Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሚድበሰበሱ ችግሮች እንዳያጠፉን!

ሰላም! ሰላም! “እዩዋት ስትናፍቀኝ…” አለ ዘመን አይሽሬው ድምፃዊ። የሰሞኑን ጉዴን እኮ ስላላያችሁ ነው። ውዷ ማንጠግቦሽ አጠገቤ ተቀምጣ ሩቅ ምሥራቅ የተሰደደች ያህል ልቤን ሲነዝረኝ ሰነበትኩ። ቢቸግረኝ የባሻዬን ልጅ፣ “የዛሬን ባይሆን ኖሮ እውነቴን ነው የምልህ ‘እዩዋት ስትናፍቀኝ’ የሚለው ግጥም የእኔ ነው ብዬ ፍርድ ቤት እቆም ነበር፤” እለዋለሁ፣ “እንደቆምክ ትቀራለህ እንጂ ከምናየውና ከምንሰማው እሮሮ አንፃር ፍትሕ አግኝተህ አትቀመጥም፤” ብሎ ‘ሙዴን’ ገደል ሰደደው። በዚህ እንደ አዲስ ፍቅር አገርሽቶብኝ ስጨነቅ በዚያ እሱ ጊዜ ይፍታው ብለን የተውነውን ነገር እየቆሰቆሰ ሲያስበረግገኝ ሰነበተ። ሰው ምናልባት እንዲህ ለነገር ‹‹3G›› እንደሚሆነው ለሥራና ለልማቱም ቢያውቅበት? እውነቴን እኮ ነው። እኔ አንዳንዴ ‘ኔትወርክ የለም’ ሲባል የማልስማማው ለዚህ ነው። ለበጎ ነገር ከምንጠቀምበት ለክፋትና ለተንኮል ፍጆታ ማዋላችን እንጂ፣ የእኛን የመሰለ ‘ኔትወርክ’ እነ አሜሪካም የላቸው። አደራ ደግሞ የስልኩን እያልኳችሁ መስሏችሁ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ እንዳትወረውሩኝ፡፡ አጣራ ካላችሁም ደግሞ የግብዣ ወረቀት አስልኩልኝና ደርሼ እመጣለሁ። ምነው ይቀራል ብላችሁ ሰጋችሁ መሰል? እንዴት አትሰጉ? ሳር ቅጠሉ፣ አገር ምድሩ ቢችል ሊሰደድ ካልቻለ ሊሸኝ አሰፍስፎ እያያችሁ እንዴት አትሰጉ? ነግሬያችሁ እንደሆነ እንጃ፣ አንድ ወዳጄ አሜሪካ ካልሄድኩ ብሎ አፍንጫችን ላይ ቆመ። እኔ አንዳንዱ ሰው አናትና አፍንጫ ላይ ምን ነገር እንዳለው አላውቅም። ኋላ ሞክሮ ሞክሮ ወደ አሜሪካ መሄድ ቢያቅተው ወደ አሜሪካ ግቢ ተጠመዘዘ። አንዳንዱ ሰው እኮ የሕይወት ‘ኩርባ’ የሌለው ይመስላል። ውሎ አድሮ መክረን ያቃተንን ወዳጃችንን ተሰብስበን ስናማው፣ “እዚያች ምድር ላይማ የሆነ ድግምት አለ፤›› አለን፡፡ ቀልባችንንና ዓይናችንን የሳበውን ሁሉ የጀርባ ታሪኩን ሳናስፈቅድ መጻፍ ጥርስ የነቀልንበት ክፉ ልማዳችን ነዋ። ልማታችን ይኼንንም ቢዳስስ ደስ አይልም? ምን ዋጋ አለው? እሴት ገንዘብ ብቻ ሆኖ እኮ ነው ነገር ዓለሙ የተሳከረብን። ቅድም ‹‹3G›› ስል ሰሞኑን አንዱ የባሰበት ስልኬን መነተፈኝና ሲም ካርዴን ላወጣ ቴሌ ጎራ ብዬ ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ። የስልኬ መሰረቅ ብዙም እንዳላበገነኝ የታዘቡ፣ እንደ ደርቢ የሰው ሕይወት አፍጥጠው ሲከታተሉ የሚውሉ ምስኪኖች፣ “እሱ ምን አለበት? ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የያዘውን ይዞ ነው። ዕድሜ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ…” ብለው ሲያሙኝ ሰማሁ። እስኪ አሁን አብዮትን ዲሞክራሲ ውስጥ ምን እንደ ዶለው በቅጡ ሳይገባን፣ የእኔ ስልክ መጥፋትና ዘና ማለት ሐሜት ውስጥ ደግሞ ምን ያመጣዋል? የቸገረ ነገር እኮ ነው ዘንድሮ! በበኩሌ ከአንድም ሁለት ሦስቴ የሞባይል ቀበኛ ጥሩ ትምህርት ስላስተማረኝ (በአንዴ ተምረን ብንታረምማ ስንት ነገር በተስተካከለ) ከአንዲ ሺሕ ብር የስልክ ቀፎ ዘልዬ አላውቅም። በዚህም፣ “ደርሶ የሌለው መምስሰል! ስንት ዓመት እኖራለሁ ብሎ አስቦ ነው?” ተብያለሁ። መባባል አይደል የውሎዋችን ትርፍ? ሌላማ ምን አለን? “ምነው እንዳፋቸው ባደረገልህ? ዘንድሮ ሰው ራሱን ከሚያውቀው በላይ ሆኗል ሌላው የሚያውቀው፤” ትለኝ የነበረው ውዷ ማንጠግቦሽ ናት። ስታፅናናኝ ብፅናናም ዳሩ ለገና የሠራችው ያለቅጥ በርበሬ የበዛው ዶሮ ወጧ ቅር አሰኝቶኝ ነበር። (ተመልከቱማ በአንድ ልቤ እያየሁዋት መራብ በአንዱ ደግሞ ማኩረፍ። ወይ ፍቅር!) ‘እንኳን አደረሳችሁ’ ሊል የመጣ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ሁለቴ ሦስቴ ይጎርስና፣ “አንበርብር የበርበሬ እርሻ ጀመርክ እንዴ?” ብሎ ሲጠይቀኝ ከስልኩ ሐሜት ጋር ተደምሮ ሰማይ ጠቀስ ትችት እንዳይገነባ ተሳቅቄ ሞትኩ። ይገርማችኋል! ያደለው ያልታደለውን አፈናቅሎ ሰማይ ጠቅስ ሕንፃ ይገነባል፣ አዳሜ ሰማይ ጠቀስ የሐሜት ብሎኬት ይደረድራል፡፡ ለነገሩ ይኼም አለመታደል ነው። ወደ ቁም ነገሩ ስመልሳችሁ. . . ወየት ሄጄ ነበር? . . . ቴሌ። ይቅርታ እንግዲህ ጨዋታዬ ከተቆራረጠባችሁ ቴሌ ተንፍሶብኝ እንደሆነ መጠርጠር ብቻ ነው። ምነው? በንክኪ የሚጋባው ኢቦላ ብቻ መሰላችሁ እንዴ? አይ እናንተ! እናላችሁ ሲም ካርዴን ቶሎ አውጥቼ ወደ ሥራዬ ልሮጥ ስጣደፍ ሌላ ዱብ ዕዳ መጣ። ሲያመጣው አከታትሎ ነዋ። “ይቅርታ ውዝፍ ሒሳብ ስላለብዎ መጀመርያ ክፍያዎን ያጠናቁ?” ተባልኩ። እግዜር ይስጣቸውና መርዶዬን ሲነግሩኝ ‘አንቱ’ አሉኝ። ጎበዝ ሦስተኛው ዓለም ላይ ስትኖሩ ድምፃችሁን ማስከበር ቢያቅታችሁ አንቱታውን ግን የግድ ነው። “ኧረ ከፍያለሁ!” ብዬ በቅድመ ጥርጣሬ የከፈልኩባቸውን ደረሰኞች ሳሳይላችሁ ደግሞ ‘አብዴት’ ባለማድረጌ እንደሆነ ተበሰረልኝ። ተበሰረልኝ ልበል እንጂ በየሄድንበት በመርዶ ‘አብዴት’ እየተደረግን ነው። እንደኔ ዓይነት የገጠማቸው አንድ አዛውንት (ለመናገር ሰበብ ሲያድኑ የቆዩ እንደሆኑ ያስታውቃል) “3G ‘አብዴት’ ማስደረጉ ላይ የበረታችሁትን ያህል ሌላውም ላይ ብትበረቱ ምን ይላችኋል? ለስሙ በስብሰባ ተወጥራችሁ ትውላላችሁ። ከትናንት ስህተት ለመማር ተሃድሶ ብሎ ነገር ግን የለም። ጭራሽ ባለህበት እርግጡም ቀርቶ ወደኋላ ያልተንሸራተተ ነገር የለም ዛሬ። ነጋ ጠባ ልማት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲ ስትሉን እኔ ስለምታወሩት ነገርም ራሳችሁ ‘አብዴት’ መደረጋችሁን እንጃ…” እያሉ ብዙ ተናገሩ። በኋላ አንድ ተገልጋይ ጠጋ ብሎ፣ “በቃ አባት ይኼ እኮ ፓርላማ አይደለም፤” ሲላቸው ረገብ አሉ። በሰው ትከሻ መኖር በሰው ተከልሎ መጮህ ከሚመርጡት ወገን የሆኑ ተስተናጋጆች ደግሞ፣ “እሰይ! ጀግና! እስኪ ልክ ልካቸውን ንጉሩልን!” እያሉ ይንጫጫሉ። ጉዳዬን ጨርሼ ቶሎ ካልወጣሁ እኔም የብሶቴን፣ በብሶተኞች ውስዋሴ እንደምዘከዝከው እርግጠኛ ነበርኩ። ሲያዩኝ ግን ብሶት ያለብኝ አልመስልም አይደል? ህም! ይህቺ ካፖርትና ስቄ ማሳቅ አለመቻሌ ተባብረው እየሸፈኑልኝ እንጂ ሆድ እኮ ሞልቶም ነገር ሆኗል ሥራው። ብቅል ጉድ እስኪሠራው አትሉም? ጥቂት ወዲያ ወዲህ እንዳልኩ ታዲያ ቶዮታ ኤክስኪውቲቭ አውቶሞቢል ላሻሽጥ መደለል ጀመር። የፀሐዩን ነገር መቼም እንደ አዲስ አይነገርም። “እሷም የልማቱ ተሳታፊ ሆና ነዋ እንግዲህ?” እያሉ የሚያፌዙት ባሻዬ ናቸው። እኔን ደግሞ ያልገባኝ አልሚ አቃጣይ የሆነበት ምክንያት ነው። ብቻ እንደምንም ብዬ ሳይመሽ ለመጨረስ እጣደፋለሁ። እግረ መንገዴን ከጤነኛውም ጤና ካጣውም ጋር እላተማለሁ። አንዱ ከመሬት ተነስቶ፣ “ለአንተ ገና በዓል ነው! ለእኔ ግን ጊዜው ገና ነው፤” ሲለኝ ሥራዬን ትቼ ስለሕይወት ልፈላሰፍ እቃጣለሁ። ደርሶ ደህና ሰው የመሰለኝ የእግዜር ሰላምታ ሰጥቼው ሳልፍ፣ “ምን ኑሮ የገፋኝ አንሶ አንተ ትጨመርብኛለህ?” ይለኝና እደነግጣለሁ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ የሚገዛ ደንበኛ ሳገኝ ለሚከፍለው ክፍያ ጥቂት እንደሚጎድለው በጆሮዬ ሹክ አለኝ። መኪናዋን አስፈትሸን ከጨራረስን በኋላ “ምን ይሻላል?” ስለው እንዲያመልጠው እንደማይፈልግ ነግሮኝ የሚያበድረው ወዳጅ ያፈላልግ ጀመር። “ማን አለ? እከሌም ለራሱ አራጣ ተበድሮ ጭንቅ ላይ ነው! ማን ነው ያም አይሰጠኝም። እሱ ሲበልጡት አይወድም!” እያለ ረጂም ሰዓት ወሰደ። “እጅህ ላይ ያለው ገንዘብ እኮ ሌላ መኪና ይገዛል! በቃ ይኼን ተወውና ሌላ ልፈልግልህ?” ስለው እጅግ ተበሳጭቶ “ለምን ተብሎ? እኔ ከማን አንሳለሁ? ጓደኞቼ ሁሉ ኮሮላ እየነዱ?” ብሎ መልሶ አፈጠጠብኝ። ኋላ ቆይቶ ከባሻዬ ጋር ስለኑሮና አኗኗራችን ስንጫወት፣ “የእኛ ነገር እኮ አያስተማምንም። ሥራችን ከላይ ከላይ፣ አስተሳሰባችን ከላይ ከላይ፣ መሠረተ ልማቱ ሲያልቅ ነገራችን ሁሉ መሠረት ይይዛል ካልተባለ በስተቀር እንጃ?” ያሉኝ ትዝ እያለኝ፣ ይህቺ በጨበጣ ከማን አንሼ እያልን የምኖራት ኑሮ አስመረረችኝ። ደንበኛዬ እንደምንም ብሎ የጎደለውን 30,000 ብር ከሞላ በኋላ መኪናውን ተቀበለ። እኔም ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ ሽው አልኩ። ደግሞ የነዳጅ መቅጃ አበድረኝ እንዳይለይ ብዬ ነዋ። እንዲህ የሽሽት ፊታውራሪ ካልሆንማ የሚባለውን አንችለውም! በሉ እስኪ እንሰነባበት። የያዝኳትን ይዤ ከባሻዬ ልጅ ጋር መሸት እስኪል እያወራን የእግር መንገድ እንጓዛለን። ሁለታችንንም አንድ ነገር አስደንግጦናል፣ አስገርሞናል። ሌላ ጊዜ በግልምጫ ብቻ ዘቅዝቆ ሊሰቅለን ምንም የማይቀረው ሰው ዛሬ ከልቡ የእግዜር ሰላምታ ይሰጠናል። አሥር ጊዜ እንተያያለን። ሰላምታ እንደ ዶላር ብርቅ የሆነበት ዘመን ላይ ነዋ የደረስነው። “ምን ተገኝቶ ነው እንደዚህ ሰው መሬት የሆነው?” ስለው፣ “የበዓል ሰሞን ስለሆነ እንግዲህ ወይ ኪሱ ወይ ሆዱ ስለሞሉ ይሆናላ ሌላማ ምን አለ? መቼም ይኼ ሁሉ ሰው ‘ሔሊኮፕተር’ አስኮብልሎ አይመስለኝም?” ብሎኝ ሳቀ። ነገረኛ! ብዙም ሳንርቅ ድካም ይሰማን ጀመር። “ሮጠው የማይደክሙ አትሌቶች በምታፈራ አገር እኛ ይህቺን ታክል ሄድን ብለን ሲደክመን አናሳዝንም?” አልኩት። ‘ስታይላችን’ ነው! በዘር ከምንወርሰው በጎ ነገር ክፋቱ፣ መሰላቸቱ፣ መዳከሙና መሳነፉ ማየሉ እንዳልከው ያበግናል፤” እያለኝ ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ስንገባ ግራ ገባን። ሌላ ጊዜ ከምናውቃቸው ታዳሚዎች ይልቅ ታዳጊዎች ቤቱን ሞልተውታል። ሴቶቹ ወንዶቹ ላይ በሙዚቃው ሥልት ወድቀው ይነሳሉ። ወንዶቹ በምዕራባዊያን የሙዚቃ ክሊፖች ላይ እንደሚያዩዋቸው ራፐሮች አቀማመጣቸውን እያሳዩ ከእኛ በላይ ላሳር ይላሉ። ሁናቴያቸውና አጠጣጣቸው ፍፁም አስደንጋጭ ነው። የግሮሰሪዋ ባለቤት ነገርዬው ተደጋግሞበታል መሰል ምንም ሳይመስለው ‘ቅዳ!’ ሲሉት ይቀዳል፣ ‘ክፈት!’ ሲሉት ይከፍታል። እኔና የባሻዬ ልጅ ተጠቃቅሰን ወጣን። ስሜታችን ተረባብሿል። “አንበርብር አሁን ያየነው እኮ የማዕበሉን ናሙና ነው፤” አለኝ። “የምን ማዕበል?” አልኩት። “አሟረትክ አትበልና የጥፋት ማዕበል። አሁን አሁን እኛ ራሳችን ብዙውን ነገር ተላመድነውና ችላ ማለት ጀመርን። ቀስ በቀስ ለችግሮቻችን እጅ መስጠታችን ሳያንስ፣ ጭራሽ በአጭሩ መቀጨት የሚችል የትውልድ ነቀርሳ ሲዛመት ዝም ብለን እናያለን፤” እያለኝ እሱም ቤቱ እኔም ቤቴ ገባሁ። ምንድነው ባሉበት ተቀምጦ ከጥፋት፣ ከውድመትና ከዝቅጠት ጋር መላመድ? አንዳንዴ ሳስበው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉብን ይገባኛል፡፡ ጉድለቶቻችንን መርምረን ችግራችንን ነቅሰን ካላወጣን በስተቀር መፍትሔ አናገኝም፡፡ ለመፍትሔው ደግሞ ራሳችንን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ማን ነበር የተድበሰበሰ ችግር መጀመርያ የሚያጠፋው ባለቤቱን ነው ያለው? እባካችሁ ችግሮቻችንን አናድበስብስ! ችግሮች ሲድበሰበሱ አጥፊ ይሆናሉ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት