Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየካቢኔ ጉዳዮችና የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ለሁለተኛ ጊዜ ከሙስና ወንጀል ነፃ...

የካቢኔ ጉዳዮችና የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ለሁለተኛ ጊዜ ከሙስና ወንጀል ነፃ ሆኑ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግብዓት አቅርቦትና አስተዳደር መምርያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው፣ በቅርቡ የካቢኔ ጉዳዮችና ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሆነው ተሹመው የነበሩት አቶ በፈቃዱ አሰፋ ለሁለተኛ ጊዜ ከሙስና ወንጀል ነፃ ሆኑ፡፡

ኃላፊው በቤቶች ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እየሠሩ በነበሩበት በሐምሌ ወር መጀመርያ ሳምንት ለጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) የሚውልና ሙቀት መቋቋም የሚችል፣ የማይለጠጥ፣ በቀላሉ የማይሰበርና ረዥም ጊዜ የሚያገለግል ዩፒቪሲ የሳኒተሪ መጋገጠሚያዎች ግዥ ጨረታ ጋር በተገናኘ ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተገልግለው፣ ጥራታቸው ዝቅ ያለ መገጣጠሚያዎችን ያቀረበውን ድርጅት አሳልፈዋል ተብለው በሙስና  ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ነበር፡፡ ጥራት የሌላቸውና ቅሬታ የቀረበባቸው የሳኒተሪ መገጣጠሚያ ዕቃዎችን አቅርበዋል የተባሉት የኤቢ ፕላስት ድርጅት ባለቤት አቶ አብርሃም ጌታቸውም ታስረው ነበር፡፡

በወቅቱ (በ2007 ዓ.ም.) ከሳሽ የነበረው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ፣ ኃላፊውና የድርጅቱ ባለቤት በጥቅም በመተሳሰር በፈጸሙት የግዥ ውል ዩፒቪሲ ያልሆነን የሳኒተሪ መገጣጠሚያ ምርት በላዩ ላይ ዩፒቪሲ የሚል ጽሑፍ በማተም የ3,211,411 ብር ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በመግለጽ ክስ መሥርቶባቸው ነበር፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ከሰማና ያቀረባቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ በተከሳሾቹ ላይ በቂና እንደ ክሱ ሊያስረዳ የሚችል ማስረጃ አለማቅረቡን ገልጾ፣ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ክስ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡ አቶ በፈቃዱም ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ በተወሰነ ጊዜ በቀድሞ ኃላፊነታቸው እየሠሩ ባለበት ወቅት፣ የካቢኔ ጉዳዮችና የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊነት ሆነው ተሹመው ነበር፡፡

በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተደሰተው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማለቱ፣ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ መርምሯል፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ተከሳሾች ‹‹ሊከላከሉ ይገባል›› በማለቱ ከስምንት ወራት በፊት በድጋሚ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ተደርጎ ነበር፡፡

አቶ በፈቃዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ ሰባት የመከላከያ ምስክሮችን ቆጥረው አሰምተዋል፡፡ የመከላከያ ምስክሮቹ በሰጡት የምስክርነት ቃል አቶ በፈቃዱ የአንድን ዕቃ ግዥ ጥራትና ብቃት የማረጋገጥ፣ በስፔስፊኬሽኑ መሠረት ዕቃው መቅረብ አለመቅረቡን የማጣራት ዕውቀትም ሆነ ኃላፊነት እንደሌላቸው መስክረዋል፡፡ የግዥ ኮሚቴና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት እንዲሁም ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጨምሮ የግዥን ሁኔታ በሚመለከት የሚሳተፉ አባላት ፊርማ ካሳረፉ በኋላ አቶ በፈቃዱ የማስፈጸም፣ በተጫራቾች በኩል ቅሬታ ከመጣ ተከታትለው ማረጋገጥና ለዋና ሥራ አስኪያጁ ማሳወቅ እንደሆነም የመከላከያ ምስክሮቹ መመስከራቸውን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ገልጿል፡፡

አቶ በፈቃዱ ያደረጉትም ይኼንኑ መሆኑን ምስክሮቹ ማረጋገጣቸውን ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡ በተቋሙ ከሥራ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያደረባቸው የተቋሙ ሁለት የሥራ ባልደረቦች ለዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው የቀረቡ ቢሆንም፣ የሰጡት ምስክርነት እውነትነት ያለው ነው ተብሎ ለመውሰድም እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ በምርምራው ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም አቶ በፈቃዱ የግዥ ጨረታ ሒደቱን ያካሄዱት በተቋሙ መመርያና በተሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት መሆኑን ከማሳየት ባለፈ፣ ያልሆነ ተግባር ፈጽመዋል ማለት እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

የኤቢ ፕላስት ድርጅት ባለቤት አቶ አብርሃምም ያቀረቧቸው የሳኒተሪ መገጣጠሚያዎች ከዝርዝር መሥፈርቱ በታችና ጥራት የሌለው ነው ስለመባሉ መከላከያ ምስክሮችን አቅርበው ማስረዳታቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥራት አክሪዲቴሽንና ከኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት የቀረቡ ኤክስፐርቶች የድርጅቱን ምርት ከዝርዝር መሥፈርቱ በታችና በላይ ነው፣ ጥራት አለውና የለም ለማለት የሚያስችል መሣሪያ እንደሌለ በመግለጻቸው አቶ አብርሃም ያቀረቡት የሳኒተሪ መገጣጠሚያ ከዝርዝር መሥፈርቱ በታች ነው ለማለት እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም አቶ በፈቃዱና አቶ አብርሃም የዓቃቤ ሕግን ክስ በሚገባ ማስተባበል በመቻላቸው፣ ከተመሠረተባቸው የሙስና ወንጀል ክስ በነፃ መሰናበታቸውን ገልጾ ዓርብ ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...