Tuesday, July 23, 2024

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡ በአንድ በኩል የልማት ዕቅዶች በስፋት ተዘርግተው ክንውኖቻቸው ሚዲያዎችን ሲያጣብቡ በሌላ በኩል ከግጭት፣ ከግድያ፣ ከማፈናቀልና ከዕገታ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሥጋቱን ያንሩታል፡፡ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከሚካሄዱ ግጭቶች በተጨማሪ፣ በንፁኃን ዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ዕገታዎች ወደ አደገኛ ሁኔታ እየተሸጋገሩ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተገታ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ባለመቆማቸው፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዕገታዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ውስብስብ ችግሮችን እየፈጠሩ ነው፡፡ ሰሞኑን በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ዕገታ በብዙዎች ዘንድ መረር ያለ ስሜት ነው የፈጠረው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት የሚጠቀመው ማን ነው የሚለው ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡   

የሰላምና የፀጥታ ዕጦት በተደጋጋሚ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ነገር ግን ‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን› እንዳለችው እንስሳ ለዘለቄታዊ ሰላም ትልቅ ሥፍራ መስጠት ይገባል፡፡ ኢንቨስተርም ሆነ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ሲያቅዱ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ሰላም ነው፡፡ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት የሚያስፈልጋቸው ትልቁ ነገር ሰላማዊና የተረጋጋ ከባቢ ነው፡፡ መቋጫ ባጣ ጦርነትና በየአካባቢው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች የሚከሰቱ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ውድመቶች፣ ዕገታዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ፀር ናቸው፡፡ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በሰጥቶ መቀበል መርህ በመሆኑ፣ የግጭት ተዋናዮች በሙሉ ከኃይል ይልቅ ሕጋዊና ሰላማዊ ድርድሮች ላይ የሚያተኩሩበት ዓውድ መፈጠር አለበት፡፡ በጉልበት የተሄደበት ርቀት ከደም መፋሰስና ከውድመት ውጪ ፋይዳ ከሌለው፣ ማንም ማንንም ማሸነፍ ወይም ማንም በማንም መሸነፍ እንደማይችል ታይቷል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሰከን ብሎ በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር ዕድሉ ይሰጥ፡፡

ዜጎች ለኮሪደር ልማት ከመኖሪያቸው እንዲነሱ ሲታሰብ በሚገባ መክረውበትና አምነውበት መሆኑ የሚጠቅመው፣ የልማት አጀንዳው ባለቤት ሕዝብ እንደሆነ ለማሳየት ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን ድንገት እንደ ደራሽ ውኃ በሁለትና በሦስት ቀናት እንዲነሱ ሲወሰንባቸውና የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ሲያጡ፣ ከባለቤትነት ስሜት ይልቅ ባዕድነት እየተሰማቸው ቅሬታዎች ይከማቻሉ፡፡ ቅሬታዎች ሲከማቹ ደግሞ ለተቃውሞ፣ ለነውጥና ለሁከት የሚዳርጉ ክስተቶች ያጋጥማሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በፒያሳ አካባቢ የተደረገው ነዋሪዎችን ከአንድ አካባቢ አንስቶ ወደ ሌላ ሥፍራ የማዛወር አሠራር ተጠናክሮ መቀጠል ሲገባው፣ ዘመቻ በሚመስል ሁኔታ በሌሎች ሥፍራዎች ውክቢያ መፍጠሩ ብዙዎችን አስከፍቷል፡፡ አሁንም ችግሩን በማመን ስህተቶችን አርሞ የነዋሪዎችን መብት፣ ክብር፣ ጥቅምና ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አሠራር መተግበር ጠቃሚ ነው፡፡ አገርና ሕዝብ ተረጋግተው ሕይወትን መቀጠል የሚቻለው፣ ሕግና ሥርዓት የሁሉም ነገር ልጥና ማሰሪያ ሲሆን ነው፡፡

መንግሥት የዘንድሮን በጀት በፓርላማ ሲያፀድቅ በአፅንኦት ማሳሰቢያ የተሰጠው ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል ነው፡፡ የአንድ ደሃ አገር በጀት አብዛኛው የሚገኘው ከየት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያም ትልቁ ገቢ ከግብርና ከቀረጥ፣ እንዲሁም ታክስ ካልሆኑ ሌሎች ምንጮች ነው፡፡ ይህንን በከፍተኛ ልፋት የሚገኝ ሀብት ከዘራፊዎች ከመከላከል በተጨማሪ፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አገራዊ ጉዳዮች የማዋል ጉዳይም ብርቱ ጥረት ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የዋጋ ግሽበቱን ሊያረጋጉ የሚችሉ የፖሊሲ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ዜጎች እንደ መርግ የከበደውን የኑሮ ውድነት ተቋቁመው ሕይወታቸውን በአግባቡ የሚመሩት፣ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች በአግባቡ እንዲሟሉ ጥረት ሲደረግ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ጥቅል ብሔራዊ ምርቱ ላይ እየተተኮረ ሌላው ሥራ አይረሳ፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገሮችን ጥቅል ብሔራዊ ምርት የሚበልጥ ኢኮኖሚ አላት ተብሎ ሲገለጽ፣ እግረ መንገዱንም ይህ ኢኮኖሚ ከሕዝብ ብዛትና ከነፍስ ወከፍ ገቢ አኳያ ሲተነተን በጣም ብዙ ርቀት የሚያስኬዱ ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከጂቡቲም ሆነ ከኬንያ ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር የኢትዮጵያ ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲተያይም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ሰላም ብታገኝ ካሏት የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ከሕዝብ ብዛቷና ካለችበት ስትራቴጂካዊ ሥፍራ አኳያ ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለገበያ መዳረሻነት ተመራጭ አገር መሆን አያቅታትም፡፡ እነዚህን የመሰሉ ዕድሎች ያላት አገር ሰላም እንድትሆን የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚስቡ የታክስና የኢንቨስትመንት ሕጎች፣ ሊያሠሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከዝርክርክነትና ከሌብነት የፀዳ ቢሮክራሲም የግድ መሆን አለበት፡፡

ሌላው ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር ስሟ መነሳት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ እያደር መሻሻል ያሳያል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ ጉዳይ ግን አሁንም የጠራ ነገር አይታይበትም፡፡ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች አሳዛኝ ናቸው፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነውና በበርካቶች ዘንድ በአዎንታዊ ተግባራቱ ስሙ የሚጠራው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች ያወጣቸው ሪፖርቶች ትኩረት ስለተነፈጋቸው በርካታ ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ ሪፖርቶቹ ትኩረት ተሰጥቷቸው ቢሠራባቸው ኖሮ በርካታ ችግሮች ይቀረፉ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፍላጎቶች ካላቸው ወገኖች ጭምር የጥላቻ ናዳ ሲወርድበት ማየት ያሳዝናል፡፡ በአጠቃላይ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ መገንዘብ ያለባቸው፣ ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...