Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የታመቀ ስሜት!

የዛሬ ጉዞ ከመርካቶ በዮሐንስ ወደ አዲሱ ገበያ ነው፡፡ ታክሲ ጠባቂ ሠልፈኛው በየራሱ ሐሳብ ውስጥ ተውጦ እርስ በርስ ከመነጋገር ይልቅ፣ በወጪና በወራጁ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ይመስል ጭልጥ ብሎ የጠፋ ይመስላል፡፡ ከስንት ጥበቃ በኋላ ተረኛው አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ ሲደርስ ተረኞች በቅደም ተከተል በሠልፋቸው መሠረት ተሳፈሩ፡፡ ልጅ እግር፣ ወጣት፣ ጎልማሳና አዛውንቶችን ጭምር ጠቅጥቆ ያሳፈረው ሚኒባስ በወያላው ‹‹ሳበው!›› በሚለው ቀጭን ትዕዛዝ ለሾፌር ሲተላለፍ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ጋቢና አንድ ጎልማሳና አንዲት ወጣት፣ ከሾፌሩ ጀርባ አንድ ልጅ እግርና አዛውንት፣ ከዚያ ቀጥሎ ያሉት መቀመጫዎች እስከ መጨረሻ ድረስ ከሁሉም ዕድሜና ፆታ አሰባጥረው ይዘዋል፡፡ አንድ ያልታወቀው ነገር ግን የብሔር ማንነትና እምነት ሲሆን፣ የሁሉም መግባቢያ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ስለነበር የተጠቀሱትን ስብጥሮች ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ይህንን እያሰላሰልኩ ሳለሁ፣ ‹‹ይህች ታክሲያችን ምስኪኗን አገራችን ትመስል ሁሉንም በውስጡ ከያዘው ፍላጎትና ልዩነት ጋር አንድ አድርጋ አጭቃን ስንጓዝ አቤት ደስ ማለቱ…›› እያለ ጎልማሳው ከጋቢና ፀጥታችንን ገፈፈው፡፡ ሳይሻል አይቀርም!

በጎልማሳው ንግግር መነሻ ይመስላል፣ ‹‹እንዲያው ልፉ ብሎን እንጂ ሆድ ነው ከአገር የሚሰፋው…›› ብላ አንዲት ወይዘሮ ከመሀል ወንበር ወጉን ስታስቀጥል፣ ‹‹ልክነሽ በዚህ አባባል እኮ ድሮ ተዘፍኖበታል፡፡ ቆይ እስቲ ምን ነበር የሚለው አዎ ለጊዜው ረሳሁት እንጂ ሆድ የማይችለው ነገር እንደሌለ ለማመልከት መሰለኝ አባባሉ ወይም ዘፈኑ የሚታወቀው…›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ጎበዝ አባባሉማ መቻል ምን ይከፋል ሆድ ከአገር ይሰፋል ነው…›› ብለው አዛውንቱ ከመናገራቸው፣ ‹‹ተው ቻለው ሆዴ ተው ቻለው ሆዴ፣ ሲቀር ለሚቀረው ምነው መናደዴ…›› ተብሎም ተዘፍኗል ብሎ ሌላው ከኋላ አከለበት፡፡ ‹‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ተብሎ በሚነገርባት አገር ውስጥ ሆድ ሞልቶ አለማደሩ ነው ሊያስቆጭ የሚገባው…›› የሚለው አዛውንቱ አጠገብ የተቀመጠው ልጅ እግር ሲሆን፣ ‹‹የሆድ ነገር ከተነሳማ ብዙ ነገር አለ ግን ይቅርብን…›› አለች ቆንጂት ከጋቢና፡፡ አረጋጉት ይመስላል!

ወያላው ሒሳብ መቀበል እየጀመረ ነው፡፡ ወጣቱ ድፍን ሁለት መቶ ብር አውጥቶ ሲሰጠው፣ ‹‹ምናለበት ደጅ ዘርዝረኸው ብትመጣ አንተ ደግሞ…›› እያለ ሲነጫነጭበት፣ ‹‹እባክህ ዝም ብለህ ተቀበል ይኼ ራሱ ዝርዝር ከሆነ ቆየ እኮ…›› ብሎ ሲመልስለት፣ ‹‹አይ እናንተ በስምንተኛው ሺሕ ተፈጥራችሁ ትልቁን የአገሪቱን ኖት እንደ ሳንቲም ስትቀልዱበት እንሳቅ ወይስ እናልቅስ…›› በማለት አዛውንቱ ደም ሥራቸው ተገታትሮ ተናገሩ፡፡ የአዛውንቱ ስሜት የተጋባባት ወይዘሮ፣ ‹‹አባቴ ያለ ጥረት፣ ያለ ልፋት፣ ያለ ድካምና ያለ ውጣ ውረድ በአንድ ጀምበር የሀብት ቆጥ ላይ ተሳፋሪው በበዛበት በዚህ ጊዜ ገና ምን ታይቶ ብራችንን እንደ ቅጠል ተሸክመን ገበያ እንወጣለን…›› ብላ ተብሰከሰከች፡፡ ‹‹አይ እህቴ ግብር አጭበርባሪውና ሰዋሪው በበዛበት፣ ኮንትሮባንድ ነጋዴው ተደራጅቶ በሚርመሰመስበት፣ የሹማምንት ቤተሰቦች ሳይቀሩ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ገብተው በሚከብሩበት፣ ምን ይኼ ብቻ ፖለቲካውን አትንኩ እንጂ ሌላውን እንደፈለጋችሁ ተብለው የተለቀቁ አፍለኞች እንደ ልባቸው በሚፈነጩበት ጊዜ አሳራችን መብዛት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ግብሩም ሆነ ጫናው እኛ ላይ ብቻ ነው የሚያናጥሩት…›› ብሎ ንዴቱን አገነፈለው፡፡ ብሶት በሉት!

‹‹ቆይ ቆይ ይህ ሁሉ ልማት እየተከናወነ ሁላችሁም በአንድ ጎራ የተደራጃችሁ እስክትመስሉ ድረስ ማለቃቀስ ብቻ አይደብርም እንዴ? ይህንን ሁሉ መንገድ ስናቆራርጥ አንድም ሰው ስለኮሪደር ልማቱ፣ ስለስንዴ ልማታችን፣ ስለኢኮኖሚ ዕድገታችን፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካሉ አገሮች በሙሉ የእኛ ጂዲፒ ስለመብለጡ፣ በግብርናም ሆነ በኢንዱስትሪ እየተገኘ ስላለው አስተማማኝ ዕድገትና በርካታ ተስፋዎች መናገር እንዴት ይከብዳል…›› እያለ አንዱ ጎረምሳ ሲተነትን ሦስተኛው መቀመጫ ላይ በጥግ በኩል የተቀመጡ እናት፣ ‹‹ልጄ ልክ ብለሃል፣ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ መነጋገሪያ መሆን አለበት፡፡ በቀደም በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልካቸውን ሁሉ በስፋት ሲዘረዝሩ በቴሌቪዥኔ አይቻለሁ፣ ሰምቻለሁ፡፡ ማንም ሳያስገድደኝ በራሴ አዕምሮ የተቀበልኩትም ያልተቀበልኩትም አለ፡፡ ማታ ከተማሩት ልጆቼ ጋር ሳወራ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ማን ነው የምትሉት ይኼ የዓለም ባንክ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን ሌላው ጉዳይ ላይ ግን እኔም ባገኛቸው አጥብቄ የምጠይቃቸው ስላሉኝ ለጊዜው ልተወው፡፡ ይሁንና በአገር ዕድገትና ተስፋ ላይ ብቻ ሳይሆን በሥጋታችንም ላይ መነጋገር አለብን…›› ሲሉ በመገረም ሰማናቸው፡፡ ግሩም ድንቅ ሐሳብ!

‹‹እናታችን ይህንን የመሰለ ሚዛናዊ አስተያየት ከእርስዎ መስማት ልብ ያሞቃል…›› ብላ አንዲት ቆንጆ ከኋላ መቀመጫ ስትናገር፣ ‹‹ወጣቱ ቲክቶክ ላይ ተጥዶ ያልበላውን ሲያክ ሲውል አባቶቻችንና እናቶቻችን የአገራቸውን ጉዳይ ወጥረው ይከታተላሉ፡፡ በቀደም በፓርላማ ስለነበረው ውሎ ከመሰሎቼ ጋር ስነጋገር አንዳቸውም ምንም አልሰሙም፡፡ ከእናቴም ሆነ ከአክስቴ እንዲሁም ከጎረቤት ትልልቅ ሰዎች ጋር ሐሳብ ስለዋወጥ ግን ሁሉም በትኩረት ነው የተከታተሉት፡፡ አሁንስ ምን ዓይነት ከንቱ ትውልድ ላይ እንደደረስን ሊገባኝ አልቻለም…›› የሚለው ዝምተኛ መሳይ ወጣት ነው፡፡ ‹‹አይዞህ ልጄ አገር ለመለወጥ እኮ የሚበቁት ጥቂቶች የተመረጡ ናቸው፡፡ ሌላው በሚችለው ድጋፍ ለመስጠት ይፈለግ ይሆናል እንጂ የግድ ሐሳብ አፍልቅ፣ ምራ፣ አቅጣጫ አሳይ፣ ተቆጣጠር፣ አፈጻጸም ገምግም፣ በጎደለ ሞልተህ የተሳሳተውን አስተካክል እየተባለ መጎትጎት የለበትም፡፡ ልክ እንደ ፈረሱ ጥቂቶች ከፊት ሲሆኑ ሌላው ይከተላል…›› ብለው አዛውንቱ ወጉን አደመቁት፡፡ እንዲህና እንዲያ እያልን ያደመቅነው ጉዞ አላልቅ ያለው በመንገድ መዘጋጋት ጭምር መሆኑን አትርሱ፡፡ እንዴት ይረሳል!

ሾፌርና ወያላ በነፃ ያገኙትን ትንተና እየኮመኮሙ እስካሁን አልተናገሩም ነበር፡፡ የመንገዱ መዘጋጋት ሲበዛ ግን የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው መነጫነጭ ጀምረዋል፡፡ ‹‹ይኼ መንገድ አንድ መፍትሔ ካልተበጀለት ዘንድሮ ቁርስ በልተን ምሳ መድገማችንን እንጃ…›› ብሎ ወያላው ነገር ጣል ሲያደርግ፣ ‹‹አንተ ምናለብህ እኛ ነን እንጂ በቀን አንዴ ለመጉረስ ሥቃይ እያየን ያለነው…›› ብላ የወያላው መከዳ ላይ የተቀመጠች የሠፈር ጉልት ነጋዴ መሳይ ስትናገር፣ ‹‹እኛም እኮ የአንቺና የመሰሎችሽን እርጥብ በቀን አንዴ ለማግኘት መከራ እያየን ነው…›› ብሎ ሾፌሩ መለሰላት፡፡ ‹‹እርጥብ ስትሉ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፣ ባለፈው አንድ ትልቅ ሰው ቀስ ብለው መጥተው ልጄ እስቲ ሰው ሳያየኝ ሸጎጥ ብዬ የምበላበት ቦታ ስጪኝ…›› ሲሉ አንጀቴ ስፍስፍ አለ፡፡ ከለልና ደበቅ ያለች ጠባብ ቦታ ውስጥ ተቀምጠው በልተው ሲሄዱ፣ ‹‹እኝህ ሰው እኮ እዚያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማትስ አስተማሪ ነበሩ ብላ የነገረችኝ አጠገቤ ቡና የምታፈላው ልጅ ነበረች፡፡ ውይ ዘንድሮ አያልቅም ተነግሮ መባል ያለበት አሁን ነው…›› እያለች ተንገፈገፈች፡፡ ጉድ አትሉም!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው፡፡ ‹‹አቤት ሐበሻ፣ እዚህ አገር ውስጥ ችግር ያልነበረ ይመስል የብልፅግና መንግሥታችንን ለማጠልሸት የማትፈጥሩት ተረት የለም…›› ብሎ የልማት አርበኛው ካድሬ ተረብ ሲጀምር፣ ‹‹አገራችን ውስጥ ከጥንት ጀምሮ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ ነጋሪ አያስፈልግም፡፡ ችግሩ ሲደራረብ ኖሮ እዚህ መድረሱ እርግጥ ቢሆንም መምህር፣ ሐኪም፣ የባንክ ሠራተኛ፣ አነስተኛ ተከፋይ የግልና የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወዘተ ገቢያቸው ከቤት ኪራይ አልፎ ለምግብ እንደማይተርፋቸው እኮ በፓርላማ እየተነገረ የምን ማለባበስ ነው? ይልቁንስ የችግሩን ፅኑነት ተረድቶ ምን ይደረግ ለሚለው ተባብረን የጋራ መፍትሔ እናፍልቅ ማለት የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ› የሚባለው እኮ ችግርን እየሸፋፈኑ ‹አሸሼ ገዳሜ መቼ ነው ቅዳሜ› ማለት አያዋጣም ለማለት ነው…›› ያለው ጋቢና ያለው ጎልማሳ ነበር፡፡ ‹‹እውነት እንነጋገር ከተባለ እኮ ልማቱ የጋራ ነበር፡፡ ግና ምን ያደርጋል አንዱ ባለቤት ሌላው እንግዳ የሆነ የሚመስልበት ነገር በዛ…›› ብላ እርጥብ ነጋዴዋ እየተናገረች ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎን በቅደም ተከተል ወርደን ተለያየን፡፡ ውስጣችን የቀረው ግን የታመቀው ስሜታችን ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት