Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየወልድያ ስታዲየም የፊፋን ዕውቅና እንዲያገኝ የሚደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑ ተገለጸ

የወልድያ ስታዲየም የፊፋን ዕውቅና እንዲያገኝ የሚደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በሼሕ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ ሙሉ ወጪ የተገነባው የወልድያ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል ለውድድር ክፍት ከሆነ ወራትን አስቆጥሯል፡፡ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የፈጀው የወልድያ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ቢሆንም እስካሁን ግን በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ዕውቅና እንዲያገኝ የሚደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ስታዲየሙ በአጠቃላይ 25,155 ተመልካቾችን የሚያስተናግድ አቅም ሲኖረው በተጨማሪም የሜዳ ቴኒስ፣ የቅርጫት፣ የመረብ፣ የእጅ ኳስና የዋና ስፖርቶች የሚካሄዱባቸው ማዘውተሪያዎችን አሟልቶ የያዘ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ የተመልካቾች የፀሐይ መከላከያ ጥላ የተገጠመለት የመጀመሪያውም ነው፡፡

ግንባታውን አጠናቆ ለከተማው አስተዳደር ያስረከበው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ለስታዲየሙ አስፈላጊው የማስተዋወቅ ሥራ እንዳልተደረገለት ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

ስታዲየሙ በአሁኑ ወቅትም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ከማስተናገዱ ውጪ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዳልተከናወነበትና ፌዴሬሽኖችም ዕድሉን ለመጠቀም አለመሞከራቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው የወልድያ ከነማ እግር ኳስ ክለብ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባከናወነው ጨዋታ ላይ 21 ሺሕ ተመልካች ከማስተናገዱ በስተቀር በሌሎች ጨዋታዎች ላይ ብዙ ተመልካቾችን እስካሁን ድረስ ለማስተናገድ ዕድሉን እንዳላገኘም የከተማው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሚዘጋጀው የሠራተኞች ውድድር ፍጻሜውን ባገኘበት አጋጣሚ ስታዲየሙ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሆነ በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ተገቢውን ዕውቅና እንዲያገኝ በፌዴሬሽኖች በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ ያን ያህል መሆኑ ብቻ ሳይሆን ስለስታዲየሙ ተገቢው የማስተዋወቅ ሥራ አለመሠራቱ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጠቅላይ ሥራ አስፈጻሚ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ዓመታዊው የሠራተኞች ውድድር ከመጋቢት 3 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. 25 ኩባንያዎችን በአራት የቴክ ምድብ በመመደብ፣ እንዲሁም 11 ሌሎች ተጋባዥ እህት ኩባንያዎችና ተቋማት ሲያሳትፍ ቆይቶ የፍጻሜውን ጨዋታ በአዲሱ ስታዲየም አከናውኗል፡፡

በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣ በሜዳ ቴኒስ እንዲሁም በመረብ ኳስ 120 ሠራተኞችን በመያዝ ወደ ስፍራው ያቀና ሲሆን፣ ከውድድር ባሻገር ስታዲየሙን የተለያዩ የስፖርት ልዑካን ቡድኖችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም እንዳለው ለማስተዋወቅ ጭምር እንደሆነ ጠቅላይ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገነባው ይህ ስታዲየም የራሱን ገቢ በማምጣት ለከተማው እንዲሁም ለአካባቢው ኅብረተሰብ መነቃቃትን መፍጠር እንደሚገባው ያመለከቱት ጠቅላይ ሥራ አስፈጻሚው ስታዲየሙ የራሱ ገቢ እንዲኖረው የኢትዮጵያ እግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች የየራሳቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

‹‹ስታዲየሙ የሚገባውን ያህል ተዋውቋል ማለት አይቻልም፡፡ ከአገሪቱ ፌዴሬሽኖች አንዳቸውም በዚህ ዘመናዊ ስታዲየም ተገኝተው ውድድር ለማዘጋጀት ፍላጎትም አላሳዩም፡፡ ስለዚህ ፌዴሬሽኖች የተለያዩ ውድድሮች በማካሄድ ስታዲየሙን ማስተዋወቅ ይገባቸዋል፤›› ያሉት ዶ/ር አረጋ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የበኩላቸውን መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ስታዲየሙ ላይ ውድድር ለማከናወን በአገር ውስጥ የሚገኙት ክለቦች ወደ ወልዲያ በማምራት ጨዋታ ማከናወን ይኖርባቸዋልም ብለዋል፡፡

ስታዲየሙ ከስፖርታዊ ውድድሩ ባሻገር የተለያዩ ስብሰባዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የእንግዳ ማረፊያ አዳራሾችን በመጠቀም በስፍራው ያለውን የቱሪስት መስህብ ማሳደግ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አረጋ አስተያየት ከሆነ፣ ወደ ስፍራው ለማምራት አንዳንድ የትራንስፖርት ጥያቄዎች እየተነሱ ቢሆንም በአውሮፕላን እስከ ኮምቦልቻ በማምራት ቀሪውን 120 ኪሎ ሜትር በመኪና በመጓዝ ጨዋታን ማከናወን እንደሚቻል ነው ያስረዱት፡፡   

በወልዲያ አካባቢ የሆቴሎች እጥረት ስላለ ትልቅ ውድድር ማከናወን አያስችልም የሚሉ አስተያየቶች ቢነሱም፣ ‹‹እስኪ መጀመሪያ እንግዶች ይምጡና የሆቴሎች እጥረት ያጋጥመን፡፡ ሆቴሎችን ለስታዲየም ብቻ ሳይሆን በስፍራው ለሚመጡ ቱሪስቶች መገንባቱ አይቀርም፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑና እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ሌሎች የውድድር አዘጋጆች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በየዓመቱ የሚደረጉ ስፖርታዊ ክንውኖችን በወልዲያ ሁለገብ ስታዲየም እንዲደረጉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ የሚገነቡት ስታዲየሞች ትንንሽ ከተሞች ላይ የተገነቡትን ስታዲየሞች ዕጣ ፈንታ እንደሚያሳጣ የሚገልጹት ዶ/ር አረጋ፣ ሁሉም ስታዲየሞች መቆራኘት አለባቸው ባይ ናቸው፡፡

ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የወልድያ ስታዲየምን ለክልሉ መስተዳድር ካስረከበ በኋላ አካሉ ለሆነው ሆዳ ሪል ስቴት ዲዛይን ሥራና ኮንትራክተር በቅርበት የሚከታተለው ሲሆን፣ በስታዲየሙ ላይ የሚያጋጥሙ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ብቻ ኃላፊነት እንደወሰደም ተናግረዋል፡፡

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዓመታዊ የእግር ኳስ ጨዋታ ቴክ አቃቂና ተጋባዥ የሆነው አዲስ ኢንተርናሽናል ኬተሪንግ ለፍጻሜ የደረሱ ሲሆን፣ ተጋባዡ ቡድን አዲስ ኬተሪንግ 5ለ3 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...