Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከልከሉን አስመልክቶ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ የላኩት ደብዳቤ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽ የሆነ ሕግ ሳይወጣና በሕግ የተቀመጠ ክልከላ ሳይኖር ከላይ ወረደ በተባለ አቅጣጫ ላይ ብቻ በመመሥረት የነዳጅ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከልከሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችንና የውጭ ኢንቨስተሮችን የሥራ እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ ነው። 

የሆልቲካልቸር ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለኤክስፖርት የተዘጋጁ የአበባ ምርቶችን ወደ ኤርፖርት ለማጓጓዝ የሚጠቀሙባቸው ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ግዥ ፈጽመው ጅቡቲ ወደብ ከደረሱ በኋላ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ባለመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት እንደማይችሉ እንደተገለጸላቸው ሪፖርተር ባለሀብቶቹን አነጋግሮ ከሁለት ሳምንት በፊት ዘግቦ ነበር።

ይህን ቅሬታቸውን ለተለያዩ የመንግሥት አካላት አቅርበው ምላሽ ሳያገኙ ቢከርሙም፣ በዚህ ሳምንት ግን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተፈጠረውን ችግር በመገንዘብ ማስተካከያ እንዲደረግ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ግልጽ ደብዳቤ ጽፏል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በሆኑት ሐና አርአያ ሥላሴ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ በቀጥታ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የተላከ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ደብዳቤውን ለመጻፍ የተገደደውም በርካታ ባለሀብቶችና የውጭ ኢንቨስተሮች በተደጋጋሚ ያቀረቡለትን ቅሬታ መሠረት አድርጎ እንደሆነ ሪፖርተር የተመለከተው ይኸው ደብዳቤ ያስረዳል።

መንግሥት ለዘላቂ የልማት ግቦችና አረንጓዴ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ፣ በተሽከርካሪ ጭስ የሚፈጠረውን የከተሞች የብክለት መጠን ለመቀነስ የወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ስለመሆኑ በማተት የሚጀመረው የኮሚሽኑ ደብዳቤ ዕርምጃው አገራዊ ጠቀሜታ እንዳለው ይጠቅሳል፡፡ አገሪቱ የተለያዩ የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መጠን ለመቀነስና ሌሎች የፖሊሲ ግቦችን ከግምት በማስገባት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ማስገባት ላይ ገደብ ማድረጉን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ማስታወቁም ያስታውሳል። በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖችን ወደ አገር ማስገባትንና አገልግሎት ላይ ማዋልን ለማበረታታት ተሽከርካሪዎቹ ወደ አገር ሲገቡ የሚጣሉ ታክሶች ነፃ መብት መሰጠቱና በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች አምራቾችና ተያያዥ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ በተፈጠረው በዚህ መልካም ዕድል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከአገራዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ጋር የተጣጣመ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ 

ነገር ግን ይህ የመንግሥት ፖሊሲ በአንዳንድ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እየፈጠራቸው ያሉ ችግሮችና ወደፊትም ሊፈጥር የሚችለውን ጫና ደብዳቤው በዝርዝር ገልጿል፡፡ 

በአሁን ወቅት ለማንኛውም አገልግሎት የሚውሉ ከባድ የጭነት መኪኖች ለእርሻ ኢንቨስትመንት አገልገሎት የሚውሉ ትራክተሮችን ጨምሮ ሌሎች ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ለቱሪስቶች ማስጎበኛነት የሚያገለግሉ አገር አቋራጭ መኪኖችና ሌሎችም በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ መግባት እንዳይችሉ ክልከላ እየተደረገባቸው መሆኑ በዘርፎቹ እንቅስቃሴ ላይ ጫና መፍጠሩን በግልጽ አስቀምጧል። በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግበርና፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ በሆልቲካልቸር፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግንባታ፣ አገልግሎት መስክና ሌሎች ዘርፎች በተሰማሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጄከቶች ትግበራ ላይ ፈተናዎች እየፈጠረ መሆኑን ኮሚሽኑ ከተለያዩ የውጭና አገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ባደረገው ውይይት ለመረዳት መቻሉን በደብዳቤው አስታውቋል። በተዘረዘሩት የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ አልሚዎችን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ብቻ እንዲያስገቡ ማስገደድና ይህንን ተፈጻሚ ማድረግ አሁን ባለው ሁኔታ ከባድ መሆኑን የኮሚሽኑ ደብዳቤ ያመለክታል።

እነዚህ ዘርፎች አሁን ባለው ሁኔታ የግድ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ብቻ እንዲያስገቡ ማስገደድ ተግባራዊ ላይሆን የሚችልበት ተጨባጭ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ደብዳቤው ሳያመላክት አላለፈም፡፡ 

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩና ለተጠቀሱት ዓይነት ኢንቨስትመንቶች የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መመረት ከጀመሩ ገና የአንድ ዓመት ዕድሜ ብቻ መቆጠሩን የጠቀሰው የኮሚሽኑ ደብዳቤ፣ ይህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ እያለሙ የሚገኙ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የግድ እነዚህን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲያስገቡ ማስገደድ ውጤታማ እንደማይሆን ያስረዳል። 

በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ከላይ በጠቀሱት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ አብዛኞቹ ኢንቨስተሮች ፕሮጀክቶቻቸው የሚገኙት ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑን በመጠቀስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና መሠረተ ልማት በበቂ ሁኔታ ባልተዳረሰባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ገብተው የሚያለሙ ባለሀብቶችን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ብቻ እንዲያስገቡ መገደብ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ኮሚሽኑ በደብዳቤው ገልጿል።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች በበቂ ሁኔታ ኃይል መሙላትና በቋሚነት አገልግሎት ለመስጠት በማይችሉባቸው የአገራችን ክፍሎች ሥራ ላይ ማዋል አዳጋች እንደሆነ የጠቀሰው የኮሚሽኑ ደብዳቤ፣ ሚኒስቴሩ ይህንንና ከላይ የተዘረዘሩ ምክንያቶችን በማጤን በተጠቀሱት ዘርፎች ላይ የተጣለውን ገደብ እንዲያነሳ ጠይቋል።

መንግሥት ለዘለቄታዊ የልማት ግቦችና አረንጓዴ ልማት ያለውን ቁርጠኝነትና የሚደግፋቸውና ለአፈጻጸማቸውም አስፈላጊውን በሙሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ከባድ የጭነት መኪኖችና ለተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ትግበራ የሚያግለግሉ ተሽከርካሪዎች መመረት የጀመሩት አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ እ.ኤ.አ በ2023 ጀምሮ መሆኑን ከግምት በማስገባት ገደቡ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዞ፣ ይህን ፖሊስ በተጠቀሱት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተፈጻሚ ማድረግ የማያስችል ስለመሆኑም ጠቅሷል፡፡ ከአዲስ አበባና ዋና ዋና የክልል ከተሞች ውጪ የሚተገበሩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተሸከርካሪዎቹን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሙላትና በቋሚነት ለማገልገል የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ክልከላው ከመጣሉ በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ላይ የነበሩና በተለያዩ ወደቦች የደረሱ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር እንዳይገቡ መከልከሉ የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ተገማችነት የሚያሳጣ እንደሆነም ኮሚሽኑ በደብዳቤው ገልጿል። ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ከመፍጠር ጋር በተያያዘ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀከቶች ትግበራ ወደ አገር የሚገቡ ከግል መገልገያነት ውጭ ያሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዲገቡና ለታለመላቸው አግልግሎት እንዲውሉ ማስቻል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለአገር የሚያበረክታቸውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ፋይዳ ስለሚኖረው ሚኒስቴሩ የወሰነውን ውሳኔ ሊያጤነው እንደሚገባም አመልክቷል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ማስገባት ከልከላ ይፋ ከመደረጉ በፊት ግዥ የተፈጸመባቸውና በመጓዝ ላይ የነበሩ፣ በአሁን ወቅት በተለያዩ ወደቦች ላይ ቆመው የሚገኙ መኪኖችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ለመጡበት አገልግሎት ማዋል ላይም ከፍተኛ መጉላላት እንደተፈጠረ መረዳት መቻሉንም ለሚኒስቴሩ የጻፈው ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል፡፡ 

በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ማስገባት ክልከላ ይፋ ከመደረጉ በፊት ግዥ የተፈጸመባቸውና በመጓጓዝ ላይ የነበሩ፣ በአሁን ወቅት በተያዩ ወደቦች ላይ ቆመው የሚኙ መኪኖችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ለመጡበት አገልግሎት ማዋል ላይም ከፍተኛ መጉላላት እንደተፈጠረ መረዳቱን አመልክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸውና ከአሠራር ጋር እየገጠሙ ናቸው ያላቸውን ችግሮች ያስታወሰው የኮሚሽኑ ደብዳቤ ለአብነት የጠቀሰው በፍራንኮ ቫሉታ ጭምር የገቡ ተሽከርካሪዎች በጉምሩክ ክልከላ መደረጉን ነው፡፡ 

በዚህ ጉዳይ ኮሚሽኑ በደብዳቤው ‹‹በገንዘብ ሚኒስቴር በአገር ውስጥ በሚገኙ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ምደባ ገደብ የተደረገባቸው ዕቃዎች ዝርዝር ባስተላለፈበት ሰርኩላር ላይ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖች የተካተቱ መሆናቸው ያለው ምንዛሪ ከፍያ ፈቃድ (ፍራንኮ ቫሎታ) ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን የሚያካትት እንደሆነ በመረዳት የጉምሩክ ኮሚሽን ላልተወሰነ ጊዜ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን ወደ ሀገር ማስገባት ላይ ክልከላ በማድረጉ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሯል›› በሚል ገልጾታል፡፡ ነገር ግን የገንዘብ ሚኒስቴር በተላለፈ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ክልከላ በተደረገባቸው ዕቃዎችና ተሽከርካሪዎች ላይ ማሻሻያና ማብራሪያ በተደረገበት ደብዳቤ ሰርኩላር ላይ የተመለከቱት የውጭ ምንዛሪ የማይፈቀድላቸው ዕቃዎች ዝርዝር በሕግ በተደነገ አስከአሁን ድረስ መስተጓጎል እንዳለ ከውጭ ባለሁበቶች በሚቀርቡ መረጃዎች ለመረዳት እንደተቻለ ሁሉ የኮሚሽኑ ደብዳቤ አመልክቷል፡፡ 

ኮሚሽኑ በደብዳቤው ደብዳቤ ማጠቃለያ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው ለተለያዩ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ትግበራ አገልግሎት የሚውሉ ለግል መልገያነት ከሚውሉ አውቶሞቢሎች ውጭ ያሉ እንደ ከባድ የጭነት መኪኖች፣ ለግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ የሚያስፈልጉ ትራክተሮችና መሰል ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ እንዲፈቀድ ጠይቋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ከፍል እየተንቀሳቀሱ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ የቱሪስት መኪኖች ምቹ ባልሆኑና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ መልክዓ ምድሮች ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉ ፒክ አፕ መኪኖችና እንደ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ልዩ ባህሪ የሚያስፈልጉ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት እንዲቻል ሚኒስትሩ ፈቃድ እንዲሰጥ አመልክቷል፡፡ ወደፊትም እነዚህን መሰል ተሽከርካሪዎች እንዲስተናገዱ ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግ ጭምር ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር ይህንን የኮሚሽኑን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ምላሽን ለማካተት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች