Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እኛን ከምርጫ ሊያስወጣን የሚችል አንዳችም የሕግ ስህተት የለብንም››

አቶ ማሙሸት አማረ፣ የመኢአድ ፕሬዚዳንት

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታኅሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በውስጣቸው የተፈጠረውን ችግር ፈትተው በአስቸኳይ ወደ ምርጫ ውድድሩ እንዲገቡ፣ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ የቀን ገደብ አስቀምጧል፡፡ ይህን የቦርዱን ውሳኔ በተመለከተ የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ባለፈው ዓርብ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው የነበረ ሲሆን፣ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑት ከነምላሻቸው ቀርበዋል፡፡

ጥያቄ፡- ጠቅላላ ጉባዔውን የጠራችሁበት ምክንያት ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. የውስጥ ችግሮቻችሁን ፍቱ ባለው መሠረት ነው፡፡ ከእናንተ በተቃራኒ ከተሠለፉ አካላት ጋር ለመወያየት ወይስ ቀደም ሲል በመግለጫው እንደተጠቀሰው ሁኔታውን ለጠቅላላ ጉባዔው ለማሳወቅ ነው? ምርጫ ቦርድ እንደ ችግር ከዘረዘራቸው ነጥቦች መካከል ለተከታታይ ወራት የፓርቲውን አባልነት መዋጮ ያልከፈለ ሰው ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችልም፣ የጠቅላላ ጉባዔው ምልዓተ ጉባዔ የተሟላ አይደለም፣ ወዘተ የሚል ነበር፡፡ እነዚህን ነጥብ በነጥብ እየጠቀሳችሁ ምላሽ ለመስጠት ሞክራችኋል ወይ?

አቶ ማሙሸት፡- ቦርዱ እኛን ከሚከስበት እንደ ምክንያት ብሎ ከሚያቀርባቸው የመኢአድ አሁን የተመረጠው አመራር አባላት የአባልነት መዋጮ ያልከፈሉ ናቸው የሚል ነው፡፡ እንግዲህ በመኢአድ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የአባልነት መዋጮ የሚከፈልባቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ አንድ ሰው አባል የሚሆነው የአባልነት መዋጮ ሲከፍል ነው ይላል፤ የአባልነት መዋጮውን ከሦስት ወራት በላይ ያለ በቂ ምክንያት ያልከፈለ አባል ይሰረዛል ይላል፡፡ እኛ ግን የአባልነት ክፍያ ያልከፈልነው በበቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱም እዚህ ቤት የነበሩ ሰዎች እኛን በፍርድ ቤት ከሰውን ዕግድ ተጥሎብን ስለነበር ነው፡፡ ወደ መኢአድ ጽሕፈት ቤትም እንዳንንቀሳቀስ በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ ሁሉ እንዳንሳተፍ ውሳኔ ተሰጥቶብን ስለነበር ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ በእንቅስቃሴ ላይ ነው የነበረው፡፡

ስለዚህ የአባልነት ክፍያ ለመክፈል ብንሞክርም ተቀባዩም ወንጀለኛ ስለሚሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ እኛም እንኳንስ ለመክፈል ለመንቀሳቀስም ታግደን የነበረ በመሆኑ የአባልነት ክፍያ ልንከፍል አልቻልንም፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት እነሱ በከሰሱ ጊዜ ያንን ዓይቶ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ከአባልነት መታገድም፣ መባረርም፣ ልንሰረዝም እንደማንችል ፍርድ ቤቱ ውስኔ ሰጥቶበታል፡፡ ውሳኔው ደግሞ ለምርጫ ቦርድ በአድራሻው ከፍርድ ቤት ተሰጥቶታል፡፡ ይኼንኑ የፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲችል መጋቢት 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ለመኢአድ በጻፈው ደብዳቤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚ ለማድረግ ጠቅላላ ጉባዔያችሁን ጠርታችሁ እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ እንድታሳውቁ፣ ማኅተሙንም በጊዜያዊነት ለዚህ ብቻ ነው የምትጠቀሙበት የሚል ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከዚህ በኋላ ይኼ ሆኖ ሳለ እነሱ ይህንን ባለመቀበላቸው ምክንያት ከሐምሌ 13 እስከ 14 ቀን 2005 ጠቅላላ ጉባዔ ጠሩ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ 281 የሚሆኑ የፓርቲው የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ስላልተጠሩ ይኼ በቦርዱ እጅ ላይ ከነበረ፣ በእኛም በፒቲሽን ተፈርሞ የገባ ስለነበረ ምልዓተ ጉባዔ ሳይሟላ ቀርቷል፡፡ ስለዚህ ከኅዳር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ቦርዱ በተደጋጋሚ ወደ አሥር የሚደርሱ ደብዳቤዎች መኢአድ ምልዓተ ጉባዔውን የተሟላ አድርጎ እንዲገኝ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ መሠረት መኢአድ የውስጥ ችግሮቹን እንዲፈታ ከጥቅምት 28 እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔውን በአስቸኳይ ጠራ፡፡ ይኼ እንግዲህ በመሆኑ የውስጥ ችግሩን ለመፍታት በመጀመሪያ የተሄደበት በሁለቱ ወገን የነበረውን አመራር ማስማማት ነበር፡፡ ወደ ጠቅላላ ጉባዔው መግባት ነበር፡፡ ስለዚህ በላዕላይ ምክር ቤት ጠሪነት ጠቅላላ ጉባዔው ተከናወነ፡፡ በላዕላይ ምክር ቤቱ ላይ የእኛ ጉዳይ ተነሳ፡፡ ላዕላይ ምክር ቤቱ መወሰን ስለማይችል መወሰን ወደሚችለው ጠቅላላ ጉባዔ ጉዳዩን አቀረበው፡፡ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የመጀመሪያው አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የፓርቲው የውስጥ ችግር ነበረ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ያንን ጉዳይ በዝርዝር ዓይቶ ያለምንም እንከን ያገዳችሁአቸው ትክክል አልነበረም፣ ለማባረር የወሰናችሁትም ትክክል አልነበረም፣ እኛ ሳናውቀው ይህንን ማድረግ ስለማትችሉ ጠቅላላ ጉባዔው በሙሉ ድምፅ እርቅ እንዲፈጸም አድርገናል፣ እስካሁን የሄዳችሁበት መንገድ በሙሉ ውድቅ አድርገናል ብሎ ይኼን ተቀብሏል፡፡ ለዚህም ውሳኔውን አረጋግጧል፡፡

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ወደ አመራር ምርጫ የተሄደው፡፡ በመጀመሪያው ሥራ ይህ ውይይትና ስምምነት ከተፈጠረ በኋላ ወደ አስመራጭ ኮሚቴ ነው የተሄደው፡፡ ይህም መተዳደሪያ ደንባችን ላይ ከጠቅላላ ጉባዔው ውስጥ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ይመረጣል ስለሚል አባላቱ የሚወክላቸውን አምስት በአስመራጭ ኮሚቴ አባላት መረጡ፡፡ ከዚህ በኋላ ቃለ ጉባዔ ያዥ የሆኑትን ሰዎች መረጡ፡፡ ቆጣሪዎችን መረጡ፡፡ በኋላም ሒደቱ ወደ ላዕላይ ምክር ቤት ነው ያመራው፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ አንደኛ ምልዓተ ጉባዔ አልተሟላም የተባለው ቦርዱ የራሱ ሰዎች ምልዓተ ጉባዔው የተሟላ መሆኑን፣ የላዕላይ ምክር ቤቱ ምርጫ ሲከናወን እስከ ማታ ሁለት ተኩል ሰዓት ድረስ ታዝበው እንደሄዱ ሪፖርት አቅርበውለታል፡፡ ቦርዱም ይህንን አምኗል፡፡ ከዚህ በኋላ እንግዲህ ጠቅላላ ጉባዔው ሲጠራ ቦርዱ የተጠራው ከጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ነው የሚለው፡፡ ጉባዔው እንዳላለቀ እያወቁ እነርሱ ነን እንመጣለን ብለው ከ2፡30 ሰዓት በኋላ ወደቤታቸው ሄዱ፡፡ ይህን በተመለከተ በማግሥቱ እንደሚመጡ አረጋግጠውልን ነበር፡፡ እኛ ሥራችንን ቀጠልን፡፡ የላዕላይ ምክር ቤቱ ሁኔታ ማለቁንና መጠናቀቁን እነሱ አረጋግጠዋል፡፡ በማግሥቱ ስንደውልላቸው ትናንት በሄደው ሒደት መቀጠል ትችላላችሁ እኛ ናዝሬት ለሥልጠና ተጠርተን ወደዚያ ስለሄድን ሒደቱን በትናንትናው መሠረት አድርጋችሁ ቃለ ጉባዔውን ለቦርዱ አስገቡ አሉን፡፡ እኛም ምርጫችንን አካሄድን፡፡

ስለዚህ አሁን ምርጫ ቦርድ ችግር ውስጥ እየገባ ያለውና መኢአድን የሚያወዛግበው የጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለምን ቢባል ማኅተሙ መወሰዱን አረጋግጧል፡፡ አንድ ግለሰብ ነው ማኅተሙን የወሰደው፡፡ ስለዚህ የጠቅላላ ጉባዔው አባላትን ውሳኔ ሽሮ ግለሰቡ ማኅተሙን ይዞ መሄዱን ራሳቸው በውይይታችን አውቀዋል፡፡ ማኅተሙን የወሰደው ግለሰብም ወስጄዋለሁ ብሎ አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ እኛ ያንን ለፖሊስ አመልክቱ ስለተባልን ፖሊስ መጥፋቱን አረጋግጫለሁ፣ ክትትል እያደረግኩ ነው አለ፡፡ ክትትሉ ቀጠለ፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ ማኅተም በትብብር እንድናስቀርፅ ፖሊስ ከሰጠን በኋላ ለምርጫ ቦርድ ወስደን ሰጠን፡፡ ነገር ግን አርባ ቀናት ሙሉ መልስ አልሰጡንም፡፡ እስካሁንም ድረስ የሚጽፉልን ደብዳቤም ሆነ የሚሰጠው መግለጫ የቃለ ጉባዔውን ሪፖርት ሳይመለከቱ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የሄድንበት የሕግ አግባብ አንድም ስህተት የለውም፡፡

ጥያቄ፡- አሁን እናንተ በፍርድ ቤት በኩል ነው እየሄዳችሁ ያላችሁት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀድሞ ፓርቲውን ሲመሩ የነበሩት እነ አቶ አበባው መሀሪ ጠቅላላ ጉባዔ ሲያደርጉ ያቀረቡትን ሪፖርት ነው ምርጫ ቦርድ እንደተቀበለ መረጃ አለ ይባላል፡፡ ለምንድነው ምርጫ ቦርድ የእናንተን መረጃ ያልተቀበለው? ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው ትላላችሁ? ከዚህ ጋር በተያያዘ መኢአድ ከምርጫ ውጪ ቢሆን የመጨረሻ ውሳኔያችሁ የሚሆነው ምንድነው?

አቶ ማሙሸት፡- በመጀመሪያ በመርህ ደረጃ ስለሕግ ነው የምናወራው፡፡ ስለሕግ እናውራ ካልን ደግሞ አቶ አበባው በምንም ዓይነት ሁኔታ የሕግ መሠረት የላቸውም፡፡ ቦርዱም ቢሆን በሕግ ነው የሚሠራው፡፡ ፍርድ ቤትም ቢሆን በሕግ ነው የሚሠራው፡፡ አቶ አበባው በጠቅላላ ጉባዔው ፊት 485 አባላት በተገኙበት የጻፉት የመልቀቂያ ደብዳቤ በተራ አባልነት እንደሚቀጥሉ በአስመራጭ ኮሚቴው አማካይነት ተነቦ፣ የጠቅላላ ጉባዔ አባላቱ አቶ አበባውን በጭብጨባ ሸኝቷቸዋል፡፡ ስለዚህ ቦርዱ አቶ አበባውን ጠርቶ የሚያነጋግርበትም ሆነ የእሳቸውን ቃለ ጉባዔ የሚቀበልበት ምንም የሕግ መሠረት የለውም፡፡ ያንን በምልዓተ ጉባዔው ፊት ጽፈውት ያቀረቡት ደብዳቤ ተቀባይነት ማግኘቱን የቦርዱ ታዛቢዎች ተመልክተዋል፡፡ አቶ አበባውም በክብር ወደ ቤታቸው ተሸኝተዋል፡፡ ሲሄዱ ግን ማኅተሙን ይዘው ሄደዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወንጀል ነው፡፡ የድርጅት ማህተም በምንም ዓይነት በግለሰብ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ቦርዱም ይህንን ሕገወጥነትን ማጠናከር አይገባውም፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ባሉበት ማኅተሙ እኔ ዘንድ ነው ያለው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ቦርዱ ያን ዕለት ማድረግ የነበረበት ይህን የድርጅት ማኅተም ይዘህ መሄድ አትችልም፡፡ ችግር ካለብህ ችግርህን በውይይት ፍታ፡፡ አለበለዚያ ደግሞ በሕግ አግባብ ፍታ ማለት ሲገባው፣ ይህን ሰምቶ ዝም ያለው ቦርዱ ነው፡፡ ስለዚህ ግለሰቡን የማነጋገር የሞራልም፣ የታሪክም፣ የሕግም ብቃት የለውም ብለን ነው የምናምነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ ውሳኔ የፖለቲካ ውሳኔ ነው ወይ ለሚለው በትክክል የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ የሕግ አግባብማ ቢሆን ኖሮ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚሻረው በፍርድ ቤት ነው፡፡ የእኛ ግን የፍርድ ቤትን ውሳኔ ሊሽር የተነሳው ቦርዱ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት አለ እየተባለ በሚነገርበት አገር ላይ ይህ ከሆነ የሕግ አግባቡ በሙሉ ገደል ገብቷል ማለት ነው፡፡ አሁን እየተወሰነብን ያለው ውሳኔ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡

በሌላ በኩል መኢአድ ከምርጫ ቢወጣ ምን ታደርጋላችሁ ለሚለው ሲጀመር መኢአድ ከምርጫ እንቅስቃሴና ውድድር ሊያስወጣው የሚችል የሕግ ስህተት የለበትም፡፡ አንድ ፓርቲ ከምርጫ እንቅስቃሴ ሊገደብ ወይም ሊከለከል የሚችልባቸው የምርጫ ቦርድ አዋጆች ተተንትነው ተቀምጠዋል፡፡ ያለአግባብ ሰላማዊነቱን ባልጠበቀ ሒደት ሲንቀሳቀስ፣ ከተቋቋመለት ዓላማ ውጪ የጦር መሣሪያ ለሌላ ነገር ይዞ ሲሄድ፣ ወዘተ ነው፡፡ እኛ ግን በሰላማዊ መንገድ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ የተቋቋምንበት መንገድ ሰላማዊ ነው፡፡ የምናደርገውም እንቅስቃሴ በሰላማዊ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ለመያዝ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሆኖ ቦርዱ የፖለቲካ ውሳኔ ቢወስን እኛ ደስታውን አንችለውም፡፡ ተጠቃሚው ማን እንደሚሆን ደግሞ ወደፊት ይታያል፡፡ እኛን ከምርጫ ሊያስወጣን የሚችል አንዳችም የሕግ ስህተት የለብንም፡፡ ነገር ግን በምርጫው አትወዳደሩም ቢለን ማን ይጠቀማል? ማን ይጎዳል? እርሱን ከሕዝባችን ጋር እንመክራለን፡፡ ወደፊት ደግሞ እናየዋለን፡፡ አሁን ውሳኔ ባልተሰጠበትና ባልተከለከልንበት ምርጫ አትወዳደሩም ባልተባልንበት ይኼ ነው ለማለት አንችልም፡፡

ጥያቄ፡- በአቶ አበባው የሚመሩ የመኢአድ አባላት ከአንድነት ፓርቲ ጋር በጋራ ለመሥራት ደብዳቤ አስገብተዋል የሚል ዘገባ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚያ በኩል እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ማለት ነው? በእናንተ በኩል ተመሳሳይ ፕሮግራምና ዓላማ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የምታደርጉት እንቅስቃሴ ምንድነው?

አቶ ማሙሸት፡- ሲጀመር አንድነት እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ይቀበላል ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም የአንድነትና የመኢአድ ውህደት የከሸፈበት ዋነኛ ምክንያት እዚህ ቤት በነበረው ውሸት ነው፡፡ ለምን ቢባል ሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔው ባለመሟላቱ ውድቅ ሆኗል ተብሎ በተከታታይ አሥር ደብዳቤዎች ተጽፈዋል፡፡ በሐሰት ሕጋዊ ፕሬዚዳንት ነኝ ብሎ ሲሄድ የነበረ ግለሰብ ሰኔ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ መሠረት ውህደቱ መቋረጡን ያውቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ሕጋዊ ነን ብለው ነሐሴ 3 እና 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ውህደት እናደርጋለን ማለታቸውና ቦርዱ ውህደቱን ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከዚያ በኋላ አንድነት እዚህ ስህተት ውስጥ እንዲያውም አሁን ደግሞ ደብዳቤ ጽፎ ከተራ አባልነት ውጪ ሌላ ኃላፊነት አልቀበልም ብሎ ያለን ግለሰብ እንደ ቡድን ወይም እንደ ፓርቲ መሪ ይቀበላል የሚል የሞኝ አስተሳሰብ የለንም፡፡ ይኼ ተራ አሉባልታ ነው፡፡

እኛ ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በኅብረትም፣ በቅንጅትም፣ በውህደትም ለመሥራት ሁልጊዜ ክፍት ነን፡፡ አንድ ፓርቲ ብቻውን በመሄዱ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፡፡ ለምን ቢባል አስርም ሃያም ፓርቲ ቢኖር አንድ የምርጫ ውድድር የሚደረግበት የምርጫ ክልል ላይ አሥር ፓርቲዎች ስንወዳደር፣ ኢሕአዴግ ለብቻው ቢገባና ቢወዳደር በእርግጠኝነት ሁላችንንም ያሸንፈናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ያገኘነውን ድምፅ ለዘጠኝ ለአሥር ነው ይዘን የምንሄደው፡፡ ኢሕአዴግ ግን ያገኘውን ድምፅ ለአንድ ለኢሕአዴግ ነው ይዞ የሚሄደው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...