ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በጣይቱ ሆቴል ከደረሰው ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ድጋፋቸውን ላሳዩ ሁሉ ለማመስገን የተዘጋጀ የኪነ ጥበብ መርሐ ግብር ሐሙስ ጥር 14፣ 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሐጎስና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በተገኙበት በጣይቱ ሆቴል ለሕዝብ ክፍት ሆኗል፡፡ የምሥጋና ዝግጅቱን ጣይቱ ኢንተርናሽናል አርት ሴንተር፣ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኀበርና ኬር ኢንቨንትስ ኮሙዩኒኬሽን አንድ ላይ ሆነው አዘጋጅተውታል፡፡ ዝግጅቱ ከዓርብ ጥር 15 እስከ ጥር 17፣ 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ለሕዝብ ክፍት ይሆናል፡፡ በመክፈቻው ዕለት 300 እንግዶች መገኘታቸውንና 400 የሚሆኑ ሥዕሎች ለዕይታ መብቃታቸውን የጣይቱ አርት ሴንተር ዳይሬክተር አቶ ዘለዓለም ግዛው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ በመርሐ ግብሩም 30 ሠዓሊያን፣ ገጣሚያን፣ ድምፃውያን፣ እንዲሁም ኢትዮከለር ባንድ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ ብዙ የኪነ ጥበብ ሰዎች ፈቃደኝነታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ለታዳሚ ክፍት የሆነው በነፃ ነው፡፡ በዝግጅቱ የሥዕል ዐውደ ርዕይ፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ሰርከስ፣ ግጥም፣ መዝናኛ፣ የሥዕል ሥልጠና፣ ለሕፃናት የአዝማሪ ጨዋታዎችና የጣይቱ መስተንግዶ ይኖራል፡፡ ዝግጅቱ ከምሥጋና ባሻገር ጣይቱ ሆቴል በአሁኑ ወቅትም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ለማሳወቅ እንደሚያስችል አቶ ዘለዓለም አክሏል፡፡