Tuesday, July 23, 2024

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (UN OHCHR) የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2023 የሰብዓ

ዊ መብት ጥሰት መጨመሩን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት በ2023 በኢትዮጵያ የተመዘገበው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አኃዝ ከቀደመው እ.ኤ.አ. 2022 በ55.9 በመቶ የጨመረ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢቀንስም፣ ነገር ግን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚካሄዱ ውጊያዎች ዋነኞቹ ለሰብዓዊ መብት መጣስ ምክንያት መሆናቸውን ይናገራል፡፡ በአማራ ክልል ከፋኖ ኃይሎች ጋር የቀጠለው እንዲሁም በኦሮሚያ ከኦነግ ሸኔ ጋር የሚካሄደው ጦርነት፣ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ ጥሏል ይላል፡፡

በአንድ ዓመት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በ594 አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መከሰቱን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ በዚህም 343 ሴቶችን ጨምሮ በ8,253 ሰዎች ላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መፈጸሙን አመልክቷል፡፡ በአጠቃላይ 202 እስር ቤቶችን ጨምሮ ወደ 600 ያህል ምርመራዎችን በባለሙያዎች ሲያካሂድ መቆየቱን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን አሳሳቢ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች የሚፈጸምባት አገር እንደሆነች አረጋግጫለሁ ይላል፡፡ በዓመቱ ወደ 18 ጊዜ የድሮን ጥቃቶች በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ መንግሥት መፈጸሙን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ በእነዚህ የድሮን ጥቃቶችም 248 ንፁኃን ተገድለው 55 መቁሰላቸውን ይጠቅሳል፡፡

ሪፖርቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከእነ ዓይነታቸው በአኃዝ ሲያስቀምጥም በአጠቃላይ 1,356 ግድያዎች፣ 796 የመቁሰል አደጋዎች፣ 346 ማሰቃየትና ኢሰብዓዊ አያያዞች፣ 82 ፆታዊ ወንጀሎች፣ 5,411 የዘፈቀደ እስራቶች፣ 243 አስገድዶ መሰወርና ጠለፋ፣ 24 የንብረት ውድመቶች መከሰታቸውን ይዘረዝራል፡፡ ሪፖርቱ በዚህ ዓመታዊ ግምገማው በኢትዮጵያ ከሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ አብላጫዎቹ ወይም 70 በመቶዎቹ በመንግሥት ኃይሎች የተፈጸሙ ናቸው ይላል፡፡

ይህን መሰሉን በኢትዮጵያ ይፈጸማል የሚባል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ደግሞ የአገር ውስጡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጭምር በሪፖርቱ ሲያጠናክረው ይታያል፡፡

ኢሰመኮ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉ የትጥቅ ግጭቶችና በተለያዩ ቦታዎች በሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረሶች ምክንያት፣ በታጠቁ ኃይሎችና በመንግሥት የፀጥታ አካላት በተወሰዱ ዕርምጃዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ የሞትና የአካል ጉዳቶች አሳሳቢነት ቀጥሏል ሲል ገልጿል፡፡ ኢሰመኮ በሪፖርቱ የሰላማዊ ሰዎች በሕይወት የመኖር መብትን ጨምሮ በርካታ ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአገሪቱ ማጋጠሙን አስታውቋል፡፡

ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው የኮሚሽኑ ሦስተኛው ዓመታዊ ሪፖርት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በአንድ ወገን መሻሻሎች ቢታይበትም፣ በተቃራኒው ግን በአሳሳቢ ደረጃ መባባሱን ያመለክታል፡፡ ባለ132 ገጽ ሪፖርት በትጥቅ ግጭት ወቅት፣ በግጭት ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎች ግጭት በሌለበት ወቅትም ጭምር የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች እጅግ አሳሳቢ ሆነው ቀጥለዋል በማለት ነው ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያትተው፡፡

በኢትዮጵያ በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ማግሥት በርካታ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ መሻሻሎች በኢትዮጵያ ስለመታየታቸው ብዙ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሙገሳዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኦሮሚያ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ኃይሎች ወደ ጫካ ዳግም መግባታቸውን ተከትሎ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የፖለቲካ ነውጦችና አመፆች መፈጠራቸው፣ እንዲሁም ከትግራዩ ጦርነት መጀመር ወዲህ ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን በሚመለከት አዎንታዊ ሪፖርቶች መውጣታቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ፖለቲከኞችን ከእስር በመፍታቷ በለውጡ ወቅት ኢትዮጵያን ሲያደንቋት ቆይተዋል፡፡ በሚዲያ ነፃነት፣ በፖለቲካ ምኅዳር ማስፋት፣ የታጠቁ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጭምር ከውጭ እንዲመጡ በመፍቀድ በርካቶች ሲያወድሷት ቆይተዋል፡፡ ፀረ ሽብር ሕጉን ጨምሮ ሽብርተኝነትን በተመለከተ አዲስ አመለካከትና የሕግ አተያይ ኢትዮጵያ ፈጠረች በሚል ስትደነቅ ቆይታለች፡፡

በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅና አያያዝ ላይ መጣ የተባለው ለውጥ በለውጡ ማግሥት ብዙ ዶክመንተሪዎችም ሲሠሩለት እንደነበረ ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡ በቀደመው መንግሥት የተፈጸሙ አስከፊ የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች አያያዞች በለውጡ ወቅት ከተፈጠሩ ክስተቶች ጋር በተነፃፃሪነት እየቀረቡ፣ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ረገድ ዳግም ወደ ኋላ ልትመለስ በማትችልበት መንገድ ዕርምጃ ስለመጀመሯ ብዙ ሲባል መቆየቱም አይዘነጋም፡፡

እንደ ማዕከላዊ ያሉ አስከፊ እስር ቤቶች ሙዚየም ተደርገው የቀደመው ዘመን አገዛዞች ጥፋትን ትውልድ የሚማርበት ቦታ ሊሆን ነው ተብሎ ብዙ ተለፈፈ፡፡ ሰዎችን ሳያጣሩ ማሰርም ሆነ አስሮ ማሰቃት ታሪክ ሊሆን ነው የሚለው ተስፋ ብዙ ሲወደስ ቆየ፡፡ ጅግጅጋ ከተማ ላይ ሰዎች ከጅብና ከነብር ጋር እየታሰሩ ይሰቃዩበት የነበረው እንደ ጄል ኦጋዴን ያለው እስር ቤትም ቢሆን ሙዚየም ሊሆን ነው የሚለውን ዜና መንግሥት ሲያስነግር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

ይህ ሁሉ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ በተከታታይ መሻሻል እያሳየ እንደሚሄድ ብዙ ተስፋ አሰንቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በየቦታው ግጭትና ብጥብጥ መባባሱ በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ብልጭ ማለት የጀመረውን የለውጥ ተስፋ ይፈትነው ጀመር፡፡ ይባስ ብሎ የሰሜኑ ጦርነት መፈንዳት የለየለት የሰብዓዊ መብት ቀውስ በኢትዮጵያ እንዲፈጠር ማድረጉ ይነገራል፡፡   

አሁን በለውጡ ወቅት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ታይቶ የነበረውን አዎንታዊ ለውጥ በናፍቆት የሚያስታውሱ ብዙ ናቸው፡፡ ወደ እዚያ ሁኔታ መመለስ ካልተቻለም የተባባሰውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ቀውስ ማስቆም በአገሪቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንዲሆን የሚወተውቱ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ እንዲሆን የሚወተውቱ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ደግሞ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከፍሪደም ሀውስ እስከ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እስከ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከኢሰመኮ እስከ ኢሰመጉ በርካታ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ለገባቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሕጎችና ቃል ኪዳኖች እንድትገዛ መወትወታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ይህን ሁኔታ የወደደው አይመስልም፡፡ በተለይ ከሰሞኑ ፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገኝተው የሰጡት ማብራሪያ ይህንን የመንግሥትን ስሜት በግልጽ ያሳየ ነበር በሚል በብዙዎች ግምት ተወስዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በነበረው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የሰብዓዊ መብት ጉዳይን የተመለከተ ሐሳብን አንስተው ነበር፡፡ ‹‹ሰብዓዊ መብት ደስ የሚል ቋንቋ ነው፡፡ ለሰው ልጆች የሚደረግ መብት እንዲያው በግርድፉ ሲታይ ደስ የሚል ቋንቋ ነው፤›› በማለት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳባቸውን የጀመሩት፡፡ ይህ ቋንቋ ግን ከዋናው የትርጉም ግንድ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንደሆነ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ብዙ የአፍሪካ አገሮች የሚታመሱት በዚህ ዕይታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለሰው ልጆች መብት ማሰብ የሰው ልጆችን ማክበር ዝም ብሎ በዩቲዩብ በመናገር ብቻ ሳይሆን የተሻለ ቤት እንዲኖራቸው፣ የተሻለ ቦታ እንዲማሩ፣ እንዲበሉ፣ ክብር ያለው ሕይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ጭምር ነው እንጂ ስለነሱ ቤት፣ ስለነሱ ምግብ ሳትጨነቅ በሚዲያ መናገር ብቻ መብት ሊሆን አይችልም፤›› በማለት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እነዚህን ሁሉ ባቀፈ መንገድ መታየት እንደሚኖርበት ተናግረው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲቀጥሉም፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት የሚባሉ አዋጅ፣ ተቋምና አሠራር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ደመወዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው፡፡ እኔ በየትም ቦታ ያሉ የሰብዓዊ መብት የሚባለውን ሐሳቦችና ተቋማትን የማያቸው ልክ እንደ መርፌ ነው፡፡ መርፌ የራሱን ቀዳዳ መስፋት አይችልም፣ እነሱም የራሳቸውን ስህተት ማየት አይችሉም፡፡ ይህ ጥሩ አይደለም አገር ያፈርሳል፡፡ ተቋሞቻችንን መፈተሽ አለብን፤›› በማለትም ጠንከር ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡  

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ግን የተለያየ አስተያየት ከተለያየ አቅጣጫ የሚያስነሳ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ ለዚህ ማብራሪያ መነሻ የሆነውን ጥያቄ በምክር ቤቱ ያነሱት በምክር ቤቱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ተወካይ አቶ አበባው ደሳለው ነበሩ፡፡ በአማራ ክልልና በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ አካላት የጅምላ ግድያን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አጣሪ አካል ገብቶ ጉዳዩን በማጣራት አጥፊዎች በፍትሕ አደባባይ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ መንግሥት ዝግጁነት ያለው መሆን አለመሆኑን በዕለቱ አቶ አበባው ሲጠይቁ ተደምጠዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ ያልተጠበቀና የተሳሳተ እንደሆነባቸው ነው አቶ አበባው ለሪፖርተር የተናገሩት፡፡

የሰብዓዊ መብት ጉዳይን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥጋቢ ምላሽ  እንዳልሰጡ የተናገሩት አቶ አበባው፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፣ ጅምላ ግድያም አለ፣ መንግሥት ጅምላ ግድያ አልፈጸመም፣ ወታደሩም ጅምላ ግድያ አይፈጽምም፣ በአጠቃላይ ጅምላ ግድያ አልተፈጸመም የሚለው ተቀባይነት የለውም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ የጠቀሱት የምክር ቤት አባሉ አገር ቤት ያሉ የዓይን እማኞች፣ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማስረጃዎች ይህን እንደሚያረጋግጡ ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናጠል ወታደሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ማመናቸውና በወታደራዊ ፍርድ ቤት አካባቢ መቅረባቸውን መናገራቸው በራሱ አንድ ነገር እንደሆነ አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን ዓለም አቀፍ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ወደ ቦታው ገብቶ ምርመራ እንዲያደርግና አጥፊዎችም ለፍትሕ እንዲቀርቡ ለመፍቀድ መንግሥት ሙሉ ተነሳሽነት ሊኖረው እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የሰብዓዊ መብት ምርመራ እንዲደረግ ዝግጁ ነን፡፡ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጉዳዩን መጥተው በነፃነት ይመርምሩት ተብሎ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ ምላሹ አጥጋቢ ይሆን ነበር፤›› በማለት ነው አቶ አበባው የገለጹት፡፡    

በቅርብ ጊዜ በተለይ የትግራይ ጦርነትን በሚመለከት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል በሚል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትከሰስና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ስትቀርብ ነበር፡፡ አገሪቱ ከዚህ በተጨማሪም በተመዱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ቀርባ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሪፖርቷን ስታስገመግምም ታይታለች፡፡ ኢትዮጵያ የተመዱ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመውን የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚቴ ገብቶ በነፃነት ምርመራ እንዲያደርግ እንድትፈቅድም፣ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ግፊትና ጫና ሲደረግባት ቆይቷል፡፡ በስተኋላም የኢትዮጵያ መንግሥት የዚህን ኮሚቴ የምርመራ ጥረትና ሒደት አደናቅፏል በሚል ተከታታይ ጫናና ግፊት ሲደረግበት ነበር፡፡

በዚህ መሰሉ ዓለም አቀፍ ግፊትና ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች መንግሥት የተሰማውን ምሬት በተከታታይ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ከሰሞኑ በፓርላማው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ የመንግሥታቸውን ምሬት አጠናክረውታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን እንደ መርፌ የራሳቸውን ቀዳዳ መስፋት የማይችሉ ሲሉ በተቹበት ንግግራቸው፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ላይ መንግሥታቸው ሊወስድ ስላሰበው ዕርምጃ ፍንጭ የሚሰጥ ንግግር አያይዘው ማቅረባቸው ደግሞ ከሁሉም በላይ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡

‹‹እነዚህ ተቋማት ከሁለት ተፅዕኖ ነፃ መውጣት አለባቸው፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ተፅዕኖ ነፃ መውጣት አለባቸው፡፡ እኛ እየገባን እንደፈለግን የምናደርጋቸው መሆን የለባቸውም፡፡ ከሌላ አገር ተፅዕኖም ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ያሉት ከእኛ ነፃ ሆኑና…፡፡ እንደ እሱ አይሠራም፣ መስተካከል ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጸምም ማለት አይደለም፡፡ ስህተቶቻችንን ማረም፣ በደንብ መገምገምና ኃላፊነት መውሰድ ይገባናል፡፡ ከዚህ አንፃር መከላከያና ፖሊስን በእጅጉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ መከላከያ በሺሕ የሚቆጠሩ አባላቱ ዛሬ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እስር ቤት ነው ያሉት፡፡ ከኮድ ኦፍ ኮንዳክቱ ውጪ በማይገባ መንገድ ኦፕሬሽን ሠርታችኋል ተብለው፡፡ በጅምላ ይገድላሉ የሚባለው የፌደራል መንግሥትና ወታደር በጅምላ አይገድሉም፡፡ በጅምላ ለማሸነፍ ይነሳና ሲሞት ነው በጅምላ ሞትኩ የሚለው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር መንግሥታቸውን ወይም የመንግሥት የፀጥታ አካላትን ከተጠያቂነት ለመከላከል የተደረገ ብቻ ሳይሆን፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚያቀርቡት ሪፖርት ተጨባጭነት የሌለው መሆኑን የሚደመድም ይዘት ያለው ነበር፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት በሰብዓዊ መብት ተቋማት በተለይ በአገር ውስጡ ድርጅቶች ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ለመውሰድ አስቧል የሚል ግምትም ንግግሩ የፈጠረ ነበር፡፡         

የሰብዓዊ መብት ተቋማት ላይ መንግሥት ጠንከር ያለ አስተያየት መስጠቱን በግላቸው እንደማይቀበሉት የተናገሩት የአብን ተወካይ አቶ አበባው ግን፣ እንዲያውም ድርጅቶቹ ከመንግሥት ሙገሳ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡    

‹‹እኔ በግሌ ጥሩ ሥራዎች ይሠራሉ ብዬ ከምገምታቸው ተቋማት አንዱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነው፡፡ እንደ ሞዴል ከሚታዩ ተቋማት አንዱ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ነው፡፡ የቁጥር ልዩነቱና የጥሰት ደረጃው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሪፖርቶችን ሲያወጣ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተቋማት በግሌ መበረታታት አለባቸው ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም መግሥትን ራሱ ያጎብዞታል፡፡ መንግሥት ሀይ ባይ ካጣ አምባገነን መሆን ይጀምራል፡፡ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ያስፋፋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ ይጠላል፡፡ እርስ በእርስ የሚደረጉ ግጭቶችም ተባብሰው ይቀጥላሉ፡፡ ነገር ግን ያሉ ጥፋቶችን ለመንግሥት እየጠቆመ በጊዜ እንዲታረሙ የሚያደርግ ተቋም ሲኖር መንግሥት ሥራውን ተጠንቅቆ ይሠራል፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም አምባገነን፣ ንዝህላልና ኃላፊነት የጎደላቸው አይሆኑም፡፡ ስለዚህ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን መጫን ሳይሆን የበለጠ ነፃ ልናደርጋቸው ነው የሚገባው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ነፃ ማድረጉ በዋነኛነት እንዲያውም የሚጠቅመው ለገዥው መንግሥት ነው፤›› ሲሉ ነው ፖለቲከኛው የመንግሥትን አቋም መስተካከል እንደሚኖርበት የገለጹት፡፡   

መንግሥት በለውጡ የመጀመሪያ ዓመታት በዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ስለተካሄዱ ሪፎርሞችና መሻሻሎች የተመዘገበውን ስኬት አዘውትሮ በመናገር ይታወሳል፡፡ ምርጫ ቦርድ ሪፎርም ስለመደረጉ ብቻ ሳይሆን፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ግለሰብ በተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፏቸው የሚታወቁ እንደሆነ ሲነገር በተደጋጋሚ የተደመጠበት ጊዜ ነበር፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነትን የያዙት በሕግ ዕውቀታቸውም ሆነ በሥራቸው ትልቅ ከበሬታን ያገኙ ሰዎች ስለመሆናቸውም ሲነገር ይታወሳል፡፡ ስለፍትሕ ሥርዓቱና ስለፍትሕ ተቋማት መሻሻልም መንግሥት ደጋግሞ ይናገር ነበር፡፡ ገለልተኝነታቸውና ነፃነታቸው የተረጋገጠ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ስለመፈጠራቸውም መንግሥት ሲሞግት መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በሒደት የለውጡ የጫጉላ ጊዜ ሲቀዘቅዝና አገሪቱም ወደ ቀውስ ማዝገም ስትጀምር ግንኧ መንግሥት በዴሞክራሲ ተቋማት ዙሪያ የሚሰጠው አስተያየትም አብሮ መቀዝቀዝ መጀመሩን ታዛቢዎች ይጠቅሳሉ፡፡

ለአብነት ኢሰመኮ ያወጣው የትግራይ ጦርነትን የተመለከተው ሪፖርት ከሕወሓትም ሆነ ከመንግሥት ተቃውሞ እንዳስተናገደ ያነሱታል፡፡ ‹‹መንግሥት ያለ አይመስልም ነበር›› በሚል ርዕስ የወጣውና የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የነበረውን ብጥብጥ የተመለከተው ሪፖርትም ተመሳሳይ ተቃውሞ ከመንግሥት ሲገጥመው ነበር፡፡ በከረዩ አባገዳዎች ግድያ ዙሪያ የወጣው ሪፖርትንም ቢሆን መንግሥት አምርሮ ሲቃወመው ነው የታየው፡፡

በሒደት ደግሞ በጋምቤላ የኢሰመኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙና የመዘጋት አጋጣሚ ስለመፈጠሩ መሰማቱ፣ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋሙን በተመለከተ አዎንታዊ አቋም እያራመደ አይደለም የሚል ግምትን ያሰጠ ሆኖ ነበር፡፡

መንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋማቱን ሪፖርት እግር በእግር ተከታትሎ ጉዳዮችን አጣርቶ ለፍትሕ ያቀርባል የሚለው ተስፋ በሒደት ግን ከዚያ ይልቅ ወደ ጋዜጣዊ መግለጫዎች መቃቃር ሲቀየር ነው የታየው፡፡ በዚህ የተነሳም የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፎርም ሲባል የቆየው እስከምን ድረስ ነው የሚል ጥያቄ መነሳት ቀጠለ፡፡    

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱን ይፋ ለማድረግ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት በኢትዮጵያ ፈተና እየገጠማቸው መሆኑንና የምርጫ ቦርድና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ኃላፊዎች መልቀቅን በማስታወስ ይህ ሁኔታ ተቋማችሁን እየፈተነው አይደለም ወይ የሚል ጥያቄ ለኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተነስቶላቸው ነበር፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና ምክትሎቻቸው ግን፣ ይህን በተመለከተ በቅብብሎሽ በሰጡት ምላሽ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ቢኖር እንኳን ተስፋ መቁረጥ አማራጭ እንዳልሆነ ነበር ደጋግመው የተናገሩት፡፡ ይህ ከተፈጠረ ከአንድ ዓመት በኋላ ከሰሞኑ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) የኃላፊነት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከሥራ መሰናበታቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

በለውጡ የመጀመሪያ ዓመታት ቁልፍ የሚባሉ የዴሞክራሲ ተቋማትን የመሩ ኃላፊዎች በየጊዜው ከሥራ መልቀቃቸው ደግሞ በሒደት በተቋማቱ ዘንድ መዳከም እንዳይፈጥር ነው አሁን እየተሠጋ የሚገኘው፡፡ የሰዎቹን ከኃላፊነት መልቀቅ ተከትሎ በተቋማቱ ዘንድ ብልጭ ሲሉ የነበሩ ለውጦች በዚያው ድርግም ብለው እንዳይጠፉ ብዙዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ መንግሥት በለውጡ የመጀመሪያ ዓመታት የነበረውን አቋም እየቀየረ መጥቷል ከሚለው ሥጋት ጋር ተዳምሮ፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ወደ ባሰ ቀውስ እንዳያመራ ብዙዎች እየሠጉም ነው፡፡  

ከሰሞኑ በሸገር ሬዲዮ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ አንድ የሕግ ባለሙያ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታዋን ማጠናከርና ማሻሻል ያለባት፣ ለወረት ወይም ለአንድ ሰሞን ብቻ መሆን እንደማይኖርበት አበክረው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አገሪቱ ብዙ ዓለም አቀፍ የሕግ ግዴታዎችን መቀበሏንና ስምምነቶችን መፈረሟን ያስታወሱት ባለሙያው፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሰነድ አብላጫውን ክፍል ስለሰዎች መሠረታዊ መብቶችና አያያዞች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን ላይ የዓለም ሰላም መሠረቱ የሰው ልጅ ያለው ክብርና መብት ነው ይላል፤›› ሲሉ የተናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ የሰብዓዊ መብትን መንግሥት ሲፈልግ የሚሰጠው ሳይፈልግ ደግሞ የሚነጥቀው ጉዳይ እንዳልሆነ ነው በአጽንኦት የተናገሩት፡፡  

ይህን ሐሳብ የበለጠ የሚያጠናክር አስተያየት የሰጡት በፓርላማው የአብን ተወካዩ አቶ አበባው በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማትን አያገባችሁም ብላ በሯን ዘግታ መሄድ የምትችልበት ዕድል የጠበበ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡

‹‹የሰብዓዊ መብትን ማስጠበቅ አንደኛ ለሕዝብ ማሰብ ነው፡፡ ሁለተኛም የተረጋጋ አገዛዝ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ መንግሥት ምቾት በሚሰጥ መንገድ አገር መግዛት መቀጠል የሚችለው የሰብዓዊ መብቶችን እያስከበረ ሲቀጥል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች አሉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪም የመንግሥት የሰብዓዊ መብቶችን ማስከበርና አለማስከበር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ጉዳት ይኖሩታል፡፡ ዓለም አቀፍ የገንዘብና ዕርዳታ ድርጅቶች እጃቸውን የሚሰበስቡትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለን ግንኙነት የሚሻክረው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ዲፕሎማሲያችን የሚዳከመው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለን አገራዊ ክብርና ሞገስ ሁሉ የሚወሰነው ኢትዮጵያዊያን ባላቸው የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ደረጃ ልክ ነው፤›› በማለት ጉዳዩ ያለውን ክብደትና ደረጃ አመልክተዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -