Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ነዋሪዎች የከፋ ችግር ውስጥ ወድቀናል አሉ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ነዋሪዎች የከፋ ችግር ውስጥ ወድቀናል አሉ

ቀን:

  • የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ችግሩ ከቀጠለ አገልግሎት ያቆማል ተብሏል

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኃይል የሚያስተላልፈው የኤሌክትሪከ ተሸካሚ ምሰሶ ላይ ታጣቂዎች ጉዳት ካደረሱበት ጊዜ ጀምሮ፣ በክልሉ ሙሉ ለሙሉ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ ነዋሪዎች የከፋ ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናገሩ፡፡  

በምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ መስመር ላይ ታጣቂ ኃይሎች ጉዳት ከሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ አሶሳ ከተማን ጨምሮ በሁሉም አካባቢ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ፣ በክልሉ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉን ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ነዋሪዎች የከፋ ችግር ውስጥ ወድቀናል አሉ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ በሚገኘው የኤሌክትሪክ
ተሸካሚ ምሰሶ የደረሰው ጉዳት

በክልሉም የጤና ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ወፍጮ ቤቶች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማት ሥራ ማቆማቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን የክልሉ ነዋሪ ረዥም ርቀትን ተጉዘው በመሄድ በነዳጅ በሚሠራ ወፍጮ እያስፈጩ የዕለት ጉርሳቸውን እንደሚያዘጋጁ አክለው ገልጸዋል፡፡

ቀደም ብሎ በመተከልና በከማሺ ዞኖች ኤሌክትሪክ አለመኖሩን፣ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ኃይል ካገኙ ቢያንስ ሁለት ዓመታት ማስቆጠራቸውን፣ አሁንም በክልሉ ሙሉ ለሙሉ ኤሌክትሪክ ከተቋረጠ ሦስት ሳምንታትን ማስቆጠራቸውን አስረድተዋል፡፡

ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኃይል የሚያስተላልፈው የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶ ያለበት አካባቢ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ የሚበዛት ቦታ በመሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት አካባቢው ላይ ሄደው ጥገና ለማድረግ እንደሚቸገሩ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን እያገኙ አለመሆናቸውን፣ መንግሥት በክልሉ ያለውን ችግር በመረዳት አፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ ተቋማት ጄኔሬተር በመጠቀም አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ፣ ነገር ግን ነዋሪዎች ትልቅ ችግር ውስጥ መሆናቸውንና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደማያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ከአማራ ክልል በኩል የሚመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ከተቋረጠ ከሁለት ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን፣ እስካሁን በመተከል ዞን በሰባት ወረዳዎች ምንም ዓይነት ኃይል አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ ኤሌክትሪክ በመቋረጡ የተነሳ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ከዚህ በፊት በዚያው አካባቢ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶ ላይ በተደጋጋሚ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስቀጠል የፌዴራል መንግሥትን፣ የኦሮሚያንና የአማራን ክልሎች ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነዋሪዎች ዘላቂና አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ማግኘት የሚችሉት፣ ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል በመሳብ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኃይል እንዳይዳረስ አድርጎታል የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

በመተከል አካባቢ ኤሌክትሪክ ከጠፋ ረዥም ዓመታት ማስቆጠሩን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁኔታውን ተላምደውት በሶላርና በጄኔሬተር እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ‹‹ታጣቂ ቡድኖች ሆን ብለው በምዕራብ ወለጋ አካባቢ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎችን በመቁረጣቸው ኤሌክትሪክ ተቋርጧል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ አካባቢ በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት ችግር እንደሚታይና አሁን ምሰሶውን መልሶ ለማቋቋም ጊዜ ስለሚወስድ፣ በጊዜያዊነት በእንጨት ለማቆም ቡድን አዋቅሮ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

‹‹በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎችን በመቁረጥና በመፍታት ከአገልግሎት ውጪ የማድረግ ተግባራት ሲከናወን ነበር፤›› ያሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ናቸው፡፡

በክልሉ የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመመለስ ከአቅም በላይ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ድርጊቱ ሆን ተብሎ የሚደረግ እንደሚመስል አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለአራትና ለአምስት ጊዜያት በተደጋጋሚ ምሰሶዎቹን የመጠገን ሥራ መከናወኑን አቶ ሞገስ ገልጸው፣ ይህንን የሚያደርጉ አካላት ሆን ብለው ድርጊቱን ይፈጽማሉ ብለዋል፡፡

ከሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. አንስቶ በአሶሳና በአካባቢው፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊና ቆንዳላ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በቄሌም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡ ታውቋል፡፡

የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ችግሩ ከቀጠለ አገልግሎት እንደሚያቆም አስታውቋል፡፡ ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም በየቀኑ ከ400 እስከ 500 ከዞን፣ ከወረዳ፣ እንዲሁም ከአጎራባች ቦታ የሚመጡ ታካሚዎችን አስተናግዶ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አኳያ በ24 ሰዓታት የማይቋረጥ ኃይል ማግኘት ያለበት ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት በክልሉ የኤሌክትሪከ ኃይል በመቋረጡ ከፍተኛ ጫና እንደተፈጠረበት ገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ ሁለት ጄኔሬተሮች ይዞ በየቀኑ ከ180 እስከ 200 ሊትር ነዳጅ ተጠቅሞ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናትን ለማቆየት የሚውሉ ማሽኖችን ማስነሳት ከባድ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከበፊትም የበጀት እጥረት የሚፈትነው ሆስፒታሉ ለጄኔሬተር የሚውለው ነዳጅ ወጪ ከአቅም በላይ እንደሆነበትና የነዳጅ ማከማቻም አለመኖሩ ፈተና እንደሆነበት ተጠቁሟል፡፡

ሆስፒታሉ ነዳጅ ከተለያዩ ተቋማትና ባለሀብቶች ማታ ማታ እየዞረ በመለመን የሚያመጣ መሆኑን፣ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ጭምር ሊቋረጥ የሚችልበት አዝማሚያ እንዳለ አስታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...