Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ለመሳተፍ 28 ኩባንያዎች ቀረቡ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ለመሳተፍ 28 ኩባንያዎች ቀረቡ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ለመሳተፍ ሰነድ ከገዙ 77 ኩባንያዎች ውስጥ 28 ኩባንያዎች ተወዳደሩ፡፡ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መንገድ) በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ቢሮ በተከፈተው ጨረታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኩባንያዎች በተናጠልና በሽርክና የመኖሪያ ቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ግንባታውን ለማካሄድ ከተወዳደሩት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች መካከል አፍሮ ጽዮን፣ እንይ ጄኔራል ቢዝነስ፣ ፍሊንትስቶን ሆምስ፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና ዮቴክ ኮንስትራክሽን ይገኙበታል፡፡ ከውጭ ኩባንያዎች ደግሞ ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ በሚዘረጋው የባቡር መስመር ግንባታ ተሳታፊ የሆነው ሲሲኢሲሲ፣ አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ መሠረተ ልማት ሥራዎች በተለይም በሪል ስቴት (ፀሐይ) እና በመስታወት ፋብሪካ የሚታወቀው ሲጂሲ ኦቨርሲስን ጨምሮ በርካታ የቻይናና የአውሮፓ ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡ የተከፈተው ጨረታ ቅድመ ብቃት ምዘና ሲሆን፣ የጨረታው ውጤት ከተተነተነ በኋላ ብቁ ሆነው ለሚገኙ ኩባንያዎች በ15 ቀናት ውስጥ ቀጣይ ጨረታ እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኔብራስ መሐመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለመፍታት በአገር ውስጥ አቅም እንዲካሄድ ያስቀመጠውን መመርያ ከወራት በፊት በድጋሚ መመርመሩ ታውቋል፡፡ በተካሄደው ግምገማ የመኖሪያ ቤቶች ጉዳይ የከተማው ዋነኛ ችግር ቢሆንም፣ ግንባታው በፍጥነት እየተካሄደ ባለመሆኑ የተሻለ አቅጣጫ ሊያዝ ይገባል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህ መሠረት የቴክኖሎጂና የፋይናንስ አቅም ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉና ይህንንም በዋነኛነት እንዲመራ በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ላለፉት ሁለት ወራት ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጨረታውን የከፈተ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ ተሳታፊ ማግኘቱ ታውቋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ጅሎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት ይህንን አቅጣጫ ተከትሏል፡፡ በዚህ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ የሚፈለጉት ድርጅቶች በመኖሪያ ቤት ግንባታ የላቀ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉና የራሳቸው የፋይናንስ ምንጭ ያላቸው ናቸው የሚሉት አቶ ኔብራስ፣ ለሚመረጡት ኩባንያዎች መንግሥት የመሠረተ ልማት አቅርቦት በማሟላት ወደ ሥራ ያስገባቸዋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከተጀመረ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ለተመዝጋቢዎች የተላለፉት አንድ መቶ ሺሕ ቤቶች ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት አንድ መቶ ሺሕ ያህል ቤቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ከ900 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው እተጠባበቁ በመሆኑ፣ ነዋሪዎችን በአፋጣኝ የቤት ባለቤት ለማድረግ አዲስ አሠራር ያስፈልጋል በሚል ይህን አዲስ አቅጣጫ በማስቀመጥ የውጭ ኩባንያዎችን ለማሳተፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...