Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በስንዴ ዱቄት እጥረት የሚሰቃዩት የቤንሻንጉል ጉምዝ ነዋሪዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግና የኑሮ ውድነት ግሽበትን ለመከላከል፣ ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ፣ በተመጣጣኝና አነስተኛ ዋጋ የስንዴ ዱቄት፣ ስኳርና ዘይት እንዲከፋፈሉ የዘረጋው አሠራር ቢኖርም፣ እየደረሳቸው እንዳልሆነ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ነዋሪዎቹ የሚያቀርቡት አቤቱታ ትክክል መሆኑን አረጋግጦ፣ ችግሩ የተፈጠረው የማከፋፈል ሥራው ለአንድ ድርጅት በጥቅል (በሞኖፖሊ) በመስጠቱ ነው ይላል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት ችግሩ መፈጠሩን ሰምተው ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እንዲደረግ ያደረጉ ቢሆንም፣ በጥናቱ መሠረት ግኝቱ ላይ ውይይት ማድረግ እንደሚቀራቸው አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በተለይ በመተከልና ካማሽ ዞኖች፣ በማንዱራ ፓዌና ሌሎችም ወረዳዎች ላይ የሚኖሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሦስት ዓመታት በፊት የማከፋፈል ሥራው እንደተጀመረ ጠቁመው፣ ለሁለትና ሦስት ወራት ብቻ እንዲያገኙ ከተደረገ በኋላ መቆሙን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴ ዱቄት፣ ስኳርና ዘይት በክልሉ እየተከፋፈለና ኅብረተሰቡም ተጠቃሚ መሆኑን በመገናኛ ብዙኃን ሲናገር የሚሰሙ ቢሆንም፣ እነሱ ግን ምንም የሚያገኙት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ስኳርና ዘይቱ ቀርቶባቸው ለልጆቻቸው የዕለት ቁርስ የሚሆነውን ዱቄቱን እንዲሰጧቸው ለወረዳ ሹሞች በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ምላሽ አለማግኘታቸውን የዞኖቹ ነዋሪዎች አቶ መሐመድ ኑሩ፣ አቶ ታዬ ኃይሌና ወ/ሮ መሠረት አስፋው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ መንግሥት እየተከፋፈለ መሆኑን በተደጋጋሚ መስማታቸውን ነገር ግን የወረዳዎቹ ነዋሪዎች የሚያገኙት እንደሌለ እስከ ዞን ድረስ በማመልከት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ‹‹እጥረት ስላለ በዚህ ወር አይመጣም፣ በቀጣይ ወራት አንድ ላይ ተደምሮ ድርሻችሁን ትወስዳላችሁ፤›› እየተባሉ ዓመታት መቆጠሩን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ጉምጉምታ ሲበዛ አልፎ አልፎ፣ በየወሩ ሊከፋፈሉት ይገባ ከነበረውና ከተመደበላቸው 800 ኩንታል ስኳር፣ 1,790 ኩንታል የስንዴ ዱቄትና 262,400 ሊትር ዘይት ውስጥ ሩቡን እንኳን ማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት ተባብረው የስንዴ ዱቄቱ እንዲደርሳቸው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይ በተጠቀሱት ዞኖችና ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታና አቤቱታ በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ፕሬዚዳንት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊው አቶ ባበከር ሀሉፋ አብደላ በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፣ መንግሥት በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኙት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ የስንዴ ዱቄት እንዲሸጥ ወስኖ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ክልሉም በሦስት ዞንና 20 ወረዳዎች ያሉትና የሕዝቡም ብዛት ከፍተኛ ነው፡፡ የስንዴ ዱቄት ከማይደርስባቸው