Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለውኃ መጥፋትና መቆራረጥ ተጠያቂው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው አለ

ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለውኃ መጥፋትና መቆራረጥ ተጠያቂው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ነው አለ

ቀን:

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በተለዩ አካባቢዎች እየደረሰ ለሚገኘው ውኃ መጥፋትና መቆራረጥ ተጠያቂው፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሆኑን አስታወቀ፡፡

ወቅቱ ክረምት በመሆኑና ክረምቱ ከወጣም በኋላ የኤሌክትሪክ መስመር የሚዘረጋባቸው ቦታዎች በሰብል የተሸፈኑ በመሆኑ፣ ኃይል የመዘርጋቱ ጊዜ ቢዘገይም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ችግሩ እንደሚቀረፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ እስጢፋኖስ ብሥራት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በውኃ አቅርቦት ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል፡፡ ነገር ግን ከውኃ ምርትና ሥርጭት ጋር ተያይዞ በሚያጋጥም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ትልቅ ችግር ተፈጥሯል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ባለሥልጣኑ 80 ጄኔሬተሮችን ተክሎ ለናፍጣም ከፍተኛ ወጪ በመመደብ ቢሠራም፣ ችግሩ ሊቀረፍ አለመቻሉን አቶ እስጢፋኖስ አስረድተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ችግሩን እስከ ዘለቄታው ለመቅረፍ ለውኃ መገኛ ጉድጓዶችና ማሠራጫ ጣቢያዎች ብቻ ኃይል የሚሰጥ ቀጥታ መስመር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲዘረጋለት ተነጋግሮ 21 ሚሊዮን ብር ክፍያ ቢፈጸምም፣ ይህ ተግባራዊ ሊደረግ ባለመቻሉ የውኃ መጥፋትና መቆራረጥ በደንበኞች ላይ ማጋጠሙን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከአቃቂ ከርሰ ምድር በቀን በሚመረተው 230 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውኃ ተጠቃሚ የሆኑ መሀል አዲስ አበባ፣ ምዕራብ አዲስ አበባና ደቡብ አዲስ አበባ የሚኖሩ ደንበኞቹ የውኃ ችግር ሰለባዎች መሆናቸውን የሥራ ሒደት መሪው ተናግረዋል፡፡ በለገዳዲ የግፊት ጣቢያዎችም ተመሳሳይ ችግር እያጋጠመ መሆኑንና የምሥራቅ አዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፍተኛ የውኃ አቅርቦት ችግር እያጋጠማቸው መሆናቸውን አክለዋል፡፡ በመሆኑም በኤሌክትሪክ ኃይል ለመቆራረጥ ምክንያት ነዋሪዎች የውኃ አቅርቦት ችግር ሲገጥማቸው በማየት ይቅርታ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ዋናው የችግሩ ፈጣሪ  ግን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋምም የኅብረተሰቡን ችግር ተመልክቶ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የውኃ አቅርቦት ለተቆራረጠባቸውና አልፎ አልፎ ለቀናት ለማያገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይቅርታ በመጠየቅ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ችግሩን የአንድ ተቋም ብቻ ማድረጉ ጥቅም ስለሌለው በመተባበር የኅብረተሰቡን ችግር መፍታት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋል ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ የውኃ አቅርቦት መቆራረጥን ለመቀነስ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቀጥታ መስመር እንዲሰጠው መጠየቁን ያስታወሱት፣ የአገልግሎቱ የዲስትሪቢውሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃኔ ናቸው፡፡ ውል ከመፈራረማቸውና ክፍያ ከመፈጸሙ በፊት ባለሥልጣኑ ስለሚፈልገው ጉዳይ ጥናት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ባደረጉትም ጥናት ባለሥልጣኑ 180 የውኃ መገኛ ጉድጓዶች እንዳሉትና 32 በቡስተር ፓምፕ አማካይነት ለሕዝቡ እንደሚደርሱ ማረጋገጣቸውን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ 22 ማሠራጫ ጣቢያዎችና 126 ንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዳሉት የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ የውኃ ማውጫና ማሠራጫ ጣቢያዎች ከ49 ማሠራጫ ጣቢያዎች አገልግሎት እንደሚያገኙም ጠቁመዋል፡፡ ይኼ ማለት 40 በመቶ የሚሆነው ኃይል ወይም 60 ሜጋ ዋት እንደሚጠቀም አክለዋል፡፡ ነገር ግን 49 መስመሮች በቀጥታ ለውኃ ማውጫና ማሠራጫ ብቻ መጠቀም ስለማይቻል፣ በ22 የውኃ ጣቢያዎች ላይ መሥራት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም በ2009 ዓ.ም. 21 ሚሊዮን ብር ከባለሥልጣኑ መቀበላቸው እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡          

ከአቃቂ ከርሰ ምድር ወጥቶ በቃሊቲ፣ ሳሪስ፣ ጎተራና መስቀል አደባባይ ለሚሠራጨው ውኃ፣ ከተለያዩ የኤሌክትሪክ ማሠራጫ ጣቢዎች ቀጥታ ኃይል እንዲያገኝ በማድረግ፣ ከአቃቂ እንዲወጣ ለብቻው መስመር ተሰጥቶት እየተሠራጨና ችግር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ያለው ችግር ቀድሞ የነበረውን የኃይል ማሠራጫ የእንጨት ምሰሶ በኮንክሪት እየተኩ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፣ ጥራቱን ለመጠበቅና ጥንካሬውን አስተማማኝ ለማድረግ መለወጡ የግድ ነው ብለዋል፡፡

የእንጨት ምሰሶን በኮንክሪት የመቀየር ሥራውን ሳያጠናቀቁ የተዘሩ ሰብሎች በመድረሳቸው (በእርሻ ላይ ስለሚያልፍ) አርሶ አደሩ ስለከለከላቸው፣ ሰብሉ እስከሚሰበሰብ ሥራውን ሊያቆሙ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ለከርሰ ምድር ውኃ  ቀጥታ መስመር የመስጠት ሥራ ቢያጠናቅቁም የሚስተካከሉ የቴክኒክ ሥራዎች መቅረታቸውን የገለጹት አቶ መስፍን፣ በቅርብ ቀን የቀሩትን ሥራዎች አጠናቀው ሙሉ አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምር ድረስ ተጠቃሚዎች እንዲታገሱ ጠይቀዋል፡፡ እስካሁን ለደረሰባቸው የውኃ ማጣትም ችግር ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ከአቃቂ ከርሰ ምድር ወደ ሃና ማርያም፣ ካራ ቆሬና ቤተል የሚሄደውን ቀጥታ የመስመር ዝርጋታ ማጠናቀቃቸውን ጠቁመው፣ የሚቀራቸው ማስተካከልና ጥቃቅን ነገሮች ቢቀሩም፣ ችግሩ ተመሳሳይ በመሆኑ ኅብረተሰቡን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ዋናው ችግር ከርሰ ምድር ላይ ያለው በመሆኑ ከባለሥልጣኑ ጋር ተመካክረው ምላሽ  እንደሚሰጡም አቶ መስፍን አክለዋል፡፡ የለገዳዲን ችግር የሚፈታ ኮተቤ በሚገኘው ማሠራጫ ጣቢያ ላይ የማስፋፊያ ሥራ በማከናወናቸው ችግሩ መቀረፉን ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...