Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግዱ ማኅበረሰብ ያቀረበውን የይዞታ ባለቤትነት ጥያቄ የሚመረምረው ኮሚቴ እየተጠበቀ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የይዞታ ባለቤትነት ዋስትና በሚመለከት የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያነሳውን ጥያቄ መርምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚያቀርብ ኮሚቴ ቢቋቋምም፣ ኮሚቴውን እንዲመሩ የተሾሙት የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አዴሎ ከሥልጣናቸው በመነሳታቸው ኮሚቴው ሥራ ማከናወን አልቻለም፡፡ የኮሚቴውን የውሳኔ ሐሳብ ይጠብቁ የነበሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና በአዲስ አበባ የሚኖሩ ባለይዞታዎች መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ኮሚቴው በፍጥነት ሥራውን አጠናቆ ያቀርባል ብለው የገመቱ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ኮሚቴው በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን ማከናወን ባለመቻሉ የሚጠብቁት መፍትሔ ሊያዘገይ እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአቶ ብርሃኑ ሲሰበሰብ የቆየው ኮሚቴ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተውጣጡ አባላት አሉ፡፡ ይህ ኮሚቴ የሚያከናውናቸው ሥራዎች በንግዱ ማኅበረሰብ አባላት በጉጉት የሚጠበቁ ቢሆንም በተለያዩ የመንግሥት ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎችና አስቸኳይ በተባሉ ሥራዎች ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሥራዎቹን ማጠናቀቅ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ከኃላፊነት በመነሳታቸው ኮሚቴው መሰብሰብ አልቻለም፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ኮሚቴውን የሚመራ ሰው እያፈላለገ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለዚህ ኮሚቴ መቋቋም ዋነኛ ምክንያት የሆነው፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በመልሶ ማልማት የሚነሱ ነባር ይዞታዎች ጉዳይ ነው፡፡ ከአሥር ወይም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣት የሚችሉ ይዞታዎች፣ በልማት ምክንያት ሲነሱ የሚከፈላቸው ካሳ ከሁለትና ከሦስት መቶ ሺሕ ብር ያልበለጠ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በአገሪቱ ያለው የይዞታ ባለቤትነት ጉዳይ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ግብይቱ ሊፈጸም ይገባል የሚል ጥያቄ ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት አስጠንተው ለንግድ ሚኒስቴር አቅርበዋል፡፡ በኮሚቴው የሚቀርበው የውሳኔ ሐሳብ በግሉና በመንግሥት የምክክር መድረክ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በምክክር መድረኩ የሚወሰነው ውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ አቅጣጫ እንደሚሰጥበት መረጃው ያሳያል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይህንን ችግር እንዲፈታ ለንግድ ሚኒስቴር ኃላፊነቱን የሰጠ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ ንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ በአቶ ብርሃኑ የሚመራውን ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ኮሚቴው የሚያመነጨው የውሳኔ ሐሳብ በቀጣዩ የይዞታ ክፍያ ላይ የራሱ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ፣ የንግዱ ማኅበረሰብና ባለይዞታ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚጠብቁት ሆኗል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ የበጀት ዓመት ከ111 ሔክታር በላይ መሬት ላይ ያረፉ ቤቶችን በማንሳት የመልሶ ማልማት ለማካሄድ አቅዷል፡፡ ከዚህ ቦታ ላይ የሚነሱ ባለይዞታዎች የኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ትልቅ ዋጋ እንዳለው እየተናገሩ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች