Monday, July 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የ‹‹ጅራፍ ሕግ›› ታሪክን የኋሊት…

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

በአንድ ወቅት ላይ የአገራችን ፕሬዚዳንት ከነበሩት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ለቀናት የዘለቀ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡

ከአዛውንቱ ፕሬዚዳንት ጋር የነበረኝ ቆይታዬም በዋናነት መሠረት ያደረገው ክቡርነታቸው፣ ‹በኢትዮ ኤርትራ ሰላም/የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና እንዲሁም በዛፍ ተከላ/በደን ልማት› ዙሪያ ያላቸውን ተሞክሮና ልምዳቸውን ለታሪክ/ለትውልድ ለማስቀረት ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ የ95ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለረዥም ዓመታት በሥራ ኃላፊነት በቆዩባትና ግዙፍ ትዝታን በውስጣቸው ባተመችው በውቧ የአስመራ ከተማ ለማክበር ዝግጅት ላይ እያሉ ነበር ሞት የቀደማቸው፣ ክቡር ሆይ ነፍስ ይማር! ብለን ወጋችንን እንቀጥል፡፡

የጅራፍ ሕግ…!!

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ያሉ አንዳድ ጸሐፍትና ሐያስያን እንደ ‹ብርሃንና ሰላም› ባሉ ጋዜጦች ላይ፣ የንጉሡን ቤተሰቦች፣ መኳንንቱንና መሳፍንቱን ሸንቆጥ የሚያደርጉ ጽሑፎችን መጻፍ ጀምረው ነበር፡፡ እንዲህ ሲሉ፡-

‹‹የንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ‹ደሃ ተበድሎ ፍርድ ተጓድሎ› ባለበት እናንተ ግን ‹በወርቅ እንክብል በሸማ ጥቅል› እየተኩነሰነሳችሁ (እየተቀማጠላችሁ)፣ በአሽከር በደንገጡር ተከባችሁ… የደሃው እሮሮ፣ የሕዝቡ ብሶት አይሰማችሁም…›› ስሜትን ያዘሉ ጽሑፎች በጋዜጣዎች ላይ መስተናገድ ተጀመረ፡፡

ይህ በየጋዜጣው መብጠልጠላቸው ያላማራቸው ንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ መሳፍንቱና መኳንንቱም ‹‹ይህች ሽንብራ ያደረች እንደሆነ አትቆረጠምም፣ ሳይቃጠል በቅጠል›› የሚለውን አገርኛ ብሒል መሠረት አድርገው ለፓርላማ አንድ ሐሳብ አቀረቡ፡፡

ይኸውም፣ ከአሁን ወዲህ በንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ላይ የማይገባ ጽሑፍ፣ ሐሜትና ስላቅ፣ አግቦና አሽሙር የሚጽፉ ሰዎች ‹‹አርባ ጅራፍ›› እንዲቀጡ የሚደነግግ የዘውዱ ፓርላማ ጥብቅ ሕግ እንዲያወጣ አቤቱታቸውን ለፓርላማው አሰሙ፡፡

ይህ ‹‹የጅራፍ ሕግ›› ጉዳይ በፓርላማ ውስጥ ብዙ ክርክርና ውዝግብ አስነሳ፡፡ በመጨረሻ ላይ ከዚያን ጊዜው የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ተወክለው የመጡ አለቃ ዓይነ ኩሉ መርሻ የተባሉ ሊቅና የፓርላማ አባል በዚህ መልኩ ተቃውሞአቸውን በማሰማት የጅራፍ ሕግን ተቃወሙ፡፡

‹‹ጃንሆይ የተከበራችሁ የፓርላማ አባላት ለመሆኑ ፈጣሪና ንጉሥ ካልታሙ፣ በነገር ካልተሸነቆጡ ማን ሊሸነቆጥ ኖሯል?! የበላይ የለባቸው፣ ይግባኝ አይባልባቸው፣ ታዲያ ፈጣሪና ባለሥልጣናቱ/መኳንንቱ ካልታሙ፣ በፈሊጥና በምሳሌ ካልሸነቆጥናቸው እንዴት ይሆናል?!

እንዴ ተዉ እንጂ የአገሬ ሰዎች… ደሃም እኮ ድህነቱን ለመርሳት ጠጁን ጠጥቶ ሞቅ ያለው እንደሆነ ፈጣሪውን ማማቱ፣ ንጉሡን ማማረሩ የት ይቀራል… ስለዚህ ጃንሆይ በእርስዎም ሆነ በሉዑላውያን ቤተሰቦችና በባለሥልጣናት ላይ ክብራችንን የሚያዋርድ ነገር ሆነብን፣ ሐሜታ ደረሰብን… በሚል ‹የዐርባ ጅራፍ› ሕግ ሊወሰን አይገባም፣ በማለት ተቃወሙ፡፡

ይህ የአለቃ ዓይነኩሉ መርሻ ሐሳብ 94 በመቶ የፓርላማውን ድጋፍ ድምፅ በማግኘቱ ‹‹የአርባ ጅራፍ ሕግ›› ቅጣት እንዳይወሰን መደረጉን- ትውስታቸውን ፕሬዚዳንት ግርማ እንዲህ ነበር ያወጉኝ፡፡

መውጫ

ፕሬዚዳንት ግርማ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የመጀመሪያው የምረጡኝ ዘመቻ ሥራ መሪ (ማናጀር) የነበራቸውና በ36 ዓመታቸው ፓርላማውን የተቀላቀሉ ወጣት የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡

ክቡርነታቸው በምርጫ አሸንፈው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ፓርላማ አባል ከሆኑ በኋላ ካከናወኗቸው ሥራዎች መካከልም፣ አገራችን የዓለም ፓርላማ አባል እንድትሆን ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም ክቡርነታቸው በ1956 በዩጎዝላቪያ ቤልግሬድ በተካሄደው የዓለም ፓርላማ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በፕሬዚዳንትነት የተመረጡ ሲሆኑ፣ በዚያ ስብሰባ ላይ በቅኝ ግዛት ሥር ለሚገኙ ለአፍሪካ አገሮችና በተለይም ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ስለተንሰራፋው የአፓርታይድ መንግሥት ዓለም ድምፁን ማሰማት እንዳለበት ያደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸው ይጠቀሳል፡፡

የዛሬውን ወጌን በፈረንሣዊው የታሪክ ሊቅ፣ የፖለቲካ ፈላስፋ፣ ደራሲና ጸሐፌ ተውኔት ቮልቴር አባባል ልደምድም፣ ‹‹በምትናገረው ባልስማማም የመናገር መብትህን ግን እስከ ሞት ድረስ እሞግትልሃለሁ›› (I disapprove of what you say, but I will defend to the death your right to say it.)፡፡

ሰላም

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles