Thursday, June 20, 2024

የፓሪሱን የሽብር ጥቃት እናወግዛለን!

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሳምንታዊው የሻርሊ ኢብዶ ሳምንታዊ መጽሔት አዘጋጆች ላይ የተፈጸመውን የሽብር ጭፍጭፋ እናወግዛለን፡፡ የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ውስጥ 12 ጋዜጠኞችና ሌሎች ሰዎችን ፍፁም አረመኔያዊ በሆነ መንገድ የጨፈጨፉ ግለሰቦች ምንም ዓይነት ምክንያት ይኑራቸው ሊወገዙ ይገባል፡፡ ሕግ ባለባት አገር ውስጥ ሕገወጦች የፈጸሙት ጭካኔ የሞላበት ድርጊት አስነዋሪ በመሆኑ ደግመን ደጋግመን እናወግዛለን፡፡ መቀመጫውን በፓሪስ ያደረገው ሻርሊ ኢብዶ መጽሔት በዓለም ዙሪያ የሚታወቀው ምፀታዊ የሆኑ ካርቱኖችንና መጣጥፎችን በማተም ነው፡፡ ይህ የግራ ክንፍ አስተሳሰብ አራማጆች የሚያዘጋጁት መጽሔት የተለያዩ እምነቶችን፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦችንና በዓለም ዙሪያ ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦችን አናዳጅ በሆነ አቀራረብ ቢያስከፋም፣ የፈረንሣይ ሕግ ጥበቃ ስለሚያደርግለት ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሥራ ላይ አለ፡፡ ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ጽንፈኛ በሆኑ ኃይሎች የቦምብ ጥቃት ቢፈጸምበትም፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚያስከብረው የፈረንሣይ ሕግ ሁሌም እንደጠበቀው ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም የዳበረ ዲሞክራሲ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ የተቀበለ በመሆኑ፣ በሚዲያው ላይ ችግር ያለባቸው ሰዎችም ሆኑ ተቋማት ቢቻል ተካሄደብን የሚሉትን ስም ማጥፋትም ሆነ ሌላ ጉዳይ ከሚዲያው ጋር እንዲፈቱ ይበረታታሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ ሕግ ፊት ቀርበው ፍትሕ ይጠይቃሉ፡፡ ማንም ሰው ከሕግ በላይ ባለመሆኑ የመጨረሻው ውሳኔ ከፍትሕ አካላት ነው የሚጠበቀው፡፡ በአሁኑ ዘመን እንኳን ምዕራባውያን አገሮች የአፍሪካና የላቲን አገሮች ሳይቀሩ ስም ማጥፋትን ከሕጐቻቸው ውስጥ በማውጣት፣ ለሐሳቦች ሙግት ሜዳውን እያመቻቹ ናቸው፡፡ ይህንን የሠለጠነ አካሄድ መገንዘብ ያቃታቸው ጽንፈኛ ኃይሎች ግን ራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገው የአውሬ ተግባር እየፈጸሙ ነው፡፡ ለዚህም ነው በዓለም ዙሪያ ይህ አረመኔያዊ ድርጊት እየተወገዘ ያለው፡፡ ሚዲያው ላይ የሚንፀባረቁ አስተሳሰቦች ከግለሰቦች አልፈው የኅብረተሰቡን ፍላጎቶች በመወከላቸው የሚፈለጉትን ያህል፣ አልፎ አልፎ የሌሎችን ጥቅሞችና መብቶች ሊጋፉ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ግን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች ቅድሚያ የሚሰጠው በተሰነዘሩት ሐሳቦች ላይ መልስ የመስጠት መብት ተግባራዊ እንዲሆን ነው፡፡ ይህ በሚደረግበት ጊዜ የኅብረተሰቡ ንቃተ ኅሊና ከማደጉም በተጨማሪ፣ ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጠቃሚ ግብዓት ይሆናል፡፡ በሙስና የተዘፈቁ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የእምነት ተቋማት መሪዎችንና የመሳሰሉትን ለማጋለጥ ሚዲያው ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት መንግሥትን ጨምሮ በሁሉም ተቋማት ውስጥ ለማስፈን የሚዲያው ሚና ተተኪ የለውም፡፡ ብልሹ አሠራሮች ተወግደው ነፃ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር ጠቃሚ ናቸው፡፡ በዚህ መሀል ተበድያሁ የሚል ወገን ካለ ሐሳቡን የማንፀባረቅ ሙሉ መብት አለው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረግ አምባገነናዊም ሆነ ሕገወጥ ድርጊት ተቀባይነት የለውም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ ከሰፈሩ መብቶች መካከል አንዱ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ነው፡፡ ይህንን ድንጋጌ ተቀብለው የሕጋቸው አካል ያደረጉ አገሮች በሙሉ ይገዙበታል፡፡ ተግባራዊም ያደርጉታል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሕጋዊ መንገድ ባለመከተል የሚፈጸም ማንኛውም ሕገወጥ ድርጊት ያስወግዛል፡፡ ቮልቴር የተባለው ዝነኛ ፈላስፋ፣ ‹‹የምትናገረውን ሁሉ ባልቀበለውም እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ ድረስ የመናገር መብትህን እከላከልልሃለሁ፤›› ያለው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እንደሆነ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በምልዓት የተቀበለ ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊ ንግግር፣ በዚህ ዘመን በሥልጣኔና በኢኮኖሚ ተመንድገዋል በሚባሉ አገሮች በሥራ ላይ የዋለ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በአገሮቹ ሕገ መንግሥታት ውስጥ ዋስትና በማግኘቱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአገሮቹ ውስጥ የወጡ ሕጐች በሙሉ ሕገ መንግሥቱን መሠረት እያደረጉ ለዚህ የተከበረ መብት ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ የፈረንሣይ ሕግም ለሻርሊ ኢብዶ አዘጋጆች ይህንን መብት ነበር ሲያስከብር የነበረው፣ ያለውም፡፡ ከሕጉ ጋር መናበብ ያቃታቸው አጉራ ዘለል ጽንፈኛ ኃይሎች ግን የወሰዱት ዕርምጃ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ነው፡፡ መወገዝ አለበት፡፡ የሚወገዙት የፈለጉትን እምነት ወይም ርዕዮተ ዓለም በማራመዳቸው ሳይሆን፣ የሐሳብ ነፃነትን በአረመኔያዊ ድርጊት ለመገደብ በመነሳታቸው ነው፡፡ በፓሪስ የሻርሊ ኢብዶ መጽሔት አዘጋጆችና ሌሎች ግለሰቦች ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ የሽብር ድርጊት የምናወግዘው፣ በማንም ጤነኛ አዕምሮ ተቀባይነት የሌለው በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ የተፈጸመ ወንጀል በመሆኑ ነው፡፡ የየትኛውም ዓይነት እምነት፣ የፖለቲካ ሥነ ሐሳብ ወይም ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ነን የሚሉ ሰዎች ሚዲያው ጉዳት አደረሰብን ብለው ሲያስቡ መልሰው መላልሰው ማጤን ያለባቸው ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ መከተላቸውን መሆን አለበት፡፡ ሕጉ በሥራ ላይ እያለ፣ ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ አካል ተሰይሞ በራስ ጊዜ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ መፈጸም አይደለም ለዱላ መጋበዝ አይቻልም፡፡ የሕጉና የፍትሕ አካሉ ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ቢገባ እንኳ የኃይል ተግባር የተወገዘ ነው፡፡ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ መሞገት በሚቻልበት በዚህ በሥልጣኔ ጣሪያ በነካ ዓለም ውስጥ አጉራ ዘለል ተግባር ተቀባይነት የለውም፡፡ የተወገዘ ነው፡፡ ሕግን የማክበር ጥያቄ የተነሳውና በሚዲያው ላይ ትኩረት የተደረገው በፓሪሱ አሰቃቂ እልቂት ምክንያት ሆኖ ነው እንጂ፣ ይህ ጉዳይ በሁሉም የሥራ መስኮችና ዓውዶች ውስጥ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ በሐኪም ተበድያለሁ፣ በዳኛ ተጉላልቻለሁ፣ በፖሊስ ተንገላትቻለሁ፣ በመሐንዲሱ ቸልታ ከስሬያለሁ፣ ወዘተ የሚል ማንም ሰው ለሕግ አቤት ይላል እንጂ በራሱ ጊዜ ዕርምጃ መውሰድ አይችልም፡፡ የሕግ የበላይነት አለ ሲባል ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው ማለት ነው፡፡ ሕጉ አያወላዳም ተብሎ ቢታሰብ እንኳ እስከ መጨረሻው የመንግሥት አመራር ድረስ አቤት ነው መባል ያለበት፡፡ ያለበለዚያ ሁሉም እየተነሳ ጐራዴና ጠመንጃ የሚመዝ ከሆነ ሕገወጥነት ሰፍኗል ማለት ነው፡፡ ሕግን የሚያስከብሩ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ካቃታቸው የሕገወጥነት መሣሪያ ከመሆን አልፈው የሚተዳደሩበትን ሥርዓት ለአደጋ ያጋልጡታል፡፡ ወረበላነት ይሰፍናል፡፡ መገዳደል የየዕለቱ ተግባር ይሆናል፡፡ ይህም መወገዝ አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር በላይ ተማምነን የምንኖረው በሕግ ነው፡፡ በፍትሕ ተደራሽነት ችግር ቢጐረብጠንም፣ የፀጥታ አስከባሪ አካላት ባይመቹንም፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ቢፈታተነንም ‹‹በሕግ አምላክ›› ነው የምንለው፡፡ ሕገወጦችና አጉራ ዘለሎች የፈለገውን ያህል ቢጨፍሩ እንኳ ክፍተት አንሰጣቸውም፡፡ በሕጋዊው መንገድ ተጉዘን እስከ መጨረሻው እንዘልቃለን፡፡ በተለያዩ ሥርዓቶች ውስጥ ያለፈው ሕዝባችን ምንም ያህል ቀንበሩ ቢከብደው ወደ ሕገወጥ ተግባራት ተሰማርቶ እንደማያውቅ ታሪክ ይናገራል፡፡ አሁንም መብቶች እንዲከበሩና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ሕጋዊውን መንገድ አሟጠን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ጉልበተኞች፣ ጽንፈኞችና ሽብርተኞች የሚያከናውኑትን አረመኔያዊ ድርጊት ማውገዝ ያለብን፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ገደብ አይጣልበትም፡፡ ምክንያቱም በሕግ ዋስትና የተሰጠው ከመሆኑም በላይ ተፈጥሯዊ መብት ነው፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሐሳብ ነፃነት መብትን ከማፈን ይልቅ ማስከበር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ነው የፓሪሱን የሽብር ጥቃት የምናወግዘው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ብዛት ያላቸው የኦዲት ክፍተት ግኝቶችን ለፓርላማ አቀረበ

ሪፖርቱ ሲቀርብ የመንግሥት ባለሥልጣናት አለመገኘታቸው ጥያቄ አስነስቷል ለኦዲተሮች የሚመደብላቸው 300 ብር የቀን አበል እንዲሻሻል ተጠይቋል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በባለበጀት የመንግሥት ተቋማት ላይ ባካሄደው...

በአዋጁ በተጀመረው የቤት ኪራይ ውል አከራዮች ከፍተኛ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑ ተከራዮችን አስጨንቋል

 ‹‹በተከራይና አከራይ መካከል ስምምነት ከሌለ አንመዘግብም›› የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤት ኪራይ ውል ምዝገባ በሁሉም ወረዳዎች ማካሄድ ከጀመረ በኋላ፣ አከራዮች ከፍተኛ...

ለግል ባለሀብቶች ከተሰጠው 2.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ እየለማ ያለው 41 በመቶ ብቻ መሆኑ ተነገረ

ለግል ባለሀብቶች ከተላለፈው 2.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ድረስ እየለማ ያለው 41 በመቶ ብቻ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር...