Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና ተሟጋቾች ጥበቃና ከለላ የሚያደርግላቸው ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ

የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና ተሟጋቾች ጥበቃና ከለላ የሚያደርግላቸው ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ

ቀን:

  • ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነት ብትፈርምም ወደ ግ መቀር አልቻለችም ተብሏል

ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅቶችና ተሟጋቾች፣ ለሥራቸው ጥበቃና ከለላ የሚያገኙበት ሕግ እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡

በርካታ አገሮች የፈረሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ለሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ያወጣውን  ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችውም ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በአገር ውስጥ ወደ ሕግ ተቀይሮ ተግባራዊ ባለመደረጉ፣ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማትና ተሟጋቾች ከሥጋት ነፃ ሆነው እንዳይሠሩ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ አመሐ መኮንን፣ በኢትዮጵያ ያለው ሕግ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችና ተሟጋቾች በነፃነት ይሠራሉ ከሚል ድንጋጌ ውጭ በሥራቸው ሳይፈሩ፣ ሳይሸማቀቁና አደጋ ሳይደርስባቸው እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ሕግ አለመኖሩን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ይህ የሕግ ከለላ በሌሎች አገሮች የተለመደ አሠርራ መሆኑን የተናገሩት አቶ አመሐ ለመብት ተሟጋቾች ጥበቃ የሚያደርግ ሕግ ከማውጣት ባለፈ መንግሥት በአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች እንዲስፋፉ፣ እንዲከበሩና ለተቆርቋሪ አካላት ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ተቋማቱ በቀላሉ ቢሮዎችና የሀብት ምንጭ የሚያገኙበት ዕድል በሕግ ሊመቻች እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም በአገር አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ ረገድ ተቆርቋሪ አካላት ለሚሠሩት ሥራ ዕውቅና በመስጠት የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ለመነሻ የሚሆን ረቂቅ የሕግ ሞዴል ቀርቦ ለውይይት መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የሲቪክ ማኅበረሰቦች እንዴት ይመዘገባሉ? እንዴት ይተዳደራሉ? የሚለው በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሕግ ውስጥ ድንጋጌ ቢኖርም፣ የሰብዓዊ መብቶች ተመዝግበው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ሕግ እንደሌለ ተገልጿል፡፡  

የተዘጋጀውን ሞዴል ሕግ ካረቀቁት መካከል በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የቦርድ አባል ወ/ሮ ተጓዳ አለባቸው ይገኙበታል፡፡

ወ/ሮ ተጓዳ እንደገለጹት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መቆም በራሱ ሥራው አደጋ ያለውና ራሳቸው የመብት ተሟጋቾችን ለሌላ የመብት ጥሰት  ያጋልጣል። ነገር ግን መንግሥት ምንም እንኳ የሰብዓዊ መብትን የመጠበቅና የማስጠበቅ የመንግሥት ግዴታ ቢኖርበትም፣ ኃላፊነቱን መንግሥት ላይ ብቻ የምትጥለውና የሚቻል ባለመሆኑ፣ የተቆረቋሪ አካላት መኖር በጣም አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ መንግሥት አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ቢኖሩበትም፣ በሒደቱ የፖለቲካ ፍላጎቶች ስለሚኖሩ ግዴታውን ይወጣል ብለው እንደማያስቡ ይናገራሉ። የመብት ጥሰቱ አንድም በራሱ በመንግሥት ወይም በሌሎች አካላት የሚፈጸም በመሆኑ፣ ሥራው ለመንግሥት የሚጣል ብቻ ስላልሆነ በዚህ ሒደት የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅቶችና ተሟጋቾች ሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃም ያለው ልምድና በተመድ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችና ተማጋቾች ለዜጎች መብቶች መጠበቅ የሰጠው ሚና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አክለው ገልጸዋል። በአደጉ አገሮች ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ በሚረዳ መንገድ የዘረጉት ሥርዓት በራሱ የሚሠራ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ገና ብዙ መንገድ በሚቀራቸው፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባላደገባቸው አገሮች የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅቶችና ተሟጋቾች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጓዳ  ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቆርቋሪ አካላት ሥራቸውን እንዲሠሩ ዕውቅና መስጠትና በሚሠሩበት ወቅት ላልተገባ ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥበቃ የሚያደርግና ከለላ የሚሰጥ ሕግ መኖሩ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ሕጉ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ሕጉ ቢኖር በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)  ስለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የተናገሩት ነገር በዚህ ሕግ ሊመዘን ይችል እንደነበር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ መጠን እንደማይናገሩ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥታቸውን ዓመታዊ ሪፖርት ለማቅረብና ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ፣ ተቋምና አሠራርን መፈተሽ ያስፈልጋል በማለት፣ ‹‹እኛ ደመወዝ የማንከፍለው ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ወ/ሮ ተጓዳ እንደሚሉት የአገር መሪ በዚህ መጠን ንግግር ሲያደርጉ በታችኛው የመንግሥት አካላትም ሆነ በሌሎች ዘንድ እንደ ሥራ አቅጣጫ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ አካላት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ጫና ከማሳደር ባለፈ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ አሉታዊ የሆነ ዕይታ ይፈጥራል፡፡ ንግግሩ በሰብዓዊ መብቶች ሥራ ላይ ትልቅ ጫና በመፍጠር ሥራቸውን ሊጎትተው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የፈረመው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ተቆረቋሪ ድርጅቶችና ተሟጋቾች ሕግ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን የጠየቁት ወ/ሮ ተጓዳ፣ ለዚህ መነሻ እንዲሆን የተዘጋጀው ሞዴል ሕግ ከተመድ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር የተቃኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደፊት የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅቶችንና ተሟጋቾችን ነፃነት የሚያሳጣ ሕግ እንዳይወጣ ድርጅቶችና ተሟጋቾች ሊታገሉበት ይገባል ያሉት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ እንዲኖራት እየጠየቅን ያለነው በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችና ድርጅቶች ከለላ የሚሰጥ ሕግ እንዲወጣ ነው፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ ድርጅቶችንና አንድ ሰው ወይም ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት ሥራ ስላከናወነ ወይም ስለሰብዓዊ መብት በመናገሩ ብቻ፣ ገደብ ሊጣልበትና ጥቃት ሊደርስበት አይገባም የሚል ድንጋጌ የያዘ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችና ድርጀቶች የመብት ጥሰት ላይ ምርመራ ሲያደርጉ ጥበቃ እንዲኖራቸው፣ በፍርድ ቤቶች ለሠራቸው የሚያስፈልጉ ጉዳዮች በፈለጉበት ጊዜ እንዲያገኙ እንዲሁም ከመንግሥት አካላት የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ የሚረዱ ሕግጋት ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

ተመድ ለሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ያወጣው ዓለም አቀፍ ከለላ የሚያደርገውን ሕግ አገሮች ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ ወደ አገራቸው በመውሰድ ወደ ሕግ ቀይረው ሥራ ላይ እንደሚያውሉት፣ በኢትዮጵያ ግን እስካሁን ሊፀድቅ አእንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት መንግሥት ሁሉንም ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና የመተግበር ዋና ኃላፊነት እዳለበት ያስገድዳል ሲሉም አክለዋል፡፡ በተጨማሪም ዜጎች እነዚህን መብቶችና ነፃነቶች በተግባር ማግኘታቸውን የመብቶች መጠበቅን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ዋስትናዎችን መስጠት እንዳለበት ተቀምጧል፡፡

አቶ ያሬድ ይህ ድንጋጌ ማዕቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማነው? ሥራው ምንድነው? ምን ዓይነት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል? በሚል የተደነገገ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥበቃ የሚሰጥ በመሆኑ እየጠየቅን ያለነው ይውጣልን የሚል ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሕግ ሥራ ላይ ሲውል በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሠሩ ጋዜጠኞችንም እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ወሳኝና አስፈላጊ የሆነውን የጥበቃና ከለላ ሕግ ኢትዮጵያ ስምምነቱን የፈረመች ቢሆንም፣ በስምምነቱ መነሻ ለድርጅቶችና ለተሟጋቾች በሚጠቅም መንገድ አለመውጣቱ በሥራቸው ላይ እንቅፋት ከመሆኑም በላይ ሥጋት እንዳሳደረባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡ ሕጉ መንግሥት ላይ ዕዳ የሚጥል በመሆኑና የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት መንግሥትን ይተቻሉ የሚል ዕሳቤ በመኖሩ መንግሥት በፈለገ ጊዜ ለማሰር፣ ለመፍታት ወይም ለማጉላላት እንዲመቸው ጥበቃ የሚያደርግ ሕግ አለመውጣቱን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ከድርጅቶችና ተሟጋቾች ጋር በመሆን የሚመለከታቸውንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን በመያዝ ምስክር በማድረግ፣ መንግሥት እንዲያስብበት የማድረግ ሥራ እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹በቅርቡ የተሰማው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ይባሱንም ሌላ ገዳቢ ሕግ ይውጣ የሚል ዓይነት ይመስላል፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ ‹‹እኛ ግን የምንፈልገው የሚቆነጥጥ ሕግ ብቻ ሳይሆን የሚጠብቀንና ከለላ የሚሰጠን ሕግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አስፈሪ ነው፤›› የሚሉት አቶ ያሬድ፣ ‹‹ጉዳዩ ከለውጡ በፊት ወደ ነበረው አፋኝ ሁኔታ እንዳይሄድ ሥጋት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...