Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተረጋጉ!

ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ እንደምን ከረማችሁ? የክራሞታችን ጉዳይ ሰኔም አልቆ ሐምሌ ከባተ ጀምሮ አስፈሪ መሆኑ ከተለመደ ጊዜ ነጎደ አይደል? ድሮ ‹‹ሰኔና ሰኞ›› ሲገጣጠሙ ፍርኃት ያርደን ነበር፡፡ አሁን ግን ሰኔ አልቆ ሐምሌ ሲተካም በፍርኃት የሚያርደን ነገር ነው አልገባን ያለው፡፡ አንዱን በቀደም፣ ‹‹ሰላም ነህ ወይ?›› ስለው፣ ‹‹ምን ሰላም አለ ብለህ ነው? በሁሉም ነገራችን ናላ የሚያዞር ሐሳብ በዝቶ…›› ብሎኝ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ። ‹‹እንዲያው ይህች ለስንቱ ዋስ ጠበቃ የነበረች አገር እንዲህ ያለ ዘመን ላይ ትድረስ? ሰው ሁሉ በሐሳብ ናላው እየዞረ መሆኑ የጤና ነው ወይ?›› ስላቸው አዛውንቱን ባሻዬን፣ ‹‹የሰው ልጅ ከገነት ከተባረረ ጊዜ ጀምሮ መቼ ሐሳብ ሳያናውዘው ቀረ ብለህ ነው? ጠበብ አድርገህ ሳይሆን ሰፋ አድርገህ ማየት ነው። ፈጣሪ በፈቀደው መንገድ ሕይወታችንን መምራት ስንጀምር የሚከብደን ምንም ነገር የለም…›› ሲሉኝ ለራሴም ሆነ ለአገሬ መፅናናት መስሎኝ ተረጋጋሁ፡፡ እኔ በዚህ የደላላ ጭንቅላቴ ነገሩን መለስ ብዬ ሳስበው አዛውንቱ ባሻዬ ያሉት መሬት ጠብ አይልም፡፡ ምክንያቱም ከፈጣሪው ጋር አንድ ላይ የሆነ ምንም አያስፈራውም፣ ምንም አይበግረውምና፡፡ አለቀ ደቀቀ አትሉም ታዲያ!

በበኩሌ ከበፊት ጀምሮ ብዙ አላቂ የተፈጥሮ ሀብቶችን አጥንቻለሁ፣ የድሮ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ቤት ሳለሁ ማለቴ ነው። ከዘንድሮ ኮሌጅ የድሮ አንደኛ ደረጃ ይበልጣል ብዬ እየተኩራራሁ እንዳልሆነ በአክብሮት ተረዱልኝ፡፡ ነገር ግን ጀግንነት ከአላቂ የተፈጥሮ ሀብቶች ጋር እንደሚመደብ ያወቅኩት ሰሞኑን ነው። ምንም እንኳ በወገኔ እስኪደርስ መጠበቅ እንዳልነበረብኝ ዘግይቶ ቢገባኝም። ለካስ ሜዳሊያ የሚታደልበት የጀግንነት ኩርማን አልቆ፣ በበቀል ጥማት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠሩ ወገኖች ያውም ንፁኃን እንደ ጠላት ታይተው ሲጠቁ ይፎከራል? አይገርምም ግን? ያደጉበትና የቦረቁበት መስክ በጠላት ሲወረር ከጠላት ጋር ተፋልሞ ገድሎ መፎከር ያለ ነው። ለከንቱ የፖለቲካ ዓላማ ሲባል ምስኪኖችን እንደ ጠላት አድርጎ ማጥቃት የእውነት ምን ይባላል? ‹ኧረ እንጃልኝ ፈራሁ!› አለ ጀግንነት ሳያንሰው ጊዜ የቀደመው የአገሬ ሰው። እኔማ ሰሞኑን ግራ ግብት ብሎኝ ቅልጥፍና የሚጠይቀው የድለላ ሥራዬ ላይ ተኝቼ ሰነበትኩ። መሰንበት አይበለውና!

‹‹አምባሰል ተንዶ ግሸን ገድቦታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው ገድሎታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው መግደሉ፣ ሥፍራ በመያዙ በመደላደሉ…›› ያለችው ማሪቱ ለገሰ ትዝ ስትለኝ፣ ‹እንዲያው ዘራፌዋ…› ደርሶ እንደ መወራጨት ያደርገኝና ቀልቤ ሳይረጋጋ ተነስቼ እብከነከናለሁ። ውዬ ቤት ስገባ ደግሞ ማንጠግቦሽን በከባዱ አስጠንቅቄያለሁ። ቴሌቪዥን የለ ሬዲዮ የሚባል ነገር እንዳትከፍትብኝ ነዋ። አበጣሪውን ከአጫጁ ምን ይለየዋል? በሉ እስኪ ንገሩኝ? ታዲያ እራት ቀማምሰን ትንሽ እንደቆየን፣ ‹‹ኧረ ቤቱ ሊበላኝ ደረሰ…›› ትለኛለች። ‹‹ስንት ነፍሰ በላ በአገርሽ ውስጥ እያየሽ ቤትሽ ምን ብሎ ይበላሻል?›› ብዬ እደነፋለሁ። ‹‹ባይሆን ድምፁን ቀነስ አድርጌ ልክፈት?›› ብላ ትለማመጠኛለች። ቤታችን እኩልነት ስለሌለ አይደለም የምትለማመጠኝ (ደግሞ ነገር እንዳይመጣ ላብራራ እንጂ፣ አላብራራ እያሉ ነገር በራሳቸው ከሚጠመጥሙት ካልተማርን ከማን እንማር?)፡፡ የምትለማመጠኝ ክፉኛ ስላዘንኩና ስሜቴ ስለተጎዳ ብቻ ነው። ሌላ ፆታዊም ሆነ ፖለቲካዊ የበላይነት እኛ ቤት እንደሌለ ልታውቁልኝ እወዳለሁ። በስንት ጭቅጭቅ አጩኻም ሆነ ቀንሳ ስትከፍተው ደግሞ፣ ትኩስ ጩኸት ሌላ ዋይታ ፊታችን ድቅን ይላል። እንቻለው እስቲ!

ታዲያላችሁ ዘንድሮ ለተወለደም ለወለደም ክፉኛ እያዘንኩ ነው። ያሳዘነኝ ምኑ መሰላችሁ? ‹‹ክፋት በሰው ልጅ ታሪክ የአንበሳውን ድርሻ እንዳልተጫወተ፣ ጥንትም የሰው ልጅ አገሩን ርስቱን ከማልማት በደም ሲታጠብ ኖሮ ዛሬ ምንድነው እንደ አዲስ የደም ሥር ሕመም የሆነብን?›› ብዬ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ድሮ ‹ፖስት›፣ ‹ሼር›፣ ‹ላይክ›፣ ‹ታግ› የለ። ዛሬ ድርጊቱ ከተፈጸመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጀንበር እዚያ ያየችውን ዓይታ፣ እዚህ ወደ አንተ ሳትዞር ዜናው ኪስህ ውስጥ በስልክህ በኩል ይንጣጣል። በዚህ አያያዛችን እኮ ወደፊት ‹የታሪክ ትምህርት› የሚባል ሳይታጠፍ ይቀራል?›› አለኝ። እሱ ሲያወራ ብዙ ነገር አሰብኩ። የተበላሸው የመርዶ ወግ ትዝ አለኝ። ‹እንዴት አድርገን ነው አሁን ቤተሰብ የምናረዳው?› እያላችሁ ተጨንቃችሁ ተጠባችሁ ሰብሰብ ብላችሁ ስትሄዱ ድንኳን ተተክሎ፣ ‹አይ የዘንድሮ ልጅ ካስማ አብሮ የማይተክል› ስትባሉ ትደርሳላችሁ። ወላጅ እንዲህ እንደ ቀልድ የልጁን አስከሬን ያያል፡፡ እንደ ዋዛ ለየዕለት ጉርሱ ሲባዝን የነበረን ሟች ያም ያም በየቲክቶኩ ሲለጥፈው ዓይቶ ባለመደንገጡ ብቻ ሲደነግጥ አውጠነጠንኩ። ከሁሉ በላይ ገና አፍ ሳይፈቱ ከእናት አባት ጠረን ይልቅ፣ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን አንስተው በመጣል ጡንቻቸውን የሚያፈረጥሙ ሕፃናት ትዝ አሉኝ። ከፍ ሲሉ ባላ ከማስፈንጠር ጀምሮ ‹ኤኬ-47 ጠብመንጃ› እያንጣጡ የአሻንጉሊት አንገት የሚበጥሱባቸው ጌሞች ታወሱኝ። የዘመኑ ታዳጊዎች ክፉኛ አሳሰቡኝ። ያየሁትን እስክነግራችሁ ከፈለጋችሁ እናንተ እየዞራችሁ የማጣራት መብታችሁ የተከበረ ነው። መቼስ በትንሽ ትልቁ አትተማመኑ ተብለን ተፈጥረን የለ!

በቀደም ዕለት በኮሪደር ልማቱ ሳቢያ ቪላ ቤቷ የፈረሰባት ሴት ደህና ቤት ፈልግልኝ ብላኝ ላይ ታች ብል የት ተገኝቶ፡፡ ከአውራው መንገድ ራቅ ብለው ከፈረሳ የተረፉ አከራዮች ኪራዩን በሦስት እጥፍ አሳድገው፣ ይህም አልበቃ ብሎ የሰውን ልጅ በኑሮ ደረጃ መረጣ ውስጥ ገብተው አሳሬን አበሉኝ፡፡ አንደኛው አከራይ፣ ‹‹ለመሆኑ ሴትየዋ ዩኤን ነው ወይስ የታወቀ ኤንጂኦ ነው የምትሠራው…›› ብሎ ሲጠይቀኝ፣ ‹‹እንዳለመታደል ሆኖ በአንድ ወቅት የታወቀች የመንግሥት ሹም ነበረች…›› ብዬ ስመልስለት ኮስተር ብሎ፣ ‹‹ቤቴን ለአስተማማኝ ዓለም አቀፍ ተቀጣሪዎች በዶላር ወይም በዩሮ ተከፋዮች እንጂ፣ መንግሥት አንገዋሎ ለሚጥላቸው ጡረተኞች አላከራይም…›› ብሎኝ አረፈው፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ዋጋ መጨመሩ ሲያስገርመኝ የሰው መረጣው በዶላርና በዩሮ ሲሆን ደነገጥኩ፡፡ ጎበዝ በአንድ በኩል ልማት በሌላ በኩል ጥፋት ሲገጥማችሁ ምን እንደሚሰማችሁ ባላውቅም እኔ ግን ግራ ተጋባሁ፡፡ ወገን በወገኑ ላይ እንዲህ መጨከኑ እያበሳጨኝ በንዴት ስራመድ አደናቅፎኝ ወድቄ ጥርሶቼ በተዓምር ተረፉ፡፡ ወይ ሰበብ!

መሀል ከተማውን በአራቱም ማዕዘናት እያካለልኩ የሚከራይ ደህና ቤት ስፈልግ ብዙ ገመናዎቻችንን አየሁ፡፡ የክፋታችን መጠን የደረሰበትን ጥግ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች የመመልከት ዕድል ቢኖረኝም፣ የአሁኑ ግን እጅግ በጣም የከፋና ለፈጣሪም የማይመች መሆኑን ነው የተረዳሁት፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር እርግጥ ነው እዚህ አገር ክፋት ከመጠን በላይ ነግሷል፡፡ የክፋቱ መገለጫም ቂም፣ በቀል፣ ሴራ፣ ጭካኔና ደንታ ቢስነት ቢሆኑም አሁን ግን ኢሰብዓዊነት የበላይነቱን ይዞ ወገን በወገኑ ላይ እየጨከነ ነው…›› ሲለኝ የነበረው ወለል ብሎ ታሰበኝ፡፡ ወይ ጉድ!

በሰኔ ማጠናቀቂያ ሳምንት መንገዱ በሙሉ ተዘጋግቶ ሥራን ማከናወን አዳጋች መሆኑን ለእናንተ መንገር አይገባኝም፡፡ ከአንዱ ዘመን አፈራሽና ንፋስ አመጣሽ ደንበኛዬ ጋር ሆነን ከቦሌ ወደ ለቡ ሙዚቃ ሠፈር እየተጓዝን ነው፡፡ እዚያ አካባቢ የምንሄደው በቅርቡ ወሽሞ ለያዛት ቆንጆ ጂፕላስ ቱ ለመግዛት ነው፡፡ በ37 ሚሊዮን ብር እንደገዛው የነገረኝ ዘመናዊ መኪና በተጨናነቀው መንገድ ላይ ቆም ሄድ ሲል የሚያወጣው ደምፅ ያሳዝናል፡፡ ከትራፊክ ጭንቅንቅ ነፃ በሆነ መንገድ ላይ በሰዓት 300 ኪሎ ሜትር የሚነዳ መኪና እንደ ታረደ በግ ሲያጓራ ደንበኛዬ መሪውን በንዴት ይጠልዛል፡፡ መንገዱ ተዘጋግቶ ወይ ወደ ፊት ወይ ወደኋላ መሄድ አልተቻለም፡፡ ሁሉም መኪኖች እንደ ባቡር ፉርጎ ተቀጣጥለው ወደፊት እንጂ ወደኋላ አዙሮ መመለስ አይታሰብም፡፡ ረፋድ አምስት ሰዓት ከቦሌ የተነሳን ከቀኑ ሰባት ሰዓት ከሩብ ለቡ ስንደርስ ከሩቅ ከተማ የተጓዝን ይመስል ልባችን ፍስስ ብሎ ነበር፡፡ ደንበኛዬ በንዴት እየደጋገመ መሪውን ቢጠልዘውም፣ ‹‹ይህ ሁሉ መጨናነቅ አልፎ ፈልሰስ ብለን የምንነዳበት ጊዜ ሩቅ አይደለም…›› እያለ ሲፅናና፣ እኔ በልቤ መንደሬ በሙሉ ፈርሶ ወዴት እንደምንገባ እየተጨነቅኩ ነበር፡፡ በኮሪደሩ ልማት ለሀብታሞች በመኪኖቻቸው መንፈላሰሻ ለእኛ ድሆች ደግሞ በእግረ መንገዶች መንቀሳቀሻ እንደምናገኝ ሲነገረን እንደነበረ አትረሱትም፡፡ ‹‹የሆነስ ሆነና ‹አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ፅዱ፣ ምቹና ውብ› ትሆናለች እየተባለ እኛ ግን ወደ ከተማው ዳርቻ የምንገፋበት ምክንያት ምንድነው…›› እያለ አንዱ ደላላ ወዳጃችን ሲነጫነጭ፣ ‹‹አይዞህ የኮርደር ልማቱ ዳሩንም መሀል ያደርገዋል…›› ብሎ ዕድሜ ጠገቡ ደላላ መለሰለት፡፡ እንዲህ እየተባባልን ጊዜው ላያችን ላይ ማለቁ ድንቅ ይለኛል፡፡ ምን ልበል ታዲያ!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ምንም እንኳ የሚሰማውና የሚታየው የመኖር ትጥቃችንን ሊያስፈታ ቢታገለንም፣ ይህን ታህል መተንፈሳችን አልጎዳንም። እሱም ተራው ደርሶ አትቁም እስኪባል ቋሚ ምን ይሆናል አትሉኝም? አዎ ተስፋ ሳለ ምን ይሆናል። አዛውንቱ ባሻዬ ምን ሲሉኝ ነበር መሰላችሁ? ‹‹እሱ ኑር እስካለ ድረስ ብታጣ፣ ብትራቆት፣ ብትታረዝ ምን ማድረግ ትችላለህ? ‹እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም› ትላለህ። ዳሩ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ማንም እየተነሳ ሲዘጋው ዝም እያለ አስቸገረን እንጂ። ግን መታገስ ነው። ሃይማኖትህም ሆነ ማንነትህ ምንም ሆነ ምን መሠረቱ ትዕግሥትና ፍቅር መሆን አለበት። ይኼውልህ ምሳሌ አንድ የቆሎ ተማሪ ‹በእንተ ስለማርያም› ይላል ጭራሮ አጥር ጥግ ቆሞ። ውስጥ ያሉ እናት ሰምተው ‹ተሜ አትቁም› ይሉታል። ‹እሜቴ እኔ መቼ ቆሜ? በእኔ ተመስሎ ፈጣሪ ነው የቆመው› ቢላቸው፣ ‹ከምኔው አንተ ዘንድ ደረሰ? አሁን ሌማቴ ባዶ መሆኑን ከፍቼ አሳይቼ ሳልከድነው?› አሉት። ተሜ በተራው፣ ‹ነው? እንግዲያስ ልቀመጥ› ብሎ ተማሪነቱን ተወው ይባላል። የሚለመን ሳይኖር ለምን ልለምን ብሎ እኮ ነው። የምሳሌያችን አመጣጥ እንደ ጀመርነው ወግ ዓውድ አልሄድ እያለ የሚያስቸግርበት ዘመን ስለሆነ ነው የተሜን ታሪክ ጣል ያደረግሁባችሁ እንጂ፣ ለተጀመረው ወግ ተመጣጣኝ የሆነ ምሳሌ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል፡፡ ለማንኛውም ጊዜውን መጠበቅ ይሻላል፡፡ አማራጭ የለም ለማለት ነው!

አዛውንቱ ባሻዬ በቀደም ዕለት፣ ‹‹ሴራ ከሚዶልት፣ አገሩን ከሚጠላና ወገኑን ከሚበድል ይሰውርህ የሚባለው ይኼኔ ነው። ስንፍና የጥበብና የተግሳፅ ጠላት ናት። አየህ ዓለም በማጣትና በማግኘት፣ በመውጣትና በመውረድ፣ በሞትና በሕይወት ውጣ ውረድ ስትከፋፈል ታግሶ ለሰነበተ፣ ቆሞ ለታዘበ፣ ታክቶ ላልተቀመጠ የማስተዋልንና የዕውቀትን ብርሃን ታበራለት ዘንድ ነው። ጅብ ቸኩሎ ምን ነከሰ? ቀንድ አትለኝም? ምንድነው እኔን ብቻ የምታስለፈልፈኝ? አዎ ሁሉን ታግሰን እኛው በእኛው እዚሁ ተረባርበን ይህችን ምድር ብናርሳት ታጠግበናለች። ‹ወንድሜ ፊት ነሳኝ› ብሎ ሰው የአባቱን ርስት ጥሎ ከሄደ ያው ባርነት ያው የባዳ በደል ነው የሚጠብቀው። አፉን የከፈተ ባህር ነው የሚውጠው። አይደለም? መቻል ያሳልፋል፣ መቻቻል ያሰነብታል። ‹ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይቀይርም› ብሎ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ይበጃል። እህ ሌላማ ያልሞከርነው ምን አለ?›› ሲሉኝ፣ ‹‹ምንም…›› ከማለት ውጪ ሌላ መልስ አልመለስኩም። ባሻዬ መልዕክታቸው ግልጽ ነው፡፡ እኛ እርስ በርሳችን ካልተደጋገፍን ማንም አይደርስልንም ነው የሚሉት፡፡ አገራችን ለሁላችንም ትበቃለች፡፡ ነገር ግን በክፉ አንፈላለግ ነው የሚሉት፡፡ በአገር ጉዳይ ትርፍና ኪሳራ አናወራርድ ነው መልዕክቱ፡፡ በማስተዋል ለሚታዘብ ማንም ሰው የሚታየው አዋጭ መንገድ እንጂ አክሳሪ ጎዳና አይደለም፡፡ ከአዋጭና ከአክሳሪ ጎዳና መምረጥ የእኛ ፋንታ ነው፡፡ የተለመደችው ግሮሰሪያችን ተገናኝተን አባቱ የነገሩኝን ለምሁሩ ልጃቸው ሳብራራለት፣ ‹‹አንበርብር አሁን ያለን አማራጭ ቆም ብሎ ማሰብ ነው፡፡ ቆም ብሎ ለማሰብ ደግሞ መረጋጋት ያስፈልጋል፡፡ ስንረጋጋ ድቅድቅ ጨለማው አልፎ ብርሃን፣ መከራው አልፎ ደስታ መከተሉ አይቀርም…›› እያለ አረጋጋኝ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት