Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አቃጥላችሁ አታቃጥሉን!

እነሆ ከቦሌ መድኃኒዓለም ወደ ካሳንቺስ ልንጓዝ ነው። ታክሲያችን ሞልታ እየተንቀሳቀስን ነው። ድንገተኛ ሠርግ አጃቢ መኪኖች መንገዱን ይዘጋጉታል። ሾፌሩ ‘እኔን ካላስቀደማችሁኝ’ አጉል ግብግብ ይገጥማል። “እኔ የምለው ከዚህ ሁሉ ከተማው ላይ ሽር ብትን ከሚል ባለ ‘ሊሞዚን’ ሙሽራ አንድ እኔን የሚጠራ ይጥፋ?” እያለ ወያላው ዕድሉን ያማርራል። ሰው ከመሆን ይልቅ ሰው መተዋወቅ፣ በራስ ጥረትና ድካም በልቶ ከመርካት በሰው ግብዣ መታደም የሚያስመካበት ዘመን ስለሆነ፣ የወያላውን ሮሮ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ ተሳፋሪዎች እርስ በርሳቸው ያጉረመርማሉ። “ያደለው ይጋባል ያላደለው ካልጠፋ ነገር ጉንፋን ይጋባበታል። አይ አንቺ ዓለም! ምፀትና ሸር ረቂቅነቱ!” ስሙልኝ ባይ ብሶተኛ ወጣት ሦተኛው ረድፍ ላይ ይናገራል። “ቆይ ግን በሽንጣም ‘ሊሞዚን’ ለመዳር የሚያስቡትን ያህል ስንቶች ይሆኑ የአብሮነታቸውን ጊዜ ርዝማኔ አረጋግጠው የሚዘምቱት?” ስትል ደግሞ መጨረሻ ወንበር ላይ አንዲት ጦረኛ መሳይ ትዳርን የጦርነት አውድማ ልታደርገው ይዳዳታል። እይታና ፍርድ እንደራስ ነውና ለምን እንዲህ አልሽ ባይ አልተናገራትም። በእንቅብ የናፈቅናት ዲሞክራሲ የእፍኝ የእፍኙ ጊዜ መሥራቷን የወደድነው ይመስላል። ዘመናዊና ቅንጡዎች አጃቢ መኪኖች ተምመው እስኪያልቁ መታገስ ያቃተው ሾፌራችን ከአንደኛው አጃቢ ጋር አፍ እላፊ ይነጋገራል። “ታክሲ አያጅብ ያለው ማን ነው? ግድ የለም ይኼን የኪራይ መኪና መልሰህ ሠልፍ ስትይዝ እንገናኛለን፤” እያለ ከአጭር ጊዜ ተድላ የረጅም ጊዜ ጉስቁልና ሲያስመካው እናያለን። ትዕይንቱ ከዚህና ከዚያ እየተሳፋ፣ በመገረም ላይ ሰቀቀን፣ በፈገግታ ላይ ሐዘን ይሸምናል። የራቀንን ልንደርስበት ያመለጠንን ልንይዘው አስበን መንገድ ብንጀመርም፣ ሕይወት እንዲህ ናትና በየፌርማታው አዲስ ድር፣ አዲስ ታሪክና አዲስ ትውስታ እንፈጥራለን። ጎዳናውና ፍጡራን በጊዜና በሥፍራ ተገድበው የሆኑትንና ያልሆኑትን የሚያጣሩበት ወንፊት ይመስላል። የሚመስለው ግን ያልተረጋገጠው ነገር ብዛቱ፡፡ ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ እናትና ጎረምሳ ልጃቸው አሉ። “እኔ በዚህ ዕድሜ ከተማ ምን አለኝ? ያውስ እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ ዘመን ሰው እንደ ባህር ማዕበል ባነፈሰው አቅጣጫ እየተወራጨ እያየሁ ምን እሠራለሁ? አንተ አለህ ብዬ አይደለም? ትምህርትህን ጨርሰህ ሰው ስትሆን አይሃለሁ እያልኩ እንጂ፣ ከእንግዲህ የነፍሴ ነገር አልነበረም ሊያሳስበኝ የሚገባው? ሲነግሩህ ስማ! አታቃጥለኝ!” ይሉታል። ጉርምስና ዓይነ ልቦናውን ያጨለመበት ታዳጊ በንቀት መንገድ መንገዱን ያያል። ከእነሱ ጀርባ አጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ “አይ ዕድሜ? ልብ አመሻሽ እየታደለ እኮ ስንቱ ሰው ሰው ሳይሆን፣ ስንቱ አገር አገር ሳይሆን ቀረ!” ይለኛል። በዕድሜ አስታኮ ቤተ መንግሥት የመግባት ሙከራውን በዝምታ አከሽፍበታለሁ። ሴትዮዋ ‘አታቃጥለኝ!’ ሲሉ ጆሯቸው የቆመ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ተሳፋሪዎች ደግሞ ስለታሪካዊው የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ መጫወት ጀምረዋል። አንደኛው “እቴጌይቱ በቁማቸው ተቃጥለው ሞቱ። እንዲችው ልባቸው እየሩሳሌምን እንደተመኘ። ለሥልጣን በተሻኮቱ ሰዎች ሴራ በቁም እስር እንዳልተንገላቱ ደግሞ ዛሬ በስማቸው የሚጠራው የአገራችን የመጀመሪያው ሆቴል ተቃጠለ። መቼስ እሳትና ሞት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መቼ ያውቃሉ? ምን ያደረጋል?” ይላል። ከጎኑ የተሰየመች ቀዘባ ተቀብላ፣ “እንኳን እሳትና ሞት መብራትና ውኃስ ሲጠፉ መቼ ያሳውቃሉ?” ትለዋለች ተቻኩላ። “እኔን የሚገርመኝ ደግሞ . . . ” ይላል ሌላው። “የዚህ ታሪካዊ ቅርስ በእሳት መውደም ሳያንስ በጭፍን ጥላቻና አሉባልታ ላይ ተመሥርተው አገር የሚያጫርስ ሰደድ እሳት የሚጭሩት ናቸው። አይገርማችሁም?” ብሎ እጁን አፉ ላይ ይጭናል። የሰው ልጅ የነገር ድር የማድራት ክህሎት እውርን ባለብርሃን ከሚያደርግ አስደናቂ ተዓምር እኩል ያፈዘኛል የሚል ይመስላል በአኳኋኑ። “ይኼ ምን ይገርማል? ዘመኑ እንደሆነ የአጥፍቶ ጠፊዎችና አሸባሪዎች ሆኗል። እንዳለመታደል ሆነና የሰው ልጅ ሥልጣኔን ደረስኩብሽ ሲላት ገልቱነት ተመልሶ እንደ አዲስ አልቅሶ ይወለዳል። ስለዚህ የእኛ ድርሻ ውኃ መሆን ይመስለኛል፤” ትላለች ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠች ወይዘሮ። አንዴ እስኪ የአቶ ከበደ ሚካኤልን ‘እሳትና ውኃ’ ግጥም በቃሉ ሸምድዶ ለክፍል ጓደኞቹ የተወጣ እስኪ እጁን ያውጣ? “እስኪ ሒሳብ ወጣ! ወጣ!” ሳይስበው ወያላው ተኮሳተረ። “እናዓይኔን ልታወጣው ነው? እናንተና መንግሥት ደርሳችሁ ሳንገብርና ሳይርበን የምንኖር ታስመስሉታላችሁ፤” በልጃቸው የበገኑት እናት አንባረቁበት። ወያላው ደንግጦ ወደ መጨረሻ ወንበር ተንደረደረ። እዚያ ደግሞ አንዱ ስልክ እያናገረ ‘ጠብቅ ይሰጥሃል’ ይለዋል በምልክት። “ሁሌ ስደውልልህ ሥራ ላይ ነኝ ትለኛለህ። ብቻውን ሮጦ የሚሸለም አትሌት ያየህ ይመስል። ቆይ የት ለመድረስ ነው?” ይላል በስልክ የሚነጋገረው ተሳፋሪ። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ “ኤድያ! ተወኝ እባክህ። እኛን የሰለቸን ባለቤቱን እንጂ ሌላውን የማያካትት ለውጥ ነው። ሁላችን ዘርተን ጥቂቶች ብቻ ካጨዱና የበይ ተመልካች ሆነን ከቀረን ምን ዋጋ አለው ያለረፍት ቀን ከሌት መልፋቱ? ይልቅ አንዳንድ ቀን እፎይ ማለት ልመድና ሻይ ቡና እንበል፤” ሲል ወዳጁን ይመክራል። ሲያሳንፈው ይሁን ሲያሳርፈው የሚያውቅ ይወቀው። ሌሎቻችን ለወያላው ሒሳብ ሰጥተን መልስ እንቀበላለን። አፍታ ሳይቆይ ሰላማዊ ጉዟችን አደጋ ያንዣበበት መሰለ። ታክሲያችን ፍጥነት ላይ የነበረን እጅግ ዘመናዊ ‘ሬንጅ ሮቨር’ መኪናን ስትሸሽ እግረኛ መንገድ ላይ ወጥታ ቆመች። የአውቶሞቢሉ አሽከርካሪ ትንኝ ባይኑ የገባች እንኳ ሳይመስለው ሞባይሉን ጆሮው ላይ እንደ ጣደ ገላምጦን ተፈተለከ። ሾፌራችን፣ “እንኳን የእኔ ብቻ የማኅበራችን ታክሲዎች በሙሉ ቢሸጡ የማላሠራለትን መኪና እያሽከረከረ እስኪ አሁን ከእኔ ጋር ይጋፋል?” ብሎ ፍረዱኝ ይለን ጀመር። አዛውንቷ፣ “ኧረ እንኳን እሱ አተረፈህ! አለበለዚያማ ሲያገኝ ዓይኑ ከሚገለጠው የሚጨልመው እንደበዛ እናውቃለን። እሱ ልቦና ይስጠን!” ብለው ያፅናኑታል። ትከሻ ለትከሻ ካልተገፋፉ፣ ሰው መሆንና ሠርቶ ማደር ጡረታቸው ብቻ መከበሩ ተሳፋሪውን እያበሳጨው ታክሲያችን ተንቀሳቀሰች። ኧረ ጎዳናውስ ገና ብዙ ሳያስተዛዝበን አይቀርም! ጉዟችን ከመጀመሩ ወዲያው ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆመች። ወያላውና ሾፌሩ በዓይን ብቻ ተያይተው የቆምንበትን ምክንያት አውቀዋል። ጋቢና የተቀመጡ ሴትና ወንድ ተሳፋሪዎች “ምንድነው እሱ?” እያሉ ሾፌሩን በጥያቄ ሲያዋክቡት፣ “ራዲያተሩ ስለተቀደደ ውኃ ያፈሳል። አንዴ ብቻ እናስቸግራችሁ ውረዱ!” ብሎ ያግባባቸዋል። ሌሎቻችን ትዕይንቱን በአትኩሮት እንከታተላለን። ከመቅጽበት ገና እንዳዩት ፅኑ ጠጪነቱን መመስከር የሚችሉለት ወጣት ምርቃትና እርግማኑን እያዥጎደጎደ በተከፈተ መስኮት አንገቱን አስገባ። “ወዮላችሁ ግቡ! አንገት ማስገቢያ ጎጆ ካጣችሁም ሱባዔ ግቡ! እንቢ ካላችሁ ጉድጓድ ግቡ! ለእኛ ፀሐይን ያወጣ አምላክ ለእናንተ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ያውጣላችሁ። ‘ሙዱ’ ካልተሰረቀም ከዚህ አገር ያውጣችሁ። እንደዚህ ታክሲና እንደ ተቃዋሚዎች ትንሽ ተራምዶ ከመቆም ይሰውራችሁ . . .” ወደ ወያላውና ሾፌሩ ዞሮ ደግሞ “ . . . በዳያስፖራ ስናሾፍ ታክሲም አልፎላት በየመንገዱ ውኃ መንጎጨት ጀመረች? አይ ጊዜ! ትንሽ ቆይታችሁ በየቀለበት መንገዱ ‘ባንኮኒ’ ካልተሠራ ብላችሁ ልማት እንዳታደናቅፉ ብቻ! ግድ የለም!” አላቸው። ቀልቡን ወደ እኛ መለሰና ደግሞ፣ “የት ላይ ነበር ያቆምነው? አዎ! ‘ሱፐር ማርኬት’ ለ‘ሱፐር ማርኬት’ መባዘን አቁሙ። ፈረንሳይ የደነገጠችው ‘ሱፐር ማርኬት’ ደጃፍ ላይ ነው። አያችሁ እኛ የእነሱን ሁሉን ነገር ስንኮርጅ እነሱ የእኛን የጉልት ገበያ አልኮርጅም ብለው እኮ ነው እንጂ ሲያንጣጣው መሹለክለኪያ ባላጡ ነበር። ‘ነበርም ለካ እንደዚህ ቅርብ ነው’ አሉ ጣይቱ! እኔን በቁም ልሙትላቸውና። ከቁም ሞት ያድናችሁ። ሞት አንድ ነው። በቁም ከምትሞቱ ለእውነት አንዴ ጠቅላችሁ ሙቱ! ታዲያ መንግሥትን ተቃውማችሁ አላልኩም። ለእውነት ነው ያልኩት! እሺ? እሺ በሉ! እንደ ገዢው ፓርቲ ያለማዳመጥ ክህሎት አታዳብሩ! እ? አዎ! አሜን በሉ! እንደ ጭፍን አማኝ ታዲያ በረባ ባረባው አሜን አትበሉ። ቦምብና ጠበንጃ ሲያስታጥቋችሁ ‘ለምን?’ በሉ!” እያለ ሲያነበንብ ሾፌሩ ታክሲዋን አስነሳ። ወያላው፣ “ዘወር በል ከዚህ ብሎ፤” ሲያባርረው እጁን እያውለበለበ ሸኘን። ነፍሱ ለእውነት ትስከር አልያም ሰውነቱ በመጠጥ ሳናረጋግጥ ራቅነው። መንገድ የማያገናኘው የሰው ዓይነት የለም መቼም! ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አትደማመጡ ሊለን ፈልጎ ይመስላል ሾፌራችን ሬዲዮ ከፍቶ ድምፁን አጉኖታል። በፈረንሳይ ስለደረሰው የሽብር ጥቃት ጋዜጠኞች እየተቀባበሉ ያትታሉ። “ኧረ ቀንሰው በፈጠረህ ይኼ ራሱ ከሽብር ምን ለየው?” ካጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ ይነጫነጫል። ከጀርባችን የተሰየመችው ወይዘሮ የበኩሏን “የደሃና የሀብታም ትከሻ እኩል አለመመዘኑ ሲገርመን ደግሞ ለአደጉ አገሮችና ለደካማ አገሮች እንባ የሚሰጠው የአየር ሰዓት ይበላለጥ ያዘ። አይ አንቺ ዓለም! ምነው ይኼን ያህል? በሽብር ጥቃት ባግዳድ የምትጠፋ ነፍስ ፓሪስ ከምትጠፋው ምኗ ይሆን ሲመዘን የቀለለው? ወይስ የባግዳዱ ቻይና ሠራሽ ነው? መቼም ቻይና የማትሠራው የለም፤” ትላለች። “ኧረ ተይ! በጫማ የተቃጠልነው አንሶ ደግሞ በነፍስ እንቃጠል እንዴ?” ይላል አጠገቧ የተቀመጠ ወጣት። ሰው ይስቃል። “ውይ እንኳንም አንዳንዱን ነገርስ ሰው አይሥራው። እስኪ አስቡት አሁን ልብ፣ ሳንባ፣ ኩላሊት፣ ጉበት፣ አንጎል፣ ወዘተ ሰው ሠርቷቸው ተገዝተው የሚገጠሙ ቢሆን ኖሮ?” ስትል ቀዘባዋ፣ “ምን ዋጋ አለው? ይኼው ሰው የማይሠራውን ሰው እያጠፋው አይደል ፍዳችንን ያየነው። ያልፈጠርነውን የምናጠፋ፣ የማናጠፋውን የምናነድ፣ ያልደከምንበትን የምንዘርፍ፡፡ ግን ሰዎች ስንባል ምን ያለነው ፍጡሮች ነን?” ብሎ ጋቢና የተቀመጠው ተሳፈሪ ተወርውሮ መጨረሻ ወንበር ሊያርፍ ምንም አልቀረው። ታክሲያችን ጥግ ይዛ ወያላው “መጨረሻ” ሲለን የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ ሠልጥኗል በሚባልበት በዚህ ጊዜ እያደር የምናየውና የምንሰማው ሬት ሬት እንዳለን እያወጋን ወረድን። ይኼን ሁሉ ወግ ሲያዳምጥ የነበረ ዝምተኛ ጎልማሳ፣ “እባካችሁ አቃጥላችሁ አታቃጥሉን…” እያለ ዓይኑን ሲያጉረጠርጥ ይኼኔ ነው መሸሽ ብለን ወደየጉዳያችን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት