Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጠ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጠ

ቀን:

  • ፍሬወይኒ ኃይሉ በ5000 ሜትር በቀጥታ እንድትወዳደር ተወስኗል

የፓሪስ ኦሊምፒክ ሊጀመር 16 ቀናት ብቻ ቀርቶታል፡፡ አገሮች የመጨረሻ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምትወዳደርበት በአትሌቲክሱ በመካከለኛና ረዥም ርቀትና ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች የተመረጡትን አትሌቶች ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጎ ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ልኳል፡፡

ይሁን እንጂ በምርጫው ደስተኛ ያልሆኑ አትሌቶች ቅሬታቸውን ለሚመለከተው አካል በማቅረባቸው ጉዳዩ ዳግም እንዲታይ ተደርጓል፡፡

ቅሬታ ካቀረቡት መካከል ፍሬወይኒ ኃይሉ በ5000 ሜትር በተጠባባቂነት መያዟን በመቃወም ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያቀረበችው አቤቱታ ተቀባይነት ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በማርዮት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጎታል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ከፓሪስ ኦሊምፒክ አትሌቶች ምርጫ ባሻገር፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቅርቡ ካደረገው ፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ እንዲሁም ከኦዲት ጋር ተያይዞ አመራሮቹ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአትሌቶች ምርጫ

በቅድሚያ የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ብሔራዊ አትሌቶች ምርጫ አስመልክቶ በተሰጠው ማብራሪያ፣ የአትሌቶች ውጤት መቀራረብ ምርጫውን በተወሰነ መልኩ አስቸጋሪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

 በኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) አገላለጽ፣ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የአትሌቶች ውጤት መቀራረብ ኢትዮጵያን እንደ አገር ዕድለኛ አድርጓታል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሁሉም አትሌቶች የኦሊምፒክ ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ካላቸው ጉጉት የተነሳ የቱንም ያህል መሥፈርት ቢቀመጥ፣ የቱን ትተን የቱን እንምረጥ የሚለው ጉዳይ ህሊናን ሳይቀር የሚፈታተን ጉዳይ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እስከ ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን እኩለ ሌሊት ድረስ የተቀመጠውን መሥፈርት በጥልቀት በመመልከት፣ በአትሌቶች በተለይም በፍሬሕይወት ኃይሉ፣ በታምራት ቶላ፣ በጽጌ ገብረ ሰላማና ሌሎችም ሲቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎች ተመልክቷል፡፡ አትሌቶቹ ወቅታዊ አቋማቸው ምን እንደሚመስል ታይቶና ተገምግሞ የመጨረሻ ውሳኔ መሰጠቱን ተነግሯል፡፡

በዚሁ መሠረት በተለይም እንደ እነ ጉዳፍ ፀጋይ የመሳሰሉ በሦስት ርቀት መወዳደር የሚያስችል ብቁ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳይ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ በ5000 ሜትር በቀጥታ እንድትወዳደር ተወስኗል፡፡

ሌሎቹ ቅሬታዎች አትሌቶቹ ወደ ፓሪስ አቅንተው በቅድሚያ በሚያደርጓቸው ውድድሮች፣ ወቅታዊ ብቃታቸው ተገምግሞ ለተጨማሪ የውድድር ዓይነት የሚመጥን ብቃት አላቸው የላቸውም የሚለው እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡

በተጠባባቂነት የተያዙት አትሌቶች በተመለከተም፣ አትሌቱ ተጠባባቂ ሆነ ማለት ከውድድር ውጪ ሆነ ማለት አይደለም በሚለው ከስምምነት መደረሱን የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢልልኝ መቆያ አብራርተዋል፡፡ የጽጌ ገብረ ሰላማ ቅሬታን በተመለከተ አቶ ቢልልኝ፣ አትሌቷ ባላት ወቅታዊ አቋም መሠረት በ10,000 ሜትር ብቻ እንድትወዳር መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

የኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ምርጫ

ከኦሊምፒክ ምርጫ ጋር ተያይዞ ምርጫው ከመደረጉ ከአንድ ወር በፊት የምርጫው ዝርዝር ጉዳይ፣ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ለክልል ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች ሰነዱ እንዲላክላቸው መደረጉን፣ ሰነዱን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀው የምርጫ መመርያ በጉባዔው አባላት አማካይነት ተገምግሞ ከፀደቀ በኋላ ምርጫው ተደርጓል ብለዋል አመራሮቹ፡፡

ምርጫው መደረግ የነበረበት ከኦሊምፒክ በኋላ እንጂ ከኦሊምፒክ በፊት አልነበረም ስለሚባለው ጉዳይ ፕሬዚዳንቱ፣ ከኦሊምፒክ በፊት እንዲሆን ያደረገው ተከስቶ የነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የምርጫው ጊዜ እንዲዛባ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ምርጫውን አስመልክቶ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ  ምርጫው ከመደረጉ በፊት የምርጫ መመርያ እየተዘጋጀ ስለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ  የሚያደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የተሟላ መረጃ ያለው ስለመሆኑ ጭምር አብራርተዋል፡፡

ከምርጫ ጊዜ ጋር ተያይዞ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) እንደማይመለከተው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ሉዓላዊ አገሮች በፈለጉት ጊዜና ሁኔታ ማከናወን እንደሚችሉ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ኦዲት 

ከኦዲት ሪፖርት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሕጋዊ ተቋም እስከሆነ ድረስ ኦዲት አልተደረገም የሚባልበት ሁኔታ በፍጹም ሊኖር እንደማይችል፣ ነገር ግን ብሔራዊ ተቋሙ ከመንግሥት በጀት የሌለው በመሆኑ ከመንግሥት፣ ከአይኦሲና ከሌሎችም አካላት የሚደረጉለት የገንዘብ ድጎማዎች የሚገቡት በአንድ አካውንት በመሆኑ ምክንያት፣ ሁኔታው ለኦዲተሮች አሠራር አመቺ አልሆነም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አሁንም ሆነ ወደፊት ኦዲት ለመደረግ ዝግጁ መሆኑም ተናግረዋል፡፡

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን በተመለከተ

የሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጉዳይ በተመለከተም ‹‹ኃይሌ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክም ሆነ ለኢትዮጵያ ስፖርት ትልቅ የድል አሻራ ነው፡፡ ኃይሌ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ከጎናችን እንዲቆም፣ ብሔራዊ አትሌቶቻችን እንዲያበረታታልን እንፈልጋለን፣ የቁርጥ ቀን ጀግናችን ነው፣ የእሱን አብሮነት አጥብቀን እንፈልገዋለን፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ክፍተቱም ሆነ ጥንካሬው እንዳለ ሆኖ፣ የፓሪስ ኦሊምፒክ ካለፈ በኋላ ሁሉንም ነገር ወደ መድረክ አውጥቶ ለአገሪቱ ስፖርት በሚበጅ መልኩ ችግር እንኳ ቢኖር ይፋ ቢያደርገው ምንኛ ደስ ባለን ነበር በማለት ነው ያብራሩት፡፡ አሁንም ወደ አትሌቶቻን በመቅረብ እንዲያበረታታቸው እንፈልጋለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሕግ የማስከበሩን ጉዳይ ግን በፈለገው መንገድ እንዲገፋበት ሙሉ ነፃነት አለው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...