Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ኩባንያዎች ለሪል ስቴት ልማት ያቀረቡት ጥያቄ ድጋፍ አገኘ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አነስተኛ ከተሞችን ለመገንባት ጥያቄ ያቀረቡ የውጭ ኩባንያዎች ድጋፍ አገኙ፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አምስት የውጭ አገር ኩባንያዎች ያቀረቡትን ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ከመረመረ በኋላ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት እንዲያቀርብላቸው ድጋፉን ሰጥቷል፡፡ ድጋፍ ያገኙት አምስቱ ኩባንያዎች አርቴምስ፣ አስሪኮም ዴቨሎፕመንት፣ ቴክኖ ፊን፣ ካስፕሪንና ኤፍዜድኢ የተባሉ የአውሮፓና የቻይና ኩባንያዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኔብራስ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእነዚህ ኩባንያዎች ፕሮፖዛል ተገምግሞ መንግሥት በሚፈልገው ደረጃ የተገኘ በመሆኑ የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡፡ ‹‹ምክንያቱም መሬት የማቅረብ ኃላፊነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊነት ነው፤›› ሲሉ አቴ ኔብራስ የድጋፍ ደብዳቤ የተጻፈበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ያቀረቡት ፕሮፖዛል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቀባይነት ካገኘ፣ በሰፋፊ ቦታዎች ላይ አንድ ዘመናዊ የከተማ ክፍል ማሟላት ያለበት መሠረተ ልማቶች ያሉት መለስተኛ ከተማ እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡ የእነዚህና የሌሎች የውጭ ኩባንያዎች የመሬት ጥያቄ በቅድሚያ ቀርቦ የነበረው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነበር፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኩባንያዎቹን ጥያቄ ለማስተናገድ የሚያስችለው አቅጣጫ እንዲሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ከመከሩ በኋላ፣ ለኩባንያዎቹ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ኩባንያዎቹ የሚስተናገዱበትን መንገድ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲፈጽም ኃላፊነት ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በበኩሉ በአገሪቱ የሚገኙ የኮንስትራክሽን ዘርፎች ለምሳሌ መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ የመኖሪያ ቤቶችና የውኃ መሠረተ ልማት ግንባታዎች አቅም እንዲያጎለብት ለተቋቋመው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ይህንን ተግባር እንዲያከናውን ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡ በዚህ መሠረት ኢንስቲትዩቱ ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ አቅምና የመሳሰሉ ተያያዥ ጉዳዮችን ከገመገመ በኋላ ለአምስቱ ኩባንያዎች ድጋፍ መስጠቱ ታውቋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች አስተዳደሩ ይሰጣቸዋል ተብሎ በሚጠበቁ ቦታዎች ላይ የሚያካሂዱት ግንባታ ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚሆኑ ተቋማት ማለትም ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ መዝናኛ ማዕከላትና የግብይት ሥፍራዎች ይኖራሉ ተብሏል፡፡ እነዚህ ግንባታዎች ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍል የሚቀርቡ ሲሆን፣ የከተማዋን ገጽታ የመቀየር አቅምም እንደሚኖራቸው ለፕሮጀክቱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች