Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአብዮቱ ስንክሳሮች ከኮሎኔሉ ማኅደር

የአብዮቱ ስንክሳሮች ከኮሎኔሉ ማኅደር

ቀን:

በአብርሃም ገብሬ ደቢ

ዕውቁ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም፣ የ1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮትና አብዮቱ ያስከተላቸው ውጤቶችን የሚያትት “Transformation and Continuity in Revolutionary Ethiopia” የተሰኘ ተወዳጅ መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ተመራማሪው በዚህ መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ አብዮት ብሉይ የማኅበራዊ አብዮቶች (Classical Social Revolutions) ጎራ ይመድቡታል፡፡ እነዚህን ብሉይ የማኅበራዊ አብዮቶች ደግሞ እ.ኤ.አ. የ1789 የፈረንሣይ፣ የ1917 የሩሲያና የ1949 የቻይና አብዮቶች ናቸው፡፡ ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጡት በአንድ በኩል አብዮቱ ፖለቲካዊ አብዮት ብቻ ሳይሆን አዲስ አይነት ማኅበራዊ ሥርዓት የማዋቀር ዓላማ ይዞ መነሳቱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ሥር ነቀል (Radical) አብዮት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ነው፡፡

ፕሮፌሰር ክላፋም እጅግ ሥር ነቀል መሆኑን ላሰመሩበት የኢትዮጵያ አብዮት ከሌሎች ብሉይ የማኅበራዊ አብዮቶች የሚጋራቸው መሠረታዊ ባህርያት በማሳያነት አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም አብዮቱ ለሰባት መቶ ዓመታት ገደማ በሰለሞናዊ ሥርወ-መንግሥት ስም አገር ሲገዛ የነበረው ዘውዳዊው ሥርዓት መጣሉን፣ ሥር ነቀል አብዮት ባካሄዱ ሌሎች አገሮች ላይ እንደታየው ዘውዳዊው ሥርዓት በወታደራዊ አገዛዝ መተካቱን፣ መሬት ላራሹ ‘መታወጁ’ን ተከትሎ የኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት ላይ መሠረታዊ ለውጥ መፈጠሩ፣ የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም መታወጁ፣ በዲፕሎማሲያዊ መድረክ ላይ የምዕራባውያን በተለይ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ‘ጥገኛ’ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ፀረ ምዕራባውያን ወደ ነበረችው ሶቪየት ኅብረት ጎራ ሙሉ በሙሉ መቀላቀሏን በማሳያነት አስፍረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት የተጓዘችበትን ‘አቅጣጫን ለማስቀየር’ ጥረት ያደረገው ይህ አብዮት ለኢትዮጵያውያን ምን ዓይነት ውጤቶችን አምጥቷል? የሚለው ጉዳይ ዛሬም ድረስ እጅግ አከራካሪ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ”ሕዝቡን ከጭሰጭነትና ከገባርነት ሥርዓት አላቅቋል፣ የብሔርና የሃይማኖት እኩልነት መብት እንዲታወቅ በር ከፍቷል”…ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “የለም! የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ በቅጡ ባልመረመሩ ወጣቶች ‘የተመራው’ አብዮት፣ የማኅበረሰቡን የአብሮነት ዕሴቶችን እንዲሸረሸሩ፣ የብሔር ጽንፈኝነት እንዲገን፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሥጋት ውስጥ እንዲወድቅና የእርስ በእርስ መጠፋፋት እንዲከሰት አድርጓል” ብለው የሚከሱ አሉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ “ወጣቶች የሕይወት መሰዋዕትነት የከፈሉለትን አብዮት በወታደራዊው የደርግ ቡድን ‘በመጠለፉ ምክንያት አብዮቱ ተቀልብሷል’፤ የቆመለትና የታገለለትን ግብ አልመታም፣ ከዚያ ይልቅ ‘ጨቋኝ’ የሆነ ወታደራዊ መንግሥት በመመሥረቱ ኢትዮጵያ ለሌላ የከፋ ግጭትና ሽብር ዳርጓታል” ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡

ይህ ዓይነቱ ሙግትና ትችት በይበልጥ የሚስተዋለው ደግሞ በአብዮቱ ወቅትና ማግስት ተሳትፎ በነበራቸው ተዋናዮች ዘንድ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ በአብዮቱ ዙሪያ የተጻፉ ግለ-ታሪኮችና የሕይወት ታሪኮች፡፡ ለአብነትም በደርግ በኩል ከተሠለፉት መካከል የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‘ትግላችን’፣ የሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግድረስ ‘እኛና አብዮቱ’ እንዲሁም በዚህ ዓምድ ላይ ለዳሰሳ የተመረጠው የሌተና ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ‘ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞና የኢትዮጵያ አብዮት’፣ በኢሕአፓ በኩል የክፍሉ ታደሰ ‘ያ ትውልድ’ ቅጾች፣ በመኢሶን በኩል ደግሞ በአንዳርጋቸው አሰግድ የተጻፈው ‘በአጭር የተቀጨ ረዥሙ ጉዞ’ የተሰኙ መጻሕፍት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በዚህ ዓምድ ላይ ለዳሰሳ የተመረጠው የኮሎኔል ብርሃኑ፣ ‘ያልታሰበው የሕይወቴ ፈታኝ ጉዞና የኢትዮጵያ አብዮት’ በይዘቱ ዘለግ ያለ ነው፡፡ የደራሲው ልጅነት፣ የትምህርትና የሥራ ሕይወትን በስፋት ያትታል፡፡ እንዲሁም በአብዮቱ ወቅት ደራሲው የነበራቸው ተሳትፎዎች፣ በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ቦታ ላይ በነበሩበት ጊዜ ያዩትንና የታዘቡትን፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ከሐረር ሦስተኛው ክፍለ ጦር አንስቶ የአገሪቱ ቁንጮ የሥልጣን ቦታ ጠቅልለው እስከያዙበት ጊዜ የሄዱበት መንገድና ሰብዕናቸውን፣ እንዲሁም ወታደራዊው የደርግ መንግሥት በደፈጣ ተዋጊዎቹ በሕወሓትና በሻዕቢያ የበላይነት ሲወሰድበት በቤተ-ምንግሥት አካባቢ የነበረው የመጨረሻ ደቂቃዎችና የደራሲው ወደ ጣሊያን ኤምባሲ የመግባትና እዚያም ውስጥ የነበረው ሁኔታ በዝርዝር ያስቃኛል፡፡

የኮሎኔሉ መጽሐፍ ከዚህ ቀደም በአብዮቱና በደርግ መንግሥት ዙሪያ ከተጻፉ ትውስታዎች በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ባለታሪኩ ያመኑበትን ‘ዕውነት’ና የታዘቧቸውን ሁነቶች ያለምንም ማድበስበስ ፊት ለፊት ፍርጥ የሚያደርጉ በመሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የትግል ጓዳቸው የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምንና ፍሰሐ ደስታን በሚመለከት በተለያዩ ገጾች ያሰፈሯቸውን ጉዳዮች መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሌላው ኮሎኔሉ ጎበዝ ወታደር ብቻ ሳይሆኑ ጎበዝ ተማሪም ነበሩ፡፡ በዚህም ደራሲው በ1959 ዓ.ም. በሕግ በከፍተኛ ውጤት ከመመረቃቸውም በላይ፣ ከአብዮቱ በፊት በውትድርናው እስከ የሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል፡፡ በተለይ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ከፍተኛ ትግል እንዳደረጉ በግለ-ታሪካቸው በስፋት ዳስሰውታል፡፡ የምን ትግል? የተባለ እንደሆን፣ ኮሎኔሉ በ1950ዎቹ አጋማሽ፣ በኦጋዴን ጦርነት ላይ በፈንጅ ቆስለው ለዕረፍትና ለሕክምና አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ ሕክምናቸውን ከመከታተል ጎን ለጎን፣ ሐኪማቸው በቂ ዕረፍት መውሰድ እንዳለባቸውና ለዚህም የሦስት ወር እረፍት ጊዜ ይጽፍላቸዋል፡፡ ኮሎኔሉ ግን ይህንን የእረፍት ጊዜ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ዕቅድ ይዙበታል፡፡ በእርግጥ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን መቀጠል የሚያስችል ከፍተኛ ውጤት የነበራቸው ቢሆንም “ያላግባብ” የመከላከያ ሚኒስቴር የፈቃድ ደብዳቤ አምጣ በሚል ከቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራር ቢሮ መጠየቃቸውና በሌሎችም ሰበብ አስባቦች የመማር ዕድላቸውን የሚያጠቡ ውጣ ውረዶችን አጋጥሟቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኮሎኔሉ የዋዛ አልነበሩምና እስከ መጨረሻ ድረስ ተጉዘው መብታቸውን ለማስከበር አልሰነፉም፡፡ ያ እንኳን ባይሆን፣ “ውሳኔዬ ከዩኒቨርሲቲ እንድወጣ ከተገደድኩ፣ ለዚህ ያበቁኝን [የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ጦር ክፍሌ እንድመለስ ግዴታ የጣሉብኝን] ሰዎች፣… ገድዬ ራሴን ለመግደል ነበር” በማለት ያለምንም መሸፋፈን በዚያን ወቅት የያዙትን አቋም በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ ደግነቱ በዚህም በዚያም ብለው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በሕግ ለመመረቅ በቅተዋል፡፡

