Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ምክንያታዊ ያልሆነና የተጋነነ የአገልግሎት ዋጋ ይታይልን!

በኢትዮጵያ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ አድጓል፡፡ ባንኮች አብዛኛው የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው ከዲጂታል የባንክ አገልግሎት ጋር የተሳሰረ ሆኗል፡፡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ሳፋሪኮምና ሌሎች በቴክኖሎጂ ታግዘው ክፍያዎችንና ግብይቶችን በዲጂታል የክፍያ ቴክኖሎጂ እንዲያሳልጡ ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎችም ከአብዛኞቹ ባንኮች በበለጠ ገንዘብ እያንቀሳቀሱ መሆኑም እየተሰማ ነው፡፡

እነዚህ ተቋማትም ሆኑ ባንኮች ለዚህ አገልግሎታቸው የየራሳቸው ታሪፍ አውጥተው እየሠሩ ነው፡፡ አገልግሎቱን በጀመሩ ሰሞን ከባንክ ወደ ሌላ ባንክ ከባንክ ወደ ቴሌኮምና ወደ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚጠይቁት የአገልግሎት ዋጋ በሳንቲም ደረጃ እንደነበር አንዘነጋም፡፡ ከኤትኤም ገንዘብ ለማውጣት ይጠየቅ የነበረውን የአገልግሎት ዋጋ በተመሳሳይ ልናስታውሰው የሚገባ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ግን ይህ የአገልግሎት ዋጋቸው አንድ ብርና ከዚያም በላይ ተሻገረ፡፡ ከባንክ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች ከአምስት ብር በላይ ተሻግረው በአብዛኛው ከአሥር ብር የሚጠየቅባቸው ሆኗል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ ባደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ደግሞ ከሞባይል ባንክ ወደ ቴሌ ብርና ወደ ሌሎች ዋሌቶች ገንዘብ ለማስተላለፍ እስከ አሥር ሺሕ ብር ድረስ ከሆነ አሥር ብር የአገልግሎት ዋጋ አስከፍላለሁ ብሏል፡፡ ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ከሆነ ደግሞ 15 ብር የአገልግሎት ክፍያ እንደሚያከፍል አስታውቋል፡፡ ሌሎች ባንኮችም በአብዛኛው የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ ተመሳሳይ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን ያደረገውን የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ በይፋ ያስታወቀ ቢሆንም ሌሎች ባንካች ግን የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ ሲያደርጉም ሆነ ሲተገብሩ በዝምታ ወይም ለተገልጋዮች ምንም ዓይነት መረጃ ሳይሰጡ ነው።

ከገንዘብ እንቅስቃሴው የአገልግሎት ዋጋ ጭማሪ ባሻገር በተለይ ኢትዮ ቴሌኮም ከሰሞኑ በአንዳንድ አገልግሎቶቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርግ ለተጠቃሚ ስለ ማሻሻያው የሰጠው ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎት ላይ ቀድም ሲል ያስከፍል በነበረው ዋጋ ላይ ማሻሻያ አድርጓል ግን ምንም ዓይነት መረጃ ለተገልጋዩ አልሰጠም። ኢትዮ ቴሌኮም በሌሎች አገልግሎቶቹ ላይ ጭማሪ ያድርግ አያድርግ ባይታወቀም የዋጋ ጭማሪ ያደረገባቸውን ሁለት አገልግሎቶች ግን በተጨባጭ ምሳሌ መጥቀስ ይሻላል፡፡ 

አንዱ በመደበኛ ስልክ አገልግሎት ለአንድ ሰዓትና ለ24 ሰዓት የኢንተርኔት አገልግሎት ለመሙላት ያስከፍል የነበረውን 12 ብር ወደ 13 ብር አሳድጓል፡፡ በተጨማሪም 55 ብር ያስከፍል የነበረውን የ24 ሰዓት ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት ፓኬጅ ደግሞ ወደ 58 ብር ከፍ አድርጓል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ቀደም ሲል ለአንድ ሰዓት ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት ይጠይቅ የነበረውን አሥር ብር ከሰሞኑ ወደ 11 ብር ከፍ አድርጓል፣ እንዲሁም 50 ብር ይከፈልበት የነበረውን የ24 ሰዓት ያልተገደበ የኢንተርኔት አገልግሎት ዋጋ ወደ 52 ብር አሳድጓል፡፡ 

ይህ የቴሌ የዋጋ ጭማሪ ተገቢ ነው ወይ አይደለም? የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ቢሆንም በሚሊዮኖች፣ ያውም 50 እና 60 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ትልቅ ተቋም እንዲህ ያለውን የዋጋ ለውጥ ሲያደርግ በተገቢው መንገድ ለደንበኞቹ ማሳወቅ ነበረበት፡፡ እንደ አንድ ጥሩ የቴሌ ደንበኛ ይህንን የማወቅ መብት ቢኖረኝም ቴሌ ትንፍሽ አለማለቱ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› የሚለውን አባባል የተላለፈ ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡ 

በነገራችን ላይ በግሌ አብዝቼ የምጠቀምባቸው የአገልግሎት ዓይነቶች እንደ ምሳሌ ጠቀስኩ እንጂ በተመሳሳይ መንገድ በሌሎች እጅግ የበዙ የአገልግሎት ዓይነቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። ቁም ነገሩ ግን አንድ ደንበኛ እስካሁን ሲከፍል በነበረው ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲደረግበት ብቻ ሳይሆን ከመደረጉ አስቀድሞ ሊነገረው ይገባል ወይም የማወቅ መብት ያለው መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል። ኢትዮ ቴሌኮም በብዙ መልኩ እያደረገ ያለውን ማሻሻያ በተደጋጋሚ እያደነቅን ቢሆንም እንዲህ ያለውን ቀላል መረጃ ለደንበኞች አለማሳወቁ ሊታረም ይገባል፡፡ 

አትዮ ቴሌኮም ፈጣን በሆነው የለውጥ ሒደቱ ውስጥ እያቀረባቸው የሚገኙ የተለያዩ የአገልግሎት ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ደንበኞቹን እያረካ እንደነበር በሙሉ ልብ እየመሰከርንለት ቆይተናል፡፡ በተለያዩ አገልግሎቶቹ ላይ ደንበኞቹን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ቅናሾች ሲደረግ በሚዲያው ያስነግር እንደነበረው ሁሉ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርግም ይህንኑ አሠራር መከተል አለበት። የዋጋ ቅናሽ ማድረግን በተለያዩ ሚዲያዎች በይፋ ማስነገር ተቋምን የማስተዋወቅ ወይም በበጎነት የመሳል ሥልት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የዋጋ ጭማሪ ማድረግን በይፋ ማሳወቅ ተቋምን የሚያጎድፍ ነው ተብሎ የሚተው ተግባር መሆን የለበትም። ይህ የደንበኞች መብት ነው፣ ምክንያቱም ደንበኞች ለሚያገኙት አገልግሎት የሚከፍሉትን ዋጋ አገልግሎቱን ከመጠቀማቸው አስቀድሞ የማወቅ መብት ያላቸው በመሆኑ። ይህንን ማድረግ ደንበኛውን የሚያከብር ተቋም መገለጫም በመሆኑ። ስለሆነም ይህ ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንደሚስተካከል ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በጥቅል ግን በተለይ በዲጂታል መንገድ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች ላይ አሁን ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ደንበኞች ሳያውቁት መፈጸም የለበትም ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊም ሊሆን ይገባል። የዲጂታል ገንዘብ ዝውውርና የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቶችን ለመሰጠት የሚያስፈልገውን የመሠረተ ልማት ወጪ የመመለስ ወይም የመሸፈን ሒደት የረዥም ጊዜ የሚጠናቀቅ እንጂ በአንድ ጀንበር የሚሆን አይደለም። አንዳንድ ተቋማት ደግሞ ለመሠረተ ልማት ያወጡት ወጪ ካስመለሱ በኋላም ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ከማጋበስ ስግብግብ ባህሪያቸው አይቆጠበቁም። ሁሉ ነገር በእጃችን ስለሆነ የፈለገነውን ያክል ገንዘብ ከተጠቃሚው ላይ እንቆርጣለን በሚል ዕሳቤ የሚሰሩ አሉና ይህን መሰሉ ተገቢነት የሌለው ዕሳቤ በፍጥነት ሊታረም ይገባል፡፡ አንድ ደንበኛ ከራሱ ሒሳብ ላይ አሥር ሺሕ ብር ወደ ሌላ ሰው ስላስተላለፈ እስከ 20 ብር የሚደርስ የአገልግሎት ክፍያ የሚቆረጥበት አግባብ ትክክል ነው? ብሎ መንግሥት ጣልቃ ከመግባቱ በፊት እራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው ለዚህ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት የሚወጣው ወጪ ቀላል ባይሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሃምሳና አንድ ብር ቢበዛ ሁለት ብር ይጠየቅበት የነበረው የአገልግሎት ዋጋዎች በአጭር ጊዜ ከእጥፍ በላይ አንዳንዶቹም ከሁለትና ሦስት እጅ በላይ ጭማሪ የሚደረግበት ምክንያትም ግልጽ መሆን አለበት፡፡ 

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እየበዙ፣ የገንዘብ እንቅስቃሴውም እየጨመረ በሄደ ቁጥር የአገልግሎት ዋጋው ዝቅ ማለት ሲገባው እንዴት ጭማሪ ይደረግበታል?

ከዲጂታል የገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሌላው እንደ ክፍተት የሚታየው 300 ብር ላስተላለፈም 10,000 ብርም ላስተላለፈውም በተመሳሳይ የአገልግሎት አሥር ብርና ከዚያ በላይ መጠየቁ ነው፡፡ 

ስለሆነም ተቋማቱ ይህንን ጉዳይ እንደራሳቸው ሊፈትሹና ማሰተካከያ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ነገሩን ጠቅለል ለማድረግ የዲጂታል የክፍያ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት ለአገልግሎታቸው የሚያስከፍሉት ዋጋ የዚህን ያህል መሆን ነበረበት ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በተጨማሪም የዋጋ ማሻሻያ በተለይም የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ለተጠቃሚው የማሳወቅ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት