Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ መብላትና መልበስን ጨምሮ ለዜጎች መድኃኒት ማቅረብ ከተቻለ ሌላው ትርፍ ነው...

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መብላትና መልበስን ጨምሮ ለዜጎች መድኃኒት ማቅረብ ከተቻለ ሌላው ትርፍ ነው አሉ

ቀን:

  • መንግሥት ከዓለም ባንክና ከአይኤምኤፍ 10.5 ቢሊዮን ዶላር ካገኘ የበጀት ማስተካከያ አደርጋለሁ ብሏል

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚበላ፣ የሚለበስና ታክሞ መድኃኒት የሚያገኝ ዜጋ ካለ ሌላው ጉዳይ ትርፍ ሊባል እንደሚችል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የፌዴራል መንግሥት የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡

ደሃውን ማኅብረሰብ ለመርዳት መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት በጀመረው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚባለውን እንቅስቃሴ ምግብ፣ መድኃኒትና ልብስ የማምረት መርሐ ግብር በግብርናውም፣ በኢንዱስትሪውም ማስፋፋት ከተቻለ አብዛኛው ከውጭ የሚገባ ፍላጎትን መሸፈን ይቻላል ብለዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ 15 አባላት መካከል፣ የኑሮ ውድነት እየከፋ መምጣቱንና የዋጋ ንረቱ ሊቆም አለመቻሉን ያነሱ ነበሩ፡፡

አቶ አቤኔዘር በቀለ የተባሉ የምክር ቤት አባል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለው ማኅበረሰብና የመንግሥት ሠራተኞች መኖር እንዳቃታቸው ጠቅሰው፣ መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አብረሃም በርታ (ዶ/ር) የሙስና ችግር እጅግ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን፣ ለዚህም የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርትን በመመልከት የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት እየባከነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በርካታ ጥናቶችና የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርቶች፣ በኢትዮጵያ ሙስና ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን እንዳመለከቱ ጠቅሰው፣ ‹‹ይህንን ሥር የሰደደ መንግሥታዊ ሌብነትና ሙስናን ለመዋጋት የብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ ቢሰማም፣ በሙስና ምክንያት ያንዣበበውን አገራዊ አደጋ ለመቀልበስ ዕርባና ያለው ሥራ ሲሠራ አልታየም፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ቁርጠኝነት ችግር መኖሩን የገለጹት አብረሃም (ዶ/ር)፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በዘረፉ ሙሰኛ ባለሥልጣናት ላይ መቀጣጫ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፣ ተጨማሪ ሹመትና የቦታ ዝውውር በመስጠት መንግሥት ከሙሰኞች ጋር አብሮ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡

‹‹የመንግሥት መዋቅር በሌቦች ተጠልፏል፣ ማንኛውም መንግሥታዊ አገልግሎት የሚገኘው በገንዘብና በእጅ መንሻ ሆኗል፡፡ ዜጎች የዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት ገንዘብ እየተጠየቁ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት ከአገር ወጥቶ እየሸሸ ነው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እያባከኑ ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

መንግሥት ከሕዝቡ የሚቀርቡ ተደጋጋሚ ቅሬታዎችንና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ግኝትን በመመልከት፣ ሥር የሰደደውን የሙስና ችግር ለመፍታት ምን ያህል ቁርጠኛ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ቃል ከመግባት ባለፈስ ምን ተግባራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ታስቧል ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አረጋሽ ተክሌ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፣ በአዳዲስ የተዋቀሩ ክልሎች ለመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈልና ከሕዝብ የሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎችን መመለስ እንዳቃተ ተናግረዋል፡፡ በሌሎች አባላትም የዩኒቨርሲቲ መምህራንና የመንግሥት ሠራተኞች ኑሮ እየከበዳቸው መሆኑን ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በምላሻቸውና በማብራሪያቸው መንግሥታቸው ከቀድሞው መንግሥት የዕዳ ቀንበር ያጎበጣት አገር መረከቡን፣ በርካታ ቃል እየተገቡ ነገር ግን ፈቀቅ ማለት ያልቻሉ ፕሮጀክቶች ቆመው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በዓለም ላይ የተፈጠረው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግር እንደ አገር መሮጥ በሚገባው ልክ ለመሮጥ የራሱ የሆነ ፈተና ጋርጦብናል፤›› ብለዋል፡፡

በርካታ አገራዊ ፍላጎቶች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአቀርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ትልቁ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ግብር ከፋዮች ዘንድ ሰፋ ያለ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከ64,000 በላይ ሰዎችና ኩባንያዎች ግብር እየሰበሰበ 120 ሚሊዮን ዜጎች ልማት እየጠየቁት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. መንግሥት ለመሰብሰብ ካቀደው 529 ቢሊዮን ብር ግብር በ11 ወራት 466 ቢሊዮን ወይም 96 በመቶ መሰብሰቡን፣ በ11 ወራት 730 ቢሊዮን ብር  ለማውጣት ታቅዶ 716 ቢሊዮን ወይም ከዕቅዱ 98 በመቶ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት መንግሥት ምንም ዓይነት የንግድ (Commercial) ብድር እንዳልወሰደ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ዕዳ ወደ 17.5 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከምርትና ከአገልግሎት ወጪ ንግድ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር፣ ከሐዋላ አገልግሎት 6.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ደግሞ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መሳብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የስንዴን ጨምሮ በተኪ ምርቶችም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በበጀት ዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ሙስናን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ሌብነት ነቀርሳ ነው፣ አገርን ይበላል፡፡ ትንሽም ሆነ ትልቅ ሌብነት መጥፋት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት የሕግ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑንና የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት መቶ በመቶ ከፈለጋችሁ አንድ ሚሊዮን ጊዜ እርግጠኛ ሁኜ መናገር የምፈልገው መንግሥታዊ ሌብነት አያካሂድም ውሸት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ክልሎች እያጋጠመ ያለው የበጀት ችግር በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ በጀት የሚለቀቀው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው ቀመርና ፓርላማው በሚያፀድቀው በጀት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ባልተገባ መንገድ ክልል እንሁን፣ ዞን እንሁን፣ ወረዳ እንሁን ይባልና ከዚያ ደመወዝ የለም የሚለው ጉዳይ በክልል ምክር ቤቶች መገምገም አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ለክልሎች የሚገባቸውን እንደሚገባቸው፣ ሁሉም በሚያስገቡት ልክ እንጂ በሌላው መጠን ሊሰጥ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

የሥራ አጥ ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረና የሚቀጥል ወደፊትም የሚጨምር መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት ከ3.8 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ሥራዎች ተፈጥረዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 3.4 ሚሊዮን በአገር ውስጥ፣ 320 ሺሕ በውጭ አገሮች ተመዝግበው ለሥራ የተላኩና 60 ሺሕ ዜጎች ደግሞ ቤታቸው ተቀምጠው ለውጭ አገር ኩባንያዎች የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ አንዳንድ አገሮች ከ60 እስከ 200 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ንረት ማየታቸውን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ቁመና ያለው የዋጋ ንረት 23 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሰብል ምርት በ2015 ዓ.ም. ከተገኘው 395 ሚሊዮን ኩንታል የምርት መጠን በተያዘው የምርት ዘመን ወደ 597 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

በባለፈው ዓመት የበጋ መስኖ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መታረሱን ጠቅሰው፣ በተያዘው ዓመት የመስኖ ወራት 24 ሚሊዮን ሔክታር ለማረስ ዕቅድ መያዙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡  

ኢትዮጵያ በስንዴ፣ በቡና፣ በእንስሳትና በማር ምርት በአፍሪካ አንደኛ ደረጃ የያዘች መሆኗን የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በመጪዎቹ ዓመታት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሩዝና በሻይ ይህንኑ ደረጃ ትይዛለች የሚል እምነት አለ ብለዋል፡፡

አሜሪካና የአውሮፓ አገሮች ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በምግብ እንዳትቸገር በርካታ የስንዴ ዕርዳታ እንዳደረጉ ገልጸው፣ ‹‹እነዚህን አገሮች እጅግ አድርገን እናመሠግናለን፣ ብድር ከፋይ ያድርገን እንላለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዕርዳታ ባንገላገልም የምንፈልገው ዕርዳታ ግን ስንዴ ሳይሆን ማሽን፣ ፓምፕና ዕውቀት ሊሆን ይችላል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ሲሳካ የድህነት ምልክትና ምሳሌ የሆነችው ኢትዮጵያ ስሟ ተቀይሮ የብልፅግና መሠረት በመጣል እናሳካዋለን ብለዋል፡፡

መንግሥት ለፓርላማው ያቀረበውና የፀደቀው 971.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣  የበጀት ጉድለት አሁን ካለበት እንዲበልጥ ባለመፈለጉ እንጂ በጀቱ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር ሰፊ ንግግር፣ ድርድርና ውይይት ሲደረግ መቆየቱን፣ ነገር ግን፣ ‹‹እነሱም አስቸጋሪ እኛም አስቸጋሪ በመሆናችን አምስት ዓመት ሙሉ የፈጀ የሪፎርም ሥራ ወስዷል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ወዳጅ አገሮች ባደረጉት ድጋፍ አብዛኛው ሐሳብ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑንና ይህ ተሳክቶ ሪፎርሙ ከፀደቀ፣ ተጨማሪ 10.5 ቢሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት እንደምታገኝና ይህን ካገኘች ግን በጀቱ ላይ ማስተካከያ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገንዘቡን ለማግኘት ኢትዮጵያ ለጊዜው ቢቆዩ የምትላቸው፣ እንዲሁም ቢሻሻል በሚል የምታነሳቸውና ጉዳዮች ተቀባይነት ካገኙ ይህንን ዕድል በመጠቀም በጀቱ ይሻሻላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥቅል አገራዊ ምርት ከለውጡ በፊት 86 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን 205 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አክለው ገልጸዋል፡፡ ከመንግሥት ለውጡ ማግሥት ኢትዮጵያ ከኬንያ ቀጥላ በምሥራቅ አፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ ኢኮኖሚ እንደነበረች፣ ነገር ግን ዛሬ ላይ ስድስቱ የጎረቤት አገሮች ተደምረው ኢትዮጵያን አያክሉም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ በብዙ አጥኚዎች ያለው ዕሳቤ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያመጣች ያለች መሆኗን፣ የዛሬ 40 ዓመት ከዓለም 16 እና 17ኛ ኢኮኖሚ የምትገነባ አገር እንደምትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2100 ወይም የዛሬ 75 ዓመት በዓለም 7ኛውን ኢኮኖሚ እንደምትገነባ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ከፍተኛ ተስፋና ሕልም ይታያል ብለዋል፡፡

በፋይናንስ ዘርፉ 32 ባንኮች የቅርንጫፎቻቸው ብዛት 12,800 መድረሱን፣ የቁጠባ ሒሳብ ደብተራቸው ደግሞ ከ100 ሚሊዮን መብለጡንና በርካታ ዜጎች ወደ ባንክ ኢንዱስትሪ እየገቡ መሆኑን ማሳያ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ባንኮች ትርፋማነታቸው እየጨመረ፣ ተደራሽነታቸው እያደገና ጤናማ ሆነው እየሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በተያዝው ዓመት 7.9 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ግብርና 6.2 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 10.1 በመቶ እንደሚይዙ አስረድተዋል፡፡

‹‹በትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ተሽከርካሪዎች  የመንግሥትም ሆኑ የግልም በሠራተኛ መውጫና መግቢያ ሰዓት ሕዝቡን ማገልገል እንዲችሉ የሚያስችል አሠራር ካልተከተልን፣ ነዳጅ እየደጎምን ገንዘቡ ደሃው ዘንድ ካልደረሰና የሕዝቡን እንቅሰቃሴ የሚያግዝ ካልሆነ እንደ አገር የዕድገት ፀር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም በቅርቡ በካቢኔ ተገምግሞ የመንግሥት መኪኖች በሥራ መውጫ ሰዓት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ ተብሎ ሙከራ መጀመሩን ገልጸው፣ ምክር ቤቱ ይህን ሥራ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...