Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ውዥንብሮች ይጥሩ!

ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃ ቅብብልና ግልጽነት በሌለበት አገር ውስጥ ውዥንብር የበላይነቱን ይይዛል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ማኅበራዊ ሚዲያው ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፅዕኖው እየበረታ በመሆኑ፣ በአንድ ሥፍራ ያጋጠመ ክስተት ወዲያው የመሰማት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን የሚቀርበው መረጃ የተጣመመ ወይም ምሉዕነት ይጎድለውና መልዕክቱ በትክክል አይተላለፍም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሐሰተኛ መረጃዎች ከመጠን በላይ እየተጋነኑ ስለሚቀርቡ ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት ጭምር እየዳረጉ ነው፡፡ አገር የሚያስተዳድር መንግሥት የአገርን ውሎና አዳር በተመለከተ ለሕዝብ ማቅረብ ያለበት መረጃ ወቅታዊና በእውነታ ላይ የተመሠረተ ካልሆነ ውዥንብር የበላይነቱን ይይዛል፡፡ ቢሮክራሲው በተለመደ ዳተኝነቱ ምክንያት መረጃ ሲነፍግ ወይም ሲንቀረፈፍ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ እያጋጠሙም ነው፡፡ የሰው ሕይወትን የመሰለ ክቡር ነገር በውዥንብር ምክንያት ሲጠፋ መስማት ከመጠን በላይ ያበሳጫል፡፡

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ ሠልፎች ዜጎች ሞተዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ስለሞት መስማት በጣም በጣም ይዘገንናል፡፡ የክልሉ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ለመደገፍ የወጡ ሠልፈኞች ምክንያቱ ሳይታወቅ ወደ ተቃውሞ ተሸጋገሩ መባሉ፣ ውዥንብር ምን ያህል የአገር አደጋ እየሆነ መምጣቱን ይጠቁማል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚጠሩ ሠልፎችን ኅብረተሰቡ እንዳይቀበልና ከሕገወጥ ተግባራት ራሱን እንዲያርቅም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ ለዚህም ሕዝቡ ከጎኑ መሠለፉን ገልጿል፡፡ ነገር ግን በተለይ ወጣቶችን በስሜታዊነት በማነሳሳት በተለያዩ አካባቢዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑ ኃይሎች እንዳሉም አስታውቋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብ በሚኖራቸው መስተጋብር በቀጥተኛ መንገድ መነጋገር ሲገባቸው፣ ጣልቃ እየገቡ የሚበጠብጡ ካሉ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ይህንን ችግር ከሥር መሠረቱ መፍታት የሚቻለው ከማንም ጋር ሳይሆን ከሕዝብ ጋር ብቻ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የክልሉን ሕዝብም ሆነ መላውን የአገሪቱ ሕዝብ ከውዥንብር የፀዳ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የግድ መሆን አለበት፡፡

በዚህ ዘመን አገርን ከሚያስተዳድር መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚስተዋለው ችግር ውዥንብር ለሚፈጥሩ አሉባልታዎች መጋለጥ ነው፡፡ ከአንድ ሥፍራ የተለቀቀ መረጃ ሲኖር ኅብረተሰቡ የተዓማኒነቱን ደረጃ የማረጋገጥ ኃላፊነት ሲኖርበት፣ መንግሥት ደግሞ ግልጽነት በተሞላበት መንገድ ቀልጠፍ ብሎ ትክክለኛውን ነገር የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ጥሬ መረጃ ሲቀርብ ለምን? እንዴት? መቼ? የት? ወዘተ በማለት መጠየቅ የተጣራ መረጃ ለማግኘት ይረዳል፡፡ መንግሥት ደግሞ ለዚህ ተብሎ በተቀመጠው መዋቅር አማካይነት የተጣራ መረጃ እንዲተላለፍ ሙሉ ጊዜውን መጠቀም አለበት፡፡ አለበለዚያ ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ግርድፍ መረጃዎች ሐሰተኛና ግጭት ቆስቋሽ በሆኑ ድምፀቶች ታጅበው ሲቀርቡ፣ የማመዛዘን ችሎታቸው አነስተኛና ስሜታዊ የሆኑ ወጣቶችን ለተሳሳተ ድርጊት ያጋልጣሉ፡፡ ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው’ በሚል ግልብ የፖለቲካ ፍላጎት የተጀቦኑና ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ውዥንብር በመፍጠር ደም አፋሳሽ ነውጦች ለመቀስቀስ ወደኋላ እንደማይሉ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀላሉና በፍጥነት ተደራሽ የሆነው ማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ትክክለኛ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ ማሠራጨት ሲቻል፣ የጠላት መጠቀሚያ ይመስል ማጥላላት ተገቢ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ውዥንብሮችን ለማጥራት ማኅበራዊ ሚዲያን ያለማሰለስ መጠቀም ይበጃል፡፡

መቼም ቢሆን ችግሮች ማጋጠማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮች ሲያጋጥሙ በብልኃት የሚፈቱበትን መፍትሔ አመላካች መንገድ ማግኘት የሚቻለው በመሸፋፈን አይደለም፡፡ እውነታውን በመጋፈጥ ነው፡፡ ለፈጣንና ለአስተማማኝ መረጃ ልውውጥ ራስን በማዘጋጀት ነው፡፡ ሕዝብ ከመንግሥት የሚፈልገው አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ነው፡፡ ይህ እንዲሆንም ሕግ ያስገድዳል፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥም ነፃና ግልጽ የውይይትና የክርክር ባህል እንዲዳብር መደረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ የሲቪክ ማኅበራት ማበብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዴሚክ ነፃነት ተጎናፅፈው የውይይትና የክርክር ማዕከል መሆን አለባቸው፡፡ ምሁራን በነፃነት በአደባባይ እንዲናገሩ ወይም እንዲጽፉ ሊበረታቱ ይገባል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሐሳቦች በነፃነት ሲንሸራሸሩና የተለያዩ ድምፆች ሲሰሙ፣ አሉባልታና ሐሰተኛ ወሬዎች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ አሁን እንደሚታየው በየጎራው ተሠልፎ በጭፍን ጥላቻና በጭፍን ድጋፍ ውስጥ ሆኖ ነገር መቆስቆስ፣ የውዥንብር መፈልፈያ ከመሆን ውጪ ፋይዳ የለውም፡፡

የተከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነት ባዳበረው የእርስ በርስ ግንኙነት ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋና በረከት ባለበት አገር ውስጥ ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ እንዲሉ፣ ማመዛዘንና ማስተዋል የጎደላቸው በርካታ አሳዛኝ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማለያየትና አንዱን በሌላው ላይ ለማነሳሳት የሚፈጸሙ እነዚህ ከንቱ ድርጊቶች፣ በስሜታዊነት እየታጀቡ አደጋ እየደቀኑ ነው፡፡ ይህ ኩሩና ተምሳሌታዊ ሕዝብ ከራሱና ከአፍሪካውያን አልፎ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለተጨቆኑ በሙሉ አርዓያ እንዳልሆነ፣ በዚህ ዘመን ሕዝብን በዘር እየከፋፈሉ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መናድ ሊወገዝ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ባለው የአገሪቱ መልክዓ ምድር ውስጥ እየኖረ በጋራ እሴቶቹ አማካይነት ዘመናትን የተሸጋገረው፣ ከልዩነቶቹ ይልቅ አንድነቱ የበለጠ ሰፊና ጥልቅ በመሆኑ ነበር፡፡ እዚህ ግባ ለማይባል ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ተጋብቶና ተዋልዶ የሚኖር ሕዝብን ማጋጨት፣ አንድነቱን መገዝገዝና አገሪቱን ለማያባራ ጦርነትና ትርምስ ለመዳረግ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ውዥንብር መቆም አለበት፡፡ ይህንን ኩሩና ተምሳሌታዊ ሕዝብ የማይወክሉ የክፋት ድርጊቶች ተጋልጠው መወገዝ አለባቸው፡፡ ይህ በተግባር ይታይ ዘንድ ደግሞ ውዥንብሮች ይጥሩ፡፡ ያኔ ምርትና ግርዱ ይለያል፡፡

አገር የምትከበረውና የምትታፈረው በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሙሉ ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ዜጎች ከራሳቸው በላይ ለዚህች ታሪካዊት አገር በጋራ መቆም ሲችሉ ነው፡፡ ከስግብግብነትና ከአሻጥረኝነት ምንም አይገኝም፡፡ የደመኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ትርፉ ሞት፣ ስደት፣ ውድመትና ትርምስ ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ የሚገነባው ደግሞ በግልጽነትና በነፃነት መነጋገር ሳይቻል ሲቀር ነው፡፡ ግልጽነት በሌለበት ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ ነፃነት በሌለበት የሚከተለው ነውጥ ነው፡፡ የማይደማመጥ ሕዝብና መንግሥት መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ጥላቻና ቂም በቀል በሚናኝበት ደግሞ ውዥንብር የበላይነቱን ይይዛል፡፡ መተማመን ጠፍቶ ሕገወጥነት ይበረታል፡፡ ነገር ግን ለሕግ የበላይነት በመገዛት ለአገር ህልውና ሲባል ከውዥንብሮች ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ከጥላቻና ከመፈራረጅ ዳዋ ውስጥ በመውጣት ለሕግ የበላይነት መገዛት መለመድ አለበት፡፡ ውዥንብርና ትርምስ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸውን ወገኖችን ማቆም ካልተቻለ መጪው ጊዜ ከባድ ይሆናል፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተችና የሁሉም የጋራ ቤት የሆነች አገር የምትኖረው ውዥንብሮች ሲጠሩ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...