Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርይድረስ ለኢትዮዽያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ይድረስ ለኢትዮዽያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ቀን:

በኤርሚያስ አማረ

ምክክር ለአንድ አገር ግንባታ ሒደት ወሳኝ ሚና አለው:: በመስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) የሚመራው የምክክር ኮሚሽን ለጥረቱ መሳካት ምኞቴን መግለጽ እወዳለሁ:: ለተወሳሰበው የኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ለማበጀት ችግሩ ብቻ ላይ ማተኮር ሳይሆን፣ የችግሩን ምንጭ ወይም ምክንያት ማወቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል:: እንደ እኔ ዕይታ በዚህ ሒደት ትልቁ ችግር የሚሆነው የሚደራደሩትን ባለድርሻ አካላት በትክክሉ ለይቶ ማወቅ ነው፡፡

ይስሃቅ ኤፍሬም (ፕሮፌሰር) ኢትዮዽያ ውስጥ ሁለት ብሔሮች ናቸው ያሉ ሲሉ ትዝ ይለኛል:: ይኸውም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኝ ብሔር የለኝም ባዩ (westernized) ልሂቅና ብሔርተኛ ነኝ እያለ ከአዲስ አበባ ውጪ ያለውን ኅብረተሰብ የሚወክል ልሂቅ ናቸው ይላሉ:: በአጭሩ ምክክሩና ድርድሩ በክልሎች መካከል ሳይሆን በሁለቱም ወገን ነው መሆን ያለበት::

በኢትዮዽያ አገረ መንግሥት ግንባታ የማይናቅ ሚና የተጫወተው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቢሆንም፣ በየጊዜው የመጡት መሪዎች በጂኦግራፊ አዲስ አበቤውን በመያዝ የሠሩት ሥራ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል:: ለመቶ ዓመት ሌላውን እያስገበረ አገር ያስቀጠለ ይኸው አካሄድ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት እንዳየነው የበይ ተመልካች አልሆንም ብሎ አገሪቱን እንደ አዲስ አዋቅሮ ሥልጣኑን ከተጋራ በኋላ፣ በታሰበው መንገድ ሳይሄድ ቀርቶ ጭራሽ የመጣበት ብሔር ውስጥ መደበቅ ሙያ ያደረገው ኃይል ነው:: ይህ ኃይል በመሀል መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር የራሱን ብሔር ቁም ስቅሉን የሚያሳይ ብሔርተኛ ነኝ የሚል ልሂቅ ሲሆን፣ ከብሔር የለኝም ባዩ ልሂቅ ባልተናነሰ አገሪቱን እያመሳት ይገኛል:: ይኸው ብሔርተኛ ‹‹የሰው ጅብ ከሚበላህ የራስህ ጅብ ይብላህ›› በሚል የተሳሳተ ሥሌት የመጣበት ኅብረተሰብ ልሂቁን ሳይሞግተው ቀርቶ ተላምዶት እየኖረ ነው::

ብሔር የለኝም ባዩ

ብሔርተኝነት ተፈጥሯዊ የፓለቲካ ክስተት ሆኖ ሳለ በክርስትና ስሙ እየተጠራ እንደ ክፉ ነገር ተደርጎ እንዲታይ በማድረግ ጫናው በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሞ ብሔር/ተወላጅ ላይ እንዲሆን ብዙ ሥራ ሠርቷል:: ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ችግር በቅጡ ያልተረዳው ብሔር የለኝም ባዩ ይኸው አዲስ አበቤው ነው:: ተጋምደናል፣ ተዋልደናል እያለ 70 በመቶ የአገሪቱ ሀብት ይዞ ፖለቲካውን ተቆጣጥሮ አላካፍል ያለን ይኸው አግላይ ጠቅላይ ቡድን ነው፡፡ የመጣ መንግሥት ላይ ተለጥፎ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲረሳ እያደረገ ያለው ይኸው መደብ ነው:: ባህሉ፣ ቋንቋው፣ ኢኮኖሚው፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራቱ፣ አንጋፋ ሆስፒታል፣ ትልቅ ዩኒቨርሲቲ፣ ውብ ኤርፖርት፣ የፌዴራል ተቋማት ለብቻው ይዞ በተቀረው ላይ መደራደር ጉንጭ አልፋ ነው የሚሆነው::

ይህንን ስል እንደ አንድ የራሱ ጠንካራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ  እንደፈጠረ መደብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕት እንደሚያደርግ ዘንግቼው አይደለም፡፡ ስለዚህ መረር ባሉ ቃላት ብናገርም ይህንን ወገን ለማሸማቀቅ ሳይሆን (እንደማይቻል ባውቅም) እስካሁን የነበረው አወቃቀር የፈጠረለት፣ ዕድል ተጠቅሞ፣ የራሱን ጥቅም ማስጠበቅ በሚፈልግበት ጊዜ በሌላኛው ወገን ያሉትን ችግሮች ተረድቶ እንዲደራደር ለማስታወስ ነው::

የሐሳብ ተቃርኖ

በአዲስ አበባና በተቀሩት ክልሎች መካከል ያለው የሐሳብ ተቃርኖ ሰፊ ነው:: ሁለታቸው ኢትዮዽያን የሚያዩበት መነፅር እጅግ ይለያያል:: አንዳቸው የአንዳቸውን ምልከታ በማጥፋት (እሳትና ጭድ እንተባለው) አገር የሚድን ይመስላቸዋል:: ግን እስካሁን እንዳየነው አልተሳካም:: ሁለቱም በየተራ ሥልጣን ይዘው እኛ ላይ ሲፈራረቁብን ይኸው ስንት ዓመት ተጉዘን ምንም ለውጥ አልመጣም:: የፖለቲካ አሠላለፉ በብሔር ከተደራጁ ኢትዮዽያውያን ይልቅ ከኤርትራ ጋር ቢያደርግ ይመርጣል:: ከትግራይ ጋር በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት የተወው ጠባሳ ቀላል አይደለም::

በወልቃይት (አማራ-ትግራይ) በመተከል (ደቡብ-አማራ)፣ በአዳይቱ ቀበሌ (ሶማሌ-አፋር)፣ ምዕራብ ጉጂና ጌዴኦ ዞን (ኦሮሚያ-ደቡብ) ከሚደረጉት የይገባኛል ጥያቄ በላይ አገሪቱ ውስጥ ካሉ ትልቁ ችግሮች ሲወዳደር ጥቂት ነው:: አብዛኞቹ ከመሀል አገር ሆነው በሚደረግ ምክክር የሚፈቱ ይመስለኛል::

እዚህ ላይ አንድ ተግዳሮት ማንሳት እፈልጋለሁ:: ከእያንዳንዱ ወገን ሙሉ ውክልና ያለው ማግኘት ይከብድ ይሆናል:: በተለይ ብዙ ክልሎች ያካተተው የመጀመሪያው ወገን ወክሎ ሊመጣ የሚችል ይኖራል ወይ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል:: ተገቢ ጥያቄ ነው:: 75 በመቶ አጀንዳቸው ተመሳሳይ ስለሆነ ችግራቸው በዘላቂነት የሚፈቱበት መንገድ ለማጥበብ ያመቻል:: ስለዚህ በቡድን ሆነ በተናጠል እወክላለሁ ስለሚለው ማኅበረሰብ እያወራ አገራዊ ግንባታው ላይ አስተዋፅኦ ካደረገ በኋላ መግባባት ሲደረስ፣ በክልል/ወረዳ ደረጃ ያሉትን ችግሮች እንደየ አካባቢው መፍታት በጣም ቀላል ይሆናል፡፡

ምዕራባውያን ጨቋኝ የአፍሪቃ መንግሥት (repressive regime) ከኋላ ሆነው ያግዙና ለምንድነው አፍሪቃውያን እርስ በራሳቸው የማይስማሙ ብለው እንደሚሳለቁብን አዲስ አበቤውም የአገሪቱን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመቆጣጠር መንግሥት ሥልጣኑን እንዲፀና ያግዝና በወልቃይት፣ በመተከል፣ በአዳይቱና በጉጂ/ጌዴኦ ያለው ችግር ምንጩ ሕገ መንግሥት ነው ብሎ ራሱን ከተጠያቂነት ያድናል፣ እሱ ተበልቶበታል:: ፈረንጆች “let’s take the bull by the horn” እንደሚሉት እንጋፈጠው:: ከተማውን ማስተዳደር ይችላል፣ የአገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ግን የእሱ ጥገኛ መሆን የለበትም::

በዚህ ጉዳይ ዘርዘር ያለ ምልከታየንና ሊሠራ የሚችል የመፍትሔ ሐሳቦችን ማቅረብ እችላለሁ:: በእርግጠኝነት ለአገራዊ ግንባታው የመጀመሪያው የማዕዘን ድንጋይ እንደ ማስቀመጥም ይሆናል ብዬ አስባለሁ:: ዳያስፖራ እንደ መሆኔ መጠን መድረኩን እንዴት እንደማገኝ ባላውቅም፣ መድረኩ ከተዘጋጀ ግን ከሚመለከተው ጋር በጥልቀት ለመወያየት ዝግጁ ነኝ:: በዚህ አጋጣሚ ዳያስፖራ የሚወከልበት መንገድ ቢመቻች ይመከራል:: እነ ገዱ አንዳርጋቸውና ይልቃል የአሜሪካ አምባሳደርን ማናገር ከቻሉ፣ እኛም እዚህ ካሉት አምባሳደሮች ጋር መገናኘት እንችላለን ማለት ነው::

አገራዊ ግንባታውን ከግቡ ለማድረስ ድርድርና ምክክር ወሳኝ ነው:: እኔ መፍትሔ ብዬ የማቀርበው 50 በመቶ ሥራ ላይ ከዋለ ኢትዮጵያ ውስጥ በአመፅ መንግሥት መቀየር ታሪክ ይሆናል::

አገር ማዳን ይቻላል!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...