Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ትኩረት የሚሰጥ ትምህርት ቤት ተመሠረተ

ለሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ትኩረት የሚሰጥ ትምህርት ቤት ተመሠረተ

ቀን:

በሳይንስ ትምህርቶች አሰጣጥ ዙሪያ ለውጥ ለማምጣትና በሳይንስ ዕውቀት የበለፀገ ትውልድ ለማበርከት ያስችላል የተባለው ‹‹አማና ሞዴል›› ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመሠረተ፡፡

በንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና በአንጋፋ ምሁራን ጥምረት የተመሠረተው የአማና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመማር ማስተማሩን ሒደት በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት፣ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አሚና መኑር (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ‹‹አማና ሞዴል›› ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘመናዊ የላቦራቶሪ ቁሳቁስ ተሟልቶለታል፡፡ ከመምህራኑም እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡

የአማና ሞዴል ትምህርት ቤት በተግባር የተደገፈ ትምህርት ክፍተትን በመሙላት የተማሪዎችን የማወቅ ጉጉት፣ ለተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ያላቸውን ዝንባሌና ግንዛቤያቸውን ከፍ የማድረግ ዓላማ አለውም ብለዋል፡፡

እንደ አሚና (ዶ/ር)፣ ትምህርት ቤቱ በትምህርቱ ዘርፍ አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎቱ ባላቸው የንግድ ማኅበረሰብ አካላት፣ ዕውቀታቸውን ለትውልድ ለማካፈል በወደዱና በጥናትና በምርምር ሥራዎቻቸው አንቱታን ባተረፉ ምሁራን ጥምረት የተመሠረተ ነው፡፡

የትምህርት ቤቱ መሥራች አባላትና ምሁራን ‹‹አማና ሞዴል›› ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ከመመሥረታቸው አስቀድሞ ‹‹አማና›› የወጣቶች ልማት ኔትወርክ የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ አቋቁመው፣ አዲሱን ትውልድ በዕውቀት የማነፅ ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

በድርጅቱም አማካይነት በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚያስተምሩ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህራን የሳይንስ ትምህርቶችን በተግባር አስደግፎ ስለማስተማር ነፃ የሥልጠና መርሐ ግብር ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

ምሁራኑ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አማካይነት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲያካሂዱ የቆዩትን ‹‹ሳይንስን በተግባር›› የተሰኘ የሥልጠና መርሐ ግብር ለማስቀጠል በነበራቸው የላቀ ፍላጎት፣ አማና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን መሥርተዋል ብለዋል፡፡

‹‹ትምህርት ቤቱ ለተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ትኩረት መስጠቱ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት አይቀንሰውም፤›› ያሉት ርዕሰ መምህሯ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 25 ተማሪዎችን ብቻ ተቀብሎ እንደሚያስተምርና በአሁኑ ወቅት የዘጠነኛና አሥረኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተናገድ ላይ እንደሚገኙ፣ በቀጣይ እነዚህን ተማሪዎች እያሳደጉ ተጨማሪ የ11ኛ እና 12ኛ ክፍሎችን የመክፈት ዕቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በከተማ አስተዳደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች የመንግሥትን የመፈጸም አቅም የሚደግፉ፣ ክፍተትን የሚሞሉና እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገናኙና የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

‹‹አማና ማለት ባለአደራ፣ ሸክም ያለበት ማለት ነው፣ በመሆኑም ትምህርት ቤቱ ለመጪው ትውልድ፣ ለወላጆችና ለአገር ትልቅ አደራ ተሸክሞ የመጣ ነው ለማለት ይቻላልም›› ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ባለአደራ ነው ሲባል ግን፣ ሳይንስ ላይ ስለሠራ፣ አዕምሮ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ስለሰጠና በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ስላፈሰሰ ሳይሆን፣ ትውልድን ወይም አገር ተረካቢውን ወገን ሰብዕናውን በሁለንተናዊ መገንባት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

 ትምህርት ቤቱ በአገር ግንባታ ሒደት ላይ የራሳቸውን ጉልህ አሻራ የሚያኖሩ ተማሪዎችን ለማፍራት አዕምሮ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች በተለየ መልኩ ሥነ ልቦናና ግብረ ገብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ትምህርት ቢሮና ትምህርት መዋቅሩ፣ ትምህርት ቤቱን ለመደገፍና ለማገዝ ዝግጁ ነው፤›› ያሉት ዘለዓለም (ዶ/ር)፣ ለተማሪዎች፣ ለወላጆችና ለአገር ትልቅ መድኅን ለመሆን አቅዶ ለተነሳው ዓላማ ቢሯቸው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህርና ከትምህርት ቤቱ መሥራቾች አንዱ የሆኑት መስፍን ረዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ትምህርት ቤቱ በአገሪቱ የሳይንስ ትምህርት አሰጣጥ ዓይነተኛ ለውጥ ለማምጣት መመሥረቱን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...