Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ሒልተን ሆቴልን ለመግዛት ፍላጎት አሳየ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ሒልተን ሆቴልን ለመሸጥ በመወሰኑ፣ በሼክ መሐመድ አል አሙዲ ባለቤትነት የሚመራው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፍላጎት ማሳየቱን ምንጮች ገለጹ፡፡

ሚድሮክ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ባለኮከብ ሆቴል የሆነውን ሒልተን አዲስ አበባ በድርድር ለመግዛት 250 ሚሊዮን ዶላር ማቅረቡን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ከድርድር ይልቅ፣ ጨረታ የመጀመርያ አማራጭ እንዲሆን በመወሰኑ የድርድር ሒደቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መንግሥት ሆቴሉን ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ በቅርቡ ጨረታ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሒልተን አዲስ አበባን የራሳቸው ሀብት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩት መካከል ሚድሮክ፣ ሰንሻይን ግሩፕ፣ የሆንግ ኮንግ ኩባንያ የሆነው ሻንግሪላና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ የሆነው አልባዋርዲ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በሆነ ወጪ የገነባው ባለ አምስት ኮከቡ ሸራተን 42 ሔክታር ስፋት ያለው የማስፋፊያ ፕሮጀክት አለው፡፡ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን ሒልተን የመያዝ ዕቅድ ማውጣቱ ተሰምቷል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም. ዕቅዱ ላይ ሒልተን ሆቴልን የመሸጥ ሐሳብ አላሰፈረም፡፡ ሚኒስቴሩ የካቲት 2009 ዓ.ም. ባሳተመው ሰነድ፣ በመንግሥት ሥር የሚቆዩ ናቸው ካላቸው ድርጅቶች መካከል የፍልውኃ አገልግሎት ድርጅትና ግዮን ሆቴሎች ድርጅት፣ እንዲሁም የሆቴል ልማት አክሲዮን ማኅበር (አዲስ አበባ ሒልተን) ይገኙበታል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ፣ አሁንም ቢሆን ሒልተን አዲስ አበባን ለመሸጥ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንዳልሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሒልተን ሆቴልን የመሸጥ ውሳኔ ላይ ሊደርስ የቻለው አገር በቀል ኩባንያዎች ለገነቧቸው ሆቴሎች የማኔጅመንት ሥራ ዓለም አቀፉ ሒልተን እንዲያስተዳድርላቸው በሚፈልጉበት ወቅት፣ ሒልተን ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጋር በገባው ውል ሌሎች ሆቴሎች በሒልተን ስም እንዳይተዳደሩ የሚከለክል በመሆኑ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥ በመጠየቃቸው ነው፡፡

በተለይ ሰንሻይን ግሩፕና ፀሜክስ ሆቴልና ቢዝነስ ኩባንያ የገነቧቸውና  የሚገነቧቸው ሆቴሎች፣ በሒልተን ኢንተርናሽናል እንዲተዳደሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ላለፉት 50 ዓመታት ሆቴሉን ሲያስተዳድር የቆየው ሒልተን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የገባው ውል ሊጠናቀቅ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ ብቻ ነው የቀረው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሒልተን የንግድ ስያሜ መተዳደር የሚፈልጉ ሆቴሎች ፍላጎታቸው እንዲሟላ፣ ሒልተን ሆቴል በመንግሥት ሥር መቆየት የለበትም ብሎ እንደወሰነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩን በበላይነት እየተከታተለ የሚገኘው በብሔራዊ ፕላን ኮሚሸነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የሚመራው የሆቴሎች ልማት አክሲዮን ማኅበር (ሒልተን ሆቴል) ሥራ አመራር ቦርድ ነው፡፡

ዶ/ር ይናገር በሒልተን አዲስ አበባ የሽያጭ ሒደት ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለማድረግ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በስድስት ሔክታር ላይ የተንጣለለው የሒልተን አዲስ አበባ ሕንፃ 12 ወለል ከፍታ ያለው ሲሆን፣ በላሊበላ ኪነ ሕንፃ ቅርፅ የተገነባ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች