Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አኃዱ ባንክ ከኪሳራ ወጥቶ ከታክስ በፊት 175 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አኃዱ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በሁሉም መስክ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንና የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅሞ ገቢውን 1.15 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከታክስ በፊት ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ፡፡

አኃዱ ባንክ በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት የ267.7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አጽፎ የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ከኪሳራ ወጥቶ ከታክስ በፊት 175 ሚሊዮን ብር ማትረፉ መቻሉን ትልቅ ስኬት ነው ብሎታል፡፡ 

ባንኩ የ2016 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ በተመለከተ ይፋ ባደረገው ተጨማሪ መረጃ፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን 1.03 ቢሊዮን ብር ማድረሱን አስታውቋል፡፡ ባንኩ በቀዳሚው የ2015 የሒሳብ ዓመት የነበረው የተከፈለ የካፒታል መጠን 672.6 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ 

ባንኩ አሁን የደረሰበት የካፒታል አቅም የባንኩን የፋይናንስ አቅም የሚያጎለብትና ባንኩን ለቀጣይ ማስፋፊያዎችና ኢንቨስትመንቶች መልካም ዕድልን የሚፈጥር ነው በማለት በዚሁ መግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡  

አሁን ያሳየውን አፈጻጸም ያመለከተው የባንኩ መረጃ አገልግሎቱን በመላው አገሪቱ ለማዳረስ በነደፈው ዕቅድ መሠረት የቅርንጫፎቹን ብዛት 104 በማድረስ ከ700 ሺሕ በላይ ደንበኞችን ማፍራት ስለመቻሉም ጠቅሷል፡፡ በቀዳሚው ዓመት የባንኩ ደንበኞች ቁጥር 201 ሺሕ ነበር፡፡ 

ባንኩ በቀዳሚው ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረውን የጠቅላላ ሀብት መጠን በ2016 ዓ.ም. መጨረሻ 6.3 ቢሊዮን ብር በማድረስ መቻሉም ተገልጿል፡፡ 

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰፊዓለም ሊበን እንደገለጹትም፣ አኃዱ ባንክ አቅዶ የተነሳበትን ብዙዎችን የሚያካት፣ የፋይናንስ ተጠቃሚነት፣ ጠንካራ ቤተሰባዊነት፣ በትብብር መሥራት፣ እንዲሁም ዘመኑ የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረጉ በደንበኞቹ ዘንድ እምነትንና ላቅ ያለ ተቀባይነትን በማግኘታችን ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ መሰብሰብ ችለናል ብለዋል፡፡ 

አያይዘው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በአስቸጋሪ የቢዝነስ ዓውድ ውስጥ ብናልፍም ልዩ ልዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ ባለ የደንበኛ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥ ይህንን ውጤት ሊያስመዘግብ መቻላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጤና መፍጠራቸውን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተለይ የብድር ክምችት ያልነበራቸው አዲስ ባንኮችን በከፍተኛ ሁኔታ የፈተነው የ14 በመቶ የብድር ዕድገት ገደብ ያሳረፈው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እንዲህ ያሉ ጠንከር ያሉ ተፅዕኖዎችን በመቋቋም ባንኩ ይህንን አበረታች ውጤት ማስመዝገቡ የሚያሳየው ባንኩ አስተማማኝ አደጋ አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጉ ጭምር ነው ይላሉ፡፡ 

አኃዱ ባንክ በቀጣይ ዓመታት ተልዕኮውንና ራዕዩን ለማሳካት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ በቢዝነስ ማስፋፋት፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ቀልጣፋ አሠራርና ቴክኖሎጂ፣ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት፣ እንዲሁም ተቋማዊ አስተዳደርና ማኅበራዊ ተጠያቂነት ላይ ያተኮረ የቢዝነስ ሞዴል መተግበር የጀመረ እንደሆነም ባንኩ ገልጿል፡፡

ዘመኑ የደረሰበትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ዲጂታል አማራጮችን በመተግበር፣ እንዲሁም ከተለያዩ አጋሮች ጋር በትብብር በመሥራት ለደንበኞቹ አስተማማኝና ምቹ አገልግሎት በመስጠት የጀመረውን ዕድገት ቀጣይነት በማረጋገጥ የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል፡፡

አኃዱ ባንክ በአሁኑ ወቅት 104 በደረሱት ቅርንጫፎች ከ865 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች