Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሳህል ቀጣና ሦስት አገሮች በኮንፌዴሬሽን መዋሃድ

የሳህል ቀጣና ሦስት አገሮች በኮንፌዴሬሽን መዋሃድ

ቀን:

በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣናቸውን ያፀኑት የቡርኪና ፋሶ፣ የማሊና የኒጀር ወታደራዊ መሪዎች፣ በኮንፌዴሬሽን ለመዋሃድ ስምምነት አደረጉ፡፡

በሦስቱ አገሮች መካከል ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈረመው አዲስ ስምምነት፣ ከዚህ ቀደም አባል የነበሩበትን የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) የሚያሽመደምድ ነው ተብሏል፡፡

የሳህል ቀጣና ሦስት አገሮች በኮንፌዴሬሽን መዋሃድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኒጀር፣ የቡርኪና ፋሶና የማሊ መሪዎች በኮንፌዴሬሽን ለመዋሃድ ተስማምተዋል (ቡርኪና ፋሶ ፕሬዚደንሲ)

በኒጀር ዋና ከተማ ኒአሜይ የመከሩት የኒጀር መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ታቻይኒ፣ የቡርኪና ፋሶ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ እንዲሁም የማሊ ኮሎኔል አስሚ ጎይታ የደረሱበት በኮንፌዴሬሽን የመዋሃድ ስምምነት፣ ዓምና ከሽምቅ ተዋጊዎችም ሆነ ከውጭ ሊሰነዘርባቸው ከሚችል ወታደራዊ ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል እንዲችሉ የተስማሙበትን ‹‹የጋራ የመከላከያ ስምምነት›› (ሚችዋል ዲፌንስ ፓክት) የሚያጠናክር ነው፡፡

ከዚህ ቀደም፣ የሳህል ግዛቶች ጥምረት (አሊያንስ ኦፍ ሳህል ስቴትስ፣ኤኢኤስ) በሚል ራሳቸውን በመከላከል ላይ ያተኮረ የጋራ መከላከያ ስምምነት መፈረማቸውና  አሁን የደረሱበት በኮንፌሬሽን የመዋሃድ ስምምነት፣ ላለፉት 50 ዓመታት ከነበሩበት የኢኮዋስ ማኅበረሰብ መነጠላቸውን የሚያረጋግጥም ነው፡፡  

በሦስቱ አገሮች በተደረጉ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ምክንያት፣ የኢኮዋስ አባል አገሮች መሪዎች በጊዜያዊነት ከኢኮዋስ አግደዋቸው የነበረ ሲሆን፣ አገሮቹም ከስድስት ወራት በፊት ከኢኮዋስ ራሳቸውን ማግለላቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

በኮንፌዴሬሽን ለማዋሃድ የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ንግግር ያደረጉት የኒጀር መሪ ጄኔራል ታቻይኒ፣ ‹‹የ50 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ኢኮዋስ ሥጋታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢኮዋስ በኒጀር በሐምሌ 2023፣ በቡርኪና ፋሶ መስከረም 2022 እና በማሊ በነሐሴ 2021 የተደረጉትን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች በማውገዝ፣ በአገሮቹ ላይ ማዕቀብ ጥሎ የነበረ ቢሆንም፣ ተመልሰው የጥምረቱ አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ ነበረው፡፡

ሆኖም የሳህል ግዛቶች ጥምረትን (ኤኢኤስ) የመሠረቱት ማሊ፣ ኒጀርና ቡርኪና ፋሶ በኢኮዋስ ምትክ የራሳቸውን ጥምረት መፍጠራቸውን፣ የኢኮዋስ መመርያዎችና ትዕዛዞች ከአፍሪካውያን ውጪ ባሉ ኃይሎች የተቃኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቡርኪና ፋሶ መሪ ትራኦሬ በበኩላቸው፣ ‹‹የውጭ ኃይሎች አገራችንን መበዝበዝ ይፈልጋሉ፤›› በማለት፣ ሦስቱ አገሮች ከዚህ ቀደም የፈረንሣይ የቅኝ አገዛዝ ሕግ በኢኮዋስ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል በማለት ሲቃወሙ የነበሩትን አጠናክረዋል፡፡

‹‹ምዕራባውያን እኛና ሀብታችን የእነሱ እንደሆንን ይቆጥራሉ፡፡ ለአገራችን የሚሆነውን ሁሉ እነሱ ብቻ መናገር እንዳለባቸው አድርገው ያስባሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የዚህ ዓይነቱ ዘመን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አክትሟል፤›› ያሉት ትራኦሬ፣ የየአገሮቹ ሀብት ለራሳቸውና ለሕዝባቸው እንደሚሆን አክለዋል፡፡

አልጄዚራ የማሊውን መሪ ጎይታን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በሦስቱ አገሮች መካከል የተደረሰው ስምምነት ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር ነው፡፡ ከሦስቱ አገሮች በአንዱ ላይ የሚፈጸም ጥቃትም በሦስቱም እንደተፈጸመ ይቆጠራል፡፡

በአገሮቹ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገ በኋላ፣ ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሻክሯል፡፡ ከቀድሞ ቅኝ ገዥያቸው ፈረንሣይ ጋር የነበራቸውን የወታደራዊና የመከላከያ ግንኙነት አቋርጠዋል፡፡ የበለጠ ግንኙነታቸውንም ከሩሲያ ጋር አድርገዋል፡፡

በማሊ የነበሩ የፈረንሣይ ወታደሮች በ2022፣ ከቡርኪና ፋሶና ኒጀር ደግሞ ዓምና ሙሉ ለሙሉ ወጥተዋል፡፡ በኒጀር ካለው የአሜሪካ የአየር ጦር ሠፈር የሚገኙ 1,000 የአሜሪካ ወታደሮችም ለቀዋል፡፡

አሜሪካም በማዕከላዊ ኒጀር ከሚገኘውና አንድ ሚሊዮን ዶላር ከወጣበት የአሜሪካ የድሮን ጦር ሠፈሯ ለመውጣትም ዝግጀት ጀምራለች፡፡ በምዕራባውያን እግር እየተተካች ከምትገኘው ሩሲያ ጋር የደኅንነትና የኢኮኖሚ ግንኙነትም እየፈጠሩ ነው፡፡

72 ሚሊዮን ሕዝብ ያላቸው ሦስቱ አገሮች፣ ዋና በሚባሉት በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በኃይል አቅርቦት፣ በውኃና በተለያዩ ዘርፎች አብረው የሚሠሩ ይሆናል፡፡

አገሮቹን እያጠቁ የሚገኙትን አክራሪ ቡድኖች በጋራ ለመምታት የተስማሙት መሪዎቹ፣ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ለአገር በቀል ቋንቋዎች ቅድሚያ እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...