Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ወይም ደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም አንዱ ነው፡፡ ተቋሙ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በፋይናንስ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ብሐራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ ለአገሪቱ የመጀመርያ የሚባለውን የማክሮ ፋይናንስ አገልግሎት በመጀመርና በማስተዋወቅ ይጠቀሳል።

በማክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ከባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመቅደም ወደ ሥራ መግባቱ የሚገለጸው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ አሁን 30ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

የደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ብርሃን ለሪፖርተር እንደገለጹትም በኢትዮጵያ የመጀመርያው የማክሮ ፋይናንስ ተቋም በመሆን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለ አገልግሎት የሚሰጥ ምንም ዓይነት የማክሮ ፋይናንስ ተቋም ስላልነበር ዘርፉን በማስተዋወቅም የሚገለጽ ነው፡፡

ደደቢት ማክሬ ፋይናንስ ለድሆች የሚሆን ፋይናንስ ተቋም መፍጠር እንደሚኖርበት በማመን ይህንን ለመተግበር ሲነሳ ለአገልግሎቱን ለማስጀመር የሚሆን ሕግና ልምድ የተወሰደው ደግሞ ከባንግላዴሽ እንደነበርም አቶ ሙሉጌታ ያስታውሳሉ፡፡ ያኔ የነበሩ ሰዎች ይህንን ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተገበር ካደረጉ በኋላ ጠቀሜታው ስለታመነበት ከደደቢት በኋላ በተለያዩ ክልሎች ተመሳሳይ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሊመሠረቱ ችለዋል፡፡ ዛሬ የክልል መንግሥታት ድርሻ ይዘው ሥራ ላይ የቆዩና በሌሎች ግለሰቦችና ኩባንያዎች የተቋቋሙ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥር እየሰፋ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተውም ከ45 በላይ ደርሰዋል፡፡ 

ተቋሙ ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ሦስተኛውን ቅርንጫፍ በከፈተበት ወቅት እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት የደደቢት ማክሮ ፋይናንስ አጠቃላይ የሀብት መጠን ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቆጣቢዎችን ማፍራት የቻለው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ከእነዚህ ቆጣቢዎች ማሰባሰብ የቻለው ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡ አጠቃላይ የብድር ክምችቱም ከ11.5 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከተቋሙ ይህንን ብድር የወሰዱ ደንበኞች ቁጥርም ከ300 ሺሕ በላይ ማድረስ የቻለ አብዛኛው ተበዳሪዎችም ገጠር የሚኖሩ በተለይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ስለመናቸው ገልጸዋል፡፡ ለእነዚህ የማኅበር ክፍሎች አነስተኛ ብድሮችን በማቅረብ ብዙዎችን መለወጥ ስለመቻሉ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው ተቋሙ ለአንድ ተበዳሪ የካፒታሉን አንድ በመቶ ድረስ ብድር መስጠት ይችላል፡፡ ይህም ማለት ለአንድ ተበዳሪ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ብር ማበደር እንደሚችል አስረድተዋል። ነገር ግን የተቋሙ ፖሊሲ ለተወሰኑ ሰዎች ብድር መስጠት ሳይሆን ለብዙኃኑ መድረስን ያለመ በመሆኑ በዚሁ አግባብ እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የቁጠባ ባህልን በማለማመድና ብድር ወስዶ መመለስን በክልል ደረጃ በማስታወቅ የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ብዙ መሠራቱም ተገልጿል፡፡ 

ተቋሙ በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ቢሆንም የክልል መንግሥታት ድርሻ ኖሯቸው የተቋቋሙ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ሽግግር በማድረግ ደረጃቸውን ከፍ ሲያደርጉ ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ግን እንደ ሌሎቹ ወደ ባንክ ሽግግር አላደረገም፡፡ 

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ፀደይ በሚል መጠሪያ ወደ ባንክ ተሸጋግሯል፡፡ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋምም ፀደይ የሚል መጠሪያ ወደ ባንክ አድጓል፡፡ ሌላው በተመሳሳይ ሲሠራ የቆየው ሌሎቹም በተመሳሳይ መንገድ ስያሜያቸውን በመቀየር ወደ ባንክ ሥራ ተሸጋግረዋል፡፡ 

ለእነዚህ ተቋማት መፈጠር እንደ ፈር ቀዳጅ የሚቆጠረው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ግን ወደ ባንክ ሳይሸጋገር የቆየው አንዱና ዋነኛ ምክንያት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ጦርነት ነው፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ ወደ ባንክ እንደተሸጋገሩ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሁሉ ደደቢትም ወደ ባንክ ለማሳደግ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር፡፡ ሆኖም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ይህንን ዕቅዱን ሊፈጸም አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ 

በጦርነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ በመሆኑ ከጦርነቱ በኋላም ወደ ባንክ ከመሸጋገር በፊት መቅደም የነበረባቸው ሥራዎች በማስቀደም ወደ ባንክ የሚደረገው ሽግግር እንዲዘገይ ቢያደርገውም አሁንም ወደዚያ ለመሸጋገር ዝግጅቶች እየተደጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ለደንበኞች የተሰጠውን ብድር ማስመለስና ተቋሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተለያዩ ውሳኔዎችን በመወሰን እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እነዚህ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት መስመር እየያዙ በመሆኑ ወደ ባንክ የሚያደርገውም ሽግግር ቀደም ብሎ ከተያዘው ዕቅድ ባጠረ ጊዜ ሊፈጸም እንደሚችል ከተደረገው ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ተቋሙን ወደ ባንክ ደረጃ ለማሸጋገር ከተያዘው ዕቅድ ጋር በተያያዘ አቶ ሙሉጌታ በሰጡት ማብራሪያ፣ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ማደግ የሚያስችላቸው መመርያ የወጣው በ2012 መጨረሻ አካባቢ ስለነበር ደደቢትም በወቅቱ ዕድሉ ነበረው ብለዋል። አሁን የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ግን ከቀድሞ የተለየ መሆኑን፣ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማክሮ ፋይናንሶች ወደ ባንክ እንዲያድጉ በፈቀደበት ወቅት ወደ ባንክ ለመሸጋገር ያስፈልግ የነበረው ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር የነበረ መሆንና አሁን ግን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ማደጉን አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን የካፒታል መሥፈርት ለማሟላት አክሲዮን ለመሸጥ መታሰቡን ከአቶ ሙሉጌታ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን በዚሁ ወቅት ተቋሙን በሁለት እግሩ ማቆም ቀዳሚው ሥራቸው መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተለይ የሰጠውን ብድር ለማስመለስና ጦርነቱ ከፈጠረበት ተፅዕኖ ለመላቀቅ የሚሠሩ ሥራዎችን አጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡ ‹‹ያበደርነው ብድር ከፍተኛ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ይህንን ብድር በወቅቱ እየተከፈለ አይደለም፡፡ ስለዚህ ብድሩን ለማስመለስ የማገገሚያ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ወደ ኖርማል እንዲመለስ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት አብዛኛው ቅርንጫፎቹ ከሥራ ውጪ ሆነው ስለነበር ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ብድሩን ለማስመለስ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከ40 እስከ 50 በመቶ ደርሶ እንደነበር ተገልጿል፡፡ 

በተደረጉ የማስተካከያ ዕርምጃዎችና ተቋሙ እየተገበራቸው ባሉ የማበረታቻ ውሳኔዎች የተበላሸ የብድር መጠኑን ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ወለል በታች ማድረስ ችሏል፡፡ 

የተቋሙ ትልቁ እምነት ግን ኅብረተሰቡን ማገልገል ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ባንክም ብንሆን ቀዳሚው ሥራችን የማክሮ ፋይናንስ አገልግሎትን ማጠናከር ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመሪያም ወደ ማክሮ ፋይናንስ የማሸጋገር ተቋም የባንክ ሥራንና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት አጣምሮ መሥራት የሚፈቅድ በመሆኑ ወደ ባንክ የሚደረገው ሽግግር ተጠቃሚ ስለሚሆን የሚገፉት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የማክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱ ግን በተለይ ትግራይ ውስጥ ተተኪ የሌለውና ሰፊ ሽፋን ያለው በመሆኑና አርሶ አደሩንና ደሃውን እስካገዝን ድረስ ባንክ ስንሆን ደግሞ የበለጠ ያግዘናል፡፡ በጦርነቱ ተቋሙ ምን ያህል ጉዳት እየደረሰበትና አሁን ላይ ያለበትን አቋም ምንድነው የሚለውን ጥያቄ አቶ ሙሉጌታ የጦርነቱ ጉዳት መገጫው በርካታ ነው፡፡ የወደሙ ቅርንጫፎች አሉ፡፡ ከቅርንጫፍ የተዘረፈ ገንዘብ አለ፡፡ ከዚያ ባሻገር አብዛኛው ተበዳሪ በጦርነቱ ምክንያት ብድሩን በወቅቱ እንዳይከፍል መሆኑ ደግሞ ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህም ለተከታታይ ዓመታት ኪሣራ እንዲመዘገብ ካፒታሉንም ለመጠባበቂያ እንደያውል ቢያስገድደውም አሁን እንደ አዲስ የተጀመረው ሪፎርም ተቋሙን ወደነበረበት በመመለስ ውጤት መታየት ስለመጀመሩ አመልክተዋል፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ባንክ ላይ የነበረው ተቀማጭና ተበዳሪዎችም እንዲመልሱ በማድረግ ብድር እየቀረቡ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ በዚህም በ2016 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለመስጠት ችሏል፡፡ ይህንን ብድር ከ29 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተበዳሪዎች የሰጡት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ካለንበት ችግር አንጻር ይህንን ያህል መጠን ያለው ብድር መስጠታችን ትልቅ ነገር ነው የሚሉት አቶ ሙሉጌታ አነስተኛ መጠን ብድር የቀረባቸውን ተበዳሪዎች ብድራቸውን እንዲመልሱ በማድረግ ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙ እንዲበረታቱ እየተደረገም ነው፡፡ 

ይህ አሠራር ተመላሽ መደረግ ያለበትን ብድር መጠን እያሳደገ ከመሆኑም በላይ ተቋሙ እይሰጠ ባለው ብድር ከተሞች አካባቢ ቢዝነሱ እንደገና እንዲንቀሳቀስ እያደረገ በመሆኑ ውጭ ያለው ብድር እየተመለሰ ይሄዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ተቋሙ ወደ ነበረበት አቋም የመመለሱ ሥራ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱ ቢገለጽም አሁን ላይ ትልቅ ችግር የሆነው በክልሉ ያለው የብድር ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ ሥራ መሥራት የሚፈልጉ ወጣቶች ለሥራ ገንዘብ እየፈለጉ ከመሆናቸው አንፃር በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደረገ ምዝገባ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር የጠየቁ ተበዳሪዎች ጥያቄ አቅርበው የብድር ጥያቄያቸውን ለመመለስ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ምዝገባው ባይቆም ብድር ጥያቄው ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው እያደገ ያለውን የብድር ፍላጎት ለማሟላት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለመሥራት አቅደዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ትልቁ መፍትሔ በቁጠባ ረገድ ሕፃናት ጭምር እንዲቆጥቡ እየተደረገ ለሌሎች የሚሰጥ ብድር አቅምን የማጠናከር ሥራ ሁሉ እየሠራ ነው፡፡ ለሕፃናት የሚደረግ ቁጠባ እንዲበረታታ ተቋሙ በራሱ አካውንት እየከፈተ የጀመረው ሥራ እየደገ መጥቶ ከሕፃናት ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰባሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ተስፋ ሰጪ በመሆኑ በዚህ ረገድ ቀጣይ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ 

ተቋሙ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን እንደ አዲስ በተጀመረው ሪፎርም ቁጠባን ከማሰባሰብ ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፎችን በመክፈት ተደራሽነቱን የማስፋት ሥራ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ላይ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁለት ቅርንጫፎቹ ሌላ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በያዘው ዕቅድ መሠረት ሦስተኛውን ቅርንጫፍ ባለፈው ቅዳሜ ሊከፍት መቻሉን የደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ላይዘን ኦፊሰር ወ/ሮ ሚዛን ገብረሚካኤል ገልጸዋል፡፡ 

ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉት ጠንካራ የማክሮ ፋይናንስ ተቋም እንዲኖረን እንፈልጋለንና አዲስ አበባ ላይ ቅርንጫፍ የማስፋቱን ሥራ በማጠናከር በአዲስ አበባ አራተኛውን ቅርንጫፍ ደግሞ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በጦርነቱ ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የነበሩት ሁለቱም ቅርንጫፎች ተዘግተው አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ተቋርጦ እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ሚዛን ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በባንክ የታገደው ገንዘብ በመለቀቁ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ ሥራው ከተጀመረ በኋላም እየታየ ውጤት ጥሩ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሚዛን ተቋሙ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በሚያገለግል ደረጃ እየተዋቀረ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ይምጣል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ጥረቶችን ጭምር በማድረግ ተቋሙን በሁለት እግሩ የማቆሙ ሥራ ውጤት እየመጣ ለመሆኑ አቶ ሙሉጌታም ገልጸዋል፡፡ ደደቢት መክሮ ፋይናንስ በአሁኑ ወቅት ከ218 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን አብዛኛው ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን በጎንደር ከተማና በአዲስ አበባ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ 

ከዚህ በኋላ በሌሎች ክልሎች አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ ይዟል፡፡ ተቋሙ ከሦስት ሺሕ ላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን የያዘ ነው፡፡ 

የደደቢት ማክሮ ፋይናንስ ባለአክሲዮኖችና መሥራቾች የትግራይ መልሶ ማቋቋም (REST) የትግራይ ክልላዊ መንግሥት፣ የትግራይ ገበሬዎች ማኅበር የትግራይ ሴቶች ማኅበርና የትግራይ ወጣቶች ማኅበር ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች