Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይትን ለመቆጣጠር ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ ጣለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የፖሊሲ ማዕቀፍ ያሸጋግረኛል ያለውን አዲስ የገንዘብ ፖሊሲ ይፋ አደረገ፡፡ የገንዘብ ፖሊሲው በዋናነት  በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይትን በመቆጣጠር የዋጋ ንረትን ለመከላከል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለማሸጋገርና ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚተገብራቸውን ሥልቶች ይፋ አድርጓል፡፡ ከነዚህም መካከል የመጀመርያውና ዋናው አጠቃላይ የገንዘብና የብድር ሁኔታዎችን ለመወሰን የሚረዳ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ (National Bank Rate) ወይም የፖሊሲ ተመን (Policy Rate) የሚተገብር መሆኑ ነው፡፡ ይህ ፖሊሲ ነክ የወለድ መጣኔ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ሁኔታን በማየት እንደሁኔታው ከፍ ወይም ዝቅ ሊል እንደሚችል ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ግን የፖሊሲ ነክ የወለድ 15 በመቶ እንደሚሆን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ 15 በመቶ የወለድ ምጣኔ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ማለትም እየቀነሰ ያለውን፣ ነገር ግን አሁንም ከፍ ብሎ የሚታየውን የዋጋ ንረት፣ ዝቅተኛ የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገትና ካለፉት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ የመጣውን የባንክ ብድር ዕድገት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ መጣኔ በአሁኑ ጊዜ ባንኮች እርስ በርስ በሚበዳደሩት ብድር ላይ ከሚከፍሉት ወለድ ጋር የተቀራረበ ነገር ግን ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጧቸው ብድሮች ላይ ከሚያስከፍሉት  ከ16 እስከ 20 በመቶ ከሚደርስ ወለድ ያነሰ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ 

ይህ የፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይትን ብቻ እንደሚመለከት ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ይህ ፖሊሲ ነክ የወለድ መጣኔ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ ተመን እንደማይመለከት አስረድቷል። በመሆኑም አለመሆኑን ባንኮች በውድድር ላይ ተመሥርተው ለደንበኞቻቸው በሚሰጡት ብድር ላይ የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን በራሳቸው መወሰናቸውን ይቀጥላሉ ብሏል፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ባንኮች በቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ዝቅተኛው የሰባት በመቶ ወለድ በዚህ በብሔራዊ ባንክ የብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ ምክንያት ለውጥ የማይደረግበት መሆኑን ገልጿል፡፡ 

ስለሆነም የፖሊሲ ነክ የገንዘብ ምጣኔው በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት ወይም እርስ በርስ በሚበዳደሩበት ጊዜ የሚያስከፍሉትን ወለድ አማካይ ምጣኔ ለመወሰን ያለመ ነው። 

ይህንንም ለማስፈጸምና ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ጨረታዎችን በየሁለት ሳምንቱ እንደሚያካሂድ ገልጿል። የዚህ ጨረታ ዓላማም፣ ባንኮች እርስ በእርስ በሚያደርጉት ግብይት ላይ የሚያስከፍሉት የወለድ መጠን ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው 15 በመቶ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ እንዳይቀንስ ወይም እንዳይጨምር ለማረጋገጥና ለመቆጣጠር ነው።

የሚደረጉት ብሔራዊ ባንኩ ከወቅታዊ ሁኔታዎች በመነሳት ከባንክ ሥርዓቱ ውስጥ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ እንዲያስችለው ነው፡፡ እነዚህ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ጋር የሚያደርጋቸው ጨረታዎች በዋናነት የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የፖሊሲ ነክ የወለድ መጣኔ እምብዛም የተራራቀ አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ናቸው ብሏል፡፡

በዚህም መሠረት በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያላግባብ የተከማቸ የገንዘብ መጠን ኖሮ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ ተመኑን ከማዕከላዊ ባንኩ ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ በእጅጉ እንዲቀንስ የሚያደርግ ከሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ ጨረታ በማውጣት በባንክ ሥርዓቱ ውስጥ የተካማቸውን ትርፍ ገንዘብ የሚሰበስብ ይሆናል። በተመሳሳይ፣ በአጠቃላይ የባንክ ሥርዓት ውስጥ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥምና የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ ተመን ከማዕከላዊ ባንኩ የፖሊሲ ተመን ከፍ ያለ እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ተጨማሪ ገንዘብ ለማቅረብ ይህንኑ ጨረታ እንደሚጠቀም አስታውቋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ይፋ በተደረገው አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የአንድ ቀን የብድር አገልግሎት (Overnight Lending Facility) እና የአንድ ቀን የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት (Overnight Deposit Facility) የሚሰጥ ሲሆን፣ እነዚህ የአንድ ቀን የብድር ወይም የተቀማጭ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ምክንያት ባንኮች የአጭር ጊዜ የገንዘብ ፍሰት አቋማቸውን ለማስተካከል እንዲረዳቸው መሆኑን አስታውቋል። ለእነዚህ የአንድ ቀን የብድርና ተቀማጭ ገንዘብ የማቅረብ  አገልግሎቶችን የሚሰጠውም ከብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን ሦስት በመቶ በማስበለጥ ወይም በማሳነስ እንደሚሆን ይኸው ትናንት የወጣው የባንኩ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ አመልክቷል፡፡ 

ባንኩ አዲሱን ፖሊሲ ለማስፈጸም ባንክ ባንኮች እርስ በርስ የሚበዳደሩበትን የተነቃቃ የገንዘብ ገበያ ለመመሥረት የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት አልምቶ መጨረሱንና በቅርቡም ወደ ሥራ እንደሚያስገባ አስታውቋል። ይህ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት በሚገባ ሥራ ላይ ሲውል ትርፍ ገንዘብ ያላቸው ባንኮች የገንዘብ እጥረት ላጋጠማቸው ባንኮች ለማበደር ወይም ለመገበያየት የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ በባንኮች መካከል የሚደረግ የገንዘብ ግብይት ወይም እርስ በርስ መበዳደር በምን ያህል የወለድ ምጣኔ እንደፈጸመ በቀላሉ ለማወቅ ያስችለዋል። በመሆኑም የባንኮች የእርስ በእርስ የገንዘብ ግብይት የወለድ መጠን፣ ከማዕከላዊ ባንኩ የፖሊሲ ነከ የወለድ መጣኔ ጋር የሚቀራረብ መሆኑን ለመከታተል፣ ይህ ካልሆነ ግን ብሔራዊ ባንኩ ሁኔታውን ለማስተካከል ከባንኮች ጋር የግብይት ጨረታን ለመወጠቀም ውሰኔ እንዲያስልፍ እንደሚረዳው አስታውቋል።

በአዲሱ ፖሊሲ መሠራት ይተገበራል ብሎ ያስቀመጠው ስድስተኛ ነጥብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ቢሸጋገርም፣ በሽግግሩ ወቅት ቀደም ሲል ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቀጥታ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች በጊዜያዊነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚቀጥሉ መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማስተላለፊያ ዘዴዎች ከተጠበቀው በላይ ዝግ ያሉ ከሆኑ፣ ብሔራዊ ባንክ ነባሮቹን ቀጥተኛ የፖሊሲ መሣሪያዎች በተጨማሪነት እንደሚጠቀምባቸውና ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደፊት የሚሰጥበት ስለመሆኑ ጠቅሷል፡፡ ይህንን ገንዘብ ፖሊሲ ለውጥ ባንኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘመንና አሠራሩን ከዓለም ማዕከላዊ ባንኮች መልካም ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣም ረገድ ፋይዳ ያለው ታሪካዊ ዕርምጃ እንደሆነም ገልጿል፡፡ የባንኩን ፖሊሲ ነክ የወለድ ምጣኔ መወሰን፣ ከባንኮች ጋር የግብይት ጨረታ መጀመር፣ የአንድ ቀን የብድርና የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግና የባንክ ለባንክ የገበያ ሥርዓት ማዘጋጀት ብሔራዊ ባንኩ በስትራቴጂአዊ ዕቅዱና በባንኩ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በአግባቡ ለመወጣት እጅግ አስፈላጊ ዕርምጃዎች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ 

‹‹ከዚህ በተጨማሪ፣ ትናንት ይፋ የተደረጉት ለውጦች በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፍ የሚታዩ አንዳንድ ሥር የሰደዱ ድክመቶችን ለማስወገድ እንደሚረዱ ብሔራዊ ባንኩ በፅኑ ያምናል፤›› የሚለው የባንኩ መግለጫ ስለሆነም፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዚህ ለአዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ይተባሩ ዘንድ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዋናነት ዝቀተኛና የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህም ከባንኩ የመካከለኛ ዘመን ስትራቴጂአዊ ዕቅዶች መካከል ቀዳሚው ሲሆን፣ ይህንኑ ለማሳካት ባንኩ ሰፊ ሕጋዊ፣ ተቋማዊና ቴክኒካዊ ዝግጅቶችን አድርጓል፡፡ በተለይም የባንኩ ቀዳሚ ዓላማ ዋጋን ማረጋጋት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከዘመናዊ የማዕከላዊ ባንክ አሠራርና ከፈጣን በገበያ ላይ ከተመሠረተ የፋይናንስ ሥርዓት ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን ለመተግበር የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የዝግጅት ሥራዎች በአብዛኛው የተጠናቀቁ በመሆናቸው ብሔራዊ ባንኩ ከሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ባንኮችና ግለሰብ ተበዳሪዎች በዚህ የገንዘብ ፖሊሲ እንደሚጎዱ፣ ነገር ግን አጠቃላይ ውጤቱ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባ ገንዘብ መጠንን በመቀነስ የዋጋ ንረትን እንደሚያዳክም አስረድተዋል። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፣ በዚህ የገንዘብ ፖሊሲ ተፅዕኖ ምክንያት ባንኮች ለግለሰብ የሚያበድሩበትን የወለድ መጠን ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ፣ ይህ ደግሞ ተበዳሪዎችን እንደሚያሸሽ በአጠቃላይ ውጤቱ ግን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንደሚጠቅም አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች