Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተሻሻለው ከረጢት እህል ሳይበላሽ በማቆየት ለገበሬዎች እፎይታን እያስገኘ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አርሶ አደሩ ዘመናዊ የአሠራር ዘዴን መሠረት በማድረግ፣ ሳይንሳዊ ሒደትን በተከተለ ሥልጠና በመታገዝ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቀናጅቶ በመጠቀም የግብርና ምርማነቱን ለማሻሻል ሲጥር ይስተዋላል፡፡

በአንጻሩ ግን አርሶ አደሮች የሚጠቀሙባቸው ግብርና ተኮር የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአብዛኛው ያልዳበሩ ወይም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ሰብል በማሳው ሳለ በድህረ ምርት ወቅትም ሆነ ቅድመ ምርት ሒደት ብክነትን ለማስተናገድ ሲገደዱ ቆይተዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 በመቶ የድህረ ምርት ብክነት የሚከሰተሰው ባህላዊ የምርት አሰባሰብ ሥርዓት ምክንያት፣ በምርት ማከማቻዎች አለመመችት፣ እንደሁም በዝናብ፣ በጎርፍና በነቀዝ ምክንያት በሚደርስ ጥፋት ነው፡፡

አርሶ አደሮች ምርታቸውን በወቅቱ ሰብስበውና በፈለጉበት ጊዜ ለገበያ ማቅረብ አለመቻላቸውን ጨምሮ በድርቅ ወቅት የእህል እጥረት እንዲባባስባቸው መንስዔ እየሆነ ሲያስቸግራቸው ቆይቷል፡፡ ባላቸው የማከማቻ ዘዴ ተጠቅመው ሲያቆዩም፣ ብዙ የለፉበት ምርት ለሻጋታና ለሌሎች ብልሽቶች እየተዳረገባቸው ዋጋ ሲሰብርባቸው ይስተዋላል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ፣ የአርሶ አድሮቹ ምርቶች ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችሉባቸው ቴክኖሎጂዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ እያሉ ነው፡፡ አዲስ የእህል ምርት ማከማቻ ዘዴዎችን ለገበሬዎች እያቀረበ ከሚገኙት መካከል ፒክስ የተሰኘው የተሻሻለ የእህል ማከማቻ ከረጢት አንዱ ነው፡፡

በበርካታ አገሮች ውስጥ በጥቅም ላይ የዋለው፣ ከኬሚካል ነፃ በሆነ መንገድ የአየር ዝውውርን በመቆጣጠር ብቻ የተከማቸ ምርትን ከተባይ ጉዳት ለመከላከል የሚያስችለው ይህ የማከማቻ ዘዴ በኢትዮጵያም ጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል፡፡

ሳሳካዋ ግሎባል 2000 የተባለው ተቋም ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ከክልል ቢሮዎችና ከዞን አስተዳደሮች ጋር በመሆን ቴክኖሎጂውን ሲያስተዋውቅ፣ ለአርሶ አደሩም ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ቴክኖሎጂውን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲቻልም የመጀመሪዎቹን 500 ከረጢቶች አገር ውስጥ በማምረት ለገበሬዎች በማዳረስ ምርት እንዴት ከብክነት መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤ ያስጨበጠበት መድረክ ተዘክሯል፡፡

ሳሳካዋ ግሎባል በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በግብርናው መስክ ድጋፍ በመስጠት የሚንቀሳቀስባቸው አገሮች ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ማሊና ናይጄሪያ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 በናይጄሪያ የፒክስ ከረጢትን ማስተዋወቅ የጀመረ ሲሆን፣ 100 ከረጢቶችን ከናይጄሪያ በማምጣት በኢትዮጵያ የማስተዋወቅ ሥራውን እንደጀመረ ወ/ሮ መሠረት አድማሱ፣ በሳሳካዋ ግሎባል 2000 የደህረ ምርት ማቀነባበሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ምርትን በቀላሉ ከነቀዝ መከላከል እንደሚቻል ስናስተምር ቆይተናል፡፡ ከረጢቱ ካልተቀደደ በስተቀር ለብዙ ጊዜ እህል ያለ ችግር ማስቀመጥ ያስችላል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የቴክኖሎጂው ባለቤት የአሜሪካው ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር 500 ከረጢቶች በአገር ውስጥ ማምረት እንደተቻለም ተገልጿል፡፡

ገበሬዎች ተሞክሮ ከቀሰሙባቸው አካባቢዎች መካከል በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን፣ የዛንጋ ዶርማሌ ወረዳ ይጠቀሳል፡፡ ይህ አካባቢ በበቆሎ አምራችነቱ ይታወቃል፡፡ በመኸርና በበልግ ወቅት የአካባቢው አምራቾች የዘሩት ምርት ለፍሬ ደርሶ ይሰበሰባል፡፡ ሆኖም ቀበሌው ግንቦት ወር በሚፈጠረው ደረቃማ የአየር ጸባይ ሳቢያ የቀበሌው አርሶ አደሮች የሚሰበሰቡትን ምርት በባህላዊ መንገድ በማከማቸት በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ ሲገደዱ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡

አቶ መንግሥቱ ንጉሤ የዛንጋ ዶርማሌ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በአዲሱ ቀረጢት ዓምና መጠቀም እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የበቆሎ ምርት ከሰበሰቡ በኋላ እንደ ዱቄት መሰል መከላከያ በመጨመር ምርታቸውን ለማቆየት ሲጥሩ እንደነበር አብራርተው፣ ሲጠቀሙበት የነበረው ዘዴ ግን በበቆሎው ላይ ጠረን እየፈጠረ በማስቸገሩ ምርቱን በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ እንደሚገደዱ ያስታውሳሉ፡፡

በተለይ በአካባቢው የግንቦት ወር በገባ ቁጥር ለሚከሰተው የምርት እጥረት አንዱ መንሥዔ በጎተራቸው ውስጥ ለወራት ሳይበላሽ የሚቆይ በቆሎ ስለማይገኝ ነበር፡፡ በአንፃሩ አሁን የመጣውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምርቱ ከተሰበሰበበ በኋላ እስከ አራት ወራት ድረስ ያለብልሽት ማቆየት ስለቻሉ፣ በኩንታል እስከ 850 ብር በመሸጥ ኑሯቸው ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችሉበት ዕድል እንደተፈጠረ ይናራሉ፡፡ በነቀዝ ምከንያት የተበላሸ በቆሎ በኩንታል ከ250 እስከ 300 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እስከ 850 ብር መሸጣቸው ለውጡን በጉልህ እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

በአንድ ሔክታር 45 ኩንታል ምርት የሚያገኙት አቶ መንግሥቱ፣ 20 ኩንታሉን ሸጠው፣ 25 ኩንታሉን ደግሞ የገበያውን ሁኔታ በማየት እንደዋጋው አዋጭነት እንደሚያቀርቡት ተናግረዋል፡፡ በሳሳካዋ ግሎባል 2000 አማካይነት በወረዳው 1,800 አርሶ አደሮች የከረጢቱን አጠቃቀም በማስመልከት ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ 70 በመቶዎቹም ከረጢቱን በመግዛት ምርታውን ለረዥም ጊዜ በማስቀመጥ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ የዛንጋ ዶርማሌ ቀበሌ የግብርና ጽሕፍት ቤት ኃላፊ አቶ አንተነህ በለጠ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አንዱ ከረጢት በ45 ብር የችርቻሮ ሒሳብ ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ የዋጋው ከፍተኛ መሆን ግን አርሶ አደሩን ቅር እንዳሰኘው አቶ አንተነህ አልሸሸጉም፡፡ ከረጢቱን ለአርሶ አደሮች የሚያቀርበው ድርጅት ሸያሾኔ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን፣ ለግብርና ምርቶች ማከማቻነት ተሻሽሎ የተመረተው ከረጢት ዋና አከፋፋይ ነው፡፡

በሸያሾኔ ድርጅት፣ የግብርናና ቢዝነስ ዘርፍ አማካሪው አቶ ሚካኤል ታሪኩ እንደሚገልጹት፣ በ2006 ዓ.ም. ከረጢቱን ማቅረብ የተጀመረ ሲሆን፣ ከ2008 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 70 ሺሕ ከረጢቶችን ድርጅቱ ለገበያ በማቅረብ እንደሸጠ ገልጸዋል፡፡ ለሽያጭ ሦስት ዓይነት መንገዶችን የሚጠቀም ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በ80 አከፋፋዮችና ከ200 በላይ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እንዲሁም በሳሳካዋ ግሎባል 2000 አማካይነት ከረጢቶቹን ለገበሬዎች ያሠራጫል፡፡

በድርብ ገጽ የሚዘጋጀው አንዱ ከረጢት ከ100 እስከ 120 ኪሎ ግራም የሚመዝን እህል የመያዝ አቅም አለው፡፡ በጥንቃቄ ከተያዘም ሁለት የምርት ዘመን ማገልገል እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

የከረጢቱን ዋጋ በተመለከተ ለሪፖርተር ያብራሩት አቶ ሚካኤል፣ ‹‹የምንከፍለው የታክስ መጠን ዋጋውን በቀላሉ ለማሻሻል አያስችለንም፡፡ ወደፊት ግን ሁሉም አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ከረጢቱን መግዛት እንዲችሉ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚሁ በጋሞ ጎፋ ዞን የኦይዳ ወረዳ ሌላኛው በበቆሎ አምራችነቱ የሚታወቅ አካባቢ ሲሆን፣ በሦስት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ አምራቾችም ቴክኖሎጂውን መጠቀም ጀምረዋል፡፡ ምርት ለሚፈለገው ጊዜ በማቆየት የሚከሰተውን ድርቅ በመጠኑም ቢሆን እንዳቃለለው አቶ ቴዎድሮስ ጴጥሮስ፣ የኦይዳ ወረዳ ምክትል አስተዳዳርና የእርሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም በ20 ቀበሌዎች የከረጢቱን ተጠቃሚዎች ቁጥር በማስፋፋት ምርት እስከሚፈልግበት ጊዜ ድረስ ለማቆየትና ለመጠቀም የሚቻልበትን ዕድል ለማስፋፋት እንደታሰበ ገልጸዋል፡፡

አካባቢው ከድርቅ ባሻገር በጎርፍ የሚጠቃ በመሆኑም ምክንያት 1998 ዓ.ም. 50 አባወራዎች በጎርፍ አደጋ ሕይወታቸውን እንዳጡ ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ ዴንሻ ተብሎ በሚጠራው አካባቢም በዓመት ቢያንስ ስድስት አባወራዎች ከመኖሪያቸው በጎርፍ ምክንያት እንደሚፈናቀሉ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱ ጊዜ የምግብ እጥረት እንዳይፈጠር ለመከላከል በአዲሱ ከረጢት አማካይነት እህል ሳይበላሽ ማቆየት መቻሉ መልካም ዕድል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ቀደም ሲል የአካባቢው አርሶ አደሮች በገበያ የሚገኘውን የትኛውንም ዓይነት ቀረጢት በ15 ብር በመግዛት ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው፣ ቴክኖሎጂ ያሻሻለውን ከረጢት መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ግን ለውጦችን ማየት እንደቻሉ ጠቅሰዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች