Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየብሔራዊ ስፖርት አካዴሚ ተልዕኮና እንቅስቃሴው

የብሔራዊ ስፖርት አካዴሚ ተልዕኮና እንቅስቃሴው

ቀን:

የስፖርት እንቅስቃሴን ለማሳደግ በታዳጊ ወጣቶች ላይ መሥራት አማራጭ የሌለው መሆኑ ይታመናል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት ማምጣት  የቻሉ አገሮች ምስጢር በተተኪዎች ላይ መሥራት መቻላቸው ነው፡፡ ስፖርቱ ያለውን አዎንታዊ ጥቅም በመረዳት በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መንገድ ለመከተል የተለያዩ የወጣቶች የአካዴሚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ አካዴሚዎች ተተኪዎችን ከማፍራት ባሻገር ለክለቦች ግብዓት በመሆን ቀድሞ ውድድር ብቻ ጠብቀው ምልመላ ያከናውኑ የነበረውን አሠራር በመቀየር ወደ አካዴሚው በማቅናት የፈለጉትን ስፖርተኛ ማግኘት የሚያችል አካሄድ መዘርጋት ተችሏል፡፡ ታዳጊዎችም የምግብ፣ የጂምናዚየም፣ የትምህርትና የውድድር ሥልጠናዎችን በማግኘትና ችሎታቸውን በማዳበር ወደ ተለያዩ ክለቦች  በመዘዋወር የራሳቸውን አቅም ለማጠናከር ያስችላቸዋል፡፡ አሁን አሁን በሁለቱም ጾታ የሚሰጠው የእግር ኳስና የአትሌቲክስ መሠረታዊ ሥልጠና ለክለቦች ሥራን ማቅለያ እየሆነም ይገኛል፡፡

በሦስተኛ ዓመት የሥልጠና ጊዜያቸው ላይ የክለቦችን ቀልብ የሚገዙት የአካዴሚ ትሩፋቶች ከስፖርታዊ ሥልጠና ጋር በትምህርት ደረጃቸውም የተሻለ ውጤት ማምጣት  እንዲችሉ ትልቅ እገዛ እየተደረገላቸውም ነው፡፡

በ2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤምፔሪያል አካባቢ ታዳጊዎችን ተቀብሎ ማሠልጠን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ ለአራት ዓመታት ያሠለጠናቸውን ታዳጊዎች ዘንድሮ ማስመረቅ ችሏል፡፡ በአካዴሚው እንቅስቃሴ ዙርያ የትምህርት ሥልጠናና ውድድር ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ከበደን ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- ብሔራዊው የወጣቶች ስፖርት አካዴሚ እንቅስቃሴ አጀማመር ምን ይመስላል?

አቶ ተሾመ፡- አካዴሚው በ2005 ዓ.ም. በሻሸመኔ ከተማ በተካሄደው የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጄክት ላይ ሠልጣኖዎችን በመመልመል በ2006 ዓ.ም. በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች በይፋ ሥራውን የጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስ፣ ውኃ ዋና፣ ቦክስ፣ እግር ኳስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶና በብስክሌት ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በምልመላ ሒደትም የተለያዩ መለኪያዎች አካቷል፡፡ በዚህም መሠረት ብቃት ላይ በማተኮር የትኛው ክልልና አካባቢ የተሻለ ስፖርተኛ አለው የሚለውን በመለየት ምርጫ  እናከናውናለን፡፡ መነሻም የሆነን በአሰላ የሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቶች ማሠልጠኛ ተቋም ነው፡፡ በማዕከሉ የተሠሩ ስህተቶችን በዚህም እንዳይደገሙ ትምህርት በመውሰድ ፌዴሬሽኖች በሚያሰናዱት ውድድሮች ላይ በመዘዋወርና አቅም ያላቸውን ታዳጊዎች በመምረጥ ወደ አካዴሚው መጥተው ሥልጠና እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፍትሐዊ የሆነ የምልመላ ዘዴን ከመከተል አንፃርስ ምን ዓይነት መንገድ ትከተላላችሁ?

አቶ ተሾመ፡- ተቋሙ የፌዴራል እንደመሆኑ መጠን ብቃትን መሠረት ባደረገ መልኩ ምልመላ እናካሂዳለን፡፡ ምክንያቱም ክልሎች በኮታ ውስጥ አይካተቱም፡፡ በአንፃሩ ግን ክልሎች ያሏቸውን ታዳጊዎች በማሳተፍ ዕድሉን መጠቀም ይኖርባቸዋል በማለት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም በፌዴሬሽኖች ከሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ታዳጊዎችን እንመርጣለን፡፡

በምርጫ ወቅት ብቃትን ብቻ እንደአማራጭ አንወስድም፡፡ ታዳጊዎቹ ወደ ማሠልጠኛ ማዕከሉ ሲመጡ የተለያዩ መለኪያዎችን ማለፍ ይገባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መነሻ ያደረጋችሁትን የሥልጠና አካሄድ ቢያብራሩልን?

አቶ ተሾመ፡- ሥልጠናው መነሻ የሚያደርገው እንደ አገር የተዘጋጀ ደረጃ አለው፡፡ እንዲሁም የተቀመጠ ሥርዓተ ትምህርት ዋነኛዎቹ የሥልጠናው መሠረታዊ አካሄድ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር በማንዋል ከሚሰጠው ስልጠና በተጨማሪ በሜዳ ላይ በተግባር የሚታይ፣ በትምህርትና በጅምናዝየም የታገዘ ሥልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ታዳጊ በአካዴሚ ውስጥ የአራት ዓመት ቆይታ ይኖረዋል፡፡ ሥልጠና ላይ ብቻ ትኩረት እንደመደረጉ መጠን ሥልጠናውን ምን ያህል እንደጠቀማቸው በምን መንገድ ማረጋገጥ ትችላላችሁ?

አቶ ተሾመ፡- በእርግጥ አካዴሚዎች ውድድር ላይ መሳተፍ አይችሉም የሚል ሕግ አለ፡፡ ሆኖም ግን እንደ አገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ የግድ ዓመታዊ ውድድሮች ላይ ታዳጊዎችን እናሳትፋለን፡፡ በዚህ ዓይነት ታዳጊዎች ሥልጠና ብቻ የሚያገኝ ከሆነ ሠልጣኝ እንጂ ተወዳዳሪ መሆን አይችሉም፡፡ ስለዚህ በሦስት ዓላማዎች ውድድር ላይ  እንገባለን፡፡ አንደኛው ሥልጠናችንን ለመገምገም፣ ሁለተኛው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ተተኪዎችን መፍጠር ሲሆን፣  ሦስተኛው ደግሞ ለክለቦች ግብዓት የመሆን ዓላማን ሰንቀን ነው፡፡ ስለዚህ ዓመታዊ ውድድሮች የታዳጊዎቹን ትክክለኛ ብቃት ለመመልከት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ግን እኛ በምናዘጋጀው ፈተና ብቻ የልጆቹን ችሎታ መገምገም ወይም ማሻሻል አይቻልም፡፡ ተመልካች፣ አሠልጣኝ፣ ተቃራኒ ቡድን ባለበትና ዳኞች በተገኙበት በሚደረገው ጨዋታ የታዳጊዎቹ ችሎታ የበለጠ ለማዳበር ስለሚያስፈልግ ፌዴሬሽኖችና ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የሚያዘጋጁት ውድድሮች ለእኛ ወሳኝ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እኛ ያዘጋጀናቸው የልጆቹን ብቃት በሚከታተሉ (Performance Analysis) ባለሙያዎች አማካይነት እንገመግማቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ታዳጊዎቹ የአራት ዓመታት ቆይታን ካደረጉ በኋላ በክለቦች ያላቸው ተቀባይነት ምን ይመስላል?

አቶ ተሾመ፡- ዘንድሮ የአራት ዓመት ቆይታቸውን አጠናቀው የተመረቁ 125 ሠልጣኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሠልጣኞች ከጥቂት የእግር ኳስ ተጫዋቾች በስተቀር ሁሉም ወደ ተለያዩ ክለቦች የሚዘዋወሩበትን ስምምነት አጠናቀዋል፡፡ እግር ኳስን በተመለከተ ለክለቦች የተጫዋቾችን ስም ዝርዝር የሰጠን ሲሆን፣ ክለቦችም መስከረም ላይ በራሳቸው ግምገማ መሠረት እንደሚያስፈሩማቸው ነግረውናል፡፡ በእርግጥ በእግር ኳሉም ቢሆን 90 ተጫዋቾች ተመርቀው ክለብ ያገኙት 30 ብቻ ናቸው፡፡ የቀሩት በቀጣይ ወራት ወደ ተለያዩ ክለቦች እንዲዘዋወሩ እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሥልጠና ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ክለቦች የተዘዋወሩትን አትሌቶች ቁጥርና የስፖርት ዓይነቶች ቢጠቅሱልን?

አቶ ተሾመ፡- ዘንድሮ ከተመረቁት ሠልጣኞች ውስጥ በአትሌቲክስ 19 ተመራቂዎች የነበሩ ሲሆን፣ ሁሉም ወደ ተለያዩ ክለቦች መግባት ችለዋል፡፡ በብስክሌት የነበሩን 15 ሠልጣኞች  ሁሉም ወደ ክለብ ሄደዋል፡፡ በቦክስም ተመሳሳይ ነው፡፡ በመረብ ኳስ ሰባት ልጆችና በቅርጫት ኳስ ከዘጠኝ ልጆች ስምንቱ ወደ ክለብ መግባት ችለዋል፡፡

      ነገር ግን ዘንድሮ ከሚመረቁት ውስጥ የወርልድ ቴኳንዶና የውኃ ስፖርት ላይ ክለብ ባለመኖሩ ወደ ክለብ መዘዋወር አልቻሉም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ወጣቶችና ስፖርት መፍትሔ እንደሚያስቀምጥ ተነጋግረንበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የታዳጊዎች ወይም የወጣቶች ውድድር ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ምን ይመስላል?

አቶ ተሾመ፡- አትሌቲክስን በተመለከተ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት በሁሉም ውድድሮች እንሳተፋለን፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ አዋቂ አትሌቶች ባይኖሩንም፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት ጀምሮ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ እናሳትፋለን፡፡ በአራተኛው የታዳጊዎች ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ በወንዶችና በሴቶች ስድሰተኛ ደረጃ ይዘን አጠናቀናል፡፡ የምንሳተፍበት  የአትሌቲክስ የውድድር ዓይነቶች ጥቂት ናቸው፡፡ የሜዳ ተግባር ላይ ምንም ዓይነት ተወዳዳሪዎች ስለሌሉንና የመቀበል አቅማችን 320 በመሆኑ ውጤታችን እምብዛም ነው፡፡ ባለን አቅም  በአጭር ርቀት ተሳትፈን አመርቂ ውጤት ማምጣት ችለናል፡፡ በአገር ውስጥ በ3,000 ሺሕ ሜትር መሰናክል በወጣቶች የወርቅ ሜዳሊያና በመቶ ሜትር ነሐስ ያስመዘገብናቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌላኛው እግር ኳስ ሲሆን፣ በወንዶችም በሴቶችም በተለያዩ ውድድሮች ላይ እንሳተፋለን፡፡ በተለይ በሴቶች ባለፈው ዓመት ከዲቪዚዮን ወደ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በማደግ ተሳታፊ መሆን ችለናል፡፡ ዘንድሮም ከኮካኮላ ሻምፒዮና የመጡትን ታዳጊዎች በመያዝ የዲቪዝዮን ዋንጫ ማንሳት ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- አካዴሚው ተገንብቶ ሥራ ከጀመረ በኋላ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲነሱበት ነበር፡፡ መገንባቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድነው ማለት ይቻላል?

አቶ ተሾመ፡- በመጀመሪያ ደረጃ አካዴሚው መነሻ አድርጎ የተነሳው በክልሎች ላይ ያለው የታዳጊዎች አቅም ለመለየት ነው፡፡ በተጨማሪም አቅም ያላቸው አካባቢዎችን ከለየ በኋላ የተመለመሉት ታዳጊዎች ወደ አካዴሚው ገብተው ሥልጠና መውሰድ እንዳለባቸው በማሰብ ነው፡፡ በታዳጊዎች ላይ ወርዶ የመሥራት ልምድ እምብዛም ስለሆነ አራት ዓመት ሥልጠና ወስደው ያጠናቀቁ ታዳጊዎችን ወደ ተለያዩ ክለቦች እንዲዘዋወሩ በማድረግና ተቆርጦ የቀረውን ሥራ አካዴሚው እያከናወነን እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ታዳጊዎችን ከማፍራት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ማለት ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ክለቦች ከአካዴሚው ጋር ያላቸው ግንኙነት  ምን ይመስላል?

አቶ ተሾመ፡- ቀድሞ የነበረው አካሄድ ለምሳሌ የአትሌቲክስ ክለቦችን ብንመለከት አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው አትሌቶችን ከውድድር ጠብቀው ነበር የሚመርጡት፡፡ አሁን ግን ታች ክልል ድረስ አብረውን በመውረድ ተሻምተው መውሰድ ጀምረዋል፡፡ ክለቦች ከእኛ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመመካከር ልምድ የመውሰድ አሠራርን ማዳበር እየቻሉ ናቸው፡፡

     ከጥሩነሽ ዲባባ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ጀምሮ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች 533 አትሌቶችን ወደ ተለያዩ ክለቦች ማዘዋወር ችለናል፡፡ እስካሁን ወደ 299 ሠልጣኞችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ችለናል፡፡ በተጨማሪ መብራት ኃይል፣ ንግድ ባንክና ክልሎች ሠልጣኞቻችንን ከእኛ  በየዓመቱ ለመውሰድ የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጅት ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ክለቦች ወደ አካዴሚው በመምጣት ታዳጊዎችን ለመልመል ሲመጡ  የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው፣ አትሌቶችን ለማስፈረም ጊዜ እንደሚወስድባቸው ይነገራል፡፡ ለዚህ መንስዔው ምንድነው?

አቶ ተሾመ፡- ሠልጣኞች ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ክለብ ለመሄድ የግድ ክለቦቹ ተጫዋቾቹን ወይንም አትሌቶቹን ማየት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ክለቦች መቀመጫቸው አዲስ አበባ ላይ እንደመሆኑ መጠን የክለብ አመራሮች ወደ አካዴሚው በማምራት የሚፈልጉትን ሠልጣኞች ለማግኘት በልምምድ ወቅት ተገኝተው ክትትል ሲያደርጉ አይስተዋልም፡፡ ውድድር ላይ ከሚመለከቱት ብቃት ባሻገር በየጊዜው በልምምድ ቦታ ላይ ተገኝተው መመልከት ቢችሉ የፈለጉትንና ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን ማግኘት ይችላሉ፡፡ ያንን የሚያደርጉ ቢኖሩ ሒደቱም አጭር ይሆኑ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡-  በአካዴሚው ላይ እንደ ችግር የሚነሳ ነገር ምንድነው?

አቶ ተሾመ፡- ሠልጣኞችን በምንመለምልበት ወቅት ከክልሎች ጋር የሚያጋጥመን ችግር አንዱ ነው፡፡ አንድ አንድ ክልሎች አቅም ያላቸውን ታዳጊዎች ማውጣት አይፈልጉም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የእኛ መመረጥ አለበት ብለው አለመግባባት የሚፈጥሩበት ወቅት አለ፡፡ ሌላኛው በአካዴሚው ውስጥ ያለ ችግር ሲሆን እሱም ለሠልጣኞች ሰርቪስ የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ዕጥረት መኖርና የውኃ ገንዳው ቴክኒካል ችግር አጋጥሞት አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑና የቦክስ ሪንግ አለመሟላት ለጊዜው ያሉብን ችግሮች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...