Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትኩረት የሚሻው አሳሳቢው የሥነ ተዋልዶ ጤና

ትኩረት የሚሻው አሳሳቢው የሥነ ተዋልዶ ጤና

ቀን:

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ ቀውሶች በኢትዮጵያ ከተፈጠሩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተደማምረው፣ በሥነ ተዋልዶ ጤናው ዘርፍ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡

በተለይ በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠሩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የእርስ በእርስ ግጭቶችና ጦርነቶች እንዲሁም ድርቅና ረሃብ ቀድሞውንም በውስብስብና አስቸጋሪ ማነቆዎች ለተተበተበው የሥነ ተዋልዶ ጤና ተደራሽነትና ግንዛቤ የማግኘት ዕድል ተጨማሪ ፈተናዎች ሆነዋል፡

ይህ ደግሞ ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ማውራትን እንደ ሃፍረት ለሚቆጥርና ልጆች ስለአካላዊ ዕድገታቸው እንዲያውቁ፣ እንዲገነዘቡና በአፍላነታቸው ወቅት ሊገጥሟቸው ስለሚችሉ ተፈጥሯዊ ክስተቶቸ ከቤተሰብ ጋር እንዲወያዩ እድል በማይሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖረውን አሉታዊ ጫና ያጎላዋል፡፡

 በትምህርት ቤት ደረጃም ቢሆን፣ የሥነ ተዋልዶ ርዕስ ነክ የትምህርት ክፍሎች ተተንትነው የማይሰጡ መሆኑ ታዳጊ ልጆችንም ሆኑ አፍላ ወጣቶችን ላልተፈለጉ የሥነ ተዋልዶ ጤና እክሎች ማጋለጡ ዕሙን ነው፡፡

በኢትዮጵያ በታዳጊ ወጣቶች፣ በወጣቶችና በእናቶች ጭምር የሥነ ተዋልዶ ጤና እክል እያስከተለ የሚገኘውን የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍ ግን፣ ዛሬም እንዲሁ በቀላሉ ወደ ኅበረተሰቡ ለማስረፅና ሰው ስለ ሥነ ተወዋልዶ ጤንነቱ ተገንዝቦ እንዲኖር ለማስቻል መንገዱ ቀላል አይደለም፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የተዳፈነ የሥነ ተዋልዶ ጤና አመለካከት፣ አሁን ተሻሽሎ ብዙዎች ራሳቸውን ከተለያዩ የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች እንዲጠብቁ ዕድል ቢፈጥርም፣ ያለ ሐሳባቸው የሚያረግዙ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት የሚሞቱ፣ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች የሚጋለጡ መኖራቸው አልቀረም፡፡

ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ የተሠሩ ሥራዎች የተሻለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ መፍጠራቸው፣ በተለይ ሴቶችና እናቶችን ፍላጎትን ካልጠበቀ እርግዝና መታደግ መቻሉ፣ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ታሳቢ ተደርገው ደኅንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ መቻሉ ለውጥ ቢያመጣም፣ አሁንም በዓመት አራት በመቶ ያህል ሴቶችና እናቶች ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡

በሥነ ተዋልዶ ጤና ዘርፍ የሚሠራው አይፓስ ኢትዮጵያ ተጠሪ ደመቀ ደስታ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ አኃዝ ቀድሞ ከነበረበት በዓመት 32 በመቶ ሞት በእጀጉ ቢቅንስም፣ አራት በመቶውንም ሞት በቅድመ መከላከል ሥራ ማስቀረት ይቻላል፡፡ 

ይህ ለውጥና ባለፉት 20 ዓመታት የተሠሩ መልካም ሥራዎች ወደኋላ እንዳይመለሱ፣ በተለይም ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ዙሪያ አይፓስ ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴርና ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር እየተከናወኑ ባሉ የሥነ ተዋልዶ ጤና ሥራዎችና ደኅንነቱ በተጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ ዙሪያ ሰሞኑን ውይይት አካሂደዋል፡፡  

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው ውይይትም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበሩ ግጭቶችና በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች የተከሰቱ የድርቅ ችግሮች ለመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች መስተጓጎል ምክንያት መሆናቸው ተነስቷል፡፡

አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ለተለያዮ ፆታ ተኮር ጥቃቶች የተጋለጡት ሴቶችና ልጃገረዶች ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከመዳረጋቸውም በላይ ላልተፈለገ እርግዝናና ለተላላፊ በሽታዎች መጋለጣቸው በውይይቱ መነሳቱን ደመቀ (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡

እንደ ደመቀ (ዶ/ር)፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና እክሎችን ትኩረት ያደረጉ የጤና አገልግሎቶችን ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠናና ድጋፍ ማድረግ፣ የሕክምና ቁሳቁሶችን፣ አስፈላጊ መድኃኒቶችንና ሌሎች ግብዓቶችን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡

የሥነ ተዋልዶ ጤና ተቃዋሚዎች በሆኑ አክራሪና የወንድ የበላይነትን በሚያቀነቅኑ ምዕራባውያን አካላት ጫና በማሳደርና ሐሰተኛ መረጃዎች በማሠራጨት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ በሚገኙና አገልግሎቶቹን ተደራሽ ለማድረግ በሚጥሩ አገሮች ውስጥ የኅብረተሰቡንና የመንግሥት አካላትን ግንዛቤ በማዛባት አሉታዊ ተፀዕኖ ለማሳደር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባ ደመቀ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሠፈረውም፣ ለአፍላ ወጣቶች በቂ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል፡፡  

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የፓርላማ ሴት ተመራጮች ኮከስ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው፣ የጨቅላ ሕፃናትን፣ የአፍላ ወጣቶችንና የእናቶችን ጤና ለመታደግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በጤናው ዘርፍ እየሠሩ ቢሆንም፣ አሁንም በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ለእናቶችና ለአፍላ ወጣቶች ሰፊ ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባ፣ ደኅንነቱ ያልጠበቀ እርግዝና ፅንስ በሚቋረጥበት ወቅት እናቶችና አፍላ ወጣቶች ለሕለፈተ ሕይወት እየተጋለጡ በመሆኑ፣ በሥነ ተዋልዶ ዙሪያ ቅደመ ግንዛቤ ማስረፅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናትና አፍላ ወጣቶች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዓለማየሁ ሁንዱማ (ዶ/ር)፣ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ በወሊድ ምክንያት 623 እናቶች ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሥነ ተዋልዶ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ በመሥራት በከፍተኛ ደረጃ የእናቶችን ሞት በመቀነሷ ለአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት መሆን እንደቻለችም ጠቁመዋል፡፡

የኮከሱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ኪሚያ ጁንዲ እንዳሉት፣ የጽንስ ማቋረጥን የትኛውም የሃይማኖት ተቋም አይደግፈውም፡፡ በመሆኑም ከጽንስ በፊት ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከሉ ረገድ ኅብረተሰቡን ማስተማር ይገባል።

ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከል የአፍላ ሴት ወጣቶችን ሕይወት ለመታደግ ሕገ ማኅበረሰብን፣ ሕገ መንግሥትንና ሕገ ሃይማኖትን በማስተሳሰር በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ዙሪያ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቅሰው አይፓስ፣ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና በተለይም በቤተሰብ ዕቅድና ደኅንነቱ በጠበቀ የፅንስ ማቋረጥ አገልግሎት የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ ለሴቶች ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ እየሠራ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...