Tuesday, July 23, 2024

[ክቡር ሚኒስትሩ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ሳይገኝ ከቀረው አንድ የተቋማቸው ባልደረባ የሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን አስጠርተው እያናገሩ ነው]

 • ለምንድነው በዚህ አገራዊ ፋይዳ ባለው ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው?
 • ክቡር ሚኒስትር ህሊናዬ አልፈቀደልኝም።
 • መቃወምና መተቸት ብቻ ውጤት የሚያመጣ መስልዎህ ከሆነ ተሳስተሃል።
 • አልተሳሳትኩም ክቡር ሚኒስትር?
 • ቆይ የመጀመሪያ ዓመት የችግኝ ተከላ ፕርግራም ላይ ግንባር ቀደም አልነበርክም እንዴ?
 • ነበርኩ።
 • እንዲያውም ችግኝ ስታድል ነበር።
 • ልክ ነው ሳድል ነበር።
 • ታዲያ አሁን ምን ተፈጠረ? ምን የተለየ ነገር መጣ?
 • ክቡር ሚኒስትር ያኔ ችግኝ ተከላውን ሳስተባብር ዜጎች ክብር ነበራቸው።
 • አሁንስ?
 • አሁንማ ችግኝ ተከላ ብቻ አይደለም የምታካሂዱት።
 • ሌላ ምን እናካሂደለን? 
 • ነቀላ።
 • የምን ነቀላ ነው ? 
 • የነዋሪዎች። 
 • ምን?
 • ነዋሪዎችን ታፈናቅላላችሁ፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ትነቅላላችሁ።
 • ለኮሪደር ልማት የተነሱትን ነዋሪዎች እኮ ምትክ ቤት ተሰጥቷቸዋል። 
 • ያልተሰጣቸው አሉ። ከቀዬአቸው ርቀው መብራትና ውኃ በሌለበት የተወረወሩ አሉ።
 • እና በዚህ ምክንያት ነው ችግኝ የመትከል ፕሮግራም ላይ ያልተገኘኸው?
 • በዚህ ብቻ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
 • ሌላው ምክንያትህ ምንድነው?
 • የመንግሥት ተቀጣሪው የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶት ቢሮ እያደረ ነው።
 • እሺ … ሌላስ? 
 • ምሳ የሚበላበት እጅ አጥሮት በእምነት ተቋማት እያሳለፈ ነው። እናንተ ግን እየሰማችሁ ምንም አላደረጋችሁም። 
 • ሌላ የምትለው አለ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ችግኝ መተከል እንዳለበት አምናለሁ ነገር ግን ሰው ይቀድማል።
 • ሰው ይቀድማል ስትል ምን ማለትህ ነው?
 • መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ለችግኝ የሰጡትን ያህል ትኩረት ለዜጋው እየሰጡ አይደለም። 
 • እንዴት? እና ማንን ነው እያገለገልን ያለነው? 
 • ዜጋው ለችግኝ የተሰጠውን ያህል ትኩረት አላገኘም። በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው። በልቶ የሚያደርው እያጣ ነው።
 • እርግጥ ነው የሁሉም ነገር ዋጋ ጨምሯል። ቢሆንም መንግሥት ዝም ብሎ አልተቀመጠም። 
 • ክቡር ሚኒስትር ተሳስተዋል።
 • ምንድነው የተሳሳትኩት?
 • እዚህ አገር የሁሉም ዋጋ ጨምሯል ያሉት ትክክል አይደለም።
 • እንዴት?
 • ዋጋው የቀነሰም አለ።
 • የምን ዋጋ ቀነሰ።
 • የሰው ልጅ።

[ክቡር ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪያቸው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው]

 • እና ሕዝቡ ሥራችንን አልወደደውም እያልክ ነው? 
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ባሰባሰብኩት መረጃ ያስተዋልኩት ያንን ነው። 
 • እስኪ ምሳሌ ጠቅሰህ አስረዳኝ? ምን ዓይነት ትችት ነው የሚቀርበው? ምን እየተባለ ነው?
 • መንግሥት የነዋሪውን የመኖሪያ ቤት ችግር ይፈታል ሲባል የቀበሌ ቤት ጣሪያ ይጠግናል እየተባለ ነው።
 • እንዴት? ድሆች በክረምት ወቅት እንደሚቸገሩ መንግሥት እያወቀ ዝም ብሎ ማየት ነበረበት? 
 • እንደዚያ ለማለት ተፈልጎ አይመስለኝም።
 • እና ምን ለማለት ተፈልጎ ነው የሚመስልህ?
 • መንግሥት ትናንሽ ጉዳዮችን ለማኅበረሰቡ ትቶ በሚመለከተው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኩር ለማለት ይመስለኛል።
 • እሺ ይኼን ተወውና ሌላ እየተባለ ያለ ነገር ካለ ንገረኝ?
 • ሌላው ትችት ምን መሰልዎት?
 • እ …?
 • መንግሥት ከሚሠራው ይልቅ ታይታ ላይ ያተኩራል ይባላል።
 • እሱ ደግሞ ምን ማለት ነው? 
 • የመንግሥት ፕሮጀክቶች ለማኅበረሰቡ ካስገኙት ፋይዳ ይልቅ ለባለሥልጣናት ያስገኙት ይበልጣል ለማለት ፈልገው ነው።
 • እንዴት? ባለሥልጣናት ምን አገኙ?
 • ባለሥልጣናት ሥራ የሠሩ መስለው ይታዩባቸዋል ይባላል።
 • እንዴት? 
 • ደጋግመው በመጎብኘት እና …
 • እና … ምን?
 • በማስጎብኘት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጃቸው ከሆነች አንድ ባለሀብት የተደወለላቸውን ስልክ አንስተው በኮሪደር ልማቱ ላይ የምታቀርበውን ቅሬታ እየሰሙ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እኔ የኮሪደር ልማቱ ላይ ተቃውሞም ሆነ ጥላቻ እንደሌለኝ የሚያውቁ ይመስለኛል? በዚህ እንኳን አትታሚም።  የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር። አውቃለሁ ስልሽ? ለኮሪደር ልማቱ አዋጡ ሲባልም ያለማመንታት አምስት ሚሊዮን...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላነጋግርህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡ እርስዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም፣ ምን ገጠመዎት? እኔማ ምን ይገጥመኛል አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ? ምን? እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል፡፡ ይንገሩኝ...

[ክቡር ሚኒስትሩ በቢሯቸው ሆነው ከአማካሪያቸው ጋር ስለወቅታዊ ጉዳዮች እየተነጋገሩ ነው]

ትናንት የሆነውን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር? አልሰማሁም፣ ምን ሆነ?  ኬንያውያን የአገሪቱን ፓርላማ ጥሰው መግባታቸውን አልሰሙም? ኧረ አልሰማሁም።  የፓርላማውን በር ጥሰው ገብተው አንደኛውን ክፍል በእሳት አያያዙት፡፡  ምንድነው ምክንያቱ?  የአገሪቱ መንግሥት ያቀረበው አዲስ...