Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር እየሠራ ይገኛል፡፡ ደመቀ ደስታ (ዶ/ር) የሕክምና ዶክተርና የማኅበረሰብ ጤና ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ የሥራ ልምድ ያካበቱት ደመቀ (ዶ/ር)፣ ረዥሙን ዓመታት በሥነ ተዋልዶ ጤና በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየሠራ በሚገኘው አይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በተቋሙና በኢትዮጵያ ባለው የሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- አይፓስ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ከጀመረ ከሃያ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ እርስዎም ለበርካታ ዓመታት በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ሠርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- አይፓስ እ.ኤ.አ. በ2000 ነው በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍቶ መሥራት የጀመረው፡፡ ከዚያ በፊት ኬንያ ከነበረው ቢሮ ሆኖ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ጋር አብሮ ይሠራ ነበር፡፡ የሕክምና ባለሙያዎችን ኬንያ እየወሰደ ሥልጠና ይሰጥ ነበር፡፡ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ መጥተውም ሙያዊ ሥልጠና ይሰጡ ነበር፡፡ በተለይ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥን ለማስቀረትና የሴቶችን ሕይወት ለመታደግ ክህሎትን መሠረት ያደረገ ሥልጠናም ይሰጡ ነበር፡፡ በወቅቱ የእናቲቱን ሕይወት ለማዳን ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ፅንስ ማቋረጥ ሙሉ ለሙሉ ክልል ነበር፡፡ በመሆኑም ሴቶች ያላቀዱት ወይም ያላሰቡት እርግዝና ገጥሟቸው ደኅንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንስ ያቋርጡ ነበር፡፡ ሴቶች በዚሁ ሳቢያ ይገጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን ለማቅለል፣ ጤንነታቸውንና ሕይወታችን ለመታደግ የጤና ባለሙያዎችን ሲያሠለጥን፣ ከጤና ቢሮዎችና ባለሙያዎች ጋር ደኅንነቱ ካልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ በኋላ ሴቶችን ይገጥሙ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመታደግ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የፅንስ ማቋረጥ ሕግ በጣም ከልካይ ከመሆኑ የተነሳ በሴቶች ላይ የተፈጠረውን ችግር ያጠናም ነበር፡፡ ጥናቱንም በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ለሚሠሩ ያስገነዝብ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው ሁኔታና እኔም የሕክምና ትምህርት ቤት ሆኜም ሆነ በሥራ ላይ እያለሁ ያየሁት እውነታ ዘግናኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አይፓስ ያጠናው ጥናትም ምን አሳየ? የእርስዎ ምልከታ እንዴት ነው?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- በወቅቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ክልክል ስለነበረ፣ ሴቶች ያልታሰበ እርግዝና በሚያጋጥማቸው ጊዜ ማንኛውንም ነገር አድርገው ፅንስ ለማቋረጥ ይሞክሩ ነበር፡፡ ባለን ልምድ በርካታ ሴቶችና እናቶች በአፍ በሚወሰድ አሊያም በማህፀን በሚገባ ፈጽሞ ፅንስ ለማቋረጥ በማይመከሩ ዘዴዎች እየተጠቀሙ ለከፍተኛ ሕመምና ስቃይ ብሎም ለሞት ይዳረጉ ነበር፡፡ ድርጊቱም ባህላዊ ሐኪሞች ነን በሚሉ ይከናወን ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ደም መፍሰስ፣ የማህፀን መጎዳት፣ ኢንፌክሽን መሥራትና መበስበስ ያጋጥማቸው ነበር፡፡ ወደ ሕክምና የሚመጡት ሕይወታቸው አሥጊ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜም እነሱን ማዳን አይቻልም ነበር፡፡ ከሞት የተረፉት ደግሞ በሆስፒታሉ ፅንስ በማቋረጥ ብቻ ለስቃይ ተጋልጠው ለመጡ በተዘጋጀ ዋርድ ተገኝተው ይታከሙ ነበር፡፡ ኢንፌከሽኑ ከማህፀን አልፎ የሰውነት ክፍላቸውን ሙሉ ስለሚያጠቃው የነበረው ጠረን ለራሳቸውም፣ ለሌሎች ታማሚዎችም ሆነ ለሕክምና ባለሙያዎች ፈታኝ ነበር፡፡ ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱበትና የሚሰቃዩበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የፅንስና ማህፀን ክፍል አልጋዎች እስከ 60 በመቶ የሚያዙት ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ውስብስብ ጉዳት ደርሶባቸው በሚመጡ ወጣት ሴቶችና እናቶች ነበር፡፡ ብዙዎቹም ይሞቱ ነበር፡፡ በብዛት ፅንስ አቋርጠው የሚመጡት ወጣቶች ቢሆኑም፣ የሶሽዮ የኢኮኖሚ ደረጃቸው ሲታይ፣ ተማሪዎች፣ በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ፣ ሥራ ያላቸውና የሌላቸው፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ በከፍተኛ ደረጃ ዕርከን የሚሠሩ፣ ያገቡና ያላገቡ በአጠቃላይም ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ነበሩ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህን ክስተት ተከትሎ ምን ተሠራ?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲሻሻልና ይህንን ተከትሎ ሌሎች ሕጎች ሲሻሻሉ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉም ተሻሻለ፡፡ እንዲሻሻል ከተደረጉት አንዱ በተወሰኑ ምክንያቶች ብቻ ደኅንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥን መፍቀድ ነው፡፡ ይህ የተደረገው ብዙ የሕግ፣ የጤና፣ ለሴቶች መብት የሚሠሩ ባለሙያዎችና የመንግሥት አካላት መክረውበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክርክር ተደርጎበትም ነበር፡፡ በወቅቱ በአገሪቱ የነበረው እውነታ የሚያሳየው ሴቶች ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ እየተሰቃዩና እየሞቱ የነበረ ቢሆንም፣ ለማሻሻል በተደረገው ውይይት ከውጭም ከአገር ውስጥም የተቃወሙ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ወደ ኅብረተሰብ ወርዶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ችግሩ ኅብረተሰቡ የሚያውቀውና የብዙዎችን ቤት ያንኳኳ እንደነበር ከውይይቱ መገንዘብ ተችሎ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት አሁንም ቢሆን ከተቀመጡ መሠረታዊ ምክንያቶች በስተቀር ፅንስ ማቋረጥ አይፈቀድም፡፡ አንዲት ሴት ተደፍራ፣ ከቤተሰብ አባል ጋር ግንኙነት ኖሮ እርግዝና ከተፈጠረ ፅንሱን ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንድታቋርጥ ሕግ ይፈቅድላታል፡፡ ለጤናዋ አስቸጋሪ ከሆነ፣ ለሕይወቷ አሥጊ ከሆነ፣ የፀነሰችው ከ18 ዓመት በታች ከሆነች እንዲሁም ልጅ ለማሳደግ አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ እክል ያለባቸው ሴቶች ፅንስ ማቋረጥ ይቻላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አይፓስ እርግዝናን ቀድሞ በመከላከል ዙሪያ ምን ይሠራል?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- የመጀመሪያውና ቅድሚያ የምንሰጠው መከላከል ላይ ነው፡፡ ሰውን ከታመመ በኋላ ከማከም ሳይታመም ቀድሞ መከላከሉ ይሻላልና ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ለሁሉም እኛ በምንሠራባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንሠራለን፡፡ በየአካባቢው ከማኅበረሰብ ጋር ከሚሠሩ አደረጃጀቶችና ከጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጋር በመሆን ኅብረተሰቡን እናስተምራለን፡፡ ለወጣቶች አጠቃላይ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ራሳቸውን ካልተፈለገ እርግዝና እንዴት መከላከል እንደሚችሉ እናስተምራለን፡፡ የምንሠራው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ራሳቸውን ማኖር እንዲችሉ ነው፡፡ የምናሠለጥነው በማኅበረሰብና በኤፍኤም ሬድዮኖች፣ በተለይ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተደራሽ በሆኑ የሞባይል መተግበሪያዎች እንዲሁም በራሪ ወረቀቶች ተጠቅመን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ያልታሰበ እርግዝና ቢከሰት ወደ ጤና ተቋም ብቻ እንዲሄዱ እንመክራለን፡፡ በጤና ተቋም በሚደረግ ምክክር እርግዝናው እንዲቀጥል ወይም ፅንስ ማቋረጥ የሚቻልበትን የሕግ አግባብ የምታሟላ ከሆነ እንዲቋረጥ አብረው እንዲወስኑ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቅድመ መከላከል አገልግሎቱ ምን ያህል ተደራሽ ነው? ከጤና ሚኒስቴር ጋር የሠራችሁት ዳሰሳ ይኖራል?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- በማስተማር በኩል ተደራሽ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በማኅበረሰብ ሬዲዮ በተለያዩ ቋንቋዎች ማስተማራችን ብዙዎችን ይደርሳል ብለን እናስባለን፡፡ በራሪ ወረቀቶችም በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መሆናቸው ተደራሽነቱን ያጎላዋል፡፡ ግንዛቤውን ተደራሽ ማድረግ የፕሮግራማችን አንዱ አካል ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የቤተሰብ ዕቅድ ላይ ከመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት ጋር እንሠራለን፡፡ በመንግሥት ጤና ተቋማት ለሚሠሩ ባለሙያዎች ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግብዓቶችን ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እናቀርባለን፡፡ አሁን ላይ ግብዓቶች በማዕከል መከፋፈል አለባቸው ስለተባለ እኛ ለሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች ሳይቋረጡ የሚደርሱበትን አሠራር እንደግፋለን፡፡ የጤና ባለሙያዎችን ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በጤና ተቋማት በርካታ ማነቆዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ችግሩን ለመቅረፍ አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቅድመ ወሊድ መከላከያ አቅርቦት በተለይ ክልሎች ላይ ተደራሽ ናቸው? ሴቶችን አስገድዶ ተቃጠሚ ማድረግ ይታይ ነበር፣ በተለይ በአንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች የወሊድ መቆጣጠሪያ አልጠቀምም ያለች ሴትን ማግለል ነበር፡፡ ይህንን እንዴት አስታርቃችሁታል?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- ጉዳዩ እንደ መረጃ አለን፡፡ በዋናነት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሴቷ በቂ መረጃ አግኝታ ፈልጋና ወስና የምትጠቀመው አገልግሎት እንጂ በግድ ተገዳ የምትጠቀመው አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሥነ ተዋልዶ ጤና መብት ነው፡፡ ኢትዮጵያም የተቀበለችው ስምምነት ነው፡፡ እኛም በዚሁ መሠረት ነው የምንሠራው፡፡ የተነሱት ሐሳቦች በተወሰነ መልኩ ይፈጠሩ የነበሩባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ እኛም እናስታውሳለን፡፡ ምክንያቱም አንድ የጤና ባለሙያ የምትገመገመው/የሚገመገመው በሰጠችው/በሰጠው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ቁጥር ነው ተብሎ ይወሰድ ስለነበር፣ የመጣውን ሁሉ ውሰዱ የሚል ግፊት እንደነበር ሰምተናል፡፡ ትክክል እንዳልነበረና ከመንግሥትና ከጤና ባለሙያዎች ጋር ሆነን አብረን ሠርተን በአሁኑ ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከአጭር ጊዜ፣ ከረዥም ጊዜና ከቋሚ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሴቶች የፈቀዱትን ነው መርጠው መውሰድ ያለባቸው፡፡ አልፎ አልፎ በክልሉ ወይ በወረዳው ጤና ቢሮ ኮታ ይቀመጥና ኮታ ለማሟላት ሲባል ሴቶች ትክክለኛ መረጃ ሳይሰጣቸው ይህንን መውሰድ አለባችሁ እየተባሉ የሚሰጣቸው እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ይህ አሠራር ችግር ስለነበረበት በጤና ቢሮዎችና በጤና ሚኒስቴር ግንዛቤ ተወስዶ እንዲስተካከል ተደርጓል፡፡ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል ባንልም፣ በብዛት በሪፖርት አይመጣም፡፡ እንደ አጠቃላይ ስናየው ግን፣ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ጨምሯል፡፡ በ2000 ዓ.ም. አካባቢ የነበረው ዝቅተኛ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሁን በፍላጎትም፣ በተጠቃሚም ደረጃ ጨምሯል፡፡ ቀድሞ ከስምንት እስከ አሥር በመቶ የነበረው ያገቡ እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ አጠቃቀም ወደ 42 በመቶ አድጓል፡፡ ዕውቀቱ፣ ግንዛቤውና ፍላጎቱ ጨምሯል፡፡ የተጠቃሚው ቁጥር ከቦታ ቦታ ቢለያይም፣ ሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ አለ፡፡ በሌሎች ከተሞች ተጠቃሚው ከፍተኛ ቢሆንም፣ በገጠር አካባቢ ያለው ዝቅተኛ ነው፡፡ በክልል ደረጃ ሶማሌና አፋር አጠቃቀማቸው በንፅፅር ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ ደኅንነቱን የጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ከቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሲነፃፀር ተደራሽነቱ አነስተኛ ነው፡፡ በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማትም አይሰጥም፡፡ 55 በመቶ ጤና ተቋማት ናቸው የሚሰጡት፡፡ ሌሎቹ የሚፈለገው ግብዓትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ስላልተሟሉላቸው አገልግሎት አይሰጡም፡፡ የግል ጤና ተቋማት አብዛኛዎቹ ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የእርግዝና መቆጣጠሪያ አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ክፍተት ይታያል፡፡ ፖስት ፒልን ብቻ እንደ እርግዝና መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙ አሉ፡፡ እዚህ ላይ ማብራሪያ ቢሰጡን?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- ፖስትፒል ለድንገተኛ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የእርግዝና መከላከያ ነው፡፡ የተሠራውም በመደበኛነት እንደ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል አይደለም፡፡ ሲሠራ ተገዳም ይሁን ሳታስበው ግንኙነት የፈጸመች እንደሆነና ግንኙነቱ ወደ እርግዝና የሚያመራ ሆኖ እሷ ካልፈለገችው ግንኙነቱ በተደረገ በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወሰድ ነው የተሠራው፡፡ ውጤታማነቱም ከሌሎቹ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቶች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ እኛ አገር በብዛት ወጣቶች ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታ አንዳንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጭምር ሲያረግዙ እያየን፣ ስለቤተሰብ ዕቅድና ሥነ ተዋልዶ ጤና በትምህርት ቤት በአግባቡ አይሰጥም፣ ወላጆችም ልጆችን አያስተምሩም፣ አያስገነዝቡም፡፡ ተማሪዎችም ግንዛቤ የላቸውም፡፡ ስለ ሥነ ተዋልዶ አካላት ዕድገት ማውራትም ለአገራችን ነውር ነው፡፡ በመሆኑም ብዙ ጊዜ ከጓደኛቸው ተነስተው፣ ተማክረውና ተገፋፍተው ወይም ተሳስተው ነው ግንኙነት የሚያደርጉትና ፖስት ፒል የሚጠቀሙት፡፡ ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ስለ ውጤታማነቱም አለማወቅ አለ፡፡ አንዲት ሴት ግንኙነት እንደምታደርግና እንደምትቀጥልበት ካወቀች እንዲሁም እርግዝና የማትፈልግ ከሆነ ፖስት ፒል ሳይሆን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መጠቀም አለባት፡፡ አንዲት ሴት የትኛውን መጠቀም እንዳለባት ለመለየት ከጤና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ማድረግ አለባት፡፡

ሪፖርተር፡- የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት የዕድሜ መነሻ አለ?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- በእኛ አገር ሕግ ሴት ግንኙነት ማድረግ ያለባት ከ18 ዓመቷ በኋላ ነው፡፡ ከዚህ በታች ከሆነና እሷ ፈቃደኛ ብትሆን እንኳ፣ ከሷ ጋር ግንኙነት ያደረገው ሰው ተጠያቂ ነው፡፡ ፈቅዳ ነው፣ ተስማምታ ነው ቢባል እንኳን አይፈቀድም፡፡ በተግባር ግን ከዚህ በታች ያሉት ታዳጊዎች ግንኙነት እያደረጉ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች አርግዘው እየመጡ ነው፡፡ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቱ የዕድሜ ገደብ ባይኖረውም፣ የጤና ባለሙያዎች የሴቷን ዕድሜና ልጀነት ዓይተው ለምን ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከቁጥጥሯ ውጭ ሆኖ ያለ ዕድሜዋ ከምታረግዝ ቀድሞ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ የሚመጣባት ችግር የለም፡፡ ይህን ሳትጠቀም ግንኙነት በማድረጓ ነው ውስብስብ ችግር ውስጥ የምትገባው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ጋዜጠኛ የተከለከለበት ውይይት አድርጋችሁ ነበር፡፡ ጭብጡ ምን ነበር?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አሠርታት ያስመዘገበቻቸውን ግቦች በተለይ ከፅንስ ማቋረጥ ጋር ተያይዞ የወጣው ሕግ እንዴት የሴቶችን ሕይወት እንደለወጠ፣ በሴቶች ሞት ቅነሳ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ አስገንዝበናል፡፡ ከሚሞቱ ከሦስት ሴቶች አንዷ የምትሞተው ደኅንነቱ ካልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት ጋር ነበር፡፡ ይህ ሕጉ ከተቀየረና አገልግሎቱ እንዲሰፋ ከተደረገ በኋላ የሞት ምጣኔው ከነበረበት 32 በመቶ ወደ አራት በመቶ መቀነሱን አስረድተናል፡፡ ደኅንነቱ ካልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ 60 በመቶ አልጋ ይዘው ይታከሙ የነበሩ ሴቶችን በርካታ ሥራዎች ተሠርተው አሁን ላይ ማስቀረት መቻላችን በወቅቱ ለነበሩና ታሪኩን ለሚያውቁት ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው ትውልድ ያለፍንበትን አይረዳውም፡፡ አዳዲስ የጤና ባለሙያዎች የአሁኑን እንጂ የድሮውን አያውቁም፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ያለውን የአራት በመቶ የሴቶች ሞት እንደ ችግር ላይቆጥሩት ይችላሉ፡፡ በዚህም ለሥነ ተዋልዶ ጤናና ለቤተሰብ ዕቅድ የሚሰጠውን አገልግሎት ችላ ሊሉት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ረዥም ርቀት ተጉዘን ያመጣነው ለውጥ እንዳይቀለበስ መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡ ሕጉን መጠበቅ ያስፈልጋል፣ ተደራሽነቱን ማጠናከርና አራት በመቶውን ሞት ቀድሞ በመከላከል መታደግ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በጅምላ የሚቃወሙ አሉ፡፡ በተለይ ፅንስ መቋረጥን እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅመው ሌሎችንም የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች የሚቃወሙ አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከተቀመጠ ሕግ ውጭ ባይሠራም፣ የተሳሳተ፣ ያልተባለና በኢትዮጵያ ሕግ ከሚተገበረው የሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር ያልተያያዘ አጀንዳ እያነሱ ሰዎችን ያሳስታሉ፡፡ ውይይቱ የሚያነሱት ጉዳይ ለሴቻችን የሚጠቅም እንዳልሆነ፣ የፓርላማ አባላቱም መረጃ እንዲያገኙና እንዲገነዘቡ የተደረገበት ነው፡፡ እኛ በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ያለውን እውነታ ካላስጨበጥን ወደ ተሳሳተ ውሳኔ ይኬዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥነ ተዋልዶ ጤና ሲነሳ አሁንም የተዛቡ አመለካከቶች አሉ፡፡ ለምንድነው?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- የሥነ ተዋልዶ ጤና በኢትዮጵያ ብዙ ምዕራፍ ተጉዟል ማለት እችላለሁ፡፡ ውጤትም አምጥተናል፡፡ በአጭር ጊዜ ለውጥ ካመጡ አገሮችም ኢትዮጵያ በሞዴልነት ትጠቀሳለች፡፡ ሌሎች አገሮችም ከእኛ ልምድ ወስደዋል፡፡ ይህ ሲደረግ ግን መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ፣ የቀድሞ ጤና ሚኒስትሮች ቴዎድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር)፣ ከሰተብርሃን አድማሱ (ዶ/ር) እና ሊያ ከበደ (ዶ/ር) ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ከፍተኛ ለውጥም ተመዝግቧል፣ ይህ መቀጠል አለበት፡፡ የሥነ ተዋልዶ ጤና አጠባበቅን በእጅጉ የሚቃወሙት የወንድን የበላይነት የሚያቀነቅኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች በአገራቸው ቴክኖሎጂው ቀድሟቸው ሲሄድ ዓይናቸውን አፍሪካና ዓረብ አገሮች ላይ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ አሁን ያገኘነውን ውጤት እንዳናጣ መሥራት አለብን፡፡ የሚዲያውም ሚና ቀላል አይደለምና ከጤና ባለሙያውና ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መሠራት አለበት፡፡ አይፓስም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሕግና ደንብ መሠረት አድርጎ ሴቶችን በሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ማጣት ከሚመጣ ሞት ለመታደግ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጦርነትና ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች የሥነ ተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ዕቅድ ፕሮግራሙ እንዴት እየሄደ ነው?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- ጦርነት ባለበት ጊዜ የጤና አገልግሎቱ፣ ትራንስፖርቱ፣ ሁሉ ነገር ነው የሚስተጓጎለው፡፡ ከዚህ በበለጠ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ማኅበራዊ ጥበቃ ይበጣጠሳል፡፡ ሴቶችን የሚጠብቀው የማኅበረሰብ እሴት በጦርነት ጊዜ አይኖርም፡፡ ሴቶች ላልተፈለገ ግንኙነት ይጋለጣሉ፡፡ አስገድዶ መድፈር የተለመደ ነው፡፡ ያልተፈለገ እርግዝና ቢያጋጥማቸውም አገልግሎት የሚያገኙበት የለም፡፡ እኛ ጦርነቱ ጋብ ሲል ያደረግነው የተጎዱ ሴቶችን ፈልገን የሥነ ልቦና ድጋፍና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ የፈራረሱ ጤና ተቋማት ባሉበት በድንኳንና ከፈራረሰው ክፍል ደህና በሆነው መሠረታዊ ጤና ተደራሽ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ከጤና ቢሮዎች ጋር በተመባበር በተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎቱን ለመስጠት ሞክረናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከሃይማኖት አባቶች ጋር ሠርታችኋል?

ደመቀ (ዶ/ር)፡- ጦርነት ብቻ ሳይሆን ድርቅ በተከሰተበት አካባቢ ፆታዊ ጥቃቱ፣ አስገድዶ መድፈሩ የተለመደ ሰዋዊ ቀውስ ነው፡፡ ይህንን ለመቀልበስ የሃይማኖት አባቶችና ተሰሚነት ያላቸው የአካባቢ ሽማግሌዎች እንዲያስተምሩ ነው የሠራነው፡፡ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች እንዳይገለሉ፣ በድጋሚ አስገድዶ መድፈርም ሆነ ጥቃት ሴቶች ላይ እንዳይፈጸም ከመንግሥት ተቋማት በመቀናጀት እንዲከላከሉና እንዲያስተምሩ ሠርተናል፡፡ የመንግሥት መዋቅር በተናጋበት አካባቢ የእነሱ ሚና ጉልህ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...