Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአገራዊ የኑሮ ጫናውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምጣኔ ሀብታዊ ምላሽ

አገራዊ የኑሮ ጫናውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምጣኔ ሀብታዊ ምላሽ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው 

        በአገራችን የተጀመረው የለውጥ መንገድ አካታች የተባለ የፖለቲካ መስተጋብርና ፈጣን የኢኮኖሚ ግንባታ ሒደት ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ የብዙዎች ቢሆንም፣ ነገሮች የታሰበውን ያህል መሄድ እየቻሉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል በአገር ደረጃ የተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ፣ የሰከነ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር ባለመስፈኑ፣ በሌላ በኩል ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊው ሁኔታ የደቀነው ተግዳሮት የጋራ ራዕዩ በቀላሉ እንዲሳካ እያደረገው እንዳልሆነ ይነገራል፡፡

     በእርግጥ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም አገር ቢሆን፣ ለዓመታት የዘለቀ አለመረጋጋትና ግጭት፣ የፖለቲካው ስክነት ማጣትና ማንነት ተኮር ጥቃቶች፣ እንዲሁም ፈጣንና ግልጽ የመልካም አስተዳዳርና የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ማስተካከያዎች በብሔራዊ መግባባት ደረጃ አለመታወቃቸው ለኑሮ ጫና መባባስ ምክንያቶች መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

    ያም ሆኖ መንግሥት በሚያገኘው ውስን ሀብት ቢያንስ አዲስ አበባን ጨምሮ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ቀላል ግምት የማይሰጣቸው የልማት ሥራዎችን ማከናውኑ ሊካድ አይችልም፡፡ የማይክሮ ፋይናንስ ለውጦችም መስተዋላቸው አልቀረም፡፡

      አገራዊ የግጭትና ጦርነት ሁኔታው በደምሳሳው ሲታይ ግን ለባለሀብቱና ለውጭ ኢንቨስተሮች አመቺ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ልዩ ትኩረት ለተሰጠው ቱሪዝም ዕድገትም እንቅፋት እየሆነ ስለመሆኑ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ መንግሥት በጥቅልና በተመረጡ መስኮች ላይ መረጃ እየሰጠ በድህነት ቅነሳ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትና መሰል ማኅበረሰባዊ የምጣኔ ሀብት መለኪያዎች ላይ እምብዛም መረጃ አለመስጠቱ እንጂ የኑሮ ጫናዎች መበርታታቸውን በርካቶች እየተናገሩ ነው፡፡ 

        ለአባባሉ ማስረጃ የሚሆኑት አሁንም በአገራችን ዋና ዋና ከተሞች በተለይ ግጭት በበረታባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሚባል የሥራ አጥ ቁጥር (በገፍ ተምሮ እየተመረቀ ያለውን ወጣት ጭምሮ) አለ፡፡ የገበያ ምርት እጥረትና የዋጋ ንረት፣ ብሎም የገበያ አሻጥርና ሰው ሠራሽ የገበያ ጫና እየተባባሰ እንጂ እየረገበ አልታየም፡፡ ከፍጆታ አንፃር እንደ ሥጋ፣ ወተትና እንቁላል ወይም ማርና ቅቤን የመሰሉ የቅንጦት ሊባሉ የሚችሉ አስቤዛዎች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ጥራጥሬ፣ እህል፣ የስንዴ ዱቄት፣ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉት አስፈላጊ የፍጆታ ምርቶችም ዋጋቸው እያናረና ከብዙኃኑ የመግዛት አቅም በላይ እንደሆኑ ነው፡፡ ምናልባት መሻሻል አለ ከተባለ አትክልትና ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደተናገሩት ሲሚንቶ ላይ ይመስለኛል፡፡

      በዚህም ምክንያት ዳቦ ገዝቶ መብላት የሚቸገሩ ሰዎች መበራከት ብቻ ሳይሆን፣ በሠልፍና በኮታ የሚሸጥባቸው ከተሞች በእጅጉ እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ ምናልባት አሁን የወጣው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ደንብ ይገራው ካልሆነ በስተቀር የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት ዋጋ ማሻቀብና እጥረት፣ የአልባሳትና መሰል መሠረታዊ ፍላጎቶች ዋጋ መናር ሲታይም ሥራና ገቢ ለሌለው አይደለም፣ ከዜጋው አማካይ ገቢ አንፃር በእጅጉ አሳሳቢ ሁኔታ መፈጠሩን አለመረዳት የሚቻል አይሆንም፡፡

      በተለይ በደመወዝ የሚተዳደረውና ወርኃዊ ተከፋዩ ሠራተኛ መቸገሩንና አንዳንዱ ቢሮ ውስጥ በማደር፣ ምሳ ሰዓቱን በእንቅስቃሴ በማሳለፍ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች መምህራን ጭምር የጉልበት ሥራ በመሥራት፣ አለፍ ሲልም በጣም የተቸገሩ እንስቶች ጎዳና ወጥቶ ገላ በመሸጥና በልመና ጎርሶ ለማደር በመሻት፣ ወዘተ እየታገሉ መሆኑ ይደመጥ ጀምሯል፡፡ ለነገሩ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ቢፈተሸ ይበልጥ አሳማኝ ይሆናል እንጂ ሌብነትና ውንብድናው እየበረታ ለመሄዱስ የኑሮ ጫናው የራሱን ድርሻ አላበረከተ ይሆን?

    በግብታዊነት የክልልነት ጥያቄን በማቅረብ መንግሥት ላይ ጫና ሲያሳድሩ የነበሩ በተለይም የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር የነበሩ ዞኖችንና ልዩ ወረዳዎችም፣ እንኳንስ ለዘላቂ ልማትና ዕድገት ለአስተዳደር ወጪ የሚበቃ ሀብት ማመንጨት አልቻሉም፡፡ ሊዚህም ነው በበርካታ አካባቢዎች ደመወዝ ለመክፈል ችግር እየተፈጠረ ያለው፡፡ ሐዋሳን የመሰሉ ከተሞች በከፍተኛ ደረጃ የምጣኔ ሀብት መዳከምና የበረታ ሥራ አጥነት እየታየባቸው ከመሆኑ ባሻገር፣ ነዋሪው የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ የሰጠበትን ቀን መርገም ጀምሯል ነው የሚባለው፡፡

      እንዲያውም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሕዝቡም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የመረዳዳትና የበጎ አድራጎት ተግባራት በመጀማመራቸው እንጂ፣ ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግርና ለከተማ ረሃብ ሊጋለጡ የሚችሉ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በባሰ ደረጃ ሊበራከቱ ይችሉ እንደነበር ነው አስተያያት  ሰጪዎች የሚናገሩት፡፡ በተለይ በልማት ተነሺነትም ሆነ በሕገወጥ ግንባታ ውስጥ በመቆየታቸው ምክንያት ይኖሩበት የነበረው ቤት እየፈረሰ፣ በአንድ ጀንበር ቤት አልባ እየሆኑ ያሉ ዜጎች የኑሮ ጫና አሳሳቢ መሆኑ ሊሸሸግ የሚችል አይመስልም፡፡

    መሬት ላይ ያለው አንዱ ገጽታ ይህ ሆኖ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት የመንግሥታቸውን የ2016 ዓ.ም. ሪፖርት  በ36ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ በተነሱላቸው ጥያቄ ላይ ተመሥርተው ሲያቀርቡ ግን፣ አገራዊና ዓለም አቀፍ ችግሮች ቢኖሩም አገራችን አስተማማኝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያመጣች መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

    ወቅታዊው ጫናም ቢኖርም፣ ‹‹የኑሮ ውድነት የበርካታ አገሮች ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከ60 በመቶ በላይ የደረሰ የዋጋ ንረት እየተመዘገበ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ መንግሥት በርካታ ተነሳሽነትና ተግባራትን  ቀርፆ እየሠራ ነው፤›› ማለታቸው የችግሩን መጠን ታሳቢ ያደረገ አባባል አይደለም የሚሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አጋጥመውኛል፡፡

     በተለይ የሌማት ትሩፋት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን፣ ምርታማነትን ማሻሻልም ሌላኛው ሥራ ነው ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በዘንድሮው ዓመት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰብ መቻሉን አውስተዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር ገቢ በመተው ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረጋቸውን በአብነት ገልጸዋል፡፡

      ይህ ሁሉ የሚከናወነው የኑሮ ውድነቱ ዜጎቻችን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል እንደሆነ፣ በዚህም የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል፡፡ ለዚህም ስንዴ ባለፈው ዓመት 395 ሚሊዮን ኩንታል ነበር ያመረትነው፣ ዘንድሮ 587 ሚሊዮን ኩንታል ነው ያመረትነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡  በቀጣዩ ዓመትም ከዚህ በላይ ምርት የማሳደግ አቅምና ዕድል አለን ብለው፣ ዘንድሮ 24 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ለማረስ ዕቅድ መያዙን በተስፋ ሰጪነት አስረድተዋል፡፡

    እንደ አንዳንድ የምጣኔ ሀብት አጥኚዎች አባባል ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ  በተለይ የስንዴን ምርታማነት ለማሳደግና በዘላቂነት የተፈጥሮ ሀብትና የአረንጓዴ ልማትን በማጠናከር ረገድ ተስፋ ሰጪ ጥረት መታየቱ ባይካድም፣ እንደ አገር እየተገኘ ያለው ምርት በተረጋጋ አገራዊ ሰላምና ደኅንነት መስተጓጎል ምክንያት ገበያው በሚፈልገው አከባቢ በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳይችልና የዋጋ ንረቱ ላይ አመርቂ ለውጥ እንዳታይ አድርጎታል፡፡

   መንግሥት ምንም የነዳጅ ድጎማን በማንሳት አንዳንድ ሸቀጦች ላይ ታክስ ማንሳቱና የቅንጦት ዕቃዎች ውስን በሆነው የውጭ ምንዛሪ እንዳይገቡ ክልከላ ቢያስቀምጥም፣ ከዚህ በፊት የወጪ ንግድንና የምንዛሪ ግኝትን ለማበረታት በሚል የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ (የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሙ) ለሕገወጡም ሆነ ምክንያታዊ ለሆነው የገበያ  የዋጋ  መናር በር ከፍቶለታል ባይ ናቸው፡፡

       በቀጣይም ቢሆን በድፍን የምጣኔ ሀብት መለኪያ ከመዘናጋት አብዛኛውን ነዋሪ ለመታደግ እንዲቻል፣ በአንድ በኩል ምርታማነትን ለማሳደግ በመረባረብና የወጪ ምርት አቅምን ለማሳደግ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል የአገር ሀብትና የመግዛት አቅምን ማሳደግ አንድ ነገር ሆኖ፣ በሌላ በኩል ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የገበያና የኑሮ ክፍተት የሚሞሉ ተግባራትን አጥንቶና አቅዶ መተግበር የመንግሥት ቀዳሚ ትኩረት መሆን እንዳለበትም ነው የሚያሳስቡት፡፡

    በሰሞኑ ማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመለካከቾችን በተመለከተ ሲናገሩ፣ በተያዘው በጀት ዓመት ከምርትና አገልግሎት ወጪ ንግድ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ፣ ከሐዋላ አገልግሎትም 6.5  ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለው፣ ኢትዮጵያ አሁንም በምሥራቅ አፍሪካ ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሳቢ አገር መሆኗን አስረድተዋል (የሐዋላ ግኝትና ሬሚታንስ በሚባለው የገቢ ምንጭ ግን መደማመጥና ዕርቅን በማስፈን የበለጠ ገንዘብ ሊገኝ እንደሚችል የታመነ ነው)፡፡

    አገራችን በበጀት ዓመቱም ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሏንም ዓብይ (ዶ/ር) በበጎ አንስተዋል፡፡ ስንዴን ጨምሮ በተኪ ምርቶች ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው፣ ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል ማለታቸው በመጪዎቹ ዓመታት በመስኩ ተስፋ እንዳለ ያመላክታል፡፡

   ዓብይ በምላሻቸው በአገር ኢኮኖሚ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ማመንጨት ቢገባውም፣  መንግሥት ከ64 ሺሕ ባልበለጡ ግብር ከፋዮች የሚሰበስበው 466 ቢሊዮን ብር ገቢ በቂ ሊባል እንደማይችል፣ ስለሆነም የግብር መረቡን ማስፋት ያስፈልገል ብለዋል፡፡ እንደ አገር በተያዘው ዓመት 716 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ከገቢው ጋር ያለመመጣጠኑን አመላካች ነው፡፡

       እዚህ ላይ መነሳት ያለበት እውነት ግን እንዲያውም የለውጡ መንግሥት ከደመወዝተኛው፣ ከአገልግሎትና ከንግዱ ማኅበረሰብ ከሚሰበስበው ግብር ባለፈ አዳዲስ የገቢ ማመንጫ ሕግጋትን በማውጣት ገቢውን ለማሳደግ እየጣረ መሆኑ ነው፡፡ አንደኛው የንብረት ታክስ ሲሆን፣ ቋሚም ሆነ ተንቀሳቃሽ ሀብት ያላቸው ሰዎች በተለይ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሀብት ለማሰባሰብ እየረዱ ነው፡፡

     በአከራይ ተከራይ አማካይነት የተጀመረው አዲስ አሠራርም ዜጎች በግልጽነት ገቢያቸውን አሳውቀው የሚጠበቅባቸውን እንዲከፍሉ መርዳቱ አልቀረም፡፡ እናም አሠራሩ እንደ አገር ሥርዓቱ ወጥ እንዲሆን ማድረግና በኑሮ ውድነት ላይ ጫና አለማሳደሩ ላይ በትኩረት ከተሠራበት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ጅምር መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

       ያነጋገርኳቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የመሪውን አኃዝ ማስተባበል ባይፈልጉም፣ ትልቁ ቁምነገር መሆን ያለበት ኢኮኖሚው እያመነጨ ያለውን ሀብት በድህነት ተኮር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ፍትሐዊነትን በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ለማዋል ቢቻል አሁን ካለው የተሻለ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊና የተመጣጣነ የኑሮ ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር ይላሉ፡፡ አጠቃላይ የገበያና የፍላጎት ክፍተትን ለመሙላት ካልተሠራ ተደጋግሞ የሚባለውን የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉም አስተማማኝ መፍትሔ እንደማይሆን በማመላከት፡፡

    ለአብነት ያለ ውዴታ የተገባባቸው የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ ብሎም አገር የማረጋጋት ተግባራቱ የሚያስከፍሉት ውድ ዋጋ ከፍተኛ ስለሚሆን በንግግርና በድርድር እንዲቋጩ ማድረግ ብልህነት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል (በነገራችን ላይ አማራ ክልልን በመሰሉ አንዳንድ ትርፍ አምራች አካባቢዎች እንኳንስ ግብዓት፣ ቴክኖሎጂና የተመረጠ አስተራረስ ለመከተል ጦም የሚያድሩ መሬቶች እንደይበረክቱ አስግቷል፡፡ አንዱ የሚሊሻ መሬት አይታረስም፣ ሌላው የፋኖ መሬት ማን ነው የሚያርሰው እየተባባለ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥጋትና ግጭት ፍርኃት በሬ መጥመድ እያሠጋ የተሳበውን ያህል ምርት ማግኘት እንዴት ይቻላል የሚሉ የመንግሥት አካላት ጭምር አጋጥመውኛል)፡፡

  መንግሥት በአዲስ ዕይታ የጀመራቸው የወደብ ተጠቃሚነትን የመፈለግ ትልሞች፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን የማውጣትና ጥቅም ላይ የማዋል ሥራዎች ብሎም አገራችን ያሉትን እምቅ ፀጋዎች (እርሻና የውኃ ሀብት የመሳሰሉትን) ወደ መጠቀም ማተኮርም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

    መንግሥት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የጀመራቸው የመሠረተ ልማት፣ የመልሶ ማልማት ግንባታና ታላላቅ ፕሮጀክቶችም ትውልዱንና አገር የሚመጥን ከተማ ለመገንባት ወሳኝ ቢሆኑም ከቅደም ተከተል አኳያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው አይገባም የሚሉም ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ በተለይ ከአዲሱ በጀት ዓመት ሥራዎች አንፃር አካሄዱ መፈተሸ እንዳለበት በማስታወስ፡፡

    የኮሪደር ልማቱ በራሱ የሚያስለቅቀው መሬትና የሚያመነጨው ሀብት ስለሚኖር ተጠናክሮ ይቀጥል ቢባል እንኳን፣ ባልተረጋጋ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚና የውጭ ጎብኚ በስፋት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ በአንድ ጊዜ ለበርካታ የቱሪስት መስህብ መዳረሻዎች ግንባታ በቢሊዮን ሀብት ሲፈስ፣ ከኢንዱስትሪና ከግብርና ልማት በምን መሥፈርት ቅድሚያ አግኝቶ ነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

      በሌላ በኩል ባለሙያዎቹ የበጀት አጠቃቀም ቋሚ ሊሆን እንደማይችልና ተለዋዋጭ መሆኑን የዓለምን ተሞክሮ በመፈተሸ መረዳት አስፈላጊ ነው ብለው፣ መንግሥት ከድንገተኛ ሥራዎችና ውሳኔዎች ብሎም ስሜታዊ ዕርምጃዎች መውጣት አለበት ይላሉ፡፡ በተቻለ መጠን ከተደቀኑ አገራዊ ቀውሶች በመውጣት የውጭ ጫናዎችና ቀጣናዊ ተግዳሮቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ በመቋቋም፣ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን ማበጀት እንዳለበትም በማስታወስ፡፡

       በእርግጥ የዜጎች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል የማድረግ ዋነኛ ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም ከሁኔታው ከባድነት ለመላቀቅ ዜጎችም የራሳቸውን የሥራ ፈጠራና የበጀት አጠቃቀም በማሻሻል ሁኔታውን ማለፍ እንዳለባቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በወቅታዊ ፈተናዎቸና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከማማረር አቅም የፈቀደውና የሚቻሉ በእጅ ውስጥ ያለ አማራጮችን መመልከት ብልኃት ነውና፡፡ ኑሮ በዘዴን ጨምሮ፡፡

      ሌላው ዘዴ ደግሞ እንኳን ግለሰብ መንግሥትም በተቻለ መጠን ራስን ከብድር ማላቀቅ ነው ያለበት፡፡ ብድር የወጪ ሁኔታን የማዛነፍ አቅም ስላለው ወደፊት የሚኖር የወጪ ምክንያት እንዳይጨምር ከብድር ራስን ማራቅ፣ እንዲሁም የነበረ ብድር ካለ በፍጥነት በተቻለ አቅም ከፍሎ ከዕዳ መላቀቅ እንደሚገባ ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

      እዚህ ላይ ዓብይ (ዶ/ር) የተናገሩትን ነጥብ መጥቀስ ጠቃሚ ነው፡፡ እንደ እሳቸው አባባል መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት ምንም ዓይነት የኮሜርሻል ብድር ያልወሰደ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ (አዲሱ መንግሥት ከፍተኛ የአገር ብድር ክምችት ተቀብሎ የነበረ ቢሆንም) አሁን ላይ ያለባት የውጭ ብድር ወደ 17.5 በመቶ ዝቅ ማለቱንም አስረድተዋል፡፡ እንደ አገር የተለመደውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት በብድርና በዕርዳታ የሚገኘው በተለይ የምዕራቡ ዓለም ሀብት (አይኤምኤፍና ዓለም ባንክን ጨምሮ) ግን አስቸጋሪ ውጣ ውረድ እንደገጠመው አልሸሸጉም፡፡

   ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አይዳሱት እንጂ ባለንበት አገራዊ ሁኔታ የሚታዩ ኢፍትሐዊነትና ሰው ሠራሽ የገበያ ብልሽቶችን በመግታት፣ ብሎም የገበያ ችግሮችን ለመቋቋም መንግሥትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ቁጥጥራቸውን ማጥበቅ ያለባቸው መሆኑም ሊሰመርበት የሚገባው ነው፡፡ በተለይ የደላላና የገበያ አሻጥር፣ እንደ ኮንትሮባንድና አየር በአየር ዓይነት ሕገወጥ ንግዶችን በሚፈለገው ደረጃ ማዳከም አስፈላጊነቱ አያጠራጥርም፡፡

         ከህዳግ በላይ ማትረፍ፣ ምርት መሸሸግና አቆይቶ በመሸጥ እላፊ ለመጠቀም መሻት፣ ሙስናና ሌብነት፣ እንዲሁም የሚዛን ቅሸባና የባዕድ ነገሮች ቅየጣ ዓይነት ጫፍ የወጡ የገበያ ነውሮችን ለመታገል ሕዝብና መንግሥት ተቀናጀተው መረባረብ እንዳለባቸውም ተደጋግሞ የተነገረ ደሃ የመታደግ መፍትሔ ነው፡፡

      እንደ አገር የሕዝብ ብዛትና የፍላጎት መጨመር ከአቅርቦት ጋር አለመመጣጣኑ የኑሮ ውድነትን እንደሚያስከትል የታወቀ ቢሆንም፣ በተለይ አዲስ አባባን በመሰሉ በከተሞች በመኖሪያ ቤት፣ በምግብና አልባሳት ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ትራንስፖርት፣ ትምህርትና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመሰሉት መስኮች ላይ እየተፈጠረ የመጣው ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከብዙኃኑ ሕዝብ የዕለት ገቢ ጋር ያልተመጣጣና ፈታኝ የሆነው በመልካም አስተዳዳር ብልሽት፣ በሙስና መበርታትና በንፋስ አመጣሽ ሀብት መበራከት መሆኑን መንግሥትም የተረዳው አደጋ መስሏል፡፡

      ለዚህም ነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሙስናና ብልሹ አሠራር በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቷል፣ ኢፍትሐዊነትና የጥገኝነት መንገድ በርትቷል፣ በሕዝብ መሬት ሳይሰሩ መበልፀግና መፋነን ተበራክቷል ምን ይሻላል፣ መንግሥትስ ምን ዕርምጃ ሊወስድ አስቧል እስከ ማለት ሥጋታቸውን የተናገሩት (እውነትም ሙስና ተባብሶ ቀደም ሲል ባልነበረ ሁኔታ ኢምባሲ ቪዝ ለማስመታት ሳይቀር ያገለግላል መባሉን ለሰማ ሰው የት እንደደረስን ያስገምታል)፡፡

      ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሙስና የአገር ካንሰርና ዋነኛ አደጋ መሆኑን ተናግረው፣ ነገር ግን ሥርዓታዊ ሳይሆን እዚያም እዚህም በተበላሹ ሙሰኞች መበራከቱን፣ መንግሥትም ችግሩን ለመታገል ቁርጠኛ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የመለየትና ሕገወጥ ሆኖ ሲገኝ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕግ ማውጣት ያስፈለገውም ከአደጋው መበራከት አኳያ ታይቶ ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም ሕጉ ከወዲሁ ተቃውሞ እንዲገጥመው እየተደረገ ያለው በጥገኛውና ሳይገባው በተደናገረው ወገን መሆኑን በመጠቆም፡፡  በአደጋው አሳሳቢነት ላይ ግን በሁሉም ወገን ቢሆን ልዩነት አለመኖሩን አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡

      በአጠቃላይ አሁን አገራችንንና ሕዝቧን የገጠመቸው የምጣኔ ሀብት ፈተና የማደግና ያለ ማደግ ጉዳይ  ብቻ ሳይሆን፣ የመኖርና ያለ መኖር የህልውና ፈተና ሆኗል፡፡ በተለይ ደግሞ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት እያረጋጋጠ ባልመጣበት ሁኔታ ከፖለቲካ ውዝግብና አተካሮ፣ ብሎም ከሁከትና ከትርምስ ወጥቶ ስለዳቦ መነጋጋር፣ ማቀድና መሥራት ሊቀድም ይገባል፡፡ የአገር ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትና ነፃነት የሚረጋጋጠው ከዳቦ በኋላ ነውና፡፡ 

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...