ኮሎኔሉ እስከ አብዮቱ ዋዜማ ድረስ በተለያዩ ክፍለ ጦሮች የሕግ አማካሪ፣ የሕግ መምህር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከሐረር የጦር አካዳሚ እስከ ደብረ ዘይት አየር ወለድ፣ ከጅግጅጋ እስከ አስመራ ድረስ የዘለቀ የሥራ ልምድ አላቸው፡፡ በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ነበሩ፡፡

ኮሎኔሉ ተማሪ እያሉ በዩኒቨርሲቲው በሚደረገው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ይሳተፉ እንደነበር በመጽሐፋቸው (ገጽ፣168)፣ “የጦር መኮንን እንደ መሆኔ መጠን በተማሪዎች ሰላማዊ ሠልፍ የማይጠበቅብኝ ብሆንም፣ እሳተፍ ነበር፡፡ የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እኛን መኮንኖችን፣ ‹ድርብ ኃላፊነት› ስላለብን እንዳንሳተፍ ቢነግሩንም፣ እኔ ግን በስሜት ስለምደግፈው ከመሳተፍ መቆጠብ አልቻልኩም” ሲሉ አስፍረዋል፡፡

“ምንም ይድረስብኝ ምን ሊደርስብኝ የሚችለውን አደጋ ሳልፈራ፣ የማምንበትን ነገር በግልጽ የመናገር ልምድና ጠባይ ስላለኝ፣ የጦር መኮንን ባልሆን ኖሮ ከተማሪዎች መሪዎች አንዱ እሆን ነበር፡፡ ይህን ከማድረግ ራሴን መግታት አልችልም ነበር፡፡ በተማሪዎች ንቅናቄም ዋና ተዋናይ መሆን ባልችልም፣ ዕድሉ ሲያጋጥመኝ ሁልጊዜም ከዳር ሆኜ እሳተፋለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ‘በረከተ መርገም’፣ ‘ነአስተማስለኪ’ እና ሌሎች ግጥሞች በአራት ኪሎ ግቢ ሲነበቡ የአብዮት ፍላጎቴን አጋሉት” (ገጽ፣169) በማለት ስለተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበራቸው አተያይና ስሜት አጋርተዋል፡፡

በነገራችን ላይ የኮሎኔሉ ታናሽ ወንድም፣ ብርሃኑ ባይህ ልክ እንደ እሳቸው የሕግ ተማሪ የነበረ ሲሆን፣ በ1959 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት በየካቲት 16 ቀን 1966 ዓ.ም. ከፈነዳ በኋላ፣ በሻለቃ አጥናፉ አባተ የሚመራ አንድ ቡድን እንደተመሠረተ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ቡድን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላሉ የጦር ክፍሎች አንድ አንድ ተወካይ እንዲልኩ ትዕዛዝ ያስተላልፋል፡፡ የሐረር ሦስተኛ ክፍለ ጦርም ከአዲስ አበባ መልክት ይደርሷል፡፡ በዚህም ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሐረር ሦስተኛው ክፍለ ጦር፣ ሻለቃ ብርሃኑ ባይህ ደግሞ የሐረር የጦር አካዳሚ እንዲወክሉ በጦር ክፍላቸው ተመርጠው ሲላኩ፣ ጉዞዋቸው በአንድ መኪና ውስጥ ነበር፡፡ በጉዞው ላይ የኮሎኔል መንግሥቱ ስሜት ምን ይመስል እንደነበር በትውስታው ተካትቷል፡፡

ከሐረር ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ከመጀመራቸውና ከጀመሩ በኋላ ያለውን ሁኔታ ጥሩ አድርገው በመጽሐፋቸው (ገጽ፣182) ተርከውታል፣ “ሻለቃ መንግሥቱ የመሣሪያ ግምጃ ቤት አዛዥ በመሆኑ አንድ አሮጌ ደብዛዛ አረንጓዴ ቀለም የተቀባ ላንድሮቨር መኪና ከነሹፌሩ ይዟል፡፡ ሁላችንም በሁለቱ ላንድሮቨር ተሳፈርን፡፡ እኔ ከሻለቃ መንግሥቱ ጋር ሆንኩ፡፡ [በጉዟችን] ሻለቃ መንግሥቱ በሐሳብ የተዋጠ ይመስላል፡፡ ሁሉም በየራሱ ሐሳብ ተውጧል፡፡ እኔ መነጋገር ፈልጌ ነበር፣ ግን ሁሉም በዝምታ ተሸብበው ፀጥ ማለታቸውን ስመለከት፣ በድንገት ስለገጠመኝ ጥሩ ወይም መጥፎ ዕድል ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ” በማለት በጊዜው በጉዞ ላይ የነበረውን ሁኔታ አውስተዋል፡፡

“ገና ተማሪ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የመንግሥት ሥርዓት እጠላውና ለለውጥ በእጅጉ እጓጓ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አብዮት እመራለሁ፣ በአገሪቱ የአመራር ቁንጮ ላይ እወጣለሁ፣ ብዬ እንኳንስ በውኔ በህልሜም አስቤው አላውቅም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሳልጠብቀውና ምንም ዓይነት ዝግጅትም ሆነ የመጀመሪያውን ተሳትፎ ሳላደርግ፣ ከ108ቱ የደርግ አባሎች አንዱ፣ እንዲሁም ከደርጉ የበላይ መሪዎች አንዱ ሆንኩ፤” በማለት የታሪክ አጋጣሚውን በመገረም ተርከውታል፡፡  

ሌላው በኮሎኔሉ ግለ ታሪክ ሰፋ ያለ ትኩረት ያገኘው የኤርትራ ጉዳይ ነው፡፡ ከአብዮቱ በፊት ኮሎኔሉ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከመሥራታቸው በተጨማሪ፣ ከአብዮቱ በኋላም የኤርትራን ችግር ለመፍታት በሚል ደርግን ወክለው የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭም ፅኑ ፍላጎት እንደነበራቸውም አስፍረዋል፡፡ ይህ አቋማቸው ‘ብርሃኑ፣ ሚስቱ ኤርትራዊት ስለሆነች ነው’ የሚል ወቀሳ እንዲሰነዘርባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

ይኼም ሆኖ ግን አብዛኛዎቹ የደርግ አባላት የኤርትራን ችግር ከሥር መሠረቱ በቅጡ በመረዳት፣ ረገድ መሠረታዊ ችግር እንደነበረባቸው አልሸሸጉም፡፡ ጄነራል አማን አንዶም፣ “ስለ ኤርትራ ችግር ሲነሳ፣ ‘ይኼ በጣም ቀላል ነው፣ ፌዴሬሽኑን መመለስ ብቻ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑን ከመለስንላቸው ሰላም ይሆናል፣ ከባዱ ችግር የሶማሊያ ጉዳይ ነው’ ይላሉ፡፡ ብዙዎች የደርግ አባሎች ስለፌዴሬሽን የሚያውቁት ነገር ስለሌለ፣ ይህ ዓይነቱ አባባል ያሳስባቸው ነበር፡፡ የሚያውቁት ነገር ቢኖር ፌዴሬሽን ጥሩ ስላልሆነ መፍረሱን ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም ሻለቃ መንግሥቱ ብዙ ጊዜ፣ ‘ፌዴሬሽን ለመገንጠል የመጀመሪያው ዕርምጃ ነው፤’ ይል ነበር” በማለት ውስብስብ የነበረውን የኤርትራን ጉዳይ ይረዱበት የነበረው አኳኋን አስፍረዋል፡፡

በኮሎኔሉ ግለ-ታሪክ ውስጥ ብዙ አነጋጋሪ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ አስተዛዛቢ ጉዳዮችን ተካተውበታል፡፡ ለአብነትም፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው መሪዎች ኋላ ላይ ወጣቱን በማንቀሳቀስ ከፍተኛ ተደማጭነት አትርፎ የነበረው የኢሕአፓ ፓርቲ መመሥረታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ዘውዳዊው ሥርዓት በማዳከምና በመጣል ሒደት ውስጥ በኢሕአፓ ስር የተሳበሰቡት ወጣቶች ጉልህ ሚና እንደነበራቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአፓ በአንድም ሆነ በሌላ፣ በኮሎኔሉ ግለ ታሪክ ውስጥ፣ በአብዮቱ ሒደት ላይ በተለይ ዘውዳዊውን ሥርዓት በመጣል ረገድ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌለው ቡድን አድርገው ነው ያቀረቡት፡፡ እንዲያውም አስተዋጽኦ ከማድረግ ይልቅ “ፀረአብዮት ነበር” በማለት በተደጋጋሚ ይወቅሱታል፡፡ (በገጽ፣196-7)፣ “…[አብዮቱን በሚመለከቱ ክርክሮች ውስጥ] የኢሕአፓ አቋም ዋጋ ቢስነት ይበልጥ እየተጋለጠ፣ እውነትም ድርጅቱ ሥልጣን ባለመያዙ በመቆጨት ብቻ አብዮቱንና አመራሩን እንዲሁም የአብዮቱን ደጋፊዎች ለማጥላላት እንደሚታገል ለብዙ ሰዎች ግልጽ እየሆነ ሄዶ ነበር፡፡”

“ኢሕአፓ…የመሬት አዋጁን እንኳን ፋሺዝምን በገጠር ለማስፋፋት የተወሰደ ዕርምጃ ነው፣ እያለ በልሳኑ በመጻፍ ያጣጥለዋል፡፡ ይህንን ካነበብኩ በኋላ ነው  የዱርዬዎች ጥርቅም እንደሆነ ያመንኩት “(ገጽ፣280)፡፡ “ኢሕአፓ በአገሪቱና በሕዝቡ ላይ ከሻዕቢያም ሆነ ከወያኔ የበለጠ ጉዳት ያደረሰ፣ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል የፈጸመ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ጠላት ድርጅት ነው” (ገጽ፣ 660) የሚሉት አረፍተ ነገሮች፣ ኮሎኔሉ ለሦስት አሥርት ዓመታት የጥሞናና የማሰላሰያ ጊዜ ወስደው ትውስታቸውን ጽፈው ያሳተሙ ሳይሆን፣ በዚያው ዘመን፣ በነበራቸው ስሜታዊ አስተያየት የጻፉት ነው የሚመስለው፡፡ 

ሌላው ኮሎኔሉ የደርግ መንግሥት የመንግሥት ሥልጣን ለመጠቅለል እየሄደበት የነበረው ሒደት አጥብቀው የተቃወሙ አብዮተኞችን ምፀታዊ በሚመስል አኳኋን (በገጽ፣ 211-12) ያጣጥሉታል፣ “…በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም በሠራተኞች ማኅበር የሚቀርቡት ጥያቄዎች ደግሞ ብስለት ስለሌላቸው እንጂ ተግባራዊ ቢሆኑ በአጠቃላይ አብዮቱን አደጋ ላይ ይጥሉት ነበር፡፡ ‘ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ!’ በማለት ወታደሮች፣ የተማሪዎች ማኅበር፣ የመምህራን ማኅበር፣ የሠራተኞች ማኅበር፣ የሴትኛ አዳሪዎች ማኅበር፣ የሥራ ፈቶች ማኅበር፣ ወዘተ አባል የሆኑበት ‘ሕዝባዊ መንግሥት’ እንዲመሠረት… ይጠይቃሉ፡፡ ሌሎች ብዙ በወቅቱ ሊተገበሩ የማይችሉ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ ደርግ እነዚህንና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ወቅታዊ አለመሆናቸውን በማጤን ከምንም አይቆጥራቸውም ነበር፡፡”

ኮሎኔሉ በግለታሪካቸው ውስጥ፣ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በወቅቱ የተፈጠሩ ዕልቂቶችን፣ ለሌላ አካል የመስጠት ወይም ኃላፊነት ላለመውሰድ የመፈለግ አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ (በገጽ፣671)፣ “ብዙ የበላይ ሹማምንት የደርግ አባላት በዚያን ዘመን በሕዝብ ላይ ይፈጸም ለነበረ ግፍና ጭካኔ ቀጥተኛ መረጃ አልነበራቸውም፡፡ ብዙውን ድርጊት የሚሰሙት እንደ ሌላው ሕዝብ ነበር፡፡ ድርጊቱንም ማን እንደሚፈጽም እርግጠኛ ግንዛቤ አልነበራቸውም፤” በማለት አስፍረዋል፡፡

ሌላው ኮሎኔሉ፣ በ60ዎቹ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ከፍተኛ ሹማምንት ላይ ለይምሰል እንኳን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መረሸናቸውን በሚመለከት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ተጠያቂ ለማድረግ የሄዱበት ርቀት ችግሮችን ወደ ሌላ አካል ለመግፋት ለሚያደርጉት ጥረት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው ፕሮፌሰር መስፍን የባለሥልጣኖቹ ጉዳይ እንዲመረምር የተቋቋመው የመርማሪ ኮሚሽን አባሎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ኮሎኔሉ በግለታሪካቸው (ገጽ፣ 220) እንዳሰፈሩት፣ ፕሮፌሰር መሥፍን “ከሞላ ጎደል እንደማስታውሰው የሚከተለውን ሲናገር ነበር፣ ደርግ ምርመራው ይጠናቀቃል የሚለው ተስፋው የተሟጠጠው፣ ‘ሪቮሉሽን (አብዮት) በምርመራና በሕግ አይደለም የሚመራው! እናንተው በሪቮሉሽነሪ መንገድ መወሰን ያለባችሁን ነገር ነው፣ እኛ በምርመራና በሕግ እንድንወስንላችሁ የምትጠይቁን፡፡ ጠብመንጃው በእጃችሁ ነው፡፡ እኛ በሕግ የተቋቋምን ስለሆነ የምንሠራው በሕግ ነው፡፡ እኛ በሪቮሉሽን ሥልጣን አልያዝንም፡፡ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ጊዜ ይወስዳል፡፡ …ስለዚህ ጉዳዩ ቶሎ እንዲያልቅና የሕዝቡ ጥያቄ ቶሎ መልስ እንዲያገኝ ከፈለጋችሁ፣ እናንተው በሪቮሉሽነሪ መንገድ መወሰን አለባችሁ” ብለው ስለመከሩን ነው “የረሸንናቸው” የሚል አነጋጋሪና አስተዛዛቢ አስተያት አስፍረዋል፡፡

እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከምናውቀው ለየት ባለ መልኩ ስለ ትምህርት ቤትና የሥራ ጓደኛቸው የመኢሶን ሊቀ-መንበር ኃይሌ ፊዳ የፖለቲካ ተሳትፎ፣  የጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የመጨረሻ ሰዓታትን፣ እንዲሁም የጄኔራል ታደሰ ብሩ “መሸፈት”ን በሚመለከት ያሰፈሯቸው ጉዳዮች አነጋጋሪ የሚባሉ ናቸው ፡፡

ሌላው የኮሎኔል መንግሥቱን ስብዕናን ለመረዳት ይህ መጽሐፍ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም መንግሥቱ ከሐረር አንስቶ እስከ ቤተ መንግሥት፣ ከቤተ መንግሥት እስከ ዚምባብዌ ድረስ ሲኮበልሉ ደራሲው በቅርበት ተመልከተዋል፡፡ ስለ ኮሎኔሉ ስብዕና ካሰፈሯቸው ነጥቦች መካከል (ገጽ፣ 546)፣ “መንግሥቱ… መጀመሪያ እንደገመትኩት ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ተንኮለኛነት አለችበት፡፡ ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ ከአብዮተኝነቱ ፖለቲከኝነቱ ያመዝናል፡፡ ፖለቲከኛነትና ሀቀኝነት ደግሞ ብዙም አይጣጣሙም፡፡ ፖለቲከኛነቱ እንዲያውም ወደ ማኪያቬሊ ፍልስፍና የሚጠጋ መሆኑን፣ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ታዝቤያለሁ፡፡”

“መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቃል ኪዳኑን አፍርሶ፣ አገሪቱን፣ ሕዝቡን፣ ሠራዊቱን፣ እንዲሁም ፓርቲውን፣ መንግሥትንና አመራሩን ከድቶ፣ ሠራዊቱን በትኖ፣ ወደ ዚምባብዌ በፈረጠጠ ልክ በሳምንቱ፣ ወንበዴ [ሕወሓት] አዲስ አበባ ገባ፡፡ አገሪቱን ያዘ፡፡ ሁሉ ነገር አበቃ!” በማለት (ገጽ፣ 692″ ጠንከር ባሉ ቃላት ጓዳቸውን ተችተዋል፡፡

በኮሎኔሉ ግለ ታሪክ፣ “ስደት በሐገር ውስጥ” በሚል፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የቀረበው ትውስታ ስሜት ይነካል፡፡ ግንቦት 19 ሕወሓት/ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ስለነበረው ሁኔታ ነው የሚያወሳው፡፡ በዚሁ ቀን በቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው አጠቃላይ ድባብ፣ ሁካታ፣ ዝርፊያ…በትውስታው ተካቷል፡፡ እንዲያውም ከቤተ መንግሥት የወጡት የመጨረሻ ባለሥልጣን ነበሩ ሊባል ይችላል፣ ደራሲው፡፡

በዚሁ ግንቦት 19 ቀን አመሻሽ ላይ ወደ ጣሊያን ኤምባሲ እንዴት እንደገቡ፣ ኤምባሲ ውስጥ ከገቡም በኋላ የገጠማቸው ግራ አጋቢ ሁኔታ፣ በጨረፍታም ቢሆን ቀርቧል፡፡ እንደ አንባቢ የመጀመሪያው የጣሊያን ኤምባሲ የገቡበትን ብቻ ሳይሆን፣ ለ30 ዓመታት ኤምባሲው ውስጥ ስላሳለፉት ‘የአገር ውስጥ ስደት’ን በሚመለከት አንዳንድ ነገሮችን ያጋሩን ይሆናል ብሎ መጠበቅ የማይቀር ነው፡፡ ነገር ግን በግለታሪኩ ውስጥ አልተካተተም፡፡ ይኼም ሆኖ ግን፣ በ699 ገጾች የተተመነው የኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ትውስታ ስለዘመኑ ሁኔታ ለማወቅም ሆነ ለመረዳት የሚሻ ሰው ቢያነበው በብዙ ረገድ ይጠቀማል፡፡ ዘርዘር ያሉ በተለይም በደርግ በኩል የነበሩ የአብዮቱን ኩነቶች ለመረዳት ያስችላል፡፡ በዚህ ላይ ግለ-ታሪኩ ልቅም ባለ አርትኦትና የኅትመት ጥራት መታተሙ ለመጽሐፉ ተጨማሪ ግርማ-ሞገስ አሰጥቶታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው abrehamgebre16@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...