Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የጀመረችው ድርድር በመጪው መስከረም ሊካሄድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • መንግሥት የንግድናፋይናንስ ዘርፎችን ለመክፈት መወሰኑ ድርድሩን ያከብደዋል ተባለ

በግንቦት ወር ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት አምስተኛ ዙር ድርድር፣ በመጪው መስከረም ወር 2017 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

ድርድሩን በበላይነት የሚመራው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሲሆን፣ በግንቦት ወር አምስተኛ ዙር ድርድር ለማካሄድ ታቅዶ ወደ መጪው ዓመት መስከረም የተራዘመበት ምክንያት፣ እ.ኤ.አ. በ2020 በነበረው ድርድር አባል አገሮች አቅርበዋቸው የነበሩ ጥያቄዎችን በሚመለከት እየተዘጋጀ ያለው ሰነድ ባለማለቁና አባል አገሮች የሚያካሂዷቸው ስብሰባዎች ላይ ትኩረት በማድረጋቸው መሆኑን፣ በሚኒስቴሩ የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታገስ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታካሂደው ሒደት በተለያዩ ምክንያቶች እየተቋረጠ ለሁለት አሠርት ዓመታት መዝለቁ ይታወሳል፡፡ ለሒደቱ መጓተትም የድርጅቱ አባል ለመሆን መሥፈርት የሆኑት የኢኮኖሚና የፖሊሲ ለውጦች መዘግየት ምክንያት እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ 

በአባል አገሮች የሚነሱ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከቱ አለመሆናቸውን ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ታገስ፣ ‹‹የሚነሱ ጥያቄዎች ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውና ተቀበሉ ወይም አትቀበሉ አይደሉም፡፡ እንድናሳውቃቸው የሚፈልጓቸው ጉዳዮችንም ነው የሚጠይቁት፤›› ብለዋል፡፡ ለአብነትም የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ምርት ወደ አገር ውስጥ ሲገባ አገሪቱ የምትከተላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማወቅ እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም 181 ያህል ጥያቄዎች እ.ኤ.አ. በ2020 በነበረው የአባል አገሮች ድርድር የተነሱ መሆናቸውንና ከውጭ ምንዛሪ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከኢንቨስትመንት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ዋና ዋናዎቹ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን ጨምሮ የአገልግሎትና የንግድ ዘርፎች ክፍት እንዲደረጉ እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል፡፡

ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት አገሪቱ ስትከተላቸው የነበሩ ፖሊሲዎች፣ ከዓለም ንግድ ድርጅት መርሆችና አባል አገሮች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች ጋር በእጅጉ የሚጣረሱ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ብልፅግና ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ እየተደረጉ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ግን በድርድሩ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሳያ ናቸው እየተባለ ነው፡፡

መንግሥት የንግድና የፋይናንስ ዘርፉን በከፊል ክፍት እያደረገ መሆኑ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ላለችው ድርድር ሁለት ገጽታ እንዳለው አቶ ታገስ ገልጸው፣ ይህም አባል አገሮች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ያላትን ቁርጠኝነትና ድርጅቱን ለመቀላቀል የሚጠየቁ መሥፈርቶች እየተስተካከሉ መሆናቸውን ስለሚያሳይ በመልካም የሚታይ መሆኑንና በተቃራኒው ግን ድርድሩን ሊያከብደው ይችላል ብለዋል፡፡

‹‹ድርድሩ አሁን ካለንበት ሁኔታ ስለሆነ የሚቀጥለው የከፈትናቸውን 70 የሚጠጉ የአገልግሎት ዘርፎችን ይዘን ለድርድር ከተቀመጥን በእነሱ በኩል የሚቀርብ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄ ይኖራል፤›› በማለት ዘርፎች ክፍት በመደረጋቸው የሚኖረውን ጫና አብራርተዋል፡፡ አክለውም ቀድመን ክፍት ያደረግናቸውን አገልግሎቶች በድርድሩ ወቅት እንደ መደራደሪያነት ቢቀርቡ ለድርድሩ ያመች እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2026 አጋማሽ ድርድሩን ለማጠናቀቅና ኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች