Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹ምርጫው እንዳልተደረገ መተማመን ላይ ከደረስን ሁሉንም ነገር ለመተው ዝግጁ ነኝ›› ሻለቃ ኃይሌ...

‹‹ምርጫው እንዳልተደረገ መተማመን ላይ ከደረስን ሁሉንም ነገር ለመተው ዝግጁ ነኝ›› ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ

ቀን:

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቅርቡ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን በፕሬዚዳንትነትና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የሚያስተዳድሩትን አመራሮች ምርጫ አከናውኗል፡፡ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ላለፉት አራት ዓመታት የነበረው አመራር የአገልግሎት ጊዜው አልተጠናቀቀም፡፡ ምርጫው መደረግ ካለበትም ከፓሪስ ኦሊምፒክ በኋላ እንጂ ቀድሞ መሆን አልነበረበትም፡፡ ምርጫው የስፖርት ማኅበራት የሚቋቋሙበት መመርያን በጣሰ አግባብ ለሦስተኛ የአገልግሎት ዘመን በምርጫው የተካተቱ አሉ፡፡ ለምርጫው ዝግጁ መሆን አለመሆኔ ሳልጠየቅ እንድመረጥ ተደርጌያለሁ፡፡ እንዲሁም ከፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ጋር ተያይዞ ሌሎችንም የደንብ ጥሰቶችን በመጥቀስ ‹‹ምርጫው እንዳልተደረገ መቆጠር አለበት›› በሚለው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በፊት ያደረገውን ምርጫ እየተቃወመ ይገኛል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው ከሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተርየኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከሰሞኑ ካደረገው ምርጫ ጋር ተያይዞ፣ በአገር ውስጥ የስፖርት ማኅበራት የሚቋቋሙበትን መመርያን፣ የዓለም አቀፍ መመርያና ደንቦችን በመጥቀስ ምርጫው እንዳልተደረገ መቆጠር ይኖርበታል የሚል ቅሬታ እያቀረብክ ነው፣ ምክንያቱን ብትነግረን?

ሻለቃ ኃይሌ፡- በግሌ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያውቅልኝ የምፈልገው ስፖርቱን በሚመለከት ካልሆነ ከማንም ሰው ጋር የግል ችግር እንደሌለብኝ እንዲረዱኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ካሉት ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሁሉም ወዳጆቼ ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ችግር የማነሳው አሠራሩ ትክክል አይደለም ነው፡፡ የምንሄድበት መስመር መጥፎ ነው የሚል ነው፡፡ እኔ ትክክል እንዳልሆነ የምገልጸውን ጥፋት፣ አውቀው እንደማያጠፉትም አውቃለሁ፡፡ ችግሩ ጥሩ ሠራን በሚል የስፖርቱን ባህሪያት ካለመረዳት ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ከዚህ በፊት ለነበረው ምርጫ ፈቃደኛ የሆንኩት ባለህ ልምድና ተሞክሮ ታማክረናለህ ስለተባልኩ ነው፡፡ እየቆየሁ ስመጣ ብዙ ነገሮች አልቀው የሚመጡ ስለነበረ ደስተኛ አልነበርኩም፡፡ ከሦስትና ከአራት ግንኙነት በኋላ ሁሉንም ነገር አቁሜ ትቼዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ እንዲህ የመሰሉ ችግሮች ከነበሩ ለምንድነው አሁን ላይ እንደምታርገው ትክክል እንዳልነበረ ያልገለጽከው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ጉዳዩ እንዲጯጯህ ስልላፈለግኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ አንተ በስፖርቱ ውስጥ እንዳለፈ ባለሙያ፣ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ተግዳሮት የምትለው ምንድነው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- አንዱና ትልቁ ክፍተት ወይም ተግዳሮት ሙያን (ፕሮፌሽን) በአግባቡ ለይቶ አለማወቅ ነው፡፡ አትሌቲክስ ምን እንደሚመስል፣ እግር ኳስ ምን እንደሚመስልና ቦክስ ምን እንደሚመስል የሚያውቁ ሰዎች አይፈለጉም፡፡ ዓለም ላይ ያለው ልምድ (ትሬንድ) ሌላ ነው፡፡ እግር ኳሱን፣ አትሌቲክሱንና ሌሎችም ስፖርቶች እንዴትና እነ ማን እንደሚመሯቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ችግር በኢትዮጵያ የአሁን ሳይሆን ከድሮ ጀምሮ ከሚኒስቴር ጀምሮ በተዋረድ ስፖርቱን የሚያውቅ ስው ስፖርቱ ላይ አይመደብም፡፡ ብዙዎቹ ሲመጡ ስፖርቱን እንደሚወዱት ነው የሚነግሩን፡፡ መውደድና ማፍቀር ስፖርት ከመምራት ጋር እንዴት ነው የሚገናኘው? ስፖርቱን ዶክተር አሊያም ፕሮፌሰር ስለሆንክ አትመራውም፡፡ ልምድ  ወሳኝ ነው፡፡ ስፖርትና አርት ሁለቱም ልዩ (ዩኒክ) ናቸው፡፡ እውነቱን ከአሠልጣኞቻችን መረዳት ይቻላል፡፡ እነማን ናቸው ዲግሪና ዶክትሬት ያላቸው? ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የዓለምና የኦሊምፒክ አሸናፊ አትሌቶችን አፍርተዋል፣ እያፈሩም ይገኛል፡፡ እውነታው ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዛሬ ሰባት ወይም ስምንት ዓመታት በፊት አሁን በምትናገረው ልክ ሲነገር ከቆየ በኋላ፣ በከፍተኛ ጫና ውስጥም ቢሆንም አንተና አንተን መሰል ሰዎች ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አመራርነት ታጭታችሁ፣ በተለይ አንተ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነህ በሙሉ ድምፅ የተመረጥክበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ይሁንና በወቅቱ አንተ ብቻ በምታውቀው ምክንያት ‹‹ጥቂት አትሌቶች ሱልልታ አካባቢ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተው ተቃወሙኝ›› በሚል ከአንድ ዓመት በኋላ ማለት ነው ኃላፊነትህን በገዛ ፈቃድህ መልቀቅህን ገልጸህ ጥለህ ወጣህ፡፡ በወቅቱ እንዴት ወጣህ? ለምን ወጣህ? ምክንያቱን እንድታብራራ እንኳ ፈቃደኛ አልነበርክም፡፡ ኃላፊነቱን የሰጠህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦም እንዲብራራ አልተደረገም፡፡ የአመራርነት ዕድል ማግኘት ከዚህ በላይ እንዴት ሊኖር ይችላል?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ያንን ኃላፊነት ትቼ የወጣሁት ከእኔ ለሚሻል ሰው ለምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ኮሚሽነር ደራርቱ በልምድም በዕድሜም ከእኔ ስለምትሻል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ እኔ እዚያ ቦታ ብቆይ ኖሮ ስፖርቱ ወደ ባሰ ወይም ወደ ማይሆን ነገር ውስጥ ይገባ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በሙሉ ድምፅ የመረጠህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ነው፡፡ መነሳትም ካለብህ በደንቡ፣ በሕጉና በመመርያው መሠረት የሠራኸው ጥፋት ካለም በጉባዔው ተገምግመህ መሆን አልነበረበትም እያልክ ነውን? ከእኔ የተሻለ ማለትስ ከምርጫ በፊት እንጂ፣ እንዴት ምርጫ ከተደረገ በኋላ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው እንዴት ነው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- እውነት ነው እኔን የማውረድም ሆነ የማቆየት የጠቅላላ ጉባዔው ሙሉ ኃላፊነት እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በወቅቱ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ያንን ከባድ ዋጋ ሲከፍል የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሳይቀር፣ ከኃላፊነትህ የለቀቀከው በራስህ ፍላጎት? ወይስ በመንግሥት ግፊት ነው? ብሎ ጠይቆኝም ነበር፡፡ የሰጠሁት መልስ በራሴ ነው የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የነበረብኝ ግፊትና ጫና ከስፖርቱም በላይ ስለነበረ ማለት ነው፡፡ የነበረውን ሁኔታ ተከታትሎ ልጆቹን የለም ልክ አይደላችሁም ያላቸው አንድ አካል እንኳ አልነበረም፡፡ እንዲያውም የእነሱን ሁኔታ እየተከታተለ የሚያቀርበው ሚዲያ ማንነት ሳይቀር በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ በወቅቱ የደረስኩበት ውሳኔ መክፈል ያለብኝን ዋጋ ከፍዬ መጯጯሁ እንዲቀር አድርጌ ነው የወጣሁት፡፡ ‹‹ልክ አይደለህም›› ከሆነ የምትለው፣ በእኔ ልክ ነኝ ነው የምልህ፡፡ በወቅቱ ኃይሌ ልክ አይደለም፡፡ አቋምም የለውም እስከ መባል ስለመደረሱም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ብዙ ነገሮች ከሚበላሹ አንድ ኃይሌ የፈለገውን ቢባል መርጫለሁ የሆነውም ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ እስካሁን ግልጽ አልተደረገም ለምንድነው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ደሩ (ደራርቱ) እኛ ስንመረጥ አልነበረችም፡፡ ያመጣናት እኛ ነን፡፡ ምክንያቱም ጭቅጭቁ ሲጀመር ጉዳዩ ከስፖርት ውጪ መሆኑ ስለገባኝ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላላ ጉባዔ የመረጠህ በሙሉ ድምፅ ነው፡፡ በዚያ ላይ በስፖርቱ ትልቅ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለህ፣ ኃይሌ ምን አለ? የሚባልልህ፣ በትልቁ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለህ ሰው እንደ መሆንህ ለምን ብለህ የምትጠይቅበት አጋጣሚ አልነበረህም ማለት ነው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- በወቅቱ የእኔ እምነት በዚህ ጉዳይ ብዙ ሰዎች አሊያም አገር እንዲጎዱ አልፈለኩም፡፡ ምናልባትም ድርጊቱን የፈጸሙት ጓደኞቼ ሊሆኑ እንደሚችሉም እገምታለሁ፣ አሁን ያ ጉዳይ አልፏል፡፡

ሪፖርተር፡- የምናወራው ስለሕግ ክፍተት አይደለም እንዴ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- አሁንም የማወራህ ለአገራችን ስፖርት የሚበጀው ነገር እንዲመጣ የምናደርጋቸውን ነገሮች ቆም ብለን እንድንመለከትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንድ ሰው የሆነ ቦታ ላይ ሆኖ ብቁ አይደለህም ቢባል በእኔ ውርደት አሊያም ስድብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስለማላውቀው አርት (ሙዚቃ) ብትጠይቀኝ ምንም የማወቀው ነገር የለም፡፡ ነገሮችን መመልከት የሚኖርብን ከዚህ አንፃር መሆን ይኖርበታል፡፡ ኦሊምፒክ ላይ ትኩረት ያደረኩበት ዋናው ምክንያት አሁን ላይ ስለምርጫ፣ ስለአገልግሎት ጊዜ፣ ስለአሠራር፣ ስለኦዲት ይወራል፡፡ ስለሆነም ይህ አሁን ተደረገ የሚባለው ምርጫ እንዳልተመረጠ ይቆጠርና የሁሉም ትኩረት ኦሊምፒክ ዝግጅት ላይ ሆኖ፣ ምርጫው ከኦሊምፒክ በኋላ ቀደም ሲል የተጠየቁት ስለአገልግሎት ዘመን፣ ስለኦዲት፣ ስለአሠራርና በአጠቃላይ ከትጥቅ ጀምሮ ዝርዝር አሠራሩ ለጠቅላላ ጉባዔ ቀርበው መተማመን ላይ ከተደረሰባቸው በኋላ ምርጫ ይደረግ ነው የእኔ ጥያቄ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በምክትል ፕሬዜዳንትነት ሆነህ መመረጥህ ይታወቃል፡፡ በቆየህባቸው አራት የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ አሁን እንደ ክፍተት የምታወራቸውን ነገሮች ስትቃወም አልተደመጥክም፡፡ ከዚህም ሌላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ወቅት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል የነበረውን እሰጥገባ በሚገባ ታውቃለህ፡፡ ይሁንና በዚያ ሁሉ ትርምስ ውስጥ የአንተ ድምፅ አልተሰማም ነበር ለምን?

ሻለቃ ኃይሌ፡- በወቅቱ መመረጤ የተነገረኝ በፕሬዚዳንቱ አማካይነት ነው፡፡ በምን መሥፈርት የሚል ጥያቄ ሳነሳ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ልምድና ተሞክሮህን እንፈልገዋለን አሉኝ፡፡ እንዲያውም መጀመሪያ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት እንድሆን ነበር ሐሳብ የቀረበልኝ፡፡ አልፈግም ብዬ ነው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ የቀጠልኩት፡፡ ቆይቶ የቶኪዮ ኦሊምፒክም እየመጣ ስለነበረ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሁለትና  ሦስት ስብሰባዎች ላይ ታድሜ የሚቀርቡት ጉዳዮች ያለቁ እየሆኑ መምጣቸውን ስመለከት ለምን የሚል ጥያቄ መጠየቅ ጀምሬም ነበር፡፡ ምክንያቱም በጉዳዩ ተከራክረን የተሻለውን ሐሳብ ወስደን መወሰን ይኖርብናል በምልበት ጊዜ አይታይም፡፡ ስለሆነም ከሦስትና አራት ስብሰባ በኋላ ኃይሌ ኦሊምፒክ አካባቢ ድርሽ ብሎ አያውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ በእያንዳንዱ ውሳኔ አለመኖርህን ጨምሮ ምንም ድምፅ አላሰማህም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም እችላለሁ፣ ለምን?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ጥያቄህ ትክክል ነው፡፡ በወቅቱ የእኔ ውሳኔ የነበረው ለምን እረብሻለሁ የሚል ስለነበረ ምንም ሳልናገር ቆይቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ታዲያ ያውም የፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት በቀናት ዕድሜ እየቀረው በምርጫ ምክንያት ማንሳትህን ለምን መረጥከው?

ሻለቃ ኃይሌ፡- የሚገርመው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነህ በድጋሚ ተመርጠሃል ተብሎ ተነገረኝ፣ እንዴት? ይህማ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ለምርጫው የቀረብነው አንዳንዶቻችን የስፖርት ማኅበራት ማቋቋሚያ መመርያው ከሁለት የአገልግሎት ጊዜ በላይ የሚለውን ሕግ እንጥሳለን፡፡ በዚያ ላይ ምርጫ የሚከናወነው ከኦሊምፒክ በኋላ ነው፡፡ አሁን ላይ ለምን ብዬ መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ እኔ በሌለሁበት ልመረጥ አልችልም፡፡ ነገር ከመበላሸቱ በፊት በአስቸኳይ እንድታስወጡኝ አልኩኝ፡፡ ለሌሎች የጉባዔ አባላት ጉዳዩን ባካፍልም ሁሉም ሊሰሙኝ አልፈለጉም፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ሚዲያ ወጥቼ ጉዳዩን ይፋ በማደርግበት ጊዜ፣ የለም አንተ አልተመረጥክም የሚል ነገር ሰማሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ከምርጫው አስወጡኝ ባልከው መሠረት እንዳልተመረጥክ ሲነገርህ በጉዳዩ መግፋትን ለምን መረጥክ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ለዚያ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ምርጫው በአንድም ይሁን በሌላ መደረግ ያለበት ከኦሊምፒክ በኋላ ነው፡፡ መረባበሹን ካልፈለግነው ምርጫው እንዳልተደረገ ተደርጎ እንዲነገር፣ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ወቅት ቀደም ባሉት ኦሊምፒኮች ወጥቶ በማያውቅ መልኩ ወጪ የወጣ እንደመሆኑ ኦዲት ሊደረግ ይገባል የሚል አቋም ስላለኝ ነው ጉዳዩ እንዲቀጥል የፈለግኩት፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግበት የራሱ የሆነ አሠራር እንደሚኖረው አስባለሁ፡፡ በእርግጥ ጉድለት እንዳለ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ማድረስ የሚቻልበት አሠራር እንዳለም አውቃለሁ፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው ጉዳይ ከኢትዮጵያ የስፖርት ጉዳይ አልፎ የግለሰቦች ጉዳይ እየመሰለ ነው የሚል አስተያየትም መደመጥ ጀምሯል፡፡ ሁለቱን ጉዳዮች እንዴት ትገልጻቸዋለህ? ሌላው የፓሪስ ኦሊምፒክ ከቀረው ጊዜ አንፃር ቀደም ሲል ላቀረብኩልህ ጥያቄዎች መረበሽ ስለማልፈልግ ነው የሚል ነገር አንስተሃል፣ አሁንስ ከመረበሽ በምን ይለያል?

ሻለቃ ኃይሌ፡- የኦሊምፒክ ጉዳይ በአራት ዓመታት አንድ ጊዜ ኦሊምፒክ በሚቃረብበት ወቅት ነው የሚነሳው፡፡ ለዚህም ነው ጉዳዩ ሌላ መልክ ከመያዙ በፊት እባካችሁ ምርጫው እንዳልተደረገ ተደርጎ ይነገርና ፊታችንን ወደ ኦሊምፒክ እናዙር የምለው፡፡ ኦዲትን በሚመለከት ላነሳኸው ጥያቄ፣ ከእኔ ይልቅ አንተም ለመግለጽ እንደሞከርከው የሚመለከታቸውን አካላት ሄደህ ጥያቄ እንድታቀርብላቸው ነው እየነገርኩህ ያለው፡፡ በኦዲት ጉዳይ ማን ምን እንደጻፈና ምን ዓይነት ደብዳቤ እንደተጻፈ የተሟላ መረጃ ስላለኝ በቀጣይ ማቅረብ ለሚገባው አካል የማቀርበው ነው የሚሆነው፡፡ ምርጫውን በሚመለከት ካለጊዜው የተከናወነ በመሆኑ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደማይቀበለው ልነግርህ እችላለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ ለስፖርቱም ሆነ ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅም አውቃለሁ፡፡ ግን ደግሞ ለምን ወደ መፍትሔው አንመጣም ነው የእኔ ጥያቄ፡፡

ሪፖርተር፡- ኃይሌ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት ስላለው ነው ጉዳዩ እንዲጮህ የፈለገው የሚሉ አሉ፡፡ ሐሳቡ ካለህ አንተ አሁን ባለህበት ሁኔታ ለመመረጥ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፉ ሕግ ምን ያህል ይደግፍሃል?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ጥሩ ነው ታዲያ ከዚህ በፊት በነበረው ምርጫ እንዴት ምክትል ሆኜ ልመረጥ ቻልኩ?

ሪፖርተር፡- ሕጉን እስከማውቀው ድረስ የዓለም አቀፉም ሆነ የአገር ውስጥ ሕግ አይፈቅድልህም፡፡ ምክንያቱም ሕጉ የሚለው የኦሊምፒክ ኮሚቴ የቦርድ አባል ሆነው ያለ ውክልና የመመረጥ ዕድል ያላቸው በአትሌቲክሱ የዕለት ዕለት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ኦሊምፒያኖች እንደሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ሕግ በመነሳት አንተ በአሁኑ አይደለም ቀደም ሲል በራሱ የቦርድ አባል እንድትሆን የተደረገበት አግባብ ትክክል እንዳልሆነ ነው የሚሰማው፣ ምን ትላለህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- እያልኩ ያለሁትም አይገባኝም፣ በምን አግባብ መረጣችሁኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የአንተን መመረጥ፣ አለመመረጥ አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ እንዳልተመረጥህ ነው ሲናገር የሚደመጠው፣ ምን ትላለህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ይህ መነገር የጀመረው መፋጠጥ ሲመጣ ነው፡፡ የኦሊምፒክ ቦርድ አባል ሆኜ ለመመረጤ በወቅቱ በጉባዔው የታደሙ በሙሉ ህሊና ካላቸው ሊክዱት የማይችሉት እውነት ነው፡፡ ለመሆኑ ፓሪስ ሄዶ መዝናናት ማን ነው የማይፈልግ? ና እኮ ነው የተባልኩት፡፡ ነገር ግን እኔ የምለው አካሄዳችን ልክ አይደለም ወደ ትክክለኛው አሠራር እንመለስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርጫው በአንተ ትክክል እንዳልሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ባለኝ መረጃ መሠረት በምርጫው ዕለት ከሁለት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በስተቀር ሌሎች የሚመለከታቸው ክልሎች፣ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ባሉበት እንደተከናወነ ነው የሚታወቀው፡፡ ጥያቄዬ የምትቃወመው መራጮቹን ነው ወይስ የተመረጠውን አካል?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ሚኒስቴሩ አያውቀውም፡፡ በነገራችን ላይ የእኔ ተቃውሞ ሚኒስቴሩ ራሱ ያወጣው የስፖርት ማኅበራት ማቋቋሚያ መመርያ ሲጣስ እንዴት ዝም አልክ የሚልም ነው፡፡ ሌላው ምርጫ የሚደረግ ከሆነ የስፖርት ቤተሰቡ እንዲያውቀው ይደረጋል፣ ይህ አልሆነም፡፡ ሲቀጥል ክልሎችም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከኦዲት ጀምሮ ምን ይዘው ወደ ምርጫ ገቡ የሚለውን ለራሳቸው መተው ካልሆነ ምንም ማለት አልፈልግም፡፡ ሌላው ይቅር ለመሆኑ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ የምትወከለው በአንድ አትሌቲክስ አይደለም እንዴ? ሌሎቹ ስፖርቶችስ የት ነው ያሉት?

ሪፖርተር፡- በምርጫው ብቸኛ ተወካይ የምትለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተሳትፏል፡፡ እንደምትለው ከሆነ ፌዴሬሽኑ ታዲያ ለምን ዝም አለ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- መረጃው የለኝም፡፡ ነገር ግን ምርጫ ሲመጣ የተለያዩ አሠራሮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ያህል ፕሬዚዳንቱ የፓርቲ አባል ናቸው ወይስ አይደሉም? ቅጥርን በሚመለከት አንድ መሥሪያ ቤት በጡረታ የተገለለ ሌላ መሥሪያ ቤት ቅጥር የሚፈጽምላቸው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ተቋሙ የሕዝብ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ተቋም ነው ብለን ካመንን ተቋሙ የሚመራበት አሠራር እንዴት ነው ተብሎ መጠየቅ አይገባም እንዴ? በእኔ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሊምፒክን ጨምሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ምርጫ ሲያደርጉ፣ የሚከተሉት አሠራር እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ዕጩዎች ለምርጫ በቀጥታ የሚቀርቡት የክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አሊያም የክልል ስፖርት ኮሚሽን ቢሮ ኃላፊዎች ውክልና ሲሰጧቸው ነው፡፡ ይህንንስ ለምን ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- መጠየቅ ይኖርብኛል ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ጥያቄው መቅረቡ ጥሩ ነው፡፡ ግን ደግሞ ምርጫው መደረግ ያለበት መቼ ነው? የሚለው ጉዳይ መነሳት እንዳለበት ግን አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም የአገር ውስጥ መመርያና ደንቦችን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫው እንደሚደረግ የሚያውቁት ኦሊምፒክ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ የምጠይቀውም እነዚህ የሕግ መነሻዎችን ይዤ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደንብና መመርያ የአገልግሎት ጊዜን በተመለከተ ሁለት ጊዜ፣ ሦስት ጊዜ አሊያም ከዚያ በላይ መሆን አለበት የለበትም የሚል አንቀጽ እንዳለው እርግጠኛ አይደለሁም?

ሻለቃ ኃይሌ፡- መመርያው የሚገድብ አንቀጽ አለው የለውም የሚለውን እንተወውና፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሕግና መመርያዎች የሉዓላዊ አገሮች የሚያወጧቸውን ደንብና መመርያዎች ያከብራሉ፣ ይቀበላሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራር ገና አንድ ዓመት ይቀረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የስፖርት ማኅበራት ማቋቋሚያ መመርያ ደንብ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ባለድርሻ አካላት ማለትም ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ በቅጡ እንዲመክሩበትና እንዲወያዩበት አልተደረገም የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፣ ምን ትላለህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- እነማን ናቸው ባለድርሻ አካላት የሚባሉት?

ሪፖርተር፡- ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ኦሊምፒክ፣ አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውኃ ዋናና ሌሎችም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እንደሚመለከታቸው ነው የማውቀው፡፡

ሻለቃ ኃይሌ፡- ጣልቃ ገብነት የሚል ነገር ስለሚመጣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን አይመለከትም፡፡ እንዲህም ሆኖ የዛሬ ስምንት ወር አካባቢ ሚኒስትሩን (አሁን ላይ ቢነሱም) ጉዳዩን በሚመለከት ጥያቄ አቅርቤላቸው የተቀበሉበት አግባብ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ በጉዳዩ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ጭምር በእጄ ይገኛሉ፡፡ እንዴት አገኘኻቸው እንዳትለኝ፡፡ አሁንም እናገራለሁ ወደ አላስፈላጊ ነገር ከምንገባ ምርጫው እንዳልተደረገ ተቆጥሮ እንዲነገር ብቻ ነው ፍላጎቴ፡፡ በግሌ ምርጫው ምርጫ አይደለም፡፡ ሕጉ ይከበር እንጂ ሕጉ ተከብሮ ከኦሊምፒክ በኋላ እኔን ጨምሮ አሁን የተመረጡትን እንዳሉ እንመርጣቸዋለን፣ ችግር የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫው ጎን ለጎን የፓሪስ ኦሊምፒክ አትሌቶች ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ድረስ ሄደው መለማመድ የለባቸውም የሚል ተቃውሞም ታሰማለህ፣ ምክንያት ይኖርሃል?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ቢሾፍቱ ከተማ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሠራውን ትራክ በግሌ አልተቸሁም፣ ልተችም አልችልም፡፡ ምክንያቱም ከትራክ ጋር ያሉብንን ችግሮች ስለማውቅ ማለቴ ነው፡፡ መሠራቱ በጣም የሚደነቅና የሚወደስ ነው፡፡ ግን አትሌቶች ቢሾፍቱ ልምምድ አድርገው አዳር አዲስ አበባ የሚለውን ነው የምቃወመው፡፡ ምክንያቱም ትራክ የፍጥነት ልምምድ ነው፡፡ እንደ እኔ አትሌቶቹ መቀመጫቸውን እዚያው ቢሾፍቱ ላይ አድርገው ልምምዳቸውን ቢያደርጉ እሰየው ከሚሉት ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ከዚህ ባለፈ ልምምድ ቢሾፍቱ ከ45 እስከ 50 ኪሎ ሜትር ጉዞ አድርጎ አዳር አዲስ አበባ ስለሚባለው ነገር ግን፣ የስፖርቱን ባህሪያት እንዳለማወቅ ነው የምቆጥረው፡፡

ሪፖርተር፡- ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአትሌቲክሱ ትልቅ የሀብት ማማ ላይ ቢደርሱም፣ ነገር ግን ለመጪው ትውልድ የሚሆን በተለይም ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በመጡ ቁጥር ከውዝግብና ከጭቅጭቅ የሚገላግሉ ደንብና መመርያዎች እንዲስተካከሉ መታገልን ጨምሮ በስፖርት መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ እንደማትሳተፉ የሚናገሩ አሉ፣ ምን ትላለህ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- ቀነኒሳ በቀለ ትራክ አልሠራም እንዴ? ለንግድም ቢሆን እንጦጦ ላይ ሠርቷል፡፡ ወደ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ስመጣልህ መናገር አልፈልግም እንጂ፣ እንድናገር ካስገደድከኝ ከየካ ክፍለ ከተማ ጋር በመነጋገር ከኃይሌ ግራንድ ሆቴል ጀርባ በጣም ብዙ ብሮች የፈሰሱበት ወደ ፊት የምትመለከቱት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደ ትራክ ባይሆንም ማንኛውም ስፖርተኛ የፈለገውን ዓይነት ልምምድ የሚያደርግበት መሠረተ ልማት እየገነባሁ ነው፡፡ እንደ እኔ ትልቁ ጥቅም ብዬ የማስበው ግን የስፖርት መሠረተ ልማት እንዲገነባ ሳይሆን እኔ ያለኝም ልምድና ተሞክሮ ባካፍል ነው፡፡ በሌላ በኩል ‹‹ሮድ ቱ ሬኮርድ›› በሚል የአዲዳስ ካምፓኒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሰጡት መመርያ መሠረት ወደ 400 ሺሕ ዩሮ ተመድቦ በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ ትራክ እንዲሠራ ትዕዛዝ አስተላፏል፡፡ ይህ በእኔና በሌሎች አትሌቶችና አሠልጣኞች ጫናና ግፊት የመጣ ዕድል ነው፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ የተለያዩ የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮከቦች በኢትዮጵያ ተገኝተው ልምዳቸው እንዲያካፍሉ ሲደረግ አልተመለከትንም? ይህንን ነው እንደ ትልቅ ዕድል የምቆጥረው፡፡ በግሌ ይህንን እያደረግኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንተ ልምድህን እንዳታካፍል የሚከለክል ሕግ አለ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- አበው ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ›› እንዲሉ አሁን ላይ ወደ ብሔራዊ አትሌቶቹ ብሄድ ምን ሊያደርግ መጣ? ነው የሚባለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፓሪስ ኦሊምፒክ ምን እንጠብቅ?

ሻለቃ ኃይሌ፡- የጀመርኩትን ሕግ የማስከበር ጥረቴን ምርጫው እስካልተሰረዘ ድረስ እንደምቀጥል ልነግርህ እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን ምርጫው እንዳልተደረገ መተማመን ላይ ከደረስን ሁሉንም ነገር ለመተው ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ አስምሬ የምነግርህ ቀጠሯችን ይህንኑ መነሻ ያደረገ በመሆኑ ነው፡፡ ከውጤት አንፃር ከሆነ ጥሩ ነገር ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ከሴቶች 800 ሜትር ጀምሮ እስከ ማራቶን ጠንካራ አትሌቶች አሉን፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የሌሎች አገሮች ጠንካራ አትሌቶች እንዳሉም ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...