Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

የምሽቱ ቅዝቃዜ ሲበረታብኝ ያለ የሌለ የሌሊት ልብሴን ደራርቤ አልጋዬ ውስጥ ከመግባቴ ስልኬ ጮኸ፡፡ ምሽቱ ገፍቶ ሰዓቴ 5፡25 ይላል፡፡ በዚህ ሰዓት ማን ይሆን የሚደውለው ብዬ ሳነሳ እህቴ ናት፡፡ በዚህ ሰዓት የደወለችው የደረሰ አስፈሪ ነገር ቢኖር እንጂ ከዚህ በፊት ደውላ አታውቅም፡፡ በድንጋጤ እየተርበደበድኩ፣ ‹‹ምን ተፈጠረ…›› እያልኩ ሳንባርቅ እሷ ትስቃለች፡፡ ንዴት ይሁን ወይም ግራ መጋባት አላውቅም ታላቅ እህቴን፣ ‹‹ምን ያስገለፍጥሻል…›› ስላት፣ ‹‹አንተ ሰውዬ ከባለጌዎች ጋር መዋል ጀመርክ እንዴ…›› እያለች አሁንም ሳቋን ለቀቀችው፡፡ ‹‹እባክሽ እታለም እኔ እኮ ደንግጬ ነው፣ ምን ጉዳይ ቢገጥምሽ ነው በዚህ ሰዓት ደውለሽ ግራ የምታጋቢኝ…›› እያልኩ በመለማመጥ ስናገር፣ ‹‹ሜላትዬ እኮ ሴት ልጅ በሰላም ተገላገለች…›› ብላ በደስታ ስታንባርቅ ልቤ ተንፈስ አለ፡፡

እህቴ ሦስተኛዋ ሴት ልጇ አሜሪካ አትላንታ ከተማ ነዋሪ ስትሆን እርጉዝ ስለነበረች እኔም በስልክ በየሁለት ቀኑ አገኛታለሁ፡፡ ከዛሬ ነገ ትወልዳለች ተብሎ በመላ ቤተሰብ ስለሚጠበቅ፣ በሰላም የመገላገሏ ጉዳይ እንጂ መውለዷ አዲስ ነገር አልነበረም፡፡ አባትየው ከአትላንታ ከሆስፒታል ለሚስቱ ደውሎ የምሥራቹን እንደነገራት ነው እናት ለእኔ ወዲያው የደወለችው፡፡ እሷ ልጇ በሰላም በመገላገሏ ተደስታ ለእኔ ስትደውልልኝ የሰዓቱ ነገር አላሳሰባትም፡፡ እኔ ደግሞ ከበርካታ ችግሮቻችን ጋር አያይዤ የሰዓቱ ወደ እኩለ ሌሊት ማምራት እንጂ፣ የእህቴ ልጅ ሆስፒታል ሄዳ መገላገል ጉዳይ ለጊዜው አልመጣልኝም፡፡ ለማንኛውም አዲስ ሕፃን የቤተሰባችን አባል መሆኗ በደስታ እያስቦረቀን ብዙ አውርተን ለበነጋታው ማለዳ ቀጠሮ ይዘን ስልካችንን ዘጋነው፡፡

ነጋ አልነጋ ብዬ እህቴ ቤት ከንጋቱ 12 ሰዓት ሄጄ በልዩ ስሜት ተቃቅፈን በሳቅና በዕንባ ደስታችንን ገልጸን፣ አሜሪካ ካሉት ዘመዶቻችን ጋር በስልክ የደስታ ምኞት ተለዋውጠንና ቁርሴን እዚያው በልቼ ረፈድ ሲል ወደ ሥራዬ ሄድኩ፡፡ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ሰላምታ ተለዋውጬ ወደ መቀመጫዬ እያመራሁ፣ የእህቴን ልጅ በሰላም መገላገል ስነግራቸው ከአንገት በላይ በሆነ ስሜት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አሰምተውኝ ሁሉም አቀረቀሩ፡፡ አንድ ሰፋ ያለ ቢሮ ውስጥ አምስት ከፍተኛ ኤክስፐርቶች የምንሠራ ሲሆን፣ እኔ የቡድን መሪያቸው ነኝ፡፡ ለጊዜው ቢሮ ውስጥ ያገኘኋቸው ሦስቱ ሲሆኑ አንደኛዋ ባልደረባችን የለችም፡፡ የእነዚህ ሰዎች የተቀዛቀዘ ስሜት ተጋብቶብኝ በሥጋት የት እንደሄደች ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ እኔ ሌሊት የገጠመኝ ጉዳይ ዓይነት ወይም ተቃራኒው እዚህም መግጠሙ እያሳሰበኝ ነው ጥያቄ ያቀረብኩት፡፡

ለአቀረብኩት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የነበረው ስሜት በጣም የቀዘቀዘ ከመሆኑም በላይ፣ በሁሉም ፊት ላይ ለመግለጽ አዳጋች የሆነ መከፋት ይታያል፡፡ የእነሱ ስሜት እኔ ላይ ተጋብቶ ነው መሰል ፊቴን ኮስተር አድርጌ ምን እንተፈጠረ እንዲነግሩኝ ደምፄን ከፍ አድርጌ ተናገርኩ፡፡ ይኼኔ አንደኛው ከእኛ አነስ የሚል ጎልማሳ ከፍተኛ ኤክስፐርት፣ ‹‹ጋሼ ፀዳለ እኮ የእናትና የአባቷ ቤት በሦስት ቀናት ማስጠንቀቂያ እንዲፈርስ ተወስኖ በድንጋጤ ታማ ተኝታለች…›› አለ፡፡ በእንግሊዝ ኤምባሲና በአዋሬ አካባቢዎች ቤቶች ሲፈርሱ የነዋሪዎቹን ሥቃይና ሰቆቃ በዓይኔ አይቼ ስለነበር በጣም ደነገጥኩ፡፡ ድንጋጤዬ ይህች የሥራ ባልደረባችን የልብ ሕመምተኛ ስለሆነች፣ ድንገተኛው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ሕይወቷን እንዳያሳጣት ከሚል ሥጋት ነበር፡፡

በድንገተኛ አንዴ ቤተዛታ ሌላ ጊዜ ደግሞ መቅረዝ ሆስፒታሎች የታከመችው ባልደረባችን ሻል ቢላትም፣ ከ60 ዓመት በላይ የኖሩበት ግዙፍ ቪላ ቤታቸው የፈረሰባቸው ወላጆቿ ልጃቸው የምትኖርበት የአፓርታማ ቤት ለጊዜው ተጠልለዋል፡፡ የኪራይ ቤት እስኪገኝ ድረስም ንብረቶቻቸው ወዳጅ ዘመዶች ዘንድ ተከፋፍለው እነሱ ልጃቸው ቤት ቢሆኑም፣ ፊታቸው ላይ የሚታየውን ድንጋጤ ለመግለጽ ያዳግታል፡፡ እኔ ከመሸ ለምን ተደወለልኝ ብዬ እህቴን ባልታረመ ቃል መሸንቆጤ (ምን ያስገለፍጥሻል ያልኩት) ውስጤን እያንገበገበው፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ የሰቆቃ ታሪክ እያበሰጫጨኝ ከረምኩ፡፡ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች መነሻ ከማውቃቸው ሰዎች ጋር ስነጋገር በበርካታ መከራዎች ውስጥ እያለፍን ጤነኛ መምሰላችንም አስገረመኝ፡፡

ከአንድ የድሮ ወዳጄ ጋር ከሥራ ሰዓት በኋላ ተገናኝተን አንድ አንድ እያልን ለማውራት ቀጠሮ ይዤ ነበር፡፡ ከቢሮ ወጥቼ መገናኛችን ቦታ ለመድረስ አሥር ደቂቃ የማይፈጀው መንገድ ከ40 ደቂቃ በላይ ወሰደብኝ፡፡ በተጨናነቀው ጎዳና ውስጥ ከጠቆረው ሰማይ የሚወርደው ካፊያ ተጨምሮበት፣ የእኔም ሆነ የሌሎች አሽከርካሪዎች ስሜት ንዴቱን መደበቅ አቅቶታል፡፡ ከፊትም ሆነ ከኋላ ሁላችንም ማለት ይቻላል መንገዱን በጥሩምባ ስናደበላልቀው፣ ትዕግሥታችን አልቆ ጣሪያ የነካ ይመስል ነበር፡፡ አንደኛው ኤፍኤም ጣቢያ ላይ፣ ‹‹…ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላደረስነው መጉላላት ይቅርታ እንጠይቃለን…›› ብለዋል ይላል፡፡ ይቅርታ መጠየቅ መልካም ነው፣ ነገር ግን በልማት ስም ለምን ሰዎች ይዋከባሉ ለሚባለውም መፍትሔ ይፈለግ ባይ ነኝ፡፡ ሰዎችን ለረዥም ዓመት ከኖሩበት ቤታቸው እያጣደፉ የራሳችሁ ጉዳይ ማለት ኢሰብዓዊነት ነው፡፡

በስንት መከራ መንገዱን አገባድጄ የቀጠሮ ቦታችን ስደርስ ወዳጄ የለም፡፡ ‹‹ደርሰህ በትዕግሥት ጠብቀኝ…›› ብሎኝ ስለነበር፣ ‹‹እኔ ደርሻለሁ አንተስ…›› ስለው መኪናው ከኋላ ተገጭቶበት መንገድ ዘግቶ ትራፊክ ፖሊስ እየጠበቀ መሆኑን ነገረኝ፡፡ ሄጄ አብሬው እንዳልሆን ራቅ ያለ ቦታ ነው ያለው፡፡ ከቻለ እሱ እስኪመጣ እኔም የመንገዱ መጨናነቅ እስኪቃለል ቢራ አዝዤ ተቀመጥኩ፡፡ ቢራዬ መጥቶልኝ መጠጣት ስጀምር አንድ የማውቀው ሰው መጥቶ ተቀላቀለኝ፡፡ ይህ ሰው ከዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲ ያስተምር ነበር፡፡ አሁን ግን በታወቀ ዓለም አቀፍ ተቋም አማካሪ ሆኖ በከፍተኛ ደመወዝ ይሠራል፡፡ ቢራችንን እየጠጣን፣ ‹‹ሥራና ኑሮ እንዴት ይዞሃል…›› የሚል ጥያቄ ሳነሳለት፣ ‹‹ለራሴና ለቤተሰቤ ስል ፈጣሪን ተመሥገን እላለሁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማየውና በምሰማው እያዘንኩ አማርራለሁ…›› ነበር ያለኝ፡፡ ‹‹ስንትሽ እዚህች አገር ውስጥ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የአዕምሮ ሁከት አስደንጋጭ ወረርሽኝ ቢሆን እንዳይገርምህ…›› ያለኝ ውስጤ ቀረ፡፡

(ስንታየሁ ወሌ፣ ከጃክሮስ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...