Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባለሀብቶች የደጎሙት የጤና መድን

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባለሀብቶች የደጎሙት የጤና መድን

ቀን:

ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ አባል ወይም ቤተሰቦች የጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው የሕክምና ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑበት መንገድ ነው፡፡

ጤና መድን አንድ ሰው በኪሱ ገንዘብ ሳይኖረው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ፣ የሕክምናን ወጪ ለመቀነስ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ መደጋገፍን ለማጎልበትና ግለሰቦችን ከዕርዳታ ነፃ ለማውጣት የሚያስችም ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ማኅበራዊ ጤና መድንና የግል የጤና መድን የተሰኙ ሦስት ዓይነት የጤና መድን ዓይነቶች ይተገበራሉ፡፡

ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በተለይ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የገጠር የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያቀፈም ነው፡፡

የግል የጤና መድን የሚባለው በግል ደረጃ፣ ግለሰቦች የጤና ኢንሹራንስ ወይም መድን የሚገቡበት ሥርዓት ሲሆን፣ ይህም ትርፋማ የጤና መድን ስለመሆኑ ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል፡፡  

ወ/ሮ ሰዓዳ አብዲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው በሞት እንደተለዩዋቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ሰዓዳ፣ ሦስት ልጆቻቸውን ያለ አባት እያሳደጉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የእሳቸውን ድጋፍ የሚፈልጉ ወላጅ እናታቸውን ሰው ቤት ልብስ በማጠብና የተገኘውን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ በመሥራት እየጦሩ ነው፡፡

ልጆቻቸው የአሥራ ስድስት፣ የአራትና የሁለት ዓመት ዕድሜ ያላቸው መሆኑን የሚናገሩት እኚሁ እናት፣ ልጆቻቸው ሲታመሙ ለሕክምናና ለመድኃኒት የሚሆን ገንዘብ ስለሌላቸው ወደ ጤና ተቋማት አይሄዱም፡፡ የልጆቻቸው ሕመማቸው ከጠና ብቻ ከዘመድም፣ ከጎረቤትም ተበዳድረው ሕክምና ተቋም እንደሚወስዱ ይናገራሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ ሰዓዳ፣ በከተማዋ ለሚኖሩ አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን መጀመሩና የዚህ ዕድል ተጠቃሚም በመሆናቸው ተደስተዋል፡፡

የጤና መድን ዋስትና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና እሳቸውን ለመሰሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መልካም ተስፋ ይዞ የመጣ ነው፡፡ በተለይም በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች ለማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የገንዘብ አቅም ለሌላቸውና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጤና ተቋም ለመውሰድ ለተቸገሩ ሰዎች የሕክምና ወጪ መሸፈን ጀምረዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምርያ፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ሒርጳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የማኅረበሰብ አቀፍ ጤና መድንን ለከተማዋ ነዋሪዎች ለማቅረብ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ የንቅናቄ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡  

እንደ አቶ ጌታቸው፣ ወርኃዊና ቋሚ ገቢ ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ቀበሌዎች ነዋሪው ሕዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የግንዛቤ ማስጨበጫና አባላት የማፍራት ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድንን በከተማዋ ተግባራዊ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ከ6,209 በላይ አባወራዎችን አባል ማድረግ የተቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ከ4.9 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ መደረጉንም አክለዋል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙና ከፍለው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን የማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የጤና መድን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል፣ ባለሀብቶች የአቅመ ደካሞችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙም አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

የዲ.አር.ቢ እምነበረድ ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ፀጋዬ በበኩላቸው፣ የገንዘብ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች የተቸገሩትንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ይገባቸዋል፡፡

በአሶሳ የሚገኘው ድርጅታቸው ዲ.አር.ቢ ትርፍም ሆነ ኪሳራ ከማኅበረሰቡ ሕይወት ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሚገናኝ ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፣ የከተማዋን ነዋሪዎች በተለይም አቅመ ደካሞችን ማገዝ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ እንደ ዜጋና ባለሀብትነት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው፡፡

በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የ50 አባወራዎችን ወጪ በመሸፈን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸውን የሚገልጹት ባለሀብቱ፣ ከደሃ ማኅበረሰብ በመወለዳቸው፣ ከደሃ ማኅበረሰብ ጋር በማደጋቸው፣ ከደሃ ማኅበረሰብ ጋር በመኖራቸውና የዜግነት ግዴታቸው በመሆኑ ጭምር መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...