Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርሶ አደሮች የሚበላሹ ምርቶችን በቀጥታ የሚሸጡበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አርሶ አደሮች ለረዥም ጊዜ መቆየት የማይችሉ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶችን የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው የገበያ ማዕከላት በቀጥታ የሚሸጡበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የንግድ ቢሮው ይህንን የገለጸው በከተማ አስተዳደሩ በተገነቡ የገበያ ማዕከላት የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማትና የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ፣ ሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

አርሶ አደሮች በቶሎ የሚበላሹ ምርቶችን ከማሳቸው ሰብስበው እጃቸው ላይ ስለሚያቆዩ በርካታ ምርቶች ያላግባብ ባክነው እንደሚቀሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የንግድ ግብይትና የገበያ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍሰሐ ጥበቡ ተናግረዋል፡፡   

ለረዥም ጊዜ መቆየት የማይችሉ ምርቶችን አርሶ አደሮች ለአንድ ወር ያህል የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጃቸው የገበያ ማዕከላት በማስገባት ሸጠው እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ ቲማቲም፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ማንጎና ሌሎች የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶች ለረዥም ጊዜ መቆየት እንደማይችሉ የገለጹት ኃላፊው፣ ምርቶቹን ለማቆየት የከተማ አስተዳደሩ ባስገነባቸው የገበያ ማዕከላት ውስጥ ማቀዝቀዣዎች በቅርቡ ለማስገጠም በሒደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና የዋጋ ንረት ለማስቆም፣ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ የእሑድ ገበያን ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን ወደ ተዘጋጁ የገበያ ማዕከላት አስገብተው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ፣ ከመንግሥት ቦታ ተሰጥቷቸው ሰፊ የእርሻ መሬቶች የሚያለሙ ባለሀብቶች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

በተለያዩ ምርቶች ላይ በከተማዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማና በኮልፌ ክፍለ ከተማ የገበያ ማዕከላት፣ በከተማ አስተዳደሩ በከፍተኛ ወጪ መገንባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ወደ ገበያ ማዕከላቱ ለሚሄዱ ሸማቾች የትራንስፖርት አገልግሎቱ የተቀላጠፈና የተሻለ እንዲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመሆን መሠረተ ልማቱ እንዲመቻች መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. የንግድ ሥርዓቱን ተላልፈው በተገኙ ከ50 ሺሕ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን፣ የቢሮው ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 21 ሺሕ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን፣ ወደፊት በሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ነጋዴዎችን በመከታተል ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑን አክለዋል፡፡

ተቋማቱ ከተላለፏቸው ጥሰቶች መካከል ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ የፈቃድ ዕድሳት አለማድረግ፣ ለንግድ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት አለመጠበቅ፣ እንዲሁም ለምርቶች ተገቢውን የዋጋ ዝርዝር በግልጽ አለማመላከት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች