖርት ቱሪዝምን በአገሪቱ እንዲስፋፋ ከማገዝ ባለፈ ገቢውን ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ማዋል መቻሉ ቦታ እንደሚያሰጠው፣ ዘንድሮም የካቲት 12 ሆስፒታል ውስጥ በአዲስ መልኩ ሊገነባ ለታሰበው የሕፃናት ድንገተኛ ሕክምና ክፍል የውድድሩን ገቢ እንደሚጠቀምበት ተገልጿል፡፡ በመዝናኛ እንቅስቃሴዎችና የአካል ብቃትን በሚያሳድጉ ስፖርቶች ታጅቦ የሚካሄደው ውድድር ለአሸናፊዎቹ ሽልማት በማበርከት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