በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ በሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ተመሥርተው ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ የዘመናችን ንጽፈ ሐሳቦች፣ ግለሰቦች በምርጫ ድምፃቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ መስጠታቸው የሁለንተናዊው ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ተግባራዊነት አካል አድርገው ይገልጿቸዋል፡፡ በአጭሩ ድምፅ የመስጠት መብትና ሰብዓዊ መብት የማይነጣጠሉ አካላት ናቸው፡፡ ዜጎች በመንግሥታት የፖሊሲና የስትራቴጂ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ከሚጠቀሙባቸው ወሳኝ ነጥቦች መካከል አንዱ ድምፅ ነው፡፡ መብቱን ተጠቅሞ ድምፁን ለመስጠት የሚዘጋጅ ማንም ዜጋ በምርጫው ዋዜማ የፖለቲካ ፓርቲ ተወዳዳሪዎችን በጥፍራቸው እንደሚያስቆማቸው ሁሉ፣ የመንግሥትን አስተዳደር ተረክበው በሚመሩበት ወቅት ደግሞ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የተሞላበት አሠራር እንዲኖራቸው ያስገድዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥልጡንና ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በበርካታ አገሮች የዜጎች ድምፅ ወሳኝ ነው፡፡ በአገራችን ምንም እንኳ የዴሞክራሲያዊው ሥርዓት ግንባታ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት አራት ጠቅላላ ምርጫዎች ተካሂደው አምስተኛውን ለማከናወን አራት ወራት ይቀራሉ፡፡ ዴሞክራሲ ሒደት እንደመሆኑ መጠን፣ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩና የመንግሥት ለውጥ መካሄድ ያለበት በምርጫ መሆን ስላለበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለዚህ ተግተው መሥራት አለባቸው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት ምርጫ ዋጋ አልባ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1948 ይፋ በሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት፣ በማንኛውም አገር የሚካሄድ ምርጫ ግልጽና ሕዝብን አሳታፊ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መንገድ የሚከናወን ማንኛውም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሕዝብ አሳታፊ የሆነ መንግሥት ከመመሥረቱም በላይ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የማዕዘን ድንጋይ ይሆናል፡፡ ሁሌም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሚፈለገው የሕዝብ ፈቃደኝነት ሲሆን፣ ይህ ፈቃደኝነት የሚገለጸው በድምፅ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ዜጎች ድምፃቸውን እንዲሰጡ ማንቀሳቀስ ያለባቸው፡፡ ምርጫ ዜጎች በእኩልነት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ወኪሎቻቸውን የሚመርጡበት ሥርዓት እስከሆነ ድረስ፣ ሕዝቡን ለመራጭነት የማንቀሳቀስ ኃላፊነት የአንድ ወገን ሊሆን አይገባውም፡፡ ምርጫው ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲፈለግ ሌሎች አሉ የሚባሉ ችግሮችን ከመፍታት ጎን ለጎን፣ መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የምርጫ ካርዱን እንዲወስድ የማድረግ ኃላፊነት የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ነው፡፡ በአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህ እየታየ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ማስታወቂያ ሕዝቡ ወጥቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ከሚያደርገው ጥሪና ገዥው ፓርቲ እያደረገ ካለው ጉትጎታ በስተቀር፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ይህ እየታየ አይደለም፡፡ ምርጫው ሲደርስ የቅስቀሳ ዘመቻ የሚደረገው ለማን ነው? ድምፅ ሊሰጡ ይችላሉ የሚባሉ መራጮች የመራጭነት ካርድ ውሰዱ ብሎ የማያሳስብ ፓርቲ በኋላ የማንን ድምፅ ሊጠብቅ ነው? ይኼ በብርቱ መታሰብ አለበት፡፡ እስከ ጥር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ረፋድ ድረስ ሊመዘገቡ ይችላሉ ከተባሉ 35 ሚሊዮን መራጮች ውስጥ ከ23 ሚሊዮን በላይ መመዝገባቸውን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ ከዚያ ወዲህም ይህ ቁጥር ይጨምራል፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቦርዱ የተሰጣቸውን የጊዜ ሰሌዳ እየተከተሉ ሥራቸውን መሥራት ካልቻሉ፣ በመራጮች ምዝገባ እንቅስቃሴ የሚታየው የፓርቲዎች ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ የቻለውን ያህል ዝግጅት አድርጎ ወደ ምርጫው ለመግባት ከቆረጠ፣ መራጩ ሕዝብ የመራጭነት መብቱን እንዲጠቀም ማንቀሳቀስ አለበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መምረጥ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት አካል ስለሆነ ነው፡፡ ይህም በታላላቅ ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች ሳይቀር ተረጋግጧል፡፡ አብዛኞቹ የመብት ድርጅቶች በጋራ የሚቀበሉት የመንግሥት ሥልጣን ለመረከብ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዜጎችን የመምረጥ መብት ማክበርና ማረጋገጥ እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ በማናቸውም ሁኔታ ዘርን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን ወይም አመለካከትን፣ ብሔራዊ ወይም ማኅበራዊ አመጣጥን፣ ንብረትና ሌሎችን አስመልክቶ ልዩነት መፍጠር የለባቸውም፡፡ ለዚህም ነው ድምፅ መስጠት ወይም የምርጫ ተሳትፎ ሁለንተናዊ መብት በመሆኑ፣ ይህ መብት ምክንያቶች እየተደረደሩ መደናቀፍ የለባቸውም የሚባለው፡፡ የአገራችን የዴሞክራሲ መጫወቻ ሜዳ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትምና የፖለቲካ ምኅዳሩ የጠበበ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነትና ተቀራርቦ በጋራ ጉዳዮች ላይ መነጋገር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ችግሮችን ተቋቁሞ ይህ እንከን እንዲወገድ መልፋት የግድ ነው፡፡ የፖለቲካ አንዱ መገለጫ ሰጥቶ የመቀበል መርህ እንደመሆኑ መጠን፣ በተቻለ መጠን ከግጭትና ካላስፈላጊ ትንቅንቅ ወጥቶ የዴሞክራሲን ቡቃያ እንዲያብብ ማድረግ የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብን መብት ማክበርና ተሳታፊነቱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ መራጩ ሕዝብ በራሱ ጊዜ ወጥቶ የምርጫ ካርድ ሲወስድ ማንን እንደሚመርጥ ከፓርቲዎች ቅስቀሳ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ዓለም አቀፉን ልምድ ስናይ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ሥራቸውን የሚጀምሩት መራጩን ሕዝብ ጎትጉተው ከቤቱ ወጥቶ ካርዱን እንዲይዝ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሒደት መምረጥ የማይፈልገውን፣ ማንን መምረጥ እንደሚፈልግ ግራ የተጋባውንና ስለምርጫ ጥቅም ግንዛቤ የሌለውን በመቀስቀስ የራሳቸው ደጋፊ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካኖችና የዴሞክራቶች ትግል የሚጦፈው በእንደዚህ ዓይነቶቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ነው፡፡ የእኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የት አሉ? ወይስ የምርጫ ተሳትፎውን ትተውታል? መልስ የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ እገኛለሁ ብሎ የሚለፍፍ ማንኛውም ፓርቲ፣ መራጮችን የማንቀሳቀስ ተግባር ውስጥ ሳይገባ በነሲብ ውጤት የሚጠብቅ ከሆነ ግራ ያጋባል፡፡ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ችግር አለብን የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መገለጫ የሆነውን ምርጫ ፈጽሞ ሊዘነጉ አይገባም፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ሲፈለግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እገዛ ይፈልጋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ተሁኖም ለሰላማዊ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ስኬት የድርሻን መወጣት ካልተቻለ ለአገር አሳሳቢ ነው፡፡ ምርጫና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ አንድ አካል በሆኑበት በዚህ ዘመን ለዴሞክራሲ ሲባል ምርጫ በሕዝብ በጎ ፈቃድ ሊከናወን ይገባል፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር እንደሚደረገው ሁሉ፣ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ታዳጊ አገሮች የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ ነው፡፡ ምርጫ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚከናወነው ወሳኙ ሕዝብ ድምፁን በነፃነት ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡ ይህንን ነፃነቱን ተጠቅሞ ለምርጫ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲያንቀሳቅሱት ነው፡፡ ሕዝቡ መብቱ ተከብሮ የምርጫ ተዋናይ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥረት ያድርጉ፡፡ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አይኖርም!
- Advertisment -
- Advertisment -