ዞኖች መካከል ካማሽ ዞን በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ለችግሩ ዋናው ምክንያት የስንዴ ዱቄቱን የሚያከፋፍሉ ማለትም መንግሥት ባስቀመጠው ዝቅተኛ ዋጋ ለተጠቃሚው እንዲያደርሱ መመረጥ የነበራቸው ድርጅቶች ሁለትና ከዛ በላይ መሆን ሲገባቸው፣ አንድ ድርጅት ብቻ መደረጉ ትልቅ ስህተትና ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ በክልሉ የስንዴ ዱቄቱ በአግባቡ ለኅብረተሰቡ መድረስ አለመድረሱን እንዲያረጋግጡ የተወከሉ አካላት፣ የተመደበው የስንዴ ዱቄትና የስኳር መጠን በአግባቡ እንደደረሰ የሚገልጽ ደብዳቤ ለንግድ ሚኒስቴር ይልኩ እንደነበር በጥናቱ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡ በተለይ ተወካዮቹ ሐሰተኛ ሪፖርት እየላኩ መሆናቸው ሲረጋገጥ በሰባት አመራሮች ላይ ዕርምጃ መወሰዱንና ሁለት አመራሮችን ደግሞ ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ መደረጋቸውን አክለዋል፡፡ ቢሮው ጥናቱን ካስጠናና ውጤቱን ካወቀ በኋላ፣ የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዱቄት አቅራቢው ድርጅትና በተወካዮቹ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ሪፖርት በማድረግ በግልባጭ ለንግድ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሕዝቡ ላይ የደረሰውን በደልና በሕዝቡ ስም የሚቀርብንና መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየገዛ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጠውን የስንዴ ዱቄት በአቅራቢነት የተመረጠው አልቀመር ዱቄት ፋብሪካና ተወካዮቹ የት እንዳደረሱት መጠየቅ ሲገባው፣ የሕዝቡን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው አቅራቢው ፋብሪካ ሊቀጥል ይገባል ብሎ መወሰኑን አቶ ባበከር ጠቁመዋል፡፡

የኮሚሽኑ ውሳኔና እንቅስቃሴ ግራ ስላጋባቸው እየተደረገ ስላለው ሁኔታ በግልጽ በማስረዳት ንግድ ሚኒስቴር አቅጣጫ እንዲሰጣቸው በደብዳቤ ሲያሳውቁ፣ ‹‹እርግጠኛ ከሆነ ዕርምጃ መውሰድ ይቻላል፤›› የሚል ምላሽ ለቢሮው መስጠቱን አቶ ባበከር ገልጸዋል፡፡ ሌላ ድርጅት አወዳድረው እንዲመድቡም አቅጣጫም ጠቁሞ እንደነበር አክለዋል፡፡

ነዋሪው በተደጋጋሚ ብሶቱን እያሰማ ስለነበር፣ በመልካም አስተዳደር ችግር ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊዞር ይችላል የሚል ሐሳብ ውስጥ በመግባታቸው፣ አልቀመር ዱቄት ፋብሪካን በማገድ ሌላ አቅም ያለውና በቀጣይ ሌሎች ድርጅቶችን አወዳድረው እስከሚመድቡ አንድ ድርጅት መመደባቸውንም ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አዲስ የተመደበው ድርጅት በአግባቡና መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በጥሩ ሁኔታ እየሠራ እያለ፣ ቀመር ዱቄት ፋብሪካ ለንግድ ሚኒስቴር በመክሰሱ፣ ንግድ ሚኒስቴር ለክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ አማካይነት አዲስ የተመደበውን አቅራቢ ድርጅት በማገድ ቀመር ዱቄት ፋብሪካ እንዲመለስ ማድረጉን ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በአግባቡ ማድረስ አለማድረሱ ተረጋግጦ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ሸንጋይና ማታለያ ደብዳቤ በመጻፍ ኅብረተሰቡ እንዲጎዳ እያደረገው ያለው ኮሚሽኑ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሊያስተካክል እንደሚገባም አቶ ባበከር አክለዋል፡፡ በተለይ የካማሺ ዞን ነዋሪዎች (በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት) ምንም ዓይነት ስንዴ ዱቄት እያገኙ እንዳልሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጭምር በስፍራው በመገኘት ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በስፋት ተንቀሳቅሶ ያለውን ችግር ማጽዳትና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን ማስፈራራት በመምረጡ፣ ጉዳዩን የፌዴራል መንግሥትና የሚመለከታቸው ኃላፊዎች እንዲያውቁት ማድረግ የቢሮው ኃላፊነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ቢሮው ጉዳዩን ለክልሉ ፕሬዚዳንት ያሳወቀ ቢሆንም፣ ‹‹ድርጅቱ ወይም ባለሀብቱ ምንም አላጠፋም፤ መጠየቅ ያለባቸው ባለሙያዎቹ ናቸው፤›› በማለት ግራ ስላጋቧቸው ፕሬዚዳንቱ በቀረበው ጥናት ላይ ውይይትና ትንተና ተደርጎ ውጤቱ እስከሚታወቅ ድረስ አዲስ የተመደበው ዱቄት አቅራቢ ድርጅት እንዲታገድ ለቢሮው ደብዳቤ በመጻፋቸው፣ አዲሱ ድርጅት ታግዶ ቀመር የዱቄት ፋብሪካ መቀጠሉን አቶ ባበከር ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ጥናት እንዳደረገ በማስመሰልና ፕሬዚዳንቱን በማሳመን፣ ችግሩ የዱቄት አቅራቢው አለመሆኑንና በአግባቡ እያቀረበ መሆኑን በመግለጽ፣ ችግሩን በአመራሩ ላይ በመደፍደፉ፣ በፋብሪካው አማካይነት የሚደረገው ተገቢነት የሌለው ድርጊት መቀጠሉንም አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ክትትል አድርጎ ዕርምጃ እንደሚወስድና ሪፖርት እንደሚያቀርብ ፕሬዚዳንቱን በማሳመኑ፣ ፖሊስ ኮሚሽኑና ዓቃቤ ሕግም ተፅዕኖ ስለተደረገባቸው ዝምታን በመምረጣቸው፣ የሕዝቡ በደል መቀጠሉን የቢሮ ኃላፊው አሳውቀዋል፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በተደጋጋሚ በጠረጴዛ ዙሪያ ከመነጋገራቸውም በተጨማሪ በርካታ ደብዳቤዎችን መለዋወጣቸውን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፣ የቀረበው ሪፖርት በኦዲተሮች ሳይረጋገጥ ዕርምጃ መውሰድ እንደማይችሉ በመናገራቸው፣ እስካሁን ድርጊቱ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን ተጠያቂነት እንደሚያመጣ ሲረጋገጥ፣ በወቅቱ የነበሩትን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ ወደ ሌላ ቦታ እንዲመደቡ መደረጉንም አክለዋል፡፡ በጥናት የተረጋገጠ ሪፖርት የደረሰው ንግድ ሚኒስቴርም ችግሩን ወደ ቢሮው ለማዞር በመንቀሳቀሱ፣ ቢሮው ለጊዜው ዝምታን መምረጡን አቶ ባበከር አስረድተዋል፡፡

ችግሩ እንዳለ የሚገልጽ ጥቆማ ስለደረሳቸው፣ ኮሚቴ አቋቁመው ማስጠናታቸውን የገለጹት ደግሞ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሊ ሀሰን አልአጀብ ናቸው፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ኮሚቴው አሉ የተባሉትን ችግሮች በዞኖቹ ተዘዋውሮ ካጠና በኋላ ሰነዱን ሰጥቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ኮሚቴውን ሰብስበው ማወያየትና መተንተን እንደሚቀራቸው ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩ ከፌዴራል መንግሥት ጋርም ስለሚገናኝ ንግድ ሚኒስቴርን ድጋፍ ጠይቀው እየተጠባበቁ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹አሁን በእኔ ደረጃ ነገሩ እንደዚህ ነው ብሎ ማስቀመጥ ይከብዳል፤›› ብለዋል፡፡ ሥራው ለአንድ ድርጅት በሞኖፖል መሰጠት እንደሌለበት እምነታቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አሻድሊ፣ የቀረበው የጥናት ሰነድ በቅርቡ ውይይት ተደርጎበትና ሰነዱ ተተንትኖ ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በቀረበላቸው የድጋፍ ጥሪና አቅጣጫ ስጡን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ለምን እንደዘገዩ ለማጣራት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው፤›› በመባሉ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች