Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየባሕር ዳር ወወክማ በ49 ሚሊዮን ብር አዲስ ማዕከል ሊያስገነባ ነው

የባሕር ዳር ወወክማ በ49 ሚሊዮን ብር አዲስ ማዕከል ሊያስገነባ ነው

ቀን:

የባሕር ዳር ወወክማ (የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) በ49 ሚሊዮን ብር አዲስ ማዕከል ሊያስገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ‹‹መልቲ ፐርፐርዝ ኢንተርናሽናል ዩዝ ሴንተር›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ማዕከል ነባሩ ማዕከል ባለበት 15 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ውስጥ እንደሚያርፍም ተገልጿል፡፡

የቀደመው ማዕከል፣ ጂምናዚየም፣ የእግር ኳስና የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችና ሌሎች ዐውደ ብዙ አገልግሎቶችን ያካተተ ሲሆን፣ በጅምናዚየሙ ውስጥ የሚገኙት አጠቃላይ የስፖርት መሣሪያዎችም 6.2 ሚሊዮን ብር ይገመታሉ፡፡ አዲስ የሚገነባው ማዕከልም ከሰባት ዓመታት በፊት በተገነባው ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚያርፍ መሆኑን ዳይሬክተሩ አቶ ጥበቡ በላይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አራት ፎቅ ኖሮት የሚሠራው አዲሱ ማዕከል 62 ማደሪያዎች፣ ካፍቴሪያ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ 22 ሱቆች፣ ሁለት አዳራሾችና ሌሎችም ዓይነት አገልግሎት ያካተተ ይሆናል፡፡

‹‹ወወክማ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ሲቋቋም የሌሎች አገሮችን ልምድ በማየት ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ወወክማዎች በርካሽ ዋጋ ሰዎችን የሚያስተናግዱ ማደሪያዎች አሏቸው፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ተሞክሮ ነበር፡፡ አራት ኪሎ ያለው ወወክማ ማደሪያዎች አሉት፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ወወክማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ፣ 62 ማደሪያዎችን ያካተተው ይኼ ማዕከል ዲዛይኑ ተጠናቆ ወደ ቀጣይ ሥራ መገባቱን ይናገራሉ፡፡

ከአጠቃላይ ገቢው አሥር በመቶ የሚሆነውን ከአገር ውስጥ፣ 90 በመቶውን ደግሞ ከውጭ ለጋሽ ድርጅቶች የሚያገኘው ወወክማ፣ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ወጪ ከወዲሁ ማሰባሰብ ጀምሯል፡፡ እስከ ዓመቱ መጨረሻ 16.2 ሚሊዮን ብር የመሰብሰብ ዓላማ ይዞ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል፡፡ ‹‹ከአገር ውስጥ የተጠበቀውን ያህል ምላሽ አላገኘንም፡፡ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ግን በተቃራኒው ጥሩ ምላሽ እያገኘን ነው፡፡ እስካሁን 24 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶልናል፡፡ ይህም ከጠበቅነው በላይ ነው፤›› በማለት የግንባታውን ወጪ ለመሸፈን እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አቶ ጥበቡ አብራርተዋል፡፡

ግንባታው በ2010 ዓ.ም. የሚጀመር ሲሆን፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አቶ ጥበቡ ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ ወርኃዊ ገቢም አሁን ካለበት 20 ሺሕ ብር ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር እንደሚያሳድገው፣ ለ120 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችልም መሆኑንም አክለዋል፡፡

በ1940 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ወወክማ በትምህርት፣ በስፖርት፣ በኪነ ጥበብ፣ በጤና፣ በሕይወት ክህሎትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከወጣቶች ጋር ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ወወክማ በተለይ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) በነበሩት ሦስት አሠርታት ባከናወነው በርካታ አገልግሎቱ በሰብአዊ አገልግሎት ዘርፍ ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት›› ሽልማት ያገኘ የመጀመሪያው የበጎ ፈቃደኞች ማኅበር ነው፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፎች በመክፈት አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ ሲሆን፣ በቅርቡም የተቋቋመበትን 70ኛ ዓመት አክብሯል፡፡ ካሉት ጠንካራ ማዕከላት አንዱ የባሕር ዳር ወወክማ መሆኑን አቶ ዳግማዊ ይናገራሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...