Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. የአሶሳ ግብርና ኮሌጅ አካዴሚክ ዲን፣ ከመስከረም ወር 2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም ወር 2009 ዓ.ም. የአሶሳ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ከ2009 ዓ.ም. መስከረም ወር እስከ ታኅሳስ 2010 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንግድና ገበያ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። ከ2010 ዓ.ም. ታኅሳስ ወር ጀምሮ እስካሁን ደግሞ የክልሉ የግብርና ቢሮ ዋና ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስኬት ስለራቀው የስንዴ ምርት፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአርሶ አደሮች ላይ እየተፈጠረ ስላለው ጫና፣ በክልሉ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ትኩረት ስላልሰጠው የግብርና ዘርፍ፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ወደ ክልሉ በሚገባው ግብዓትና ከክልሉ በሚወጣው ምርት ላይ እያሳደረ ስላለው ጫና፣ የክልሉ የኢንቨስትመንት መሬት አሰጣጥ ክፍተቶች፣ የባንኮችን ሚናና አሁንም ድረስ በልማት ባንክ ተይዘው ስላሉ የክልሉ መሬቶች፣ በታጣቂዎች ጫና ምክንያት ብሔራዊ ባንክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ስላሳለፈው ውሳኔ፣ ለታጣቂ ቡድኖች ስለሚከፈሉ ቀረጦች፣ በመንግሥት ደረጃ በጥቁር ገበያ እየተገዛ ስላለ ነዳጅን ጨምሮ፣ ሌሎችም የክልሉ ከግብርናው ዘርፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ናርዶስ ዮሴፍ ከአቶ ባበከር ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተርባለፉት አሥር ወራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረጉ ዋና ዋና ግብርና ላይ የተከናወኑራዎች ምንድናቸው?

አቶ ባበከር፡ እንደ አገር ግብርና ላይ ትኩረት ተደርጓል። እንደ ክልልም ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ ነው። በየጊዜው ከሚገመገሙ ሥራዎች አንዱ ግብርና ነው። ባለፈው ዓመት እስከ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሸፍነናል። በዚህ ዓመት 200 ሺሕ ሔክታር መሬት ጨምረናል። ማለትም በ2017 ዓ.ም. 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዘር ይሸፈናል ብለን ዕቅድ ይዘናል። በእኛ ክልል ዝናብ ዘግይቶ ነው የጀመረው። በዚህ ዓመት መጀመሪያም ዝናብ ሲመጣ በጥቅምት ወር ነበር መምጣት የነበረበት፡፡ ነገር ግን አንድ ወር ዘግይቶ እስከ ኅዳር ድረስ ቆይቶ ነበር። ይህ ቀጥሎ ሚያዝያ መጀመሪያ ላይ መምጣት ሲኖርበት በተመሳሳይ አንድ ወር ዘግይቶ ግንቦት 15 ላይ ነው የጀመረው። አሁን እርሻ ላይ ነው ያለነው። አሁን ከ600 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ታርሷል። ከ400 ሺሕ ሔክታር በላይ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል። አንዱ የምናቀርበው ዘር ነው። እሱን ወደ አርሶ አደሩ አከፋፍለናል። በቆሎና ማሽላ በጣም ከፍተኛ ክፍሉን ይይዛሉ፣ ማለትም ከ1.2 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ 600 ሺሕ ሔክታር በላይ ይሸፍናሉ። ስለዚህም ትኩረት የሚደረገው እነዚህ ሁለቱ ላይ ነው። ቀሪውን 600 ሺሕ ሔክታር ከሚይዙት ምርቶች መካከል አኩሪ አተር፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ ከቅባት እህሎች ሰሊጥ፣ ኑግና ኦቾሎኒ ይጠቀሳሉ። በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ስንዴ እናመርታለን።

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት እንደ አገር ትኩረት ከተሰጠባቸው ምርቶች ዋነኛው ስንዴ ነው። በስንዴ ምርት ላይ የተወሰነ እንቅስቃሴዎች እንዳደረጋችሁና ብዙም ውጤታማ እንዳልነበረ ነው የሰማነው። ከስንዴ ምርት ጋር በተያያዘ ያለው እውነት ምንድነው?

አቶ ባበከር፡- ስንዴ ሁሉም ወረዳ ላይ ለማምረት ጥረት አድርገን ብዙ ውጤታማ አይደለም። ዝናብ በጣም ይበዛል። ሙቀትና ዝናብ ሲፈራረቅበት የተዘራው ስንዴ ዘር የማጥፋት አዝማሚያው በጣም ከፍተኛ ነው። እናም ሁሉም ወረዳ ላይ ማምረት አልተቻለም። አሁን የመረጥነው ወደ ሦስት የሚሆኑ ወረዳዎችን ነው። ሁለት ዓመታት በሁሉም ላይ ሞክረን ከሦስቱ ወረዳዎች ውጪ ስንዴ ማምረት እንደማይቻል ዓይተናል። እነዚህ ክልል ቆላማ ከመሆኑ አንፃርና ሙቀት ስለሚበዛ ያመጣናቸው የስንዴ ዝርያ ዓይነቶች (Varieties) ሙቀቱንና ዝናቡን መቋቋም አልቻሉም።  የእርሻ ግብዓትን በተመለከተ ከምርጥ ዘር ቀጥሎ ዋናው ማዳበሪያ ዩሪያና ኤንፒኤስ ነው። ይህ 203 ሺሕ ኩንታል ተፈቅዶልን እስካሁን 162 ሺሕ ኩንታል ወደ ክልሉ ገብቷል። ይህ በሁሉም ዞኖች አሠራጭተን አርሶ አደር እጅ ገብቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የግብዓት ሥርጭት አሠራር መመርያ (Manual) አዘጋጅተን የክልሉንም ደንብ አሻሽለናል። ከዚህ በፊት በኅብረት ሥራ (Union)፣ በማኅበር በኩል ወረዳ እናደርስ ነበር። ነገር ግን ገንዘቡ ሳይመለስ ሲቀር ብድር ችግር ውስጥ ሲገባ ስለተመለከትን አሠራሩን ቀይረን በዞን ማዕከላት ማውረድ ጀመርን። በዞን ማዕከላት በኩል አርሶ አደሩ ራሱ ቀጥታ ማዳበሪያዎቹን ማግኘት እንዲችል በወረዳ ተደራጅቶም ይሁን በተናጠል መውሰድ የሚችልበት መንገድ ዘርግተናል። በዚህ መልኩ ግብዓቱን ሸጠን እስካሁን ድረስ ባለው በዚህ ዓመት ከተበደርነው ከ737 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ 50 በመቶውን መልሰናል።  በመተከል ዞን ግብዓት ሸጠን ጨርሰናል ማለት እንችላለን። በዚህ ዞን ወደ 62 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ ሸጠን አጠቃለናል። እጥረት በሚገጥምባቸው አካባቢዎች ከአሶሳ ነው የሚጓጓዘው። ከአሶሳ ወደ ተለያዩ ዞኖች ሲሠራጭ ከከማሺ ወደ ተለያዩ ዞኖች ማጓጓዝ ስላልቻልን የተወሰነ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች አሉ። ነገር ግን ከአሶሳ መውሰድ ይችላሉ። እንደ በቆሎ ባሉ የጥራጥሬ ምርቶች በኩል 33 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደምናገኝ ጥርጥር የለንም።

ሪፖርተር ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ምክንያቱም ስንዴ በአብዛኞቹ ዞኖችና ወረዳዎች ሞክረን ውጤታማ ስላልሆነ በሦስት ወረዳዎች ላይ መርጠን ተወስነን ነው እየሠራን ያለነው ብለዋል። ከምርምር አንፃር ኢንስቲትዩቱ ደግሞ በምርምር ያለበትን አካባቢ መላመድ የሚችል (Adopt) የዝርያይነት ማቅረብ እንዳለባቸው ነው በኃላፊነት የተሰጣቸው። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ከኢንስቲትዩቱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ነው?

አቶ ባበከር በመጀመሪያ ደረጃ የእኛ ክልል ላይ ትኩረት ማነስ ነበር። ከፓዊና ከአሶሳ ግብርና ኢንስቲትዩት ጋር እንሠራለን። እነሱም ትኩረት የሚያደርጉት አኩሪ አተርና ሰሊጥ ማባዛት ላይ ነው። አሶሳ ላይ የሚሠራው ለምሳሌ አሶሳ አንድና አሶሳ ሁለት ተብሎ ማሽላ ላይ ነው በስፋት ሠርተው አውጥተው ውጤታማ የሚባሉ ዘሮችን አስገኝተዋል። በመተከልም በአኩሪ አተር ላይ በተሻለ ደረጃ ሄደውበታል። ስንዴ ግን ትኩረት ያገኘው አሁን ነው። ስንዴ እንደ አገር ቀድሞ ሲጀመር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ምርምር አልተደረገም፣ በዩኒቨርሲቲም ሆነ በምርምር ኢንስቲትዩት ወይም በእርሻ ምርምርም ብዙም ትኩረት ሲያደርጉ አልነበረም። እንዲያውም ግብርና ቢሮው ከሁሉም ተቋማት ቀድሞ ነው ስንዴን የሞከረው። ስንዴን በተመለከተ እንደ አገር የተቀመጠ አቅጣጫ ስለነበር በቢሮው ነው ቀድሞ እንቅስቃሴ የተደረገው። በዚህም ወንበራ ላይ ከዚህ በፊት አምጥተን ተላምዷል በተሻለ ደረጃ፡፡ ማለትም በአንድ ሔክታር ከ30 ሺሕ ኩንታል በላይ እናገኛለን። እንዲሁም ማኦ ኮሞ ቀድመን በነበሩን ፕሮጀክቶች እነዚህ አካባቢዎች በተነፃፃሪ ደጋማ ስለሆኑ ቦታዎች ከሌሎች ደጋማ የአገሪቱ አካባቢዎች ጋር ተመሳሳይ የአየር ጠባይ ሁኔታ ስላላቸውም እነሱም ጋር ሞክረን ውጤታማ መሆናቸውን ዓይተናል። በእነዚህ አካባቢዎች በአንድ ሔክታር ከ40 እስከ 46 ኩንታል ምርት እናገኛለን። የአሶሳ ዞን ወረዳዎች ላይ እስካሁን ድረስ አንድ አብራሞ የሚባል ወረዳ ላይ ብቻ ነው ውጤታማ የሆነው። ወረዳው ቀደም ሲል ከጠቀስኩት ከማኦ ኮሞ ወረዳ ጋር የሚገናኝ ቦታዎች አሉት።

ሌላ ወይን አደጋ የሚመስል የአየር ጠባይ ሁኔታ ያላቸው አካባቢዎች አሉ። ወደ እነዚህ የክልሉ አካባቢዎችም የስንዴ ምርት ጥሩ ውጤት የማሳየት ሁኔታ አለው። ከእነዚህ አካባቢዎች በስተቀር ሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ጋር ያለፈውን ሁለት ዓመታት ሞከርን፣ ነገር ግን ውጤቱ በጣም ዝቅ ያለ ነው። በአንድ ሔክታር ሰባትና ከዚያ በታች የሆነ ኩንታል ነው ያገኘንበት። በአካባቢዎቹ ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ በበጋም በክረምትም ሞክረናል፣ ግን እንዳልኩት ከጠቀስኳቸው ሦስት ወረዳዎች ውጪ ብዙም ውጤት ማየት አልቻልንም። በካማሺ የፀጥታ ችግር ስለነበር ገና በእዚህ ዓመት ነው የሞከርነው። ብዙም ውጤት ግን አላየንበትም 10 ወይም ሰባት ኩንታል ነው እየመጣ ያለው። ስለዚህ ዕቅዳችን ውጤት ያመጡት ወረዳዎችን መሬት እንዲያገግም እያደረግን እያሰፋን ለመሥራት ነው። ከዚህ ባለፈ ግን እርሻ ምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲው በዚህ ላይ ምርምር አልሠሩም። ቀድመናቸው ወደ ሥራ ገባን፣ ከዚያ በኋላ ከእኛ ጋር እንዲሠሩ አደረግን፣ ስንሠራ እየተከታተሉ የዝርያ ዓይነቶች (Varieties) ወሰዱ፣ ከፌዴራል እርሻ ምርምር ግብዓቶች እየተሰጣቸው ከእኛ ጋር አብረው እንዲሠሩ እየሞከሩ ነው ያሉት። ስንዴን በተመለከተ አሁን ባለው ሁኔታ አንዱ ችግራችን ውጤታማ የሆነ የዝርያ ዓይነት ማግኘት ነው። ዝም ብለን ለቆላማ አካባቢ ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸውን እነ ቂንቂበርት፣ እነ ቀቀባ፣ እነ አኩልቾና ሾሪማ የሚባሉ የዝርያ ዓይነቶችን እንዲሁ አመጣናቸውና ሙከራ አደረግንባቸው። ስንሞክር ትንሽም ቢሆን ደህና የሚባል አፈጻጸም የማምረት ውጤት ያገኘንበት አኩልቾ የተባለው የዝርያ ዓይነት ነው፡፡ ማለትም በሔክታር ከ30 ኩንታል በላይ። ሌሎቹ ዝቅ ያሉ ናቸው። ስለዚህ የስንዴ ጉዳይ ምርምር አሁንም ይጠይቃል። ለእዚሀ ቆላማ አካባቢ የሚሆን ዝርያ ያስፈልጋል ብለን ለግብርና ሚኒስቴር ሪፖርት አድርገናል። በምላሹ ከግብርና ሚኒስቴርና ከገዥው ብልፅግና ፓርቲ የተላኩ አመራሮች ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መጥተው አርሶ አደሩን ሲያገኙና ሲያዩ ያለውን ሁኔታ ተመልክተው ሪፖርት እንዳደረጉ እናውቃለን። 

ሰፋፊ እርሻዎች አሉ። ሜዳዎች ናቸው። ከአንድ ሺሕ በላይ ባለሀብቶች በክልላችን መሬት ይዘዋል። ከ400 ሺሕ በላይ ሔክታር ሰጥተናቸዋል። ስንዴ ላይ የሞከርናቸው ሙከራዎች በአርሶ አደር መሬት ላይ ነው። ምክንያቱም አንደኛ እንደሚታወቀው በክልሉ ለረዥም ጊዜ የሰላም ዕጦት ችግር ነበር። በዚያ ሰበብ እርሻ የወሰዱ ሰዎች ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉበት ሁኔታ ነበር። አሁን ግን ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። አምና ከጠቀስኳቸው አንድ ሺሕ ባለሀብቶች 69 ባለሀብቶች 13 ሺሕ ሔክታር አልምተው ነበር። በዚህ ዓመት በተሻለ ደረጃ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እየገቡ ነው። እንዲያውም አሁን  ምርጥ ዘር ማባዛት፣ በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመተከልና በአሶሳ ዞን ላይ ዘር የማዳቀል ሥራ እየተሠራ ነው።

ሪፖርተር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር የተሳሰሩ ምርቶቻችሁ ምን ያህል ናቸው? ይህንን ያልኩት ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አኩሪ አተር ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሚገኘው አብዛኛው ምርት እንዲባክን የሚያደርገው ከመጋዘን ጋር ወይም ከምርቱ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ ያለው ሒደት ነው የሚል ጥናት ከጥቂት ወራት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር። በመኸር ወቅትና በኋላ የሚባክነውን ምርት ከመቀነስ አንፃር፣ እንዲሁም አርሶ አደሩንም ከገበያ ጋር ከማስተሳሰር አንፃር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር እየሠራችሁት ያላችሁት ሥራ አለ ወይ? ከምርት ገበያው ጋር ያላችሁ ግንኙነት በጥቅሉ ራሱ ምን ይመስላል?

አቶ ባበከር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ያለን ግንኙነት ትንሽ ወደ መውረድ ያዘነበለ ነው። ለምሳሌ አኩሪ አተር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በአማራ ክልል በብዛት ይመረታል፡፡ እናም ምርት ገበያው ውስጥ የምርቱ ዋጋ ወርዶ ነው ያለው። እዚህ ክልል ውስጥ ብዙ ክምችቶች ነበሩ። አንድ ባለሀብት እስከ አርባ ሺሕ ኩንታል፣ 10 ሺሕ፣ 30 ሺሕ ኩንታል የሚያከማቹ አምራች ባለሀብቶች ነበሩ። እነዚህን ክምችቶች ወደ ገበያ ለማድረስ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላይ ያለውና ውጪ ላይ ያለው ገበያ እኩል መመጣጠን አልቻለም። በክልሉ በአርሶ አደር ደረጃ በአንድ ሔክታር ከ18 ሺሕ እስከ 24 ሺሕ ኩንታል ድረስ ምርት ይገኛል። ሰፋፊ ኩታ ገጠም እርሻዎች ላይም በአኩሪ አተር ምርት ላይ ጥሩ ሥራ ተሠርቷል። ዋጋው ግን እየወረደ እየወረደ መጥቶ አሁን ላይ እየፈተነን ነው ያለው። በአሁኑ ወቅት ባለሀብቶች የሚጠይቁን ይፈቀድልንና ከምርት ገበያው ውጪ ለድርጅቶች እንሽጥ የሚል ነው። ከእነሱም ጋር ይህንን ጥያቄ በተመለከተ በተደጋጋሚ የግብርና ሚኒስቴር የሚጠራቸው መድረኮች ላይ ሄደን ውይይት አድርገናል። ነገር ግን ይህንን ለማሻሻል አልቻልንም። እነሱም ዘንድ ወደ ምርት ገበያው የሚሄዱ እንደ ሰሊጥ፣ ቡና፣ አኩሪ አተር፣ የተለያዩ የቦሎቄ ዓይነቶች አሉ። 

ሪፖርተርየአማራ ክልል አርሶ አደሮች 2015 .ም. የገጠማቸውን ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት የገበያ ዕጦት ችግር የመፍታት ግዴታ ጀርባው ላይ የወደቀው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የፌዴራል አዋጅን የሚቃረን አሠራር ሥራ ላይ መዋሉን፣ ይህም ክልሉ ከምርት ገበያ ውጪ የአኩሪ አተር አቀነባባሪዎች ቀጥታ ምርቱን ከአርሶ አደሮች እንዲገዙ ማስቻሉን፣ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ (/) በኅዳር ወር በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተደረገ አንድ ጉባዔ ላይ አሳውቀው ነበር።  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም አርሶ አደሩ እንዲሁ ምርቱን ቀጥታ መሸጥ የሚያስችለውን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር አልሞከራችሁም?

አቶ ባበከር ተደጋጋሚ መድረኮች ነበሩ። አዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በነበረ ውይይት የይፈቀድልን ጥያቄ አቅርበን መልስ አላገኘንም። ይህንን ዓይነት አሠራር ተግባራዊ እናድርግ ቢባል እንኳን ጭነው ሲሄዱ ይያዛሉ፣ የገዙት ምርትም ይወረሳል። ያለ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጫን አትችሉም፣ አርሶ አደሮች በቀጥታ ለአቀነባባሪዎች መሸጥ አትችሉም የሚል አካሄድ ነው ያለው። የአማራ ክልል ይህንን ማድረጉን መረጃ የለኝም። እኛ ጋር ግን እንዲህ ዓይነት የግብይት ሒደቶች ሲኖሩ ከክልሉ ሳይወጡ እዚሁ ነው የሚወረስባቸው። ብዙ ሰዎችም በእንዲህ ዓይነት መንገድ ለመሸጥ ሲሞክሩ ተይዞባቸዋል። እኛ ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻም ቢሆን አርሶ አደሩ በቀጥታ ከምርት ገበያ ሸጠው እንዲበረታቱ ብለን ጠይቀን ነበር። ምክንያቱም አርሶ አደሩ ያገኘውን ምርት በትክክል ካልሸጠና ትርፍ ካላገኘበት፣ የግብዓት ዋጋ ካልመለሰለት፣ ለማምረት ያወጣው ጉልበት ዋጋ ከሽያጩ የሚያገኘው ገቢ የማይሸፍንለት ከሆነ ምርቱን በቀጣዩ እሺ ብሎ ወደ ማምረት አይሄድልንም። እነዚህን ምክንያቶች ጠቅሰን ጉዳዩን በተደጋጋሚ ብናነሳም አልተግባባንም፣ ወደ ውሳኔ አልደረስንም። እናም ሁኔታው በዚህ ዓይነት ተንጠልጥሎ እያለ ምርቱና የማምረት ፍላጎቱ ደግሞ እየቀነሰ መጥቷል። ዋናው ምክንያት ደግሞ ዋጋው ከምርት ገበያው ጋር ተሳስሮ በገበያው የሚሰጠው ዋጋ ለምርት ከሚወጣው ዋጋ ያነሰ ነው። 

ሪፖርተር ከውል እርሻ (Contract Farming) ጋር በተያያዘ በክልሉ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? 

አቶ ባበከር እሱ ጥሩ ነው። ከዚህ በፊት የውል እርሻ (Contract Farming)  እንደ አገር ከመፅደቁ በፊት እዚህ ክልል ቀድመን ነው የጀመርነው። አርሶ አደሮችን ከነጋዴዎች ጋር ለማስተሳሰር ቀድመን ነው የሠራነው። እናም በዚህ መንገድ አኩሪ አተር ላይ በስፋት ይሠራሉ። በመተከልና በአሶሳ ዞን በውል እርሻ አስተሳስረን በስፋት እየሠራን ነው።  አስቀድሞ  ባለሀብቶች ምንም ግብዓት አስቀድመው ለአርሶ አደሩ ሳያቀርቡ የውል እርሻ ተፈራርመናል ብለው ሰነድ የሚያቀርቡበትና ምርቱ ሲደርስ ከአርሶ አደሩ ምርት የሚቀበሉበት አካሄዶችን ስላየን መመርያ አወጣን። በዚህ መመርያ መሠረት ባለሀብቶች ለሚዋዋሉት አርሶ አደር መጀመሪያ ሥልጠና ይሰጣሉ፣ በውል መሠረት ቀድመው የእርሻ ግብዓት ያቀርባሉ፣ እንዲሁ ቀድመው መፈጸም የሚገባቸውን ገንዘብም ይከፍላሉ፣ መጨረሻ ላይ ምርቱ ሲደርስ ወቅቱ ላይ በሚኖረው የተሻለ ዋጋ መሠረት ምርቱን ይገዛሉ። ባለሀብቶቹ በየጊዜው የደረሱበትን ሒደቱን ማሳያ ሰነድ ለግብርና ቢሮ እያቀረቡ እኛ ከአርሶ አደሩ እያረጋገጥን መቀጠል የሚችሉበትን ማረጋገጫ እንሰጣቸዋለን። 

ሪፖርተር በውል እርሻው አካሄድ ላይ አርሶ አደሩ ዘንድ ያለው ምላሽ ምን ይመስላል?

አቶ ባበከር ውጤታማ ነው፣ ተግባብተው እየሠሩ ነው። 

ሪፖርተር፡ የግብርና ኢንቨስትመንቶች ላይ ከፀጥታም ጋር በተያያዘ ላለፉት ጥቂትመታት ክልሉ በጣም እየተጎዳ እንደነበረ ሪፖርቶች ያሳያሉ። እርስዎም ቀደም ሲል ፈቃድ ከነበራቸው አንድ ሺሕ ባለሀብቶች አምና 69 ባለሀብቶች ነው ተመልሰው ወደ ሥራ የገቡና ያመረቱት ብለዋል። አሁን እየወጡ ባሉ ሪፖርቶች መሠረት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ከአምናው በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሲገልጹ ይደመጣል። የግብርና ኢንቨስትመን አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ እንዴት ነው? 

አቶ ባበከር በክልሉ ውስጥ የተሻለ ነገር አለ። ከአጎራባች ክልሎች ጋር በተያያዘ ግን በጣም እየተቸገርን ነው ያለነው። በኦሮሚያ ክልል በወለጋ በኩል ግብዓት ለማስገባት እንቸገራለን። በአማራ ክልል በኩልም በተመሳሳይ አልፈው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመግባት የሚቸገሩበት ሁኔታ ነው ያለው። ኢንቨስተሮች ከአጎራባች በኩል ባሉ ሁኔታዎች ወሰን አካባቢ እየሠሩ ያሉ በተለይ በጣም ይቸገራሉ። ለምሳሌ መተከል ዞንን ብንወስድ ሰፋፊ መሬቶች ወደ እነ አቡልጉስና እናቡልዳ የተባሉ አካባቢዎች ኢንቨስተሮች በሺዎች የሚቆጠር ሔክታር ነው ለማልማት የወሰዱት። አንድ ኢንቨስተር ከአምስት ሺሕ ሔክታር አንስቶ፣ 14 ሺሕ ሔክታር፣ 17 ሺሕ ሔክታር ይወስዳል፡፡ እስከ 20 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማልማት የወሰዱ ኢንቨስተሮች አሉ። ታዋቂ የአገሪቱ ኢንቨስተሮች በትልልቅ አቅም መንቀሳቀስ እየቻሉ እየገጠሟቸው ባሉ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በጣም በተወሰነ ትንሽ አቅም እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት። እነዚህ ኢንቨስተሮች በፀጥታው ሁኔታ ተገፍተው አሁን ከክልሉ የአገር ውስጥ አዋሳኝ አካባቢዎች ይልቅ፣ ከሱዳን አጠገብ ባሉ የድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎቻቸው ላይ ነው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት። በዚህ በኩልም ማኦ ኮሞ ወደ ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎቻችም እንዲሁ ሰፋፊ እርሻዎች ያሏቸው ኢንቨስተሮች አሉ። ግን ባለሀብቶች እነዚያ አካባቢዎች ላይ እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አይችሉም። ለምሳሌ እንደ ዳንጉራና ጉባ በመሳሰሉ መሀል ላይ ባሉ አካባቢዎች እርሻዎች ያሏቸው ባለሀብቶች ሥራዎቻቸውን በደንብ ጀምረዋል፣ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። አሶሳ ዞን እንደፈለጉ የሚንቀሳቀሱበት ነው። በሌላ በኩል በካማሺ በየወረዳው ከአርባ እስከ ሃምሳ የሚደርሱ ሰፋፊ ሔክታር መሬት የሚሸፍን እርሻዎች የወሰዱ ፈቃድ ያላቸው ኢንቨስተሮች አሉ። ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል አልፈው ወደ እዚያ ለመግባት ይቸገራሉ። በሌላ በኩል ወደ ካማሺ መግቢያ የለም፡፡ ክረምት ሲገባ ትራንስፖርት ይቋረጣል፡፡ በዚያ ምክንያት በካማሺ የሥራ እንቅስቃሴያቸው እንደምንፈልገው አልሄደም። ለምሳሌ ምርጥ ዘር ከዚህ በፊት በአገር ደረጃ ራሱ የሚመረተው በሎጂከንፎና በያሶ ወረዳዎች ውስጥ ነበር። 80 በመቶው ያህል የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ፍላጎት ከዚህ በሚመረተው ነበር የሚሸፈነው። አሁን ግን በወለጋ በኩል ወደ እዚያ ለማለፍ ስለሚቸገሩ እነዚያ እርሻዎች ሥራቸውን ሲያቋርጡ ነው በኢትዮጵያ ደረጃ የምርጥ ዘር ነገር አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ የተነሳው። ከዚያ በፊት በነበረው ሒደት ምርጥ ዘር በጭራሽ አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ሆኖ ተነስቶ አያውቅም ነበር። በፊት የተሻለ ደረጃ ላይ ነበር። ስለዚህም ነገሮቹ ውስብስብ ናቸው። በአሶሳ ዞንና ሌሎች በክልሉ መሀል ውስጥ ባሉ ሰላም በሆኑ ቦታዎች ላይ ኢንቨስተሮች እየተንቀሳቀሱ ነው ያለው። የግብርና ቢሯችን ግን  ምን ያህሉ በሥራ ላይ ነው? ምን ያህሉ ደግሞ በቶሎ ወደ ሥራ ሊገባ ይችላል? የሚለውን መረጃ እየሰበሰብን የመከታተያ የአሠራር ሰነድ አዘጋጅተን፣ የመለየት ሥራዎችን እየሠራን ነው ያለነው፣ በቢሮው ሥር የክትትል ዘርፍ አለን፣ ይህ ዘርፍ አሁን እንዳልኩት መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ላይ ነው። 

ሪፖርተር ባለሀብቶች ምን ያህል የተመዘገበ ካፒታል አላቸው? ወደ ሥራ ሲገቡስ ምን ያህል ካፒታል ማንቀሳቀስ ይችላሉ ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?

አቶ ባበከር– የተወሰነ ጭማሪ ወይም ቅናሽ ታሳቢ ተደርጎ ራሱ አጠቃላይ ያስመዘገቡት ካፒታል መጠን በየጊዜው ሲታይ ይለዋወጣል። ባለሀብቶች አንዳንዴ ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ ገንዘቡን ከሌላ አካል ገንዘብ የራስ አስመስሎ በማምጣት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት የሚጥሩ አሉ። ብዙውን ጊዜ እዚህ መጥተው መረጃዎችን የሚሰጡ ኢንቨስተሮችን በምንመለከትበት ጊዜ ግን በእነዚህ አካሄዶች የሚመጡትን እየተቀበልን በኋላ የማረጋገጥ ሥራዎችን ስንሠራ፣ የባንክ ሒሳባቸው ባዶ ሆኖ የሚገኙ አሉ። እነዚህ አብዛኞቹ መሬት ለመያዝ፣ ብድር ለማግኘት ነው ጥረታቸው። በእንዲህ ዓይነት ተግባራት ተሳታፊ የሆኑ ከ18 በላይ የሚሆኑ መሬት ያስያዙበትን ካርታ ሳይቀር ለልማት ባንክ የማስረከብ ሥራ ሁሉ የሄዱበት ሁኔታ አለ። ያው ተቀራርበን ለመሥራት እየሞከርን ነው። ግን እነዚያ ካርታዎች አሁን በልማት ባንክ እጅ ነው ያሉት፡፡ ባለሀብቶች ዘንድ መኖር የነበረባቸው ነገሮች የሉም፣ ምን የለም፡፡ ብድሩ እንዴት እንደተሰጠ ሁሉ ጭራሽ ግልጽ አይደለም። እና አሁን እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እስከ መፈጠር ድረስ የተደረሰበትና የሚታይባቸው ሁኔታዎች አሉ። በሌላ በኩል ትክክለኛ የተረጋገጠ የሀብት ምንጭ ያላቸው ባለሀብቶች ደግሞ አሉ። 

ሪፖርተር ከልማት ባንክ ጋር የተያያያዘው ነገር መታትም የቆየ እንደሆነ በተለያዩ መረጃዎች ሪፖርቶች ሲያመላክቱት ነበር። እርስዎ ያነሱት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በተለይ የተቆራኘው ጉዳይስ መፍትሔ አግኝቷል ወይ? 

አቶ ባበከር እነዚህን 18 ባለሀብቶች በተመለከተ ከልማት ባንክ ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ አልተፈታም፣ መፍትሔ አላገኘም። 

ሪፖርተር ያለፈው አልፏል በሚለው መርህ ቢኬድ እንኳን አሁንስ እንዲህ ዓይነቱባለሀብቶች እንቅስቃሴ በክልሉ ኢንቨስትመንቶች እንዳይደገም፣ ግለሰቦች ክልሉን በእንዲህ ዓይነት መንገድ እንዳይጠቀሙበት የሚያደርጉ መፍትሔዎች አዘጋጅታችኋል ወይ? 

አቶ ባበከር አዎ፣ ባለፉት ጊዜያት የኢንቨስትመንት ፈቃድ በዘፈቀደ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። አሁን ግን ማረጋገጫዎች እየተሠራ፣ ያስያዙት ፈቃድ ለማውጣት የሚያቀርቡት ሰነድ በራሱ ከባንክ መሆኑን፣ ባንክ ጋር ተመልሰን በመሄድ የማረጋገጥ ሥራዎች የምንሠራበት አሠራር አለን። በዚህ አሠራራችን ውስጥ ተጻጽፈን የባንክ ምላሽ ቀጥታ ወደ መሬት አስተዳደር ቢሮ፣ ከመሬት ቢሮ ወደ እኛ ከመጣ በኋላ ነው የኢንቨስትመንት ቦርድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለግምገማ የሚያቀርባቸው። ከዚህ ቀደም ዝም ብሎ በመጣው የማረጋገጥ ሥራ ሳይሠራበት፣ እነዚህ በኢንቨስተር የቀረቡ ወረቀቶች እውነተኛ ማስረጃ ናቸው? እዚያ ባንክ ላይ ሲፈተሽ አለ? ወይስ የለም? የሚለው ሳይጣራ ፈቃድ የማስተላለፍ ሥራ ሲከናወን ነበር። አሁን ግን ሰነዱ ወደ ባንኮች ይመለሳል፣ ባንኮቹ እነሱ ጋር ስለመኖሩ ማረጋገጫ ሲያቀርቡልን ነው መሬት የሚተላለፈው። 

ሪፖርተርየካቲት ወር በአዳማ ከተማ በሰላም ሚኒስቴር በተዘጋጀ መድረክ ላይ ተገኝተው የነበሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ስለአጠቃላይ የክልሉ ሁኔታ ሲናገሩ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ ግብዓቶችን ማስገባትም ሆነ ምርቶችን ለመላክ በአማራ ክልል በኩል በሚያልፈው መንገድ በኩልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል በኩል ባለው መንገድ ማለፍ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረውብናል ብለው ነበር። ኃላፊው በንግግራቸው ተሽከርካሪዎች የማይመለሱበትና እኛም ዘንድ የማይደርሱበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ማለታቸው ይታወሳል። የግብርና ምርቶች የገበያ ትስስሩም ሆነ መቀበል የሚቻለው የግብዓት መጠን ጉዳዮች ከዚህ አንፃር በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነው ያለው? 

አቶ ባበከር በአጠቃላይ የወረደው መዓት ነው። በዚህ ሰበብ ብቻ የክልሉ መንግሥት ፈርሞ ይወስደው የነበረ 516 ሚሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ የተበደርነው ገንዘብ ተቋርጧል። ይህ እንግዲህ በዚህ ዓመት ብቻ ነው። ልማት ላይ ለማዋል የምንቀበለው የነበረውን ይህንን ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ እንዳንወስድ በአንዴ ነው ያነሳው። ይህ ደግሞ የክልሉን ደመወዝ የመክፈል አቅም ሁሉ አደጋ ላይ እስኪወድቅ ያደረሰ ሁኔታ ላይ ሁሉ ጥሎን ነበር። ለምሳሌ በ2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ለማድረስ  ዩሪያ ማዳበሪያ ጭነው ሲመጡ የነበሩ 11 ተሳቢ መኪኖች መንዲ የሚባል ሥፍራን አልፈው መጨረሻ አካባቢ ሲደርሱ በሙሉ በሸኔ ታጣቂ ኃይሎች ተወስደዋል። ይህ ማለት 11 ተሳቢ መኪኖችና የተሸሟቸው ግብዓቶች በሙሉ ሄዱ፣ በቃ አለቀ፣ ዕዳ ሆነ። ማኦ ኮሞ  ሙሉ በሙሉ ያኔ ወረራ ተደርጎበት ተመቶ ስለነበረ መጋዘኖችን በሙሉ ከፍተው ነበር ምርት የሚዘርፉት፡፡ ዘርፈው ጭነው ነው የወሰዱት። በሎጂከንፎ፣ በቲባቲ መተከል አካባቢ፣ ቡለን በሚባሉ አካባቢዎች ሁሉ ገብተው ግብዓቶችን እስከ መውሰድ ደርሰው ነበር። በዚህ ዓመት መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመጓጓዝ ላይ የነበሩ አምስት መኪኖች ተወስደውብናል። ሙሉ በሙሉ ጠፍተውብናል። ያኔ ዩሪያ ማዳበሪያ ገዝተን ለሕዝቡ ለማድረስ እያመጣን ሳለ መንገድ ቆርጠው እዚያ ቀረ። የመከላከያ ኃይሎች እየተከታተሉም ቢሆን ችግር ውስጥ ወድቀዋል። በእንዲህ ዓይነት መንገድ ያጣናቸው ነገሮች ሁሉ ለሚመለከታቸው የፖሊስና የመከላከያ ኃይሎች በጠቀስኩት ሁኔታ መወሰዳቸውን ማረጋገጫ ደብዳቤዎች በክልሉ መንግሥት ተጽፈውልን፣ የክልሉ መንግሥት የከሰረባቸው ሁኔታዎችን እንመለከታለን። ከክልላችን መኪኖች ወጥተው ሲሄዱ ይወሰዳሉ፡፡ በተለይ አብዛኛው መሰል ድርጊቶች በአንዳንድ ውስን መንገዶች ላይ ነው የገጠሙን። በመስከረም ወር ለዘንድሮ እርሻ የሚውል ግብዓቶች ሲመጡልን አደጋዎች ውስጥ የገበቡት ሁኔታ ገጥሞናል። 

ሪፖርተር እርስዎ እንደገለጹት በዚህ ዓመት በክልሉ ይሠራበታል የተባለው 1.2 ሚሊዮን ሔክታር ነው፣ ይህ ሰፊ መሬት ነው። በዓይነት ደረጃም ይመረታሉ የተባሉት ምርቶች ብዛት አላቸው። አሁን ያቀዳችሁትን ለመሥራት ግን አሁንም የፀጥታና የሰላሙ ጉዳይ አደጋ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ሁኔታው ክልሉን ራሱ አደጋ ላይ አይጥለውም ወይ? ምን ዓይነት መፍትሔዎችን ነው ያሰባችሁት? 

አቶ ባበከር ይህ ችግር እንደ አገር ነው ሊፈታ የሚችለው፡፡ እንደ አገርና እንደ መንግሥት የምንነጋገርበት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ባለሀብቶች የሚንቀሳቀሱት ለኦነግ ሸኔ እየከፈሉ ነው። በዚህ ምክንያት ከሌላው ክልል በበለጠ በዚህ ክልል የኑሮ ውድነት ሁኔታ በጣም ከፍ ብሎ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ከፍለው ነው የሚመጡት። በእኛ ክልል ብዙ ባለሀብቶች ተዘርፈዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ነጋዴዎቹም እርስ በርስ ይጠላለፋሉ። መረጃዎቻችን እንደሚጠቁሙት ከኦነግ ሸኔ ጋር በጣም የሚተዋወቁ፣ የሚገናኙ አሉ። ገና መኪና ከአዲስ አበባ ወደ ክልላችን ሳይንቀሳቀስ ‹‹የእገሌ መኪና እየተንቀሳቀሰ ነው›› ብለው የሚነግሯቸው አሉ፣ በርካታ መኪናዎችን ያጣነው በዚህ መንገድ ነው። የመንግሥት መኪኖች ተጭነው ከዚህ ሲንቀሳቀሱ ‹‹እንዲህ እንዲህ ዓይነት መኪኖች እየተንቀሳቀሱ ነው›› ተብሎ ከተማዎቹን ጨምሮ ለታጣቂዎቹ መረጃ ይሰጣቸዋል። ጠብቀው የታጣቂ ቡድን ድርጊታቸውን ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ መኪኖችም አጥተናል። ወስደውብን ይሸጡታል፣ የፈለጉትን ያደርጉታል። የባለሀብቶችም በተመሳሳይ። ወደ ክልሉ ሲመጣ ግን ተከፍሎበት ነው የሚመጣው።

ሪፖርተር ይህ ሁሉ እየሆነ እንዴት ነው ነገሮችን አስተካክሎ የተረጋጋ ለማድረግ የሚቻለው?

አቶ ባበከር እዚህ ክልል ነገሮችን አስተካክሎ የተረጋጋ ለማድረግ ከባድ የሚሆነው ለብዙ ዓመታት በነዳጅ ማደያ ነዳጅ የለም። በመንግሥት ሆነ በሌላ በፍፁም ከነዳጅ ማደያ መግዛት አንችልም። 

ሪፖርተር ለምን? እንዴት? እዚህ ላይ በደንብ ማብራሪያ ሊሰጡ ቢችሉ? 

አቶ ባበከር ነዳጅ የለም፣ አይመጣም። የሚመጣው መንገድ ላይ ሳይደርስ ይቃጠላል። ብዙ ባለሀብቶች ተቃጥሎባቸዋል። ስለዚህ ምን ተፈጥሯል? በመከላከያ ታጅቦ ካልመጣ በስተቀር አያልፍም። ብዙ አስመጪዎች ደግሞ ሁልጊዜ መታጀብ አይፈልጉም። ከፍለው ማለፍ የሚፈልጉ አሉ፣ በክፍያ ሲጣሉ ደግሞ ይቃጠልባቸዋል። እዚህ ክልል አብዛኛው የምንጠቀመው ነዳጅ የሚገባው በጥቁር ገበያ ነው። ለእርሻ መኪኖችና ለትራክተሮች መንቀሳቀሻ፣ በአጠቃላይ ለመንግሥት መኪኖችች እንኳን በመንግሥት ታሪፍ እናወራርዳለን፣ ግን የምንገዛው በጥቁር ገበያ ዋጋ ነው። ክልሉ ክበብ ውስጥ ነው ያለው። በአጎራባች አገር በሱዳን በኩል መንገድ ዝግ ነው (ከሱዳን ራሱ ወደ ክልላችን ከ90 ሺሕ በላይ ተፈናቅለው የገቡ አሉ ተጨናንቋል)፡፡ በኦሮሚያ በኩል በጣም ብዙ ወደ እኛ ከተሞች የሚፈናቀሉ አሉ፣ በአማራ ክልል በኩልም ለሥራ እንዲሁ ብዙ ወደ ክልላችን የሚመጡ አሉ። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ አሁን በጣም ሰላም ነው፡፡ ማንም ሰው የፈለገው ቦታ እንደፈለገ ይሄዳል፣ ይመጣል። ከአሶሳ ወደ መተከልም ካማሺም ማኦ ኮሞም እንሄዳለን፣ እንመጣለን፡፡ በውስጥ ሁሉም ቦታ ሰላም ነው። ግን አጎራባቾቻችን ዘንድ ያለው ነገራችን ሰላም አይደለም። የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክም ጫና ፈጥሯል፡፡ ይህ በክልላችን ዕቃዎች በጣም ውድ ውድ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከዚህ ሲወጡም ወደ እዚህ ሲመጡም ለፀረ ሰላም ቀረጥ ይከፍላሉ፣ ያን ማስተናገድ ግዴታችን ነው የሚሆነው። አለበለዚያ ሕዝባችን ማግኘት የሚፈልገው ምርትና ሸቀጣ ሸቀጥ ይጎድለዋል። ይህንን ሁኔታ በማለፋችን ሕዝባችን ቢያንስ ቢያንስ የሚያስፈልገውን ነገር በውድ ዋጋም ቢሆንም የሚያገኘው ይኖረዋል። ነጋዴው እሱ ከፍሎበት በሆነ መንገድ የሚያስገባውን እንዲያስገባ ከማድረግ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም። ይህ ችግር እስኪፈታ ድረስ መንግሥት እየሠራበት ነው፣ እየተዋጋበት ነው ያለው፡፡ ይህንን ችግር ግን አልተፈታም። 

ሪፖርተር፡- ይህ ችግር እንዲፈታ መንግሥት ምንድነው ማድረግ ያለበት ብለው ያምናሉ? 

አቶ ባበከር መንግሥት ማድረግ ያለበት? አንደኛ በየቀበሌው ከሕዝቡ ጋር ለረዥም ጊዜ የተላመዱ፣ የፀጥታ ኃይል ሲመጣ ልብስ የሚቀይሩና ሕዝብ ውስጥ የሚቀላቀሉ፣ ለመምታት የሚቸግሩ፣ ሁኔታውን እያዩ ሲመቻቸው ወጥተው የሚዘርፉና ብዙ ሰዎች ሥራ ፈት ሆነው ለዘረፋ የተዘጋጁበት ሁኔታ አለ። በዚህ አግባብ የፀጥታ ኃይል ቀጥታ ሄዶ ተዋግቶ ፀረ ሰላምን ማጥፋት ሜዳ ላይ ያለ ነገር አይደለም፣ በጣም አስቸጋሪ ነው። ሕዝብ መሀል፣ ሴቶችና ሕፃናት ዘንድ ነው ያሉት። የፀረ ሰላም ኃይሎች አካሄድ ሁኔታዎች ቀለል ያሉ ሲመስል እየገቡ መዝረፍ ነው ሥራቸው። ይህ እስኪፀዳ ረዥም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። ረዥም ጊዜ ወስደናል፣ አሁንም መቀጠሉ አይቀርም። እና በርግጥ አሁን የጠቀስኩትን ሁሉ ሕዝቡ ይረዳል። መንግሥት ማድረግ ያለበት ነገር አለ። በሕዝቡ በኩል ወደ እርሻ መሄድ ይችላሉ፣ ወደ ድንበርና አዋሳኝ ቦታዎች እስከ መጨረሻ ድረስ ይሄዳሉ፣ በየትኛውም አቅጣጫ በኩል በክልሉ ውስጥ እስከ መጨረሻ የድንበር፣ እንዲሁም የክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ድረስ እንደፈለጉ መሄድ ይችላሉ፣ ይህንን በደንብ ያውቃሉ። ሕዝቡ የክልሉ መንግሥት በሰላም ጉዳይ ላይ ያደረገውን ጥረት በጣም ይረዳል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ዕውቅናም ይሰጠዋል። ከክልሉ ውጪ ያለው ሁኔታ ደግሞ ይታገዛል። የፌዴራል መንግሥት ወደ ክልሉ መጥቶ በተደጋጋሚ ሕዝብ ያወያያል። የሚያነሱትን ጥያቄዎች ለምሳሌ የመንገዶች መዘጋጋት፣ በዚህም ተዘግቶብን፣ በዚያም ተዘግቶብን ነው ያለነው። ባለፉት ወራት ወደ አዲስ አበባ የሄዱ የክልሉ መንግሥት አመራሮች በተደጋጋሚ ሲያነሱት በሚዲያዎች ተደምጠዋል። ሁልጊዜ በሚደረጉ ውይይቶች የሕዝባችን ጥያቄዎች ይነሳሉ፣ ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው። የሆነ ሒደት፣ የሆነ ዕርምጃ ተጉዞ አንድ ቀን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል ተብሎ ይጠበቃል። በትዕግሥት መጠበቅ ነው፣ ጊዜ መግዛት ይጠይቃል። 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...