Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምዜጎቹን መታደግ ያልቻለው የናይጄሪያ መንግሥት

ዜጎቹን መታደግ ያልቻለው የናይጄሪያ መንግሥት

ቀን:

የናይጄሪያው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሐራም በታሪኩ አድርጎት የማያውቀውን ጅምላ ጭፍጨፋ ባለፈው ሳምንት ፈጽሟል፡፡ በናይጄሪያ ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው ባጋ ከተማና በሌሎች 16 ሥፍራዎች ባደረሰው ጥቃት ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎችን ጨፍጭፏል፡፡ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል የዓይን እማኞችን ጠቅሰው ሚዲያዎች ሲዘግቡ፣ የናይጄሪያ መንግሥት ደግሞ ከ150 አይበልጡም ብሏል፡፡ ከጥቃቱ ማምለጥ የቻሉ ደግሞ በሺዎች ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ የናይጄሪያ መንግሥት ወታደሮች ጥበቃ ማድረግ የማይፈልጉበትና መንግሥትም ለምርጫ እንደማይወዳደር ያሳወቀበት ነው፡፡ አካባቢው ለዓመታት ከመንግሥት ተቋማት አስተዳደር ተገልሏል፡፡ የአካባቢው ውጥረት ደግሞ ለቦኮ ሐራም ጥንካሬን ፈጥሮለታል፡፡ እስከዛሬ ማንኛውም አሸባሪ የተባለ ቡድን በአገሮችና በሰዎች ላይ ካደረሰው ጥቃት በበለጠና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሕዝብ ጨፍጭፏል፣ ቤትና ንብረት አውድሟል፡፡ ቦኮ ሐራም በተለይ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ከዚህ የከፋ ጥቃት ሊሰነዝርም ይችላል፡፡ በናይጄሪያ መንግሥት ላይ አይሎ ሕዝቡን ለከፋ ችግር፣ ስቃይና ስደት እንዲዳርግ ብሎም በጅምላ እንዲጨፈጭፍ ዕድል የሰጠው ደግሞ የናይጄሪያ መንግሥት ነው፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከናይጄሪያ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነው ቦኮ ሐራም ጥቃቱን የፈጸመው በናይጄሪያ ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማደናቀፍ ነው፡፡ ቦኮ ሐራም ምንም ዓይነት የነዳጅ ሀብት በሌለበት አካባቢ ጥቃቱን ቢያደርስም፣ ነዳጅ በሚወጣባቸው አካባቢዎች ላይ አላደረገውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን የተወለዱበትና በነዳጅ ሀብት የበለፀገው ገሚሱ የናይጄሪያ ደቡባዊ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ ነው፡፡ በናይጄሪያ ሰሜን ምሥራቅ በአብዛኛው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አካባቢውም የተገለለና ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያልተጋራ ነው፡፡ የቦኮ ሐራም ታጣቂ ቡድን መነሻውም ይህ የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ነው፡፡ ከተገለለውና በድህነት ከታጠረው ሰሜናዊ ክፍል የወጣው ቦኮ ሐራም፣ በናይጄሪያ እየተፍረከረከ ያለውን የተለያዩ ጎሳዎች አብሮ የመኖር ልማድ፣ ዴሞክራሲና ከሃይማኖት ገለልተኛ የሆነ መንግሥታዊ ሥርዓት ይበልጡኑ ለማደናቀፍ በዋና ከተማዋ አቡጃ ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ቦምብ በማፈንዳትና ጥቃት በመፈጸም ለዓመታት ዘልቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ያደረሰው ጥቃትም እ.ኤ.አ. በ2014 አጋማሽ 200 ሴት ተማሪዎችን ሲያግት፣ ተማሪዎቹን ለማስለቀቅም ሆነ ቡድኑን ለመምታት የተደረገው ጥረት አናሳ ከመሆን ጋር የተያያዘ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ቡድኑ በሰሜን ምሥራቅ ቺቦክ ሴት ተማሪዎችን ማገቱ በዓለም ታዋቂ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በመቀጠል የአገሪቱን የሰሜን ምሥራቅ ክፍል መቆጣጠር ችሏል፡፡ ቀጥሎም በሥፍራው ‹‹ካሊፌት›› ማቋቋሙን አሳውቋል፡፡ ይህም አይኤስአይኤስ በመካከለኛው ምሥራቅ መመሥረት የሚፈልገው ‹‹ካሊፌት›› አስተዳደር ነፀብራቅ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ናይጄሪያዊው ምሁር ብራንዶን ኬንሃመር ለቢዝነስ ኢንሳይደር እንደተናገሩት፣ ቦኮ ሐራም በናይጄሪያ መንግሥት ላይ የበላይነት እያገኘ የመጣው አዋጪ ስትራቴጂ ስለቀየሰ ሳይሆን በናይጄሪያ መንግሥት ድክመት ሳቢያ ነው፡፡ ‹‹ቦኮ ሐራም ቀጣናውን ለማፍረክረክ እየጣረ ነው፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት ወታደሮችም ሰሜናዊ ክፍሉን መታደግ አልቻሉም፡፡ ፍላጎትም የላቸውም፡፡ በመሆኑም ቦኮ ሐራም እየመራ ነው፡፡ ማድረግ የሚፈልገውን ሁሉ እያደረገም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ቦኮ ሐራምን ፊት ለፊት የሚከላከሉ ታማኝ የመንግሥት ወታደሮች የሉም ማለት በሚቻልበት በአሁኑ ወቅት፣ ታጣቂዎቹ አሁን ማድረግ ከሚችሉት በላይ መፈጸም ብሎም በርካታ ከተማዎችን እየተቆጣጠሩ መሄድ ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን አላደረጉትም፡፡ ይህም የሚያሳየው የመንግሥት ወታደሮች ጠንካራ ቢሆኑና መንግሥቱም ቦኮ ሐራም በተፈጠረበት የአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ ክፍል ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ መቆጣጠር ይችል እንደነበር ነው፡፡ ቦኮ ሐራም በአሁኑ ጊዜ በናይጄሪያ ሰሜን ምሥራቅ በቻድና በካሜሩን ድንበር አቅጣጫ ተደላድሎ ተቀምጧል፡፡ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ተቆጣጥሮ የያዘውን ቦታ በሚፈልገው መንገድ ያስተዳድራል፡፡ ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ አየር ኃይል ባልደረባ የነበሩት ሩዲ አታላህ፣ ‹‹ቦኮ ሐራም ለረዥም ጊዜ አንድን ሥፍራ ይዞ ለመቆየት መሠረት እየጣለ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህም ከአፍሪካ በጠንካራነቱ ይታወቅ የነበረውን የናይጄሪያ መንግሥት ወታደራዊ ክፍል በሰሜን ምሥራቅ አቅም እንዲያጣ አድርጓል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ቦኮ ሐራም በናይጄሪያ ላይ እንዲጎለብት ካደረጉት ጉዳዮች የናይጄሪያ ፖለቲካና ዋና ዋና ተቋማት በብሔርተኝነት የተተበተቡ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ቀደም በዝግጁነቱና በጠንካራነቱ ይታወቅ የነበረው የአገሪቱ ወታደራዊ ክፍል፣ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተለይም በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ እንደሚፈጽም ይነገራል፡፡ በዚህም ሳቢያ አሜሪካ ለናይጄሪያ ወታደራዊ ክፍል ታደርግ የነበረውን ድጋፍ አቋርጣለች፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት በሰሜን ምሥራቅ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ፍላጎት የለውም፡፡ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታንም ትኩረት ያደረጉት የአገሪቱ የኢኮኖሚ እምብርት ወደሆነውና የትውልድ አካባቢያቸውን የናይጄሪያ ደቡባዊ ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም ቡድኑ በናይጄሪያ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ቀጥሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ብቻ 11 ሺሕ የሚገመቱ ዜጎችን ገድሏል፡፡ ሕፃናት ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት ወንጀል እየተጠቀመባቸውም ይገኛል፡፡ ሆኖም ቡድኑ በናይጄሪያ እያደረሰ ላለው እልቂት በዓለም አቀፍ ሚዲያ የሚሰጠው ሥፍራና ዓለም አቀፍ ምላሽ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በናይጄሪያ ከ2,000 በላይ ሰዎች በቦኮ ሐራም የተጨፈጨፉበትና በፈረንሳይ ‹‹በቫርሊ ኤቢዶ›› ጋዜጣ ዝግጅት ቢሮና በሱፐር ማርኬት በጠቅላላ 17 ሰዎች የሞቱበት የሽብር ጥቃት በአንድ ሳምንት ውስጥ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ሁለቱም ጥቃቶች የደረሱት በእስልምና አክራሪነት በሚፈረጁ ወይም አሸባሪ በሚባሉ ቡድኖች ነው፡፡ ሆኖም በፈረንሳይ ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሰላማዊ ሠልፍ ሲወጡ፣ ከአሥር ሺሕ በላይ ወታደሮችና ከአምስት ሺሕ በላይ ፖሊሶች ከተማዎችንና ወሳኝ ሥፍራዎችን እንዲጠብቁ ተደርጓል፡፡ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ምላሽም ቀላል አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ወሬያቸው ሁሉ ቫርሊ ኤቢዶ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ በናይጄሪያ ከ2,000 በላይ የሞቱበት የቦኮ ሐራም ጥቃት በታዳጊ ሴት ሕፃናት የደረሱ የአጥፍቶ መጥፋት ግድያዎች ያገኙት ዓለም አቀፍ የሚዲያ ዘገባ እዚህ ግባ አይባልም፡፡ የናይጄሪያ መንግሥትም ቢሆን ቦኮ ሐራምን ለመምታት ያሳየው ቁርጠኝነት የተዳከመ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰሞኑን በተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ሲተቹ ነው የሰነበተው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...