Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን በወቅቱ ማካሄድ ያልቻልኩት በንግድ ሚኒስቴር ጫና ነው አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የንግድ ኅብረተሰብ በቀዳሚነት ይወክላል የተባለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ለዓመታት ያዘገየውን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚካሄድ ለመሆኑ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት መላኩ ዕዘዘው (ኢንጂነር) በጠቅላላ ጉባዔውና በምርጫው ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ ከአዋጁና ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጪ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳይካሄድ የቀረበትን ምክንያትም አብራርተዋል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው ሳይካሄድ እንዲቆይ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል በዋናነት የጠቀሱትም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ዕገዳዎችን ነው፡፡  

እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም በ2014 ዓ.ም. ለማካሄድ ታስቦ የነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ያልተካሄደበት ምክንያት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ ጉባዔውን ላልተወሰነ ጊዜ በማገዱ ነው ብለዋል። በተመሳሳይ የዘገየውን ይህንን ጉባዔ በኅዳር 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ ከቆየ በኋላ ሚኒስቴሩ ጠቅላላ ጉባዔ ለአጭር ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ በደብዳቤ በማዘዙ ሳይካሄድ መቅረቱን አስረድተዋል።

በመጨረሻም ሚያዝያ 2016 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባዔው በዚህ በጀት ዓመት ውስጥ እንዲካሄድ በማለቱ፣ በዚሁ መሠረት ጉባዔውን ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማካሄድ ተወስኖ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም ሊሆን የቻለው ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ ሚኒስቴሩ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ከምክር ቤቱ በቀረበለት ምክረ ሐሳብ መሠረት እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በኋላ የሚዘገይበት ምክንያት እንደሌለ፣ በመሆኑም ጉባዔው በተሰጠው ቀን እንደሚካሄድ እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

‹‹በእኛ በኩል ለጠቅላላ ጉባዔው አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮች በሙሉ ተዘጋጅተዋል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የምርጫ አስተባባሪውም ለሁሉም አባል ምክር ቤቶች ምን ያህል ተሳታፊ ማሳተፍ እንደሚችሉ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጸዋል፡፡ 

ከሕግና ደንብ ውጪ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫው ሳያካሄድ ይህን ያህል ጊዜ ለመቆየቱ ሲቀርቡ የነበሩ ምክንያቶች ተቀባይነት የሌላቸውና ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳይደረግ ሰባት ዓመታት መቆየት አግባብ ባለመሆኑ ተጠያቂነት ሊኖር አይገባም ወይ? ለሚለው ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹እኛ ላለማካሄድ ፈልገን ሳይሆን አስገዳጅ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የተቀመጡ መሥፈርቶችን አባል ምክር ቤቶች አሟልተው መቅረብ ያለመቻላቸው እንቅፋት ነበር ይላሉ፡፡ መሥፈርቱን ያሟሉትን ሁለትና ሦስት የምክር ቤቱ አባላት ይዞ ጉባዔውንና ምርጫውን ለማካሄድ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም፣ ይህንንም ማድረግ እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

የምክር ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅና መተዳደሪያ ደንብ መከበር ያለበት በመሆኑ፣ ሁለትና ሦስቱ አባል ምክር ቤቶችን ብቻ ይዞ ምርጫ ለማካሄድ ሙከራ ቢደረግም አባል ምክር ቤቶች አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ምክንያት የተጠየቀውን መሥፈርት አሟልተው መሳተፍ እንደማይችሉ በማሳወቃቸው ጠቅላላ ጉባዔውን በወቅቱ ለማካሄድ መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ ሊካሄድ የነበረው ጉባዔ የቀረውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።  

ሆኖም የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ በተቀመጠው አዋጅና መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እንዳይፈጸም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጠቅላላ ጉባዔዎቹ እንዳይካሄዱ እየተባሉ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል የሚታገዱትን ነገሮች ማስቆም ቢቻል ኖሮ፣ ጠቅላላ ጉባዔው በተያዘለት የጊዜ ገደብ መካሄድ ይችል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ 

ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲዘገይ፣ በ2012 ዓ.ም. በኋላም 2015 ላይ የፈቀደው፣ ከዚያም ጥቅምት 2016 ዓ.ም. ላይ ሊካሄድ የነበረውን የከለከለው፣ እንደገናም የፈቀደው ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሆኑን ማስረገጥ እንደሚፈልጉና ለጠቅላላ ጉባዔው መዘግየት ከባዱ ምክንያት የሚኒስቴሩ ዕገዳዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አንድ ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ይጠየቁ የነበሩ መሥፈርቶች ቀርተው፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄዱ አግባብነት ላይም በሰጡት ምላሽ፣ ከዚህ ቀደም ይካሄዱ የነበሩ ጠቅላላ ጉባዔዎች ተመሳሳይ ችግር እንደነበረባቸው ገልጸዋል፡፡ 

በ2010 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ተመሳሳይ ችግሮች ነበሩበት በማለት፣ በወቅቱ አባል ምክር ቤቶች በተለያየ ምክንያት በተለይ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ባለማካሄድ ለአገር አቀፉ ንግድ ምክር ቤት መክፈል ያለባቸውን ዓመታዊ መዋጮ መክፈል ባለመቻላቸው፣ ጠቅላላ ጉባዔው ሦስት ዓመታት ከስምንት ወራት ዘግይቶ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም በወቅቱ የነበረው የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አማካይነት ጠቅላላ ጉባዔው ሊካሄድ መቻሉና በጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ቀድሞም የነበሩ ናቸው የሚል አምድምታ ያለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

የዘንድሮው ምርጫ የነበሩ መሥፈርቶችን በማስቀረት የሚካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹የዘንድሮው ጠቅላላ ጉባዔ ልዩ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ እንደ ቀድሞው በአባላቱ ብዛት ሳይሆን እያንዳንዱ ክልልና ማኅበር ባለው የፀና ንግድ ፈቃድ መሠረት ስለሆነ፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመጣ መረጃ መሠረት ሬሾው በምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴው በኩል ተሠርቶ፣ ሁሉም አባል ምክር ቤቶች መቀመጫ ኖሯቸው የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ይህ ሚኒስቴሩ በላከው የፀና የንግድ ፈቃድ ቁጥር ልክ ድልድሉ የተካሄደ ሲሆን፣ ጠቅላላ ጉባዔው 177 ወንበሮች ኖሮት፣ ፕሬዚዳንቱ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱንና የቦርድ አባላቱን በሚስጥር ይመርጣሉ፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ በዚህን ያህል ጊዜ ዘግይቶ መካሄዱ ከአዋጅና መተዳደሪያ ደንብ ጥሰት ባሻገር የፈጠረውን ተፅዕኖ በተመለከቱ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ይህ ኃላፊነት ላይ ያለው ቦርድ በሰዓቱ ሥልጣን አስረክቦ የሥልጣን ሽግግርን ማረጋገጥ ነበረበት፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ባለመደረጉ ምክንያት ሥራዎች ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ እና ባለፉት አራት ዓመታት በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ ይካሄዳል እያልን እያሰብነው የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን አንዱ ምክንያት መጥቶ ሲሄድ፣ ሌላው ምክንያት ሲመጣ፣ ተረጋግቶና አቅዶ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠር አለማድረጉ ትልቅ ተፅዕኖ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ሆኖም እስካለን ጊዜ ድረስ አቅማችን በፈቀደ ጊዜያችንን ሰጥተን ሠርተናል፡፡ አሁን ላይ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ቦርዱ ለንግድ ሚኒስቴር ሲያቀርብ ከጊዜ አንፃር ከዚህ በላይ በተለይም የቻምበር አገልግሎት የነፃ አገልግሎት ስለሆነ፣ ከዚህ በላይ እዚህ ኃላፊነት ላይ መቆየት ከግል ሥራችንና ቢዝነሳችን አንፃር ተገቢ ስለማይሆን፣ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ የጠየቅነውም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አሁን የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ አግባብ ነው? ወይስ አይደለም? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀትን የተመለከተውን አዋጅ ከማሻሻል ጋር ይያያዛል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል ረዥም ጊዜ ዝግጅት እየተደረገ የነበረ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ንግዱንና ዘርፉን ለየብቻ በመነጣጠል ለየብቻ አዳዲስ አዋጆች እንደሚወጡ ተገልጾ ነበር፡፡

የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዋጅና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በሚል ሁለት የተለያዩ አዋጆች ፀድቀው፣ አዲሱ አደረጃጀት ንግድ ምክር ቤቶችን ለሁለት ይከፍላል የተባሉት አዋጆች እንደሚፀድቁም መገለጹ አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ አለ በሚባልበት በዚህ ወቅት ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ባለው አዋጅ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ምን ያህል አግባብ ነው? በተለይ ረቂቅ አዋጆቹ የሚፀድቁ ከሆነ በአዲስ አደረጃጀት ድጋሚ ሊከናወን ነው? ወይስ የተለየ ነገር አለ? ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ መላኩ (ኢንጂነር)፣ እስካሁን ሲገለጽ የቆየውን ጉዳይ እንደ አዲስ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ 

የንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው ረቂቅ አዋጁ ሰሞኑን በተሰጠው ውሳኔ መሠረት በአንድ እንዲጠቃለል ሆኗል፡፡ ስለዚህ ንግድ ምክር ቤቱ ለሁለት ተከፍሎ ይደራጃል የሚለው ጉዳይ ተገቢ ያለመሆኑ ታምኖበት፣ በመንግሥት ውሳኔ እንደተሰጠበት ከተሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት መላኩ ኢንጂነር ምክር ቤቱ የማሻሻያውን አዋጁ በተመለከተ ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፣ አሁን ላይ ማረጋገጥ የተቻለው በአንድ ደረጃ አንድ የንግድ ምክር ቤት የሚቋቋም መሆኑ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ዙሪያ መረጃ ሳይሰጡ የቆዩት ማሻሻያ አዋጁ እየተሠራ የነበረው ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ነው፡፡ በኋላም አዋጁ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤትና ወደ ፓርላማ የሚሄድ መሆኑ፣ ሰፊ ውይይትና ምክክር የሚጠይቅ ስለነበር ጊዜ መውሰዱንም አስታውሰዋል፡፡ 

ከዚህ አንፃር አሁን የመጨረሻ ላይ የተደረሰበት ስምምነት የንግድ ምክር ቤቶች ማሻሻያ አዋጅ ለሁለት የማይከፈል መሆኑ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በነበረን ምክክር ማረጋገጥ የተቻለው አዋጁ አንድ ሆኖ የሚወጣ መሆኑ ነው በማለት አዋጁ አንድ ሆኖ የሚወጣበት መሠረታዊና አሳማኝ ምክንያቶች በመኖራቸው የተወሰነ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ምክንያት ደግሞ በአዋጅ ለአስፈጻሚ አካላት በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በተመለከተ አዋጁን የማውጣት፣ የመከታተል፣ የማቋቋም፣ ሰፐር ቫይዝ የማድረግ፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ብቻ የተሰጠ ሥልጣን በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ በፊት እንደ ሰማነው ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተብሎ ለማቋቋም ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የኢንዱስትሪ ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ማኅበራትን የሚመለከተው አዋጅ ላይ ማኅበራቱን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ነው እንጂ፣ ንግድ ምክር ቤቱን ሊቆጣጠር ስለማይችል፣ አዋጁ አንድ ሆኖ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚወጣ ይሆናል ብለዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ሳይከፋፈል በአንድ አዋጅ ሥር እንዲተዳደር የሚደረግበት ሌላው ምክንያት ብለው የጠቀሱት፣ ከንግድ ጋር የተያያዙ ወደ ዘጠኝ የሚደርሱ ሚኒስትሮች መሥሪያ ቤት ያሉ በመሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢንዱስትሪዎችን ስብስቤ ንግድ ምክር ቤት አቋቁማለሁ ካለ፣ ግብርና ሚኒስቴርም የኢትዮጵያ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ግብርና ስለሆነ የግብርና ንግድ ምክር ቤት እፈልጋለሁ ሊል በመሆኑ ችግር ሊፈጠር ስለሚችል፣ አዋጁ በአንድ እንዲወጣ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ኢንዱስትሪውንም፣ ትራንስፖርቱንም፣ ቱሪዝሙንና ሌሎች ዘርፎች አንድ የሚያደርጋቸውና ለሁሉም ንግድ ፈቃድ የሚሰጣቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመሆኑ፣ እንዲሁም አንድ አገር ላይ በፓርላማ እየወጣ የሚደረገው አንድ ንግድ ምክር ቤት በመሆኑ፣ በተናጠል ይወጣሉ የተባሉ ማቋቋሚያ አዋጆች ሁሉንም ዘርፍ አጠቃልለው በአንድ እንዲወጣ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡    

ምርጫውን በተመለከተ በሪፖርተር ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባቀረበው የፀና የግድ ፈቃድ ቁጥር ልክ የተደለደለው የመቀመጫ ቁጥር መሠረት፣ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት 51 ወንበሮች ይኖሩታል፡፡ ይህም በክልሉ ከ800 የፀና ንግድ ፈቃድ ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ከ600 ሺሕ በላይ የፀና የንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ያሉ በመሆኑ፣ በዚሁ ሥሌት መሠረት በጠቅላላ ጉባዔው 40 ወንበሮች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት 17፣ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ደግሞ 22 ወንበሮችን በመያዝ ትልልቅ ድምፅ የሚኖራቸው መሆኑን ነው፡፡  

የቦርድ አባላት ድጋሚ መመረጥ ይችላሉ ወይ? ለሚለው ጥያቄም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መንደርደሪያ ባስቀመጡት ደንብ መሠረት፣ ‹‹ንግድ ምክር ቤቱን ከዚህ በፊት በቦርድ አባልነት ያገለገለ ሰው ተቋርጦ እንደገና በቦርድ አባልነት መመረጥ አይችልም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

ነገር ግን ይህ ቦርድ አባል ለቦርድ ሳይሆን ለፕሬዚዳንትና ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ተወዳድሮ መምረጥ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ ከተሰናባቹ የቦርድ አባላት ውስጥም ከሁለት ተርም በላይ ያገለገሉ ከሆነ ባሉበት ቦታ መወዳደር የሚችሉበት ዕድል እንዳለ አመላክተዋል፡፡ 

ይህ ብቻ ሳይሆን አገር አቀፉን ንግድ ምክር ቤት በምክትልና በፕሬዚዳንትነት ያገለገለ ሰው አቋርጦ ከሆነ አሁን ሊወዳደር የሚችለው ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ያገለገለ አሁን ላይ በፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችልም፡፡ 

በዕለቱ ለመላኩ (ኢንጂነር) የቀረበው ሌላው ጥያቄ በዘንድሮ ምርጫ በተለይ ለፕሬዚዳንትነትና ለምክትል ፕሬዚዳነትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች እነ ማን ናቸው? ስንት ናቸው? የሚል ነበር፡፡ 

ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸውን የጀመሩት ‹‹ዕጩዎችን በተመለከተ ይህ የእኔ ማንዴት አይደለም፤›› በሚል ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ መመርያ መሠረት ለጠቅላላ ጉባዔው ሪፖርት የሚያቀርበው የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ነው፡፡ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴው ዕጩዎቹ እነ ማን እንደሆኑ አላሳወቅም፡፡ ነገር ግን በዘንድሮ ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት ሦስት ዕጩዎችና ለምክትል ፕሬዚዳንትን አምስት ዕጩዎች እንደሚወዳደሩ እንደነሯቸው ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ደግሞ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ለፕሬዚዳንትነት ሁለት ዕጩዎች፣ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤቶች እንዳቀረቡ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ አላምረው፣ ሦስተኛው ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት እስካሁን ባለው መረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት ለማገልገል ከየምክር ቤታቸው የታጩት አቶ ሰብስብ አባፊራ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንና አቶ አሰፋ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

የዘንድሮው ምርጫ አዳዲስ አባላትን የሚያሳትፍ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ይህም አዳዲስ ክልሎች ከመፈጠራቸው ጋር ተያይዞ የሲዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የደቡብ ምዕራብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የደቡበ ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን አቋቁመዋል፡፡ እነዚህ ንግድ ምክር ቤቶች በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ለጠቅላላ ጉባዔ ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል የአዲስ አባልነትን ውሳኔ ያፀድቃል ስለሚል፣ በዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔ የመጀመርያው አጀንዳ እነዚህን ምክር ቤቶች በቀረቡት ጥያቄ መሠረተ አባልነታቸውን ተቀብለን ተሳታፊ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ንግድ ምክር ቤት አባላት ከ18 ወደ 21 ከፍ ሊል ስለመቻሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡   

ንግድ ምክር ቤቱ አደረጃጀትንና ባለፉት ዓመታት የሠራቸውን ሥራዎች የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ከአባልነት ምንም የተገኘ ነገር የለም ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር አደረጃጀት አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

ጠቅላላ ጉባዔውን የተመለከተ መሥፈርትን ያላማሉ ሥራዎች ሲሠሩ መሥፈርቱን ያለማሟላት እንዲህ ያለውን ችግር የሚያመጡና አገራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የሥራ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ግን ተሰናባቹ ቦርድ ሲመጣ አራተኛውን ስትራቴጂካዊ ፕላን ቀርፆ ነው የገባው፡፡ ሲወጣም የጀመረውን ጨርሶ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በተቋም ግንባታ የተሻለ ነገር ተሠርተዋል፡፡ በግል ዘርፉ አቅም ግንባታ ዙሪያ የተሻለ ነገር ስለመሥራታቸው ጠቅሰዋል፡፡ 120 ሺሕ በላይ ለግሉ ዘርፍ ሥልጠና መስጠቱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ለንግድ ምክር ቤት አመራሮች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከመንግሥት ጋር በዓመት በዓመት በአማካይ ሦስት ጊዜያት ምክክር መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ከ140 በላይ የንግድ ኅብረተሰቡ ጉዳያችን መቅረብ መቻሉንም በማመልከት የተሻሉ ሥራዎች ተሠርተዋል በማለት ንግድ ምክር ቤቱ ሥሩ ያሉትን ሥራዎች ጠቅሰዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች