Wednesday, July 24, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎና ፖለቲካዊ ማብራሪያዎቻቸው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በነበረው ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በርካታ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር፡፡ ከሙስና ነቀርሳ እስከ ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ተጠይቀዋል፡፡ ከጅምላ ግድያ እስከ የፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች እስራት ተነስቶላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ የበላይነትን የተመለከተ ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ የመንግሥት በጀት አመዳደብ ፍትሐዊነትን፣ ከአገራዊ ምክክር እስከ ሽግግር ፍትሕ፣ ከሰላም ድርድር እስከ የባህር በርና የውጭ ግንኙነት ባሉ መስኮች በርካታ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ቀርበው ነበር፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎችም ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በርካታ አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ በተለይ ፖለቲካዊ በሆኑ ነጥቦች ዙሪያ ያነሷቸው ጉዳዮች ትኩረት የሚስቡ ነበሩ፡፡

ከፓርላማ አባላቱ የተነሱ ጥያቄዎችም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ያነሷቸው ጉዳዮች አገሪቱ አሁን የምትገኝበትን ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን በሚመጥን ሁኔታ የቀረቡ ነበር ወይ የሚለው ሒደቱን ሲከታተሉ ለዋሉ ጥያቄ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙም ባይሆንም ጥቂት ጠንከር ያሉና አንገብጋቢ የሕዝብ ብሶቶችን የሚያስተጋቡ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካዩ አብረሃም በርታ (ዶ/ር) ሙስናን በተመለከተ አሳሳቢ ያሏቸውን ችግሮች በትኩረት አንስተዋል፡፡

‹‹ብዙ አገሮችን ለውስብስብ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ከሚዳርጉ ችግሮች አንዱና ዋናው ሥር የሰደደ መንግሥታዊ ሌብነት ነው፡፡ ሙስና የአገራችንን መዋቅር የሚበላ የሕዝብን ማኅበራዊ ትስስር የሚበጣጥስ፣ የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽር፣ አገር እንዳታድግ የሚይዝ ማኅበረሰባዊ ካንሰር ነው፡፡ አገራችን የምትገኝበት የሙስና ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የፌደራል ኦዲት መሥሪያ ቤት የሚያቀርበው ሪፖርትና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይህንኑ አሳሳቢ የምዝበራ ደረጃ ያረጋግጣሉ፤›› የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ሌላኛው የምክር ቤት አባል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ተወካዩ አቶ አበባው ደሳለው ያነሱት ጥያቄ ኮስተር ያለ ይዘት ነበረው፡፡ ተወካዩ ባነሱት ጥያቄ፣ ‹‹ከአገራዊ ምክክርም ሆነ ከሽግግር ፍትሕ በሕዝብ ዘንድ አመኔታን መገንባት አይቀድምም ወይ? የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ወቅት የመንግሥት ኃይሎች በአማራ ክልል አሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጽመዋል፡፡ የጅምላ ግድያዎች ተፈጽመዋል፡፡ ፆታዊ ጥቃት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ፣ ንብረት ማውደምን የመሳሰሉ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ጭምር አረጋግጠዋል፡፡ በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት የፓርላማ አባላት ጭምር ታስረዋል፡፡ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ማኅበራዊ አንቂዎች ታስረዋል፡፡ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር)፣ ታዬ ደንደአ፣ እንዲሁም ሀብታሙ በላይነህ ታስረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አብቅቶም አማራ ክልል በኮማንድ ፖስቱ እየተዳደረ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ በሆነበት ስለሽግግር ፍትሕና ስለምክክር መንግሥት ቢያወራ እንዴት ይታመናል?›› በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ለእነዚህ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ስለአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታ በመተንተን ነበር የተንደረደሩት፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል በታሪክ ቅብብሎሽ የመጣ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ችግሮች ነባርና ወቅታዊ ሲሉ በሁለት የከፈሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ከቅድመ አያት፣ አያት፣ አባት እያለ ግጭትና ችግር በኢትዮጵያ ሲወራረስ መምጣቱንም አመልክተዋል፡፡ የኢኮኖሚ ስብራት ያሉትን ደግሞ ከወቅታዊ ችግሮች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ አገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕ፣ የተቋማትና የሕጎች ማሻሻያ፣ አቃፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር፣ የአገር ዕዳን መቀነስ፣ የበጋ ስንዴን ማምረትና ከተረጂነት መውጣት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ጉዳዮችም አገሪቷ ለገጠሟት ቀውሶች መፍትሔ ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡

‹‹ችግር ሲፈጠር እንጂ ስንፈታው ቀላል አይደለም፤›› የሚል አባባል የተጠቀሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ጥያቄ እናነሳለን፣ ነገር ግን ጥያቄው ሲመለስ ደግሞ ጥያቄ እናነሳለን፤›› የሚል አገላለጽም አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥታቸው የአገሪቱን ችግሮች በተዋረድ እየመለሰ ቢገኝም እንኳ፣ ነገር ግን ተጨማሪ ችግር ከመደርደር በዘለለ አመስጋኝነትና አድናቂነት በኅብረተሰቡ ዘንድ መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡

ዋልታ ረገጥ ፖለቲካን በማስቀረት ተቃዋሚዎችን ጭምር አሰባስቦ ለአገር በጋራ የመሥራት ጥረትን መንግሥታቸው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን ስለብሔር ፖለቲካ ‹‹የሚያቀረሹ›› ቡድኖች መንግሥታቸውን በዘረኝነት እንደሚተቹ ተናግረዋል፡፡ መንግሥታቸው የኦሮሞ፣ የአማራ ወይም የሌላ ብሔር ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑንም አጠንክረው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሁሉ ቢሉም ነገር ግን አንድ ነገር ያመኑ መስለዋል፡፡ እርሳቸው የሚመሩት መንግሥት በሁሉም መስክ አገር ስለመቀየሩ ከገለጹ በኋላ፣ የአገሪቱ ዕድገትና ለውጥ በማይረባ ምክንያቶች እየተደናቀፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ብዙ አስደማሚ ውጤት እያመጣች ያለች አገር በትንንሽ ነገር ስሟ እንዲጎድፍ ጉዞዋ እንዲቆም፣ የጀመረችው ግንባታ እንዲደናቀፍ የሚሠሩ ወገኖች አሉ፡፡ የሞተ ትንሽዬ ትንኝ የተቀመመ ሽቶን ያበላሻል፡፡ እኛም ጋር የሚሠሩ ሥራዎች ወንድም ወንድሙን የሚገድል ከሆነ፣ ሰላም ከሌላ፣ በብሔር የምንገፋፋ ከሆነ ምንም ያህል ለውጥ ብናመጣ ትርጉም የለውም፤›› በማለትም ጠንከር ያለ መልዕክት ያዘለ ሐሳብ አስተጋብተዋል፡፡

አንዱ ሲገድል ኃጢያት/ጄኖሳይድ ሌላው ሲገድል ደግሞ ትክክል ተደርጎ መቅረብ እንደሌለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታቸው በሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በግድያ መወንጀሉን አምርረው ተቃውመዋል፡፡ ስለመፈንቅለ መንግሥት ጉዳይ ያነሱት ዓብይ (ዶ/ር) የመንግሥት ግልበጣ በኢትዮጵያ የማይሳካ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹ኢትዮጵያዊያን ከማንም አገር ጋር ብንዋጋ መከራው እንደ አሁኑ አይከፋም፤›› ብለው፣ መገዳደል እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ መንግሥታቸው ለሰላም ያለውን ዝግጁነት ጠቁመዋል፡፡

የፓርላማ አባል፣ ሚኒስትር፣ ጋዜጠኛ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መሆን ከተጠያቂነት አያስጥልም በማለት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ደካማ መንግሥት ኢትዮጵያ እንዲኖራት መፈቀድ እንደሌለበት ጭምር ተናግረዋል፡፡

የሙስና መባባስን በሚመለከት ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ መንግሥታዊ ሌብነት እንደሌለ የተከራከሩ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ አወዛጋቢውንና አዲሱን የንብረት ማስመለስ አዋጅ፣ እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አጀንዳዎቻቸውን መፍትሔነት ለማሳየት ሞከረዋል፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ያሉ ግጭቶችን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹ሦስት ክላሽ ሲታጠቁ አራት ኪሎ የሚታያቸው›› በሚል የወቀሷቸውን የታጠቁ ኃይሎች መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከንቱ ድካም የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሞላ ጎደል ይህን መሰል ይዘት የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ ወሳኝና አንገብጋቢ በሚል ለተነሱ የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ የሰጠ ስለመሆን አለመሆኑ ሪፖርተር ሁለት የሕዝብ እንደራሴዎችን አነጋግሯል፡፡

በቅድሚያ ስለሙስና ነቀርሳ ጠጠር ያሉ ጥያቄዎችን በዕለቱ ያነሱትን የኢዜማ ተወካዩን አብረሃም በርታ (ዶ/ር)ን ለጥያቄዎ አጥጋቢ ምላሽ አገኙ ወይ የሚል ጥያቄ ሪፖርተር አቅርቦላቸው ነበር፡፡ አጥጋቢ ምላሽ አገኘሁም አላገኘሁም ለማለት እንደሚቸገሩ በመጥቀስ ምላሻቸውን የጀመሩት አብረሃም (ዶ/ር)፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ስርቆት ስርቆት እንደሆነ መቀመጡ አሳማኝ ቢሆንም፣ ነገር ግን ደግሞ መንግሥታዊ ሌብነት እንደሌለ ለማስተባበል የተሄደበት ርቀት አሳማኝ አይደለም ብለዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔ የጠየቅኩበትን ዓውድ ወይ አልተረዱትም ወይ ደግሞ የተባለውን መቀበል አልፈለጉም፡፡ በመንግሥት መዋቅር በተለይ ታችኛው እርከን ላይ ባለ ማንኛውም መንግሥታዊ አገልግሎት በጉቦና ሙስና ሆኗል እንጂ እሳቸው ይሰርቃሉ የሚል ጥያቄ ማንሳት አልፈለግኩም፡፡ ማኅበረሰባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በሙስና እየተጠቃ ነው፣ ነገርዬው አገር ይጎዳል ነበር ያልኩት፡፡ እሳቸው ግን ሚኒስትሮቻቸው እንዲያውም በትንሽ ደመወዝ እየደከሙ እንደሚሠሩ ነበር የተናገሩት፣ ይህ አሳማኝ አይመስለኝም፡፡ ሙስናው አለ ነገር ግን እንታገላለን ተብሎ ቢቀርብ ነበር የሚያስኬደው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሙስናን ችግርነትን ለማመንና ለመቀበል የመቸገር ሁኔታ በመንግሥት በኩል መኖሩን እንደታዘቡ የጠቀሱት አብረሃም (ዶ/ር)፣ ይህ ደግሞ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ያለው ቁርጠኝነት ምን ድረስ ነው የሚለውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የፓርላማውን ውሎ ሲገመግሙም መንግሥት ከፖለቲካ መባላት እንውጣ፣ አገር በጋራ እናስቀጥል የሚል ሐሳብ ማንሳቱን በገንቢነት እንዳዩት ተናግረዋል፡፡ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን በመጥቀስ ለሰላምና ለንግግር ዝግጁ ነኝ ማለቱንም አዎንታዊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኢዜማው ተወካይ አብረሃም (ዶ/ር) በፓርላማው ያሉ የሕዝብ እንደራሴዎች ያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት የፓርላማ ክፍለ ጊዜ የሕዝብን ጥያቄ ከማቅረብ ይልቅ፣ ረዥም ሰዓት በመውሰድ የመንግሥትን ፕሮጀክቶች ሲያደንቁ መዋላቸው ተገቢ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡

የአብን ተወካይ አቶ አበባው ደሳለውም ቢሆን በፓርላማው ክፍለ ጊዜ ላነሷቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አለማግኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የፓርላማ አባላት እየታሰሩ ነው ብለው ላነሱት ጥያቄ የእሳቸውን አለመታሰር በተነፃፃሪነት ማቅረቡ ስህተት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹ክርስቲያን ታደለ ወንጀል ስለሠራ አይደለም የታሰረው በፖለቲካ አመለካከቱ ነው እንጂ፡፡ ክሱን አይተነዋል፣ የሕግ ባለሙያዎችም አማክረናል፡፡ የሚያስከስስ የወንጀል ፍሬ ነገር አላገኘንም፡፡ የፖለቲካ እስረኛ እንደሆነ ነው እኛ የምናምነው፡፡ እኔ እስካሁን አለመታሰሬ ወንጀል አለመሥራት፣ የእሱ መታሰር ደግሞ ወንጀል መሥራት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ባለው መረጃና ማስረጃ መሠረት ነው ሊታይ የሚገባው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትም አጥጋቢ መልስ አለመሰጠቱን የጠቀሱት አቶ አበባው፣ የዓይን እማኞችና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የመሰከሩትን ጉዳይ በቀላሉ አጣጥሎ ማለፍ እንደሚከብድ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ ገለልተኛና ሀቀኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ወደ ቦታው ገብተው ጉዳዩ ተመርምሮ አጥፊዎች ለፍትሕ የሚቀርቡበት ሁኔታ መፈለግ አለበት እንጂ እንዲሁ አልፈጸሙም ማለት አይቻልም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቋማቶች መጥተው እንዲመረምሩት ዝግጁ ነን ቢሉ ነበር መልሳቸው አጥጋቢ የሚሆነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የሐሙሱን የፓርላማ ውሎ የተቀዛቀዘ ሆኖ እንዳገኙት የተናገሩት አቶ አበባው፣ ‹‹መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር፣ ካለው አገራዊ ችግር አንፃር የሚስተካከል ጥያቄ በስፋት አልቀረበበትም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች እንደ መሆናችን መጠን የመንግሥትን ፕሮጀክቶችን ከማድነቅ ባሻገር በየክልሉ ያሉ ችግሮችን ማቅረብ ብንችል ይሻላል፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